የቄሳርን ለቄሳር

ሼር ያድርጉ
393 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

በኣላህ ስም እጅግ ኣዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን የመጨረሻ ነብይ ተደርገው በተላኩት ሙሐመድ ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን ቀጠልን፡፡ወዳጄ እንደምን ከረሙ? የዛሬው ወጋችን ኢትዬጵያዊው ሙስሊም በጥቅሉ በየግዜው ቁብ በሌላቸው ጉዳዮች ስለምን ይተክናል? ስለምንስ ውል-ኣልባ ኾኖ በየጊዜው እየተፈታ ይቋጠራል? ለሚል ሐሳባዊ ጥያቄ የመሰለኝን ላካፍሎ ወድጃለኹ፡፡ በዚህ ወግ ውስጥ ራሳቸውን ዓሊም ያደረጉና አስኳላዊ እውቀት ብቻ ያላቸው ኹለት ጎሳዎች ይዘከራሉ፡፡

[ከኢስላማዊ እውቀት መራቆት]

ዛሬ ላይ ወዳጄ እርሶም እንደሚታዘቡት ሙስሊሙ ከኢስላማዊው እውቀት ዓለማዊውን ከፊት ለፊት አድርጎ ማሰብና መጓዝ ከመረጠ ሰነባብቷል፡፡ ኢስላማዊ ወይም ዓለማዊ ስንል ምን ለማለት እንደተፈለገ ልብ ይሏል!!! ኹለቱን አጣምሮ መጓዝ እየተቻለ፣ ዛሬ ላይ ኢትዬጵያዊው ሙስሊም በምልዓት ከኢስላማዊው ፍኖተ-ዕውቀት እጅጉን እየሸሸ ይገኛል፡፡ ዓለምን ማነጋገር የሚቻለው በዓለማዊው እውቀት ብቻ እንደኾነ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ማመን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከዓመታት በፊት መሳጂድ መሰረታዊ ዕውቀትን የሚፈልጉ ሕጻናትና ወጣቶችን ያስተናግዱ ነበር፡፡ በደረሳው መካከልም የዕውቀት ፉክክር እንጂ የመድረክና የእውቅና ፍትጊያ አልነበረም፡፡ ዘመን ለዘመን ቦታውን ሲለቅ ግን፣ ያ ኹሉ ቀረና ዛሬ በጥቅሳ ጥቅስ የተሞላ ጭንቅላት ያላቸው ከመሰረታዊው ዕውቀት ማዕድ ያልቆረሱና ከምንጩም ዝቅ ብለው ያልተጎነጩ፣እንደ ቃጭል በሚጮህ ባዶ ኣእምሮ ስለኹሉም ነገር እንናገር ብቻ ኣይደለም እንፍረደም፣አንመድብም፣ ደረጃም እንስጥ ሲሉ ማየት የእለት እለት ኣጋጣሚ ኾኗል፡፡ ወዳጄ ባዶ ጣሳ ውስጥ ጠጠር በትነው ቢነቀንቁት የጣሳው ጩኸት እንደሚረብሾ ኹሉ፣ጣሳውን በጠጠር ሞልተው ቢነቀንቁት ግን፣ እጆ ይዝል እንደሁ እንጂ ጣሳው ግን ኣይጮህም፡፡ በዕውቀት መሞላትና በጥራዝ ነጥቅ ማውራት የዚህ ምሳሌ ነው፡፡

ሰዎች ከዕውቀት በራቅን ልክ ለወሬና ለንግግር ደግሞ እንቀርባለን፡፡ ኣላዋቂ ኣዕምሮ ኣላዋቂነቱን ብዙ በማውራትና መድረኮችን በመሻማት ሸፍኖ ማሳየት ይፈልጋል፡፡ ወዳጄ የመታወቅ ፍቅር ካሳቃዬ፣ እመኑኝ እርሶ ከዕውቀት ነጻ ኖት!!! እርሶ ጋር ያለው እውቀት ሳይኾን በእስስት ቆዳ ተሸፍኖ የሚታይ ዕውቀት የመሰለ ትልቅ ኣላዋቂነት ነው፡፡ ኣስኳላ (ዘመናዊው ት/ቤት) ረዥም ጊዜ መመላለስ በራሱ ለኢስላማዊ እውቀት አጋዥ እንጂ፣ በራሱ ግን በቂ እውቀት ኣይደለም፡፡ በኣስኳላ ብቻ የታጠረ አሰላስሎ መቼ ከኢስላም ጋር እንደሚኋኋን (እንደሚስማማ) መቼስ እንደሚላተም ለአሰላሳዩ እንኳ ግልጽ ስላልኾነ፣ ብቻውን ኢስላማዊ ማኅበረሰብና ፍልስፍና ሊፈጥር ኣይችልም፡፡ እነ “ጋሽ አስኳላ ብቻ” ይህንን መረዳት ኣልቻሉም ወይም ኣይፈልጉም፡፡ የነርሱ ደርቅ አስኳላዊ አስተሳሰብ ብቻውን መፍትሄ እንዳለው፣ ብቻውን ያሉብንን ምንድልድልና ዝብርቅርቅ ችግሮች ወደ ኣንድ ጎራ ሰብስቦ ማከም የሚችል ይመስላቸዋል፡፡

[ካባህንና ዘውድህን አውልቀህ መሬት ውረድ]

ኣንተ ራስህን ምሉዕ-በኩልሄ (በኹሉም ነገር ሙሉ) አድረገህ የሳልህ ያላዋቂዎች ቁንጮ ሆይ! በራስህ ልክ ያሰፋኸውን ካባና ዘውድ አውልቅና እንደ ሰው ቦላሌህን አጥልቅ፡፡ ራሳህን ሰቅለህ ከራስ ዳሽን ጫፍ ያመቻቸህ የሰው ንዑስ ሆይ! ውረድና ከጉንዳኖች ሰፈር ውርውር በል፡፡ ኣንተ በራስህ አሰላስሎ ፍቅር ያበደህ፣በራስህም ኣዋቂነት የተሸነገልህ የመድረክና የመንደር ውስጥ ጋጋኖ ሆይ! ድምጽህ የስንቱን ጆሮ እንደበሳ ብታውቅ ቃልም ባልተነፈስህ ነበር፡፡ መታየት የማትችል ድቃቅና ቅንጣት መኾንህን ባወቅህ ኖሮ፣ ፈጽሞ ከሰው ፊትም ባልቆምህ ነበር፡፡ እክባለው ብለህ የደረደርከው ድንጋይ ለስንቱ መወገር ምክንያት እንደኾነ ብታውቅ፣ የደረደረክበትን አጋጣሚ በረገምህ ነበር፡፡ እናንት ትናንሽ ግዙፍ ዛፎች!!! ፍሬኣችሁ መርዛማ ነውና በርካታዎችን ገድሏል፤ በርካቶችም ለመሞት እያጣጣሩ ነው፡፡ ስለኾነም ወይ ለራሳችኹ የሰጣችኹትን ሰፊ ቦታ አጥብቡና በሰው ልክ ኹኑ፣ አሊያም የኣዛዚል (ኢብሊስ) ጓዶችና የጥፋትም አርበኞች እንደኾናችኹ እወቁ፡፡ በልባችኹም ያዙ፡፡

[ጥምጣሙንና ጀለቢያውን ከኣህያው ላይ እናንሳ]

ወዳጄ ኣህያን ከሩቅ ሲያዩት በቅሎ እንደሚመስል ልብ ይሏል፡፡ ከሩቅ አይተህ ኣህያን በኣህያነቱ መለየት ከቸገረህ፣ ቀርበህ መርምረው፡፡ ያኔ ፈጽሞ ኣህያነቱን ታስረግጣለህ፡፡ አኹንም አህያነቱን መረዳት ከከበደህ ግን፣ ኣህያው ኣናፍቶ (ጮሆ) ኣህያነቱን በነቢብ (theoretically) እስኪያሳይህ ጠብቅ፡፡ ደግመህ አልሰማኹም፣አልተረዳኹምም ካልክ ደግሞ በኋላ እግሮቹ ረግጦ ኣህያነቱን በገቢር (practically)ያሳውቅሃል፡፡ ከዚህ ኹሉ በኋላ ኣህያው በቅሎ ከመሰለህ ግን፣ ኣህያው እርሱ ሳይኾን ኣንተ ነህ፡፡ ወዳጄ በቅሎ መስሎ የቀረበው ኣህያ በኣዋቂዎች ካባ የተሸፈኑ በየመድረኩና መጣጥፉ ውስጥ የተቀመጡ አፈ-ቀላጤ ኣላዋቂዎች እንደኾኑ ይረዷል፡፡

እነዚህን ኣላዋቂዎች በቅጡ መለየት ስለቸገረን፣ እነርሱ ለራሳቸው የተጎናጸፉት የኢማምነት ካባ ሳያንስ፣የሙፍቲነት ጥምጣምና ጀለቢያ ያለበስነው እኛው ነን፡፡ ስለኾነም ጥምጣሙንና ጀለቢያውን ከኣህያው ላይ እናንሳና ለሚገባው እናስረክብ፡፡ ያኔ ኣህያው እንደፈለገ ቢያናፋ፣ ቀድሞውኑ ምንም ዓይነት ቦታ ስላልሰጠነው፣ ማናፋቱ ጩኸት ብቻ ይኾናል፡፡

ወዳጄ ይህንን ወግ ትንሽ ዘወርወር ኣድረጌ ማቅረቤ፣ በየጊዜው እገሌ እንዲህ አለ፤ እንዲህም ጻፈ፤ እያልን ምንቀባበላቸው ዜናዎች መበርከታቸውን አየኹና ነው፡፡ አስቀድመን እነ “እገሌን” በድቅድቅ ጨለማ የሚንቦጎቦግ ሙሉ ጨረቃ አድርገን በመሳላችን፣ ከነርሱ በኩል የሚነሱ ስህተቶችና ኾን ተብሎ የሚፈጽሙ ጥፋቶች ያብከነክኑን ጀምሯል፡፡ ያ እንዳይደገም የቄሳርን ለቄሳር እናድርግ፤ ሰዎችን በሚገባቸው መሰፈሪያ ብቻ እንስፈር፡፡ እነ “እገሌም” ልካችኹን ዕወቁ፡፡ በእንቁራሪት ቁመና ኾናችኹ ዝሆን ነን አትበሉ፡፡

اللهم اغفر وارحم وهدينا إلى سبل السلام

Shortlink http://q.gs/Eye1b