የቁርዓን ኩረጃዎች?

1,968 Views

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

ቁርዓንን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ከሚነሱ የክርስቲያኖች መከራከሪያ ሚዛኑ ከፍ ያለ ጥቀስ ብባል ይህኛውን የሚገዳደር ያለ አይመስለኝም። “ቁርአን ከመጽሀፍ ቅዱስ ኮርጇል” የሚለውን በተመለከተ ከአዋቂዎቻቸው እስከ ጀማሪዎቻቸው ድረስ በተመሳሳይ ልሳን ተቀባብለውታል። ይህንን አጀንዳ እጅግ ከመውደዳቸው የተነሳ ስለመጽሀፍ ቅዱስ ጥናት ከተጻፈ መጽሀፍ ውስጥ ሳይቀር አጀንዳውን ሸጎጥ አድርገውት ሲያልፉ ታገኙታላችሁ። መምህር ያሬድ ሽፈራው “የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥ” በሚለው መጽሀፉ ሁለተኛው ቅጽ ላይ በገፅ 37 ላይ ስለዚሁ ጉዳይ ሊዘረዝር ሞክሮ ታገኙታላችሁ።

አንዳንድ እስልምናን በመሀየስ በአማርኛ ቋንቋ መጽሀፍ የፃፉ ሰዎች ደግሞ በዚያው መጽሀፋቸው ያላስተዋሏቸው ተቃርኗዊ ድምዳሜዎችን በዚህ ርዕስ ዙሪያ ፈጽመው ታገኛላችሁ። ለምሳሌ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያወሩ ሁለት መጽሀፍትን ጠቅሸ በቀላሉ ላሳያችሁ።

፩- መጋቢ ዲሰን መንዲድ የተሰኘ ፀሀፊ “እውነቱ ይህ ነው” በሚል ርዕስ ባሳመው መጽሀፉ ገፅ 107 ጀምሮ ቁርአን “ከመጽሀፍ ቅዱስ ስለኮረጃቸው ታሪኮች ያወራል”። የሚገርማችሁ ግን ከዚያ በፊት ጥቂት ገፅ ቀደም ብሎ የቁርአንና የመጽሀፍ ቅዱስ መስማማት በተመለከተ ሲያወራ “..ቁርአንን ሙሉ በሙሉ ስናጠናው የሚያስተምረው ትምህርት ከመጽሀፍ ቅዱስ ጋር የማይስማማና ተቃራኒ ሲሆን ..” ብሎ ሲያትት ነበር። አስቡት እንግዲህ ከመጽሀፍ ቅዱስ ጋር የማያስማማና ተቃራኒ ያሉትን መጽሀፍ ነው መልሰው ደግሞ ከዚያው መጽሀፍ ኮርጇል የሚሉት 🙂 ጸሀፊው ትውስታው አጭር በመሆኑ ምክንያት እንጅ ሁለቱን አርጊውመንቶች አንድ መጽሀፍ ላይ ለመጠቀም አይቸኩልም ነበር።

፪- አማን ገረመው የተሰኘ ፀሀፊ ስሞቹን የሙስሊም በማድረግ ከሚያሳትማቸው መጽሀፍት ውስጥ አንዱ የሆነው “ኢስላም መለኮታዊ ሀይማኖት ነውን?” በተሰኘው መጽሀፉ ገፅ 103 ላይ የቁርአን ምንጭ ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ አንዱ “ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” መጽሀፉን ከክርስቲያኖች የተማረው” እንደሆነ ለማስረዳት ሲደክም እናየዋለን። የሚያስቀው ክፍል ግን ቀደም ብሎ ከገፅ 63 ጀምሮ ደግሞ “የቁርአን ምንጭ ሰይጣን ነው” በሚል ሊያስረዳ ሲደክም እንደነበር ስታሳስታውሱ ነው። አንድ ሰው የቁርአን ምንጭ መጽሀፍ ቅዱስ ነው ብሎ “ከተነተነ” በኃላ መልሶ “ቁርአን የሰይጣን ቃል ነው” ካለ በተዘዋዋሪ መጽሀፍ ቅዱስ የሰይጣን ቃል መሆኑን መስክሯል ማለት ነው።

የአብዛኛዎቹ የክርስቲያን ፀሀፍት የለመደ ስህተት ይህ ነው። ዋነኛ ግባቸው እስልምናን መተቸት ብቻ ስለሆነ የሚሰድሯቸው አርጊውመንቶች በራሱ እርስበርስ እንደማይባሉ ዞረው ቸክ ማድረግ አይችሉም።

እንደ መነሻ ይህንን ካልን ዛሬ ወደተነሳንበት አጀንዳ ለማለፍ እንሞክር። ዛሬ በመጠኑ ላሳያችሁ የምሞክረው በተደጋጋሚ የሚነሳው የኩረጃ ትርክት ከአመክንዮና ከማስረጃ አንፃር የሚቀርቡ ድረታዎች መሠረት አላቸውን? የሚለውን በመጠኑ ነው።

1- መመሳሰል ሁሌም ኩረጃ አይደለም

ስለቁርአን ኩረጃ የሚያነሱ ክርስቲያኖች የሚነሱበት አንድ የተሳሳተ ምንስኤ/Premise/ አለ። እሱም ቁርአን ውስጥ የሚገኙና ከመጽሀፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሉ ታሪካዊም ሆነ አስተምህሯዊ ምንባቦች ከመጽሀፍ ቅዱስ የተቀዱ ብቻ ናቸው የሚል ነው። የዚህ መሠረቱ መጽሀፍ ቅዱስ ቅድሚያ የነበረ መጽሀፍ ከመሆኑ አንፃር መመሳሰሎች ካሉ በኩረጃ ሊወነጀል የሚገባው የኃለኛው ነው የሚል ጥቅል ድምዳሜ ነው። ይህ ድምዳሜ ግን ሁሌም ትክክል አይሆንም። ከኔ በፊት የነበሩ ግለሰቦች የተናገሩት እውነት እኔ በዘመኔ ብደግመው ኩረጃ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ 1+1 ስንት እንደሆነ ከኔ በፊት የነበሩ ሰዎች የሚያውቁትና የገለፁት ሁኔታ ነው። ያ ማለት ግን ዛሬ ላይ እኔ 1+1 ስንት ነው? ተብየ ብጠየቅና 2 ብየ ብመልስ ከነሱ ቀድቻለሁ ማለት አይደለም። ይህ ከሰው የማትቀዳው ዝንተ አለም የማይቀያየር እውነታ ነው። በተመሳሳይ ምንጫቸው አንድ የሆኑ ነብያት ያመጡት መልዕክት በይዘት ቢመሳሰል አንደኛው ከአንደኛው ቀድቶ ሳይሆን መሠረቱ አንድና አንድ ስለሆነ ብቻ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለክርስቲያኖች እንደ አብነት የተወሰነ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ ከኦሪትም ሆነ ከወንጌላት መፃፍ በፊት ከአይሁድም ሆነ ከክርስትና እምነት በፊት የነበሩ እምነቶች ውስጥ መጽሀፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሰሉ አመለካከቶች አሏቸው። የጥንት ፋርሶች/Persian Religion/ ብንመለከተ በከፉ መናፍስትና በአምላክ ማንነት ዙሪያ በመጠኑም ቢሆን ከክርስትናው ጋር የሚያስማሙ አስተምህሮቶች ነበሩት። ያ ማለት መጽሀፍ ቅዱስ ከነዚህ እምነቶች ነው ኮርጆ አስተምህሮውን የቀመመው ማለት ነው? ከዚህ በተጨማሪ የጥንት ሜሴፖታሚያ ሀይማኖት ዘንድ የሚታመነውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ታሪክ ከመጽሀፍ ቅዱሱ የኖህ ታሪክ ጋር ይመሳሰላልና ምንጩ እሱ ነው ማለት ነው?

2- በኩረጃ የተፈረጁ ታሪኮች

ተኮርጀዋል በሚል በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ታሪኮች በዋነኛነት ጥንተ ነገር አጥኝዎች/Orentalists/ የገለጿቸው ናቸው። ለዚህ ስራ በብዙዎች ዘንድ እንደ መነሻ ተደርጎ የሚቀርበው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አብርሐም ጊገር በተሰኘ አይሁድ የተፃፈው መጽሀፍ ነው። መጽሀፉ እንዲሁ መመሳሰሎችን ከመዘርዘር በዘለለ በነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ጊዜ የትኛው የአይሁድ መጽሀፍ በየትኛው ክፍል እንደነበር እራሱ አያትትም። ከዚያም በተጨማሪ ነብዩ ሙሐመድን “ﷺ” በምን መልኩ ይህን ሊያውቁ ቻሉ? የትኛው ራባይ አስተማራቸው? የሚለውን አሰመልክቶም ምንም የሚሰጠው ማብራሪያ የለም። ይህንን በመያዝ ክርስቲያኖቹ በእንግሊዝኛ አጅግ ብዙ መጽሀፎችን አዘጋጅተዋል። በአንድ ወቅት ከሸይኽ አህመድ ዲዳት ጋር የተከራከረው አረብ ክርስቲያን አኒስ ሽሮሽም የአብርሀምን ስራ መሠረት አድርጎ መጽሀፍ አሰናድቶ ተመልክቻለሁ። የሀገራችን ተርጓሚዎችም እንደተመቻቸው ልክ የተወሰኑትን በየስራዎቻቸው ለመዝገን ሞክረዋል። መምህር ያሬድ ሽፈራው “የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥ” በሚለው ስራው ቅጽ ፪ በገፅ 37 ከብሉይ ኪዳን ሁለት ጠቅሷል። መጋቢ ዲሰን መንዲድም በተመሳሳይ “እውነቱ ይህ ነው” በተሰኘው መጽሀፉ ገፅ 107-109 ባለው ክፍል ከብሉይ ኪዳን 12 ለመጥቀስ ሞክሯል።

❐ ታዲያ እነዚህ መመሳሰሎች ኩረጃዎች ናቸው?

ከላይ እንደገለፅኩት የታሪኮቹ መመሳሰል “ኩረጃ ነው” የሚል ድምዳሜ ውስጥ አይከተንም። የኖህ አስተምህሮና የሙሴ አስተምህሮ መመሳሰል አንደኛው ኮራጅ ነው አያስብልም። ሁለቱም መሠረታቸው ተመሳሳይ ከመሆኑ አንፃር የአስተምህሯቸው መመሳሰል የሚጠበቅ ነው። ከዚያ በዘለለ ደግሞ እርምት የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ቅጥፈቶችም አሉ። ለአብነት አንዳንድ ፀሀፍት ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ከብሉይና አዲስ ብቻ ሳይሆን ከአይሁድ ታልሙዶችም ጭምር ወስደዋል የሚሉ ክሶችን በማቅረብ ብዙ መመሳሎችን ይጠቅሳሉ። የመጽሀፍቱን መብዛት የተመለከተ ተራ ሰው እንኳን ቢሆን “ነብዩ ሙሐመድ ከአይሁዳውኑም በላይ ስለነዚህ ሁሉ መጽሀፍት የሚያቁ ሊቅ ነበሩንዴ?” ብሎ መገረሙ አይቀርም። የሚጠቀሱ የአይሁድ ምንጮች ብዛት ምን ያክል ክሱ እንደተጋነነ ያሳያል። ወይንም እንደ እውቁ ኦሬንታሊስት ኸርበርት በርግ ገለፃ  Polemic/ ስህተትን የመፈለግ ብቻ አዝማማያን የተከተሉ ናቸው።

ከነዚህ ውስጥ ግን ምናልባት መዳሰስ የሚኖርባቸው የተወሰኑ ቅጥፈቶች ይኖራሉ። ለአብነት በቁርአን የተጠቀሰው የሰበዕ ታሪክ (በሱራ 27) በአይሁድ መጽሀፍት ውስጥ ይገኛል የሚለው የተዛባ ክስ ነው። ይገኝበታል የተባለው የመጽሀፈ አስቴር “ታርጉም” መጽሀፍ የተፃፈበትን አመት ለተመለከተ ሰው ከነአካቴው ከቁርአን በኃላ እንደሆነ ይገነዘባል። የመጀመሪያው ታርጉም የተፃፈው በ700 ገደማ ሲሆን ሁለተኛው ታርጉም ደግሞ የተፃፈው በ800 አመት ገደማ ነው። ይህ ማለት ከነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” መሞት ከብዙ አመታት በኃላ ማለት ነው (“Esther”, The Jewish Encyclopedia ገፅ 238)

እንደ ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ገለፃ ከሆነ ደግሞ የዚህ መጽሀፍ ፀሀፊ የተወሰኑ የአረብኛ ፁሁፎችን እንደምንጭነት ተጠቅሞ ነበር ይለናል (Targum Sheni”, Encyclopaedia Judaica) ይህ ማለት ፀሀፊው እራሱ የነበረው ከነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ህልፈት ከብዙ አመታት በኃላ ሲሆን ለዚህ ፁሁፉም የተለያዩ አረብኛ ምንጮችን ተጠቅሞ ነበር። ከዚህ የምንረዳው የመመሳሰሉ ምክንያት ቁርአን ከዚህ መጽሀፍ በመውሰዱ ሳይሆን ኃላ ላይ የመጣው ይህ ግለሰብ ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ እንዳለው ቁርአንን እራሱንም ሆነ ሌሎች ቁርአንን መሠረት አድርገው የተፃፉ አረብኛ ፁሁፎችን በመጠቀሙ ሳቢያ ነው።

❐ ሲጠቃለል

የኩረጃ ታሪኮች ከላይ ከጠቀስናቸው ሁለት ምክንያቶች አይወጡም። አንደኛው ቁርአን መለኮታዊ ከመሆኑ አንፃር ቀደምት ነብያት ካስተማሯቸው ትምህርቶች ጋር የሚመሳሰሉ ይዘቶችን መያዙ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከታች እንደገለፅነው በእርዕስቱ ዙሪያ የሚነሱ ቅጥፈቶች ናቸው። አሏህ ﷻ ቢፈቅድና እድሜውን ቢሰጠኝ ከቅጥፈቶቹ ብዙዎችን በአሏህ ﷻ ፍቃድ ወደፊት ለማብራራት እሞክራለሁ። ለመግቢያ ይሆን ዘንድ በአርዕስቱ ዙሪያ የፃፍኩት ፁሁፍ ይህንን ይመስላል፤ ወቢሏህ ተውፊቅ ወሰላሙ ወረህመቱላሂ ወበረካቱሁ..!