የነቢያት ማንነትና አስተምህሮአቸው ክፍል ሶስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
385 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

በ “ነቢይ” እና “ረሱል” መካከል ያለው ልዩነት፡-
የተወሰኑ ወንድምና እህቶች ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት፡ የኢስላም ሊቃውንት (ዑለማእ) ዘንድ በ ነቢይ እና በ ረሱል መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት እንደሚያስቀምጡት በመጠኑ ለማቅረብ እሞክራለሁ ኢንሻአላህ፡፡
ባለፈው በክፍል ሁለት ያነሳሁትን ሀሳብ ዛሬም እደግመዋለሁ፡፡ በነቢይና በረሱል መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅም ሆነ አለማወቅ በአንድ ሙስሊም እምነት ውስጥ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ጉዳዩ ተጨማሪ ዕውቀት የማግኘትና ያለማግኘት ከመሆን በዘለለ መልኩ፡ እምነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ የለውም፡፡ በአምልኮ ላይም የሚፈጥረው ክፍተት የለም፡፡ ምክንያቱም፡-

አንድ ሙስሊም፡- ነቢይነትም ሆነ ረሱልነት የአላህ መለኮታዊ ምርጫ እንጂ የሰዎች የስራ ውጤትና ልፋት አለመሆኑን ካመነ፣ ነቢያትም ሆኑ ሩሱሎች ከአላህ ዘንድ መለኮታዊ ራእይ (ወሕይ) የሚወረድላቸው እንጂ ፈላስፋ ወይም ልብ-ወለድ ተናጋሪ አለመሆናቸውን ከተቀበለ፣ ነቢያትም ሆኑ ሩሱሎች አላማቸው ሰዎችን ከአላህ ጋር በማስተዋወቅ ከጨለማ ወደ ብርሐን መንገድ ሰበብ ሁኖ በማውጣት የጀነትን መንገድ ማመላከት እንደሆነ ከተረዳ፣ ነቢያትም ሆኑ ሩሱሎች በዚህ ተልእኮአቸው የጌታቸውን ውዴታና እሱ ዘንድ ያለውን አምላካዊ ስጦታ እንጂ፡ ምድራዊ ደሞዝና ስልጣን ፈላጊዎች አለመሆናቸውን በአግባቡ ከተገነዘበ፣ ነቢያትም ሆኑ ሩሱሎች ከሰዎች መካከል የተመረጡ ሰዎች እንጂ፡ ከመልአክ ወይም ከጂንኒ ወገን እንዳልሆኑ ካስተዋለ ለአማኝነቱ ይህ በቂው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በነቢይ እና ረሱል መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ደፋ ቀና ማለቱ ወይም አለማለቱ ተጨማሪ ዕውቀት ከማግኘት ወይም ከማጣት ውጪ በእምነቱ ላይ የሚያደርሰው ምንም ጉድለት የለውም፡፡

የአላህ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርኣን እንዲሁም የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ንግገር የሆነው ሐዲሥ፡ በነቢይ እና በረሱል መካከል ልዩነት መኖሩን የሚጠቁሙ የቃላት አገላለጾችን በውስጣቸው ይያዙ እንጂ፡ ልዩነቱ ይህ ነው የሚል ቀጥዒይ (ፍጹማዊ) የሆነ ማስረጃን አናገኝባቸውም፡፡ የኢስላም ሊቃውንትም በጉዳዩ ላይ የተለያየ እይታ ነው ያላቸው፡፡ ከፊሎቹም ከዚህ በመነሳት፡- በነቢይ እና በረሱል መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ማንኛውም ነቢይ ረሱል ነው፡ ማንኛውም ረሱል ነቢይ ነው! የሚል ድምዳሜ ሰጥተዋል፡፡ አብዝኃኞቹ ሊቃውንት ግን ልዩነት እንዳለ አበክረው ገልጸዋል፡፡ ልዩነቱ ምንድነው? በሚለው ላይ ግን የጋራ አቋም የላቸውም፡፡ እናንተ እነዚህ ሊቃውንት ያቀረቡትን በነቢይ እና በረሱል መካከል ያለውን የመለያ ሀሳብ ማወቁ ይጠቅመናል ካላችሁ ቀጥሎ ያለውን በጥሞና ያንብቡ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ሀ/ መልእክትን ከማድረስ አንጻር፡-

ከአላህ ዘንድ መልእክት የሚመጣለት ሆኖ፡ መልእክቱን ራሱ እንዲተገብረው እንጂ ለሌሎች እንዲያደርስ የማይታዘዝ ከሆነ ነቢይ ይባላል፡፡ ይህንኑ የመጣለትን መልእክት ለሌሎች እንዲያደርስ ከታዘዘ ግን ረሱል ተብሎ ይጠራል የሚል ነው፡፡ (ሸርሑል ዐቂደቲ-ጠሓዊየህ 158)፡፡
ከዚህ ሀሳብ በመነሳት፡- ማንኛውም ረሱል ነቢይ መሆን ሲችል፡ ነቢይ ግን ረሱል አይሆንም የሚለውን ሀሳብ መያዝ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ለዛ ነቢይ የመጣለት ነገር ረሱሉም መጥቶለታልና፡፡

ለ/ ከወሕይ (ራእይ) አመጣጥ አንጻር፡-

ከአላህ ዘንድ የሚመጣው መለኮታዊ ራእይ (ወሕይ) በመልአክ በኩል ከሆነ፡ ይህ ወሕይ የመጣለት አካል ረሱል ተብሎ ሲጠራ፡ ወሕዩ የመጣለት (የተገለጠለት) ግን በመልአክ በኩል ሳይሆን በህልሙ ወይንም በንቃተ-ህሊናው ሳለ በልቦናው በማስቀመጥ ከሆነ ግን ነቢይ ተብሎ ይጠራል የሚል ነው፡፡ (ተፍሲር አል-ኢማሙል ቁርጡቢይ፡ አል-ጃሚዑ ሊአሕካሚል ቁርኣን 12/75)፡፡

ሐ/ ከመጽሐፍ መውረድ አንጻር፡-

ለነቢይነቱ ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ከሚሰጠው ተአምራት በተጨማሪ፡ ከአላህ ዘንድ መለኮታዊ መጽሐፍ የሚወርድለት ከሆነ ረሱል ተብሎ ይጠራል፡፡ መለኮታዊ መጽሐፍ ሳይወርድለት ከሱ በፊት የቀደመውን የረሱሉን መንገድ በማደስ ወደሱ ጥሪ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ ነቢይ ይባላል የሚል ነው፡፡ (አል-ኢማሙ ነሰፊይ፡ መዳሪኩ-ተንዚል 3/108)፡፡

መ/ አዲስ ሸሪዓህ ይዞ ከመምጣት አንጻር፡-
ከአላህ ዘንድ አዲስ ሸሪዓህ (ህግጋት) የሚመጣለት ከሆነ ረሱል ተብሎ ይጠራል፡፡ አዲስ ሸሪዓህ የማይመጣለት ሆኖ የቀደመውን ረሱል ሸሪዓህ የሚከተልና አማኞችንም የሚያስተምር ከሆነ ነቢይ ይሆናል ነው፡፡ (ዶክተር. ዑመር ሱለይማን አል-አሽቀር፡ አር-ሩሱሉ ወር-ሪሳላት 15)፡፡
ከላይ የምናነባቸው ሀሳቦች የሃይማኖቱ ሊቃውንት እይታና ድምዳሜ ነው፡፡ ፍጹማዊ እንከን አልባነት የአላህና የመልክተኛው ቃል ብቻ በመሆኑ፡ የእነዚህ ሊቃውንት ሀሳብም፡ በሌሎች ሊቃውንት ዘንድ ትችት ገጥሞታል፡፡ ይህ ማለት በሩ አሁንም ለምርምር ክፍት ነው ማለት ነው፡፡

• ነቢይ ለራሱ እንጂ ለሌሎች እንዲያደርስ አልተላከም የሚለውን ሀሳብ፡ አላህ ረሱልን ብቻ ሳይሆን ነቢይንም እንደላከ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ሊቃንት (ዑለማእ) ሀሳቡን ውድቅ አድርገዋል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

” وَمَا أَرْسَلْنَا مِنْ قَبْلِكَ مِنْ رَسُولٍ وَلَا نَبِيٍّ إِلَّا إِذَا تَمَنَّى أَلْقَى الشَّيْطَانُ فِي أُمْنِيَّتِهِ فَيَنْسَخُ اللَّهُ مَا يُلْقِي الشَّيْطَانُ ثُمَّ يُحْكِمُ اللَّهُ آيَاتِهِ وَاللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٌ ” سورة الحج 52
“ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አልላክንም፣ ባነበበ (ና ዝም ባለ) ጊዜ፣ ሰይጣን በንባቡ ላይ (ማጥመሚያን ቃል) የሚጥል ቢሆን እንጂ፤ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል፤ ከዚያም አላህ አንቀጾቹን ያጠነክራል አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው።” (ሱረቱል ሐጅ 22፡52)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥ፡- ከአላህ ዘንድ የሚላክ ማንኛውም ነቢይም ሆነ ረሱል፡ ከአላህ የወረደለትን መለኮታዊ ቃል አንብቦ በጨረሰ ጊዜ ሰይጣን የማጥመሚያ ቃልን በንባቡ ላይ ለመጨመር እንደሚሞክርና፡ ሙከራው ሳይሳካለት አላህ ድርጊቱን ወዲያው በማክሸፍ የሱን ቃላቶች እንደሚያጠናክር ሲነግረን፡ እግረ-መንገዱም ነቢይም የሚላክ መሆኑን እንረዳለን ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም፡- ነቢይ የወረደለትን ራእይ (ወሕይ) ለሰዎች አለማድረስ፡ የአላህን መልክት መደበቅ ይባላል፡፡ አላህ ደግሞ የሱ መልክት እንዲደበቅና በአንድ ነቢይ ልብ ውስጥ የተቀበረ ሆኖ እንዲቀርና ከዛው ነቢይ መሞት ጋር አብሮ እንዲሞት አላወረደም፡፡ (አር-ሩሱሉ ወር-ሪሳላት 14-15)፡፡

• መልአክ የሚመጣው ለረሱል ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ነቢይ ብቻ ከሆነ ግን በህልም ወይም በኢልሃም (በንቃተ ህሊናው እያለ በልቦናው ማስቀመጥ፣ ማሳወቅ) ነው የሚመጣለት የሚለውም ትችት ገጥሞታል፡፡ (ኢማም አል-ማወርዲይ፡ አዕላሙ-ኑቡዋህ 33)፡፡
ጉዳዩ በራሱ ማስረጃ የሌለው ከመሆኑ ጋር፡ በተጨማሪም በአንድ ሐዲሥ ላይ እንደተዘገበው፡- አይሁዶች ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘንድ በመምጣት፡- ‹‹ማንኛውም ነቢይ ከመልአክ በኩል ወዳጅና ረዳት ይኖረዋል፡፡ ያንተ ወዳጅህና ረዳትህ ማነው?›› ብለው በጠየቋቸው ጊዜ፡ የነቢዩም ምላሽ፡- ‹‹መልአኩ ጂብሪል ነው!›› የሚል ነበር፡፡ እነሱም፡- ‹‹ይህ በቅጣትና በጦርነት ጊዜ የሚወርደው መልአክ ነው እንዴ! እሱማ ዋና ጠላታችን ነው፡፡ በዝናብና በእጽዋት ላይ ኃላፊነት የተሰጠው መልአኩ ሚካኢል ቢሆን ኖሮ በተከተልንህ ነበር›› አሉ፡፡ ጌታ አላህም ‹‹ለጂብሪል (ለገብርኤል) ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው፡፡ እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና፡፡›› (አል-በቀራህ 2፡97)፡፡ የሚለውን መለኮታዊ ቃሉን በሳቸው ላይ አወረደው፡፡ (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 2483)፡፡

በዚህ ሐዲሥ ውስጥ ነቢያት በጠቅላላ ከመልአክ በኩል ወዳጅ እንደሚኖራቸው የሚያሳይ ሀሳብ አልለ፡፡ በወቅቱ አይሁዶች የተናገሩት ስህተት ቢሆን ኖሮ፡ የአላህ መልክተኛም ከምላሻቸው በፊት የነሱን የተሳሳተ አመለካከት ባስተካከሉ ነበር፡፡

• አዲስ ሸሪዓህ ይዞ የሚመጣ ከሆነ ረሱል ይሰኛል፡፤ የቀደመውን ሸሪዓህ ይዞ የሚከተል ከሆነ ግን ነቢይ ብቻ ይሆናል የሚለውም ብዙ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ነቢዩላህ ዳዉድና ልጁ ሱለይማን (ዐለይሂማ-ሰላም) ረሱል እንደነበሩ የታወቀ ነው፡፡ ሆኖም ሁለቱም ይከተሉና ይመሩበት የነበረው የሙሳን (ዐለይሂ-ሰላም) ሸሪዓህ፡ የተውራትን ህግ ነበር እንጂ አዲስ ሸሪዓህ አልመጣላቸውም፡፡ (ኢብኑ ተይሚይያህ፡ አን-ኑቡዋት 184)፡፡

የተሻለው አማራጭ፡-
በነቢይና በረሱል መካከል ያለው ልዩነት፡- ረሱል የሚላከው መልክቱን ለተቀበሉት አማኞችም ላልተቀበሉት ከሀዲያንም ጭምር ነው፡፡ መልእክቱ በአዲስ ሸሪዓህ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ነቢይ ግን የቀደመው ረሱል አስተላልፎት የሄደውን መልእክት፡ እርሱ ለአማኞች እንዲያደርስና እንዲያድሰው ይላካል እንጂ፡ ልክ እንደ ረሱሉ መልክቱን ላልደረሳቸውና ለሚቃወሙ ህዝቦች የማድረስ ግዳጅ የለበትም የሚለው ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡ (ኢብኑ ተይሚይያህ፡ አን-ኑቡዋት 184)፡፡

ይህ ሀሳብ ከመጀመሪያዎቹ የሚለየው፡-
1/ ነቢይ ለራሱ እንጂ ለማንም አልተላከም የሚለውን በመቃወም፡ ለአማኞች ግን በቀደመው የረሱል መንገድና ሸሪዓህ መሰረት መላኩን ያጸድቃል፡፡
2/ ረሱል አዲስ ሸሪዓህ ይመጣለት ዘንድ ግድ ነው የሚለውን መስፈርት በመቃወም፡ አዲስ ሸሪዓህ ሊመጣለትም ወይንም የቀደመውን የረሱልን ሸሪዓህ ሊከተል ይችላል በማለት፡ ዳዉድንና ሱለይማንን በምሣሌነት ጠቅሶ በሩን ክፍት ያደርገዋል፡፡
3/ ለነቢይ መልአክ አይመጣም፡፡ መልአክ የሚገለጠው ለረሱል ብቻ ነው የሚለውን ማስረጃ የሌለውን ሀሳብም አይቀበልም፡፡

ማጠቃለያ፡-

ከሁሉም የሊቃውንት ሀሳብ የምንወስደው የጋራ ስምምነት፡- ረሱልነት (መልክተኝነት) ከነቢይነት የጎላ እና ከፍ ያለ ደረጃ መሆኑን፣ እንዲሁም ማንኛውም ረሱል ነቢይነትንም እንደሚላበስ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ፈኩልሉ ረሱሉን ነቢይ፡ ወለይሰ ኩልሉ ነቢይዪን ረሱል›› (ማንኛውም ረሱል ነቢይ ሲሆን፡ ነቢይ ሁሉ ግን ረሱል አይደለም) የሚለው ሀሳብ ትክክል ይሆናል ማለት ነው፡፡
በሂሳብ ህግ መሰረት፡- all equilateral triangles are also isosceles. But all isosceles triangles are not equilateral. የሚል መርሕ አለ፡፡ ሶስቱም ጎንኖቹ እኩል (60 ዲግሪ) የሆነው equilateral triangle ይባላል፡፡ ሁለቱ ጎንኖቹ ብቻ እኩል የሆኑት ደግሞ isosceles triangle ተብሎ ይጥጠራል፡፡ ሶስቱም ጎንቹ እኩል በሆነው equilateral triangle ውስጥ ሁለት ጎንኖቹ እኩል በመሆናቸው isosceles triangle የሚለውንም አብሮ ያቅፋል ማለት ነው፡፡ ባለ ሁለት እኩል ጎንኖቹ ግን በሶስተኛው እኩል አለመሆን ምክንያት equilateral triangle የተባለውን ሊያቅፍ አይችልም፡፡
በረሱልነት ውስጥ ነቢይነት በመኖሩ፡ ማንኛውም ረሱል የተባለ ሁሉ ነቢይም ተብሎ ይጠራል፡፡ በነቢይነቱ ብቻ የሚታወቀው ግን ረሱል ተብሎ በኢጥላቅ (በስድ) አይጠራም፡፡ ይህ የቀጥታ ስያሜ የአላህን መልእክት ወደ ከሀዲያን እንዲያደርስ ለተላከው ብቻ የሚሰጥ ነው ማለት ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡

” مَا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَا أَحَدٍ مِنْ رِجَالِكُمْ وَلَكِنْ رَسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ وَكَانَ اللَّهُ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا ” سورة الأحزاب 40
“ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድንም ሰው አባት አይደለም፤ ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤ አላህም በነገሩ ሁላ ዐዋቂ ነው።” (ሱረቱል አሕዛብ 33፡40)፡፡

” وَاذْكُرْ فِي الْكِتَابِ مُوسَى إِنَّهُ كَانَ مُخْلَصًا وَكَانَ رَسُولًا نَبِيًّا ” سورة مريم 51
“በመጽሐፉ ዉስጥ ሙሳንም አዉሳ፤ እርሱ ምርጥ ነበርና መልክተኛ ነቢይም ነበር።” (ሱረቱ መርየም 19፡51)፡፡

” وَاذْكُرْ فِي الْكِتَابِ إِسْمَاعِيلَ إِنَّهُ كَانَ صَادِقَ الْوَعْدِ وَكَانَ رَسُولًا نَبِيًّا ” سورة مريم 54
“በመጽሐፉ ኢስማዒልንም አዉሳ፤ እርሱ ቀጠሮን አክባሪ ነበረና፤ መልክተኛ ነቢይም ነበር።” (ሱረቱ መርየም 19፡54)፡፡

ሐቅን ከገጠምኩ ከአላህ ተውፊቅ ሲሆን፡ ስህተቱ ግን የነፍሲያዬና የሸይጧን ጉትጎታ ነው፡፡ አላህና መልክተኛው ከኔ ስህተት የጸዱ ናቸው፡፡