የመጀመሪያው ሙስሊም ማነው?

ሼር ያድርጉ
615 Views

እውን ቁርአን ይጋጫልን?

ክፍል -3

የመጀመሪያ ሙስሊም ማን ነው?

ይህ ጥያቄ አብዛኛውን ጊዜ ተጠይቆ ምላሽ የተሰጠበት ቢሆንም ተደጋግሞ ከመነሳቱ አንጻር በዚህ ተከታታይ ክፍልም ምላሹን ማቅረብ አስፈላጊ ስለሆነ ኢንሻአላህ ከዚህ በታች መልሶችን ዘርዘር አድርጌ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

(በነገራችን ላይ ይህ ፁሁፍ የዛሬ አራት አመት ለፌስቡክ ጥያቄ አቅርቤው የነበረ ምላሽ ሲሆን እየዘገሙ የሚመጡ ሁሉ እንዲያገልግል ዛሬም በቋሚና ተከታታይ ምላሼ ውስጥ አካትቸዋለሁ)

በነኝህ ሰዎች ተደጋግሞ የሚነሳው ጥያቄ በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፦

“በብዙ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ነብያት ሙስሊም እንደሆኑ ከተገለጸ በኋላ በሌላ ቦታ ደግሞ ነብዩ ሙሀመድ “ﷺ” የመጀመሪያ ሙስሊም እንደሆኑ ይገልጻል ይህ አይጋጭም ወይ?” የሚል ነው።

❐ መንደርደሪያ

መልሱ በአጭሩ “አዎ በርግጥም አይጋጭም” የሚል ነው። እንዴት? ካሉ በጥያቄ መልኩ የሚቀርቡ አንቀጾችን ከታች ካስቀመጥን በኋላ ወደ ምላሹ እንዘልቃለን፡፡

ቁርአን ኢብራሂምን፣ እስማኢልን ሙስሊም ይላቸዋል፡-

رَبَّنَا وَاجْعَلْنَا مُسْلِمَيْنِ لَكَ وَمِن ذُرِّيَّتِنَا أُمَّةً مُّسْلِمَةً لَّكَ وَأَرِنَا مَنَاسِكَنَا وَتُبْ عَلَيْنَا ۖ إِنَّكَ أَنتَ التَّوَّابُ الرَّحِيمُ

«ጌታችን ሆይ! ላነተ ታዛዦችም አድርገን፡፡ ከዘሮቻችንም ላንተ ታዛዦች ሕዝቦችን (አድርግ)፡፡ ሕግጋታችንንም አሳየን፤ (አሳውቀን)፡፡ በኛም ላይ ተመለስን፤ አንተ ጸጸትን ተቀባዩ ሩኅሩኅ አንተ ብቻ ነህና፡፡»
(አል-በቀራህ – 128)

ቁርዓን ያዕቁብና ልጆቹ ሙስሊም መሆናቸውን ይገልጻል፦

وَوَصَّىٰ بِهَا إِبْرَاهِيمُ بَنِيهِ وَيَعْقُوبُ يَا بَنِيَّ إِنَّ اللَّهَ اصْطَفَىٰ لَكُمُ الدِّينَ فَلَا تَمُوتُنَّ إِلَّا وَأَنتُم مُّسْلِمُونَ

በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፡፡ ያዕቁብም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ)፡፡ «ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ» (አላቸው)፡፡
(አል-በቀራህ – 132)

በተመሳሳይ እየሱስ እና ሐዋሪያቱ እንኳ ሙስሊሞች መሆናቸውን ይናገራል፡፡

وَإِذْ أَوْحَيْتُ إِلَى الْحَوَارِيِّينَ أَنْ آمِنُوا بِي وَبِرَسُولِي قَالُوا آمَنَّا وَاشْهَدْ بِأَنَّنَا مُسْلِمُونَ

ወደ ሐዋርያትም «በኔና በመልክተኛዬ እመኑ» በማለት ባዘዝኩ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «አመንን፤ እኛ ሙስሊሞች መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡
(ሱረቱ አል-ማኢዳህ – 111)

ነብዩ ሙሀመድ “ﷺ” የመጀመሪያ ሙስሊም እንደሆኑ የሚገልጽበት አንቀጽ ደግሞ

لَا شَرِيكَ لَهُ ۖ وَبِذَٰلِكَ أُمِرْتُ وَأَنَا أَوَّلُ الْمُسْلِمِينَ

«ለእርሱ ተጋሪ የለውም፡፡ በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ፡፡ እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ» (በል)፡፡
(ሱረቱ አል-አንዓም፣ – 163)

ተጨማሪ ሱረቱ-ዙመር 39፡11-12

❐ አሁን ወደ መልሱ እንዝለቅ!

በመጀመሪያ ኢስላም ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን በመጠኑ እንመልከት፦

ኢስላም የሚለው ቃል ሁለት ትርጓሜዎች አሉት። የመጀመሪያው እጅ መስጠት፤ ያለ ተቃውሞ መታዘዝ የሚል ሲሆን በአረብኛው “ኢስቲስላም” ተብሎ ይጠራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “ሰላም” ማለት ነው ሲሆን በአጠቃላይ ኢስላም ማለት በአጭሩ “ለአላህ ያለ ተቃውሞ በመታዘዝ እጅ በመስጠት ሰላምን መጎናጸፍ” ማለት ነው፡፡

እስልምና ማለት ይህ መሆኑን ከተረዳን ታዲያ ሁሉም ነብያት ሙስሊሞች እንደነበሩ እንረዳለን፡፡ ሁሉም ነብያት ለአላህ እጅ የሰጡ፣ ለፈቃዱ ያደሩ፣ ትእዛዙን የተገበሩ በመሆናቸው በቁርአኑ አገላለጽ “ሙስሊሞች” (ለአላህ ታዛዦች) ተሰኝተዋል፡፡ ኢብራሂም፣ ኢስማኢል፣ ኢየሱስ፣ ሙሳ፣ የእየሱስ ሐዋሪያት፣ ዩሱፍና ሌሎችም በየዘመናቱ የነበሩ አማኞች ሁሉ “ሙስሊሞች” የተባሉትም ከእዚህ አንጻር ነው፡፡ አምላክ ከጥንት ጀምሮ ለሰው ልጅ የመረጠው ሐይማኖትም እስልምና ብቻ ነው፡፡ እርሱም የአምላክን ትእዛዝ ያለ ተቃውሞ መፈጸም ነው፡፡

ታዲያ ነብዩ ሙሀመድ “ﷺ” የመጀመሪያ ሙስሊም መሰኘታቸው ከምን አንጻር ነው? ከተባለ የመጀመሪያነታቸው ከነበሩበት ማህበረሰብ አንጻር ነው የሚል ይሆናል፡፡

ተፍሲር ኢብን ከሲር ለአንቀጹ ማብራሪያ የሰጡትን ማብራያ ይመልከቱ፡፡ ለዚህ ንግግር “ማስረጃው ምንድን ነው? ከተባለ ሌሎችም ነብያቶች ተመሳሳይ ገለጻ ተጠቅመዋል የሚል ይሆናል፡፡

ለምሳሌ ሙሳ የአምላክን አንድ ታአምር ባዩ ጊዜ እንዲህ ብለዋል፡-

“ሙሳም ለቀጠሯችን በመጣና ጌታውም ባነጋገረው ጊዜ፡- «ጌታዬ ሆይ! (ነፍስህን) አሳየኝ ወደ አንተ እመለከታለሁና» አለ፡፡ (አላህም)፡- «በፍጹም አታየኝም ግን ወደ ተራራው ተመልከት፡፡ በስፍራውም ቢረጋ በእርግጥ ታየኛለህ» አለው፡፡ ጌታው ለተራራው በተገለጸ ጊዜ እንኩትኩት አደረገው፡፡ ሙሳም ጮሆ ወደቀ፡፡ በአንሰራራም ጊዜ «ጥራት ይገባህ፡፡ ወዳንተ ተመለስኩ፡፡ እኔም (በወቅቱ) የምእምናን #መጀመሪያ ነኝ» አለ፡፡”
(ሱረቱ አል-አእራፍ ምዕ.7፡143)

ሙሳ ይህንን ቃል ሲጠቀም ከሱ በፊት የነበሩ ነብያት እነ ኑህ አብርሀምና ሌሎችም ነብያትእንዲሁም ምዕመናን አማኞች አይደሉም ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሙሳ ህዝብ አንጻር አላህ ﷻ እንደማይታይ ካረጋገጡና ካመኑ ሰዎች መካከል ሙሳ የመጀመሪያነታቸውን ነው የሚገልጸው፡፡ ይህ አገላለጽ ቁርአን ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ ተጨማሪ እንጥቀስ፦

የፊርአውን ደጋሚዎችም እንዲህ ብለዋል፡-

«እኛ የምእምናን #መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን፡፡» (ሱረቱ አል-ሹአራእ ምዕ.26፡51)

የፊርአውን ደጋሚዎች የመጀመሪያ አማኞች መሆናቸውን ሲገልጹ ሙሳንና ወገኖችን አማኞች አይደሉም እያሉ ነው? አይደለም ይልቅስ ከፊርአውን ወገኖች መካከል የመጀመሪያዎቹ አማኞች መሆናቸው መግለጻቸው ነው ፡፡

ስለዚህም ነብዩ ሙሀመድ “ﷺ” የሌሎች ነብያት እምነት የሆነውን እስልምና የሰበኩ ቢሆንም ከነበሩበት ትውልድ አንጻር የመጀመሪያ ሙስሊም መሆናቸው ነው፡፡ አንቀጹ በአጭሩ ሲብራራ ይህን ይመስላል፡፡ ግጭት ተብለው የሚፎከርባቸው ትችቶች እንዲህ ሲፍታቱ በዚህ መልኩ ገለባዎች ናቸው፡፡

ይቀጥላል

ይህንን ርዕስ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ካስፈለገዎ የኡስታዝ አቡ ሀይደርን ጹሁፍ በተጨማሪነት መመልከት ይችላሉ

የመጀመሪያው ሙስሊም ማነው – ኡስታዝ አቡ ሀይደር

Shortlink http://q.gs/EybCL