የማይነጣጠሉት ሲነጣጠሉ

ሼር ያድርጉ
150 Views

የስላሴ ዶክትሪን እንደሚያስተምረው አንድ አምላክ በሶስት አካላት የተገለፀ ሲሆን እነዚህም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ናቸው። እነዚህ አካላት የማይነጣጠሉ ሲሆኑ በአካልም ደግሞ አንድ አይደሉም። ይህም ማለት አብ ብቻውን አምላክ አይደለም፣ ወልድም ብቻውን አምላክ አይደለም በተመሳሳይ መንፈስ ቅዱስም ብቻውን አምላክ አይደለም፤ ነገር ግን ሁሉም በአንድነት አምላክ ይሆናሉ።

ይህ በምስራቅም ሆነ በምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተመሳሳይ የሆነ የእምነት ዶክትሪን ነው። ከነዚህ ከሶስቱ አንዱን ነጥሎ አውጥቶ የተቀሩትን ሁለቶች ብቻቸውን አምላክ ናቸው ተብለውም አይጠሩም። አምላክ ለመባል እነዚህ ሶስት አካላት በአንድ ላይ መኖር አለባቸው፤ ያም ሆኖ ግን በጥሪ ደረጃ ሶስት ሳይሆኑ አንድ ተብለው ነው የሚጠሩት። አካላቱ ሶስት ቢሆኑም መለኮቱ አንድ ብቻ ነው ተብሎ ይታመናል።

እንግዲህ ይህ ከሆነ ከሶስቱ አካላት መካከል አንደኛው ብቻውን ሶስቱ አንድ ላይ ከሚሰጡት «ሀያሉ አምላክ» ጋር እኩል አይሆንም። ያ ማለት ተጣምረው የሚሰጡት «ሀያሉ አምላክ» ከሁሉም አካላት ይበልጣል ማለት ነው። ጉዳዩ ይህ ከሆነ ታዲያ እነዚህ አካላት የዛ ሀያል አምላክ ክፍልፍል አማልክት ናቸው ማለት ነው። ነገር ግን ስላሴያውያን ይህንን ያስተባብላሉ – ሲያስረዱንም – እያንዳንድ አካል ለአንዱ የተሟላ አምላክ እኩል ድርሻ እንዳላቸው ይነግሩናል። ጥያቄው ታዲያ «አንዱ አምላክ እዚህ ውስጥ የቱ ጋ ነው?» የሚል ነው። ለስላሴ በአብዛኛው የሚቀርበው ማስተባባያ «ሚስጥር ነው» የሚለው ነው፤ ይህ “ሚስጥር ነው” የሚለው ማስተባበያ ርዕሱን አስመልክቶ የሚመጡለትን ጥያቄዎች መመለስ ተስኖት ዘመናትን ተሻግሯል።

የክርስቲያን ቲየሎጂያን የሆኑት ሮጀር ኦልሰንና ክርስቶፎር ሃል ይህንን አስመልክቶ ሲናገሩ “እንደ ብዙ ክርስቲያኖች እምነት የስላሴ ዶክትሪን በቀላሉ የማንረዳውና ከጭንቅላታችን በላይ እንደሆነ ያምናሉ” [1]

ከዚህ በታች አብሬ የማያያዝላችሁን የካቶሊክ ፍሬስኮ ተመልከቱት። በስዕሉ እንደምትመለከቱት “አብ” ይህችን ምድር ይዟታል። ልጁ ደግሞ መስቀሉን ይዟል መንፈስ ቅዱስንም ልክ እንደ እርግብ አምሳያ አስቀምጠውታል። በዚህ ምስል ውስጥ ስንት አካል ትመለከታላችሁ? አንድ ወይንስ ሶስት? የታለ አንዱ አምላክ? የምንመለከተው ሶስት እንጅ አንድ አይደለም። ቁርዓን ይህንን ሁሉ የሰው ፈጠራ ውዥንብር ይተውት ዘንድ በአጭሩ እንዲህ ይገስጻል

« (አማልክት) ሦስት ናቸው» አትበሉም፡፡ ተከልከሉ፤ ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ” (4:171)

© የሕያ ኢብኑ ኑህ

Reference:

[1] – Olsen, R. E. & Hall, C. A. (2002). The Trinity. Grand Rapids, Michigan: William B. Eerdmans Publishing Company. p. 1

Shortlink http://q.gs/F5Fnn