የመጀመሪያው ሙስሊም ማነው?

ሼር ያድርጉ
461 Views

አቡ ሀይደር

” قُلْ إِنَّ صَلاَتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ* لاَ شَرِيكَ لَهُ وَبِذَلِكَ أُمِرْتُ وَأَنَاْ أَوَّلُ الْمُسْلِمِينَ ” سورة الأنعام 163-162
“«ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው» በል፡፡ «ለእርሱ ተጋሪ የለውም፡፡ በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ፡፡ እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ» (በል)፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡162-163)፡፡

” قُلْ إِنِّي أُمِرْتُ أَنْ أَعْبُدَ اللَّهَ مُخْلِصًا لَّهُ الدِّينَ* وَأُمِرْتُ لِأَنْ أَكُونَ أَوَّلَ الْمُسْلِمِينَ ” سورة الزمر 12-11
“በል፦ እኔ አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ያጠራሁ ሆኜ እንድግገዛው ታዘዝኩ፤ የሙስሊሞችም መጀመሪያ እንድሆን ታዘዝኩ።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡11-12)፡፡

በነዚህ ሁለት ቁርኣናዊ ጥቅሶች ውስጥ ‹‹የሙስሊሞች መጀመሪያ›› የሚል ቃል አልለ፡፡ ወገኖቻችንም ይህን ቃል በመያዝ፡ እስልምና የተጀመረው በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነው፡፡ እሳቸው የመጀመሪያ ሙስሊም ተብለዋልና፡፡ ይህ ደግሞ ከሳቸው በፊት ሙስሊም እንዳልነበረ ይጠቁማል እያሉን ነው፡፡ የኛም ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

1/ ኢስላም የነቢያት ሃይማኖት ለመሆኑና፡ ነቢያትም ሙስሊሞች ለመሆናቸው በክፍል ሁለት ትምህርታችን ላይ ዘጠኝ ምሳሌዎችን ለአብነት አቅርበናል፡፡ ይህ በራሱ እናንተ የሄዳችሁበትን አካሄድ ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡ እሳቸውን የመጀመሪያ ሙስሊም ናቸው ስንል ከሳቸው በፊት የነበሩት ነቢያት ሙስሊም አልነበሩም ማለትን ካስያዘን፡ ታዲያ ነቢያትን ካፊሮች (ከሀዲያን) ነበሩ እንበላቸው? ሌላ ሶስተኛ ምርጫ የለምና!! ወይ ሙስሊም ወይንም ደግሞ ካፊር ማለት!፡፡ ዓለም ላይ ያለ ሰው ከነዚህ ሁለቱ አይወጣም (ሱረቱ-ተጋቡን 64፡2)፡፡

2/ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከላይ ባየናቸው ሁለት ቁርኣናዊ አንቀጾች መሰረት ‹‹የሙስሊሞች መጀመሪያ›› ተብለው መጠራታቸው፡ ከሳቸው በፊት ሙስሊም አለመኖሩና ሳይሆን የሚያመላክተው፡ እሳቸው ለዚህ ኡምማ ፈር ቀዳጅና ብርሀን ሰንጣቂ፡ የመጀመሪያው ሙስሊም መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ መጀመሪያነታቸው ከተላኩበት ማኃበረሰብ አንጻር ነው ሊታይ የሚገባው እንጂ፡ ከአጠቃላይ የሰው ዘር አንጻር መሆን የለበትም፡፡

ታላቁ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኝ (ሙፈሲር) አል-ሓፊዝ ኢብኑ ከሢር (701-770) ረሒመሁላህ፡ በዚህ ዙሪያ እንዲህ ይላሉ፡-

وقال السدي في قوله : ( قُلْ إِنِّي أُمِرْتُ أَنْ أَعْبُدَ اللَّهَ مُخْلِصًا لَهُ الدِّينَ * وَأُمِرْتُ لِأَنْ أَكُونَ أَوَّلَ الْمُسْلِمِينَ ) الزمر/ 11، 12 ، قال : ” يعني من أمته صلى الله عليه وسلم ” .”تفسير ابن كثير” (7 /89) .
አል-ኢማም ሱድዲይ (ረሒመሁላህ) ‹‹የሙስሊሞችም መጀመሪያ እንድሆን ታዘዝኩ›› የሚለውን አንቀጽ፡- ከኡምመታቸው (ከተላኩበት ማኃበረሰብ) አንጻር ነው በማለት ገልጸዋል፡፡ (ተፍሲር ኢብኑ ከሢር፡ ሱረቱ-ዙመር 12)፡፡

ኢማሙል ቁርጡቢይም (ረሒመሁላህ) በበኩላቸው እንዲህ ይላሉ፡-

وقال القرطبي رحمه الله :” فإن قيل : أوليس إبراهيم والنبيون قبله ؟ قلنا عنه أجوبة … ومنها : أنه أول المسلمين من أهل ملته ؛ قاله ابن العربي ، وهو قول قتادة وغيره ” انتهى .
“الجامع لأحكام القرآن” (7 /155) ، وينظر : “تفسير الطبري” (21 /270)

‹‹እሳቸው የሙስሊሞች መጀመሪያ ሲባሉ፡ ኢብራሂምና ሌሎች ነቢያት ከበፊታቸው አልነበሩምን? ከተባለም፡ ለዚህ ምላሾች ይኖረናል፡፡ አንደኛው፡- እሳቸው ‹‹የሙስሊሞች መጀመሪያ›› የተባሉት፡ ከተላኩበት ማኃበረሰብና (ኡምመት) ከተከተላቸው ህዝብ አንጻር ነው የሚል ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ኢብኑል-ዐረቢ እንደዚሁ ገልጸውታል፡፡ እንዲሁም የታቢዒዩ ቀታደህ እና የሌሎችም አቋም ነው›› (ቁርጡቢይ፡ አል-ጃሚዑ ሊአሕካሚል-ቁርኣን 7/155)፡፡ በተጨማሪም ተፍሲር ኢብኑ ጀሪር አጥ-ጠበሪይ (ጃሚዑል በያን 21/270) ይመልከቱ፡፡

አዎ! የሳቸው ‹‹የሙስሊሞች መጀመሪያነት›› ለተላኩለት ለዚህ ማኃበረሰብ ነው፡፡ ሌላው ሙስሊም ሙስሊም የተሰኘውና የሐቅን ጎዳና ያገኘው በሳቸው ሰበብ ነውና፡፡ በተጨማሪም ይህ ‹‹የመጀመሪያ›› የሚለው አነጋገር በአንጻራዊነት ሊቀርብ እንደሚችል፡ የቅዱስ ቁርኣን ድጋፍ አለን፡፡ እሱም ሌላ ማጠናከሪያ ይሆነናል፡፡ ቀጣዩን ምሣሌ እንመልከት፡-

ሀ/ ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም)፡-

” وَلَمَّا جَاء مُوسَى لِمِيقَاتِنَا وَكَلَّمَهُ رَبُّهُ قَالَ رَبِّ أَرِنِي أَنظُرْ إِلَيْكَ قَالَ لَن تَرَانِي وَلَكِنِ انظُرْ إِلَى الْجَبَلِ فَإِنِ اسْتَقَرَّ مَكَانَهُ فَسَوْفَ تَرَانِي فَلَمَّا تَجَلَّى رَبُّهُ لِلْجَبَلِ جَعَلَهُ دَكًّا وَخَرَّ موسَى صَعِقًا فَلَمَّا أَفَاقَ قَالَ سُبْحَانَكَ تُبْتُ إِلَيْكَ وَأَنَاْ أَوَّلُ الْمُؤْمِنِينَ ” سورة الأعراف 143
“ሙሳም ለቀጠሯችን በመጣና ጌታውም ባነጋገረው ጊዜ፦ ጌታዬ ሆይ! (ነፍስህን) አሳየኝ ወደ አንተ እመለከታለሁና አለ (አላህም) ፦ በፍጹም አታየኝም፣ ግን ወደ ተራራው ተመልከት፤ በስፍራውም ቢረጋ በእርግጥ ታየኛለህ አለው፤ ጌታውም ለተራራው በተገለጸ ጊዜ ንኩትኩት አደረገው፤ ሙሳም ጮኾ ወደቀ፤ በአንሰራራም ጊዜ ጥራት ይገባህ፤ ወዳንተ ተመለስኩ፤ እኔም (በወቅቱ) የምእመናን መጀመሪያ ነኝ አለ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡143)፡፡
በዚህ አንቀጽ ስር ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ‹‹የምእመናን መጀመሪያ ነኝ›› እያለ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን፡ ከሱ በፊት የነበሩት እነ፡- ዩሱፍ፣ የዕቁብ፣ ኢስሐቅ፣ ኢስማዒል፣ ሉጥ፣ ኢብራሂም፣ ኑህ… ሙእሚን አልነበሩም ማለቱ አይደለም፡፡ ሊልም አይችልም፡፡ ማለት የተፈለገው ግን፡ ከህዝቦቹ በማመን ቀዳሚው እሱ መሆኑን መግለጹ ነው፡፡ ወይንም ደግሞ በተራራው ላይ የተፈጸመውን አስደናቂ ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ፡ አላህ በዚህ ምድር ላይ በፍጹም ሊታይ እንደማይችል ቀድሞ ያመነ እሱ ነው ማለት ነው፡፡ ከሱ ጋር የነበሩት ሰባዎቹ ግን አላህን ካላየነው በስተቀር አናምንልህም ብለውት ነበርና (አል-በቀራህ 55-56)፡፡ ይህ መጀመሪያነት ምክንያትን መሰረት ያደረገ እንጂ፡ ሌላ አይደለም፡፡

ለ/ የፊርዐውን ደጋሚዎች፡-
” قَالُوا لَا ضَيْرَ إِنَّا إِلَى رَبِّنَا مُنقَلِبُونَ* إِنَّا نَطْمَعُ أَن يَغْفِرَ لَنَا رَبُّنَا خَطَايَانَا أَن كُنَّا أَوَّلَ الْمُؤْمِنِينَ ” سورة الشعراء 51-50
“(እነርሱም) አሉ «ጉዳት የለብንም፡፡ እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን፡፡ «እኛ የምእምናን መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን፡፡»” (ሱረቱ-ሹዐራእ 26፡50-51)፡፡
እነዚህ አስማተኞች በሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በኩል የተፈጸመውን የበትርዋን ተአምር ካዩ በኋላ እጅ ሰጡ፡፡ በሙሳና በሀሩን ጌታ አመኑ፡፡ ፊርዐውንም እኔ ሳልፈቅድላችሁ እንዴት ታምናላችሁ በማለት፡ እጅና እግራቸውን አፈራርቆ በመቁረጥ በስቅላት እንደሚቀጣቸው ዛተባቸው፡፡ እነሱም፡- እኛ ወደ አላህ ተመላሾች በመሆናችን የፈለከውን ብታደርግ ምንም ጉዳት የለብንም፡፡ አሁን የምእመናን መጀመሪያ ሆነናልና በማለት ቁርጡን ነገሩት፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፡- እኛ ‹‹የምእመናን መጀመሪያ ነን›› ሲሉ፡ ምን ማለታቸው ነው? የሚለው ነው፡፡ መቼም ለነሱ መስለም ሙሳ ሰበብ እንደሆናቸው የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ታዲያ እነሱ በአላህ ተውፊቅ (እገዛ)፣ በሙሳ ሰበብ መስለማቸውን እያወቁ ‹‹እኛ የምእመናን መጀመሪያ ነን›› ማለታቸው ትርጉሙ፡- ከፊርዐውን ህዝቦች መካከል ተአምሩ ከተገለጸላቸው በኋላ እውነትን በፍርሀት ሳይደብቁ የመጣው ይምጣ! በማለት ያመኑ ቀዳሚዎች ናቸው ማለት እንጂ፡ ከሰው ዘር ሁሉ የመጀመሪያ አማኝ እነሱ ነበሩ ማለትን በፍጹም አያስይዝም፡፡

ሐ/ በቁርኣን የካዱት፡-
” وَآمِنُواْ بِمَا أَنزَلْتُ مُصَدِّقاً لِّمَا مَعَكُمْ وَلاَ تَكُونُواْ أَوَّلَ كَافِرٍ بِهِ وَلاَ تَشْتَرُواْ بِآيَاتِي ثَمَناً قَلِيلاً وَإِيَّايَ فَاتَّقُونِ ” سورة البقرة 41
“ከናንተ ጋር ያለውን (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ ሆኖ ባወረድኩትም (ቁርኣን) እመኑ፡፡ በርሱም የመጀመሪያ ከሓዲ አትሁኑ፡፡ በአንቀጾቼም ጥቂትን ዋጋ አትለውጡ፡፡ እኔንም ብቻ ተጠንቀቁ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡41)፡፡
ሱረቱል በቀራህ በመዲና የወረደ ሱራ ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይም እያናገረ ያለው አይሁዶችን ነው፡፡ ቁርኣን ተውራትን የሚያረጋግጥ መጽሐፍ ሁኖ ሳለ፡ እናንተ ግን ለምን በቁርኣኑ የመጀመሪያ ከሀዲዎች ሆናችሁ? በማለት እየወቀሳቸው ነው፡፡ አይሁዶች ‹የመጀመሪያ ከሀዲ› ተብለው የተገለጹት፡ ስለሳቸው ነቢይነት ዕውቀቱ እያላቸው፡ በመጽሐፋቸውም ምልክቱ ተነግሮ ሳለ፡ እውነቱን ደብቀው ባለማመናቸው ከአህሉል ኪታብ (ከመጽሐፉ ሰዎች) የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚ ከሀዲያን በመሆናቸው ነው፡፡ ከአጠቃላይ ሰው አንጻር ከታየማ፡ በቁርኣኑ መጀመሪያ የካዱት በመካ የነበሩት ሙሽሪኩ ቁረይሽ ነበሩ፡፡
ስለዚህ ‹‹መጀመሪያነት›› በሁኔታዎች፣ በጊዜና በአይነት ሊከፋፈል ይችላል ማለት ነው፡፡

መ/ አቡ ሀይደር የመጀመሪያው የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው! የሚል ጽሁፍ ብታነቡ፡ ስህተት ነው ብላችሁ ከመቃወማችሁ በፊት ‹መጀመሪያነቱ› ከምን አንጻር ነው ብላችሁ ጥያቄ ማንሳቱ ነው አግባብነቱ፡፡ ፌስቡክ ከተከፈተ ጀምሮ ማለት ነውን? ወይንስ ከኢትዮጵያዊያኖች አንጻር ማለቱ ነውን? ወይንስ ከሙስሊሞቹ በኩል ማለቱ ነው? ወይስ ምን? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡
ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹የሙስሊሞች መጀመሪያ›› ተብለው መገለጻቸው፡ ይህ መጀመሪያነት ለተላኩበት ማኃበረሰብ (ለዚህ ኡምማ) የመጀመሪያው ብርሀን ሰንጣቂ ነቢይ በመሆናቸው እንጂ፡ ከአጠቃላይ የሰው ዘር አንጻር አይደለም፡፡ ከሳቸው በፊት የነበሩት ነቢያት ሁሉ ሙስሊሞች ነበሩና!!! አላህ የበለጠውን ዐዋቂ ነው፡፡

ወሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ

Shortlink http://q.gs/EybBF