የሂጅራ አቆጣጠር ታሪካዊ አጀማመር

972 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1ኛ/ የቃላት ፍቺ፡- ሂጅራ ማለት፡- ቀጥታ ፍቺው ስደት ማለት ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ፍቺው ደግሞ፡- ክህደት ከሰፈነት ሀገርና መንደር፡ አላህን በነጻነት ለማምለክና ህጉን ለመጠበቅ ወደ እምነትና መረጋጋት ወደሰፈነት ሀገር የሚደረግ እንቅስቃሴ (ቅዱስ ጉዞ) ማለት ነው፡፡

2ኛ/ የአላህ መልክተኛና የነቢያቶች ኹሉ መደምደሚያ የኾኑት፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በተወለዱባት በመካ ከተማ፡ እድሜያቸው ዐርባ በሞላ ጊዜ፡ ከዓለማቱ ጌታ ከአላህ ዘንድ ለዓለማት ህዝቦች ነቢይና መልክተኛ ኾነው ተመረጡ፡፡ ተወልደው ባደጉባት የመካ ከተማ ላይ ለአሥራ ሶስት ዓመታት የአላህን መልእክት ለሕዝባቸው፡ የሚደርስባቸውን መከራና ስቃይ በመቋቋም በታማኝነት አድርሰዋል፡፡ በመጨረሻም ከሕዝባቸው በኩል መከራውና ስቃዩ እየበረታባቸው ሲሄድ፡ በጌታ አላህ ትእዛዝ፡ ትውልድ ሀገራቸውን ለቀው፡ ወደ የሥሪብ (የአሁኗ መዲነቱል-ሙነወራህ) ቅዱስ ጉዞ እንዲያደርጉ ትእዛዝ መጣላቸው፡፡ ይህ ቅዱስ ጉዞ ‹‹ሂጅረቱ-ረሱል›› በመባል ይታወቃል፡፡

3ኛ/ ይህን የሂጅራን ክስተት በመያዝ፡ ለሙስሊሞች ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠር አድርጎ መያዝ የተጀመረው፡ ረሱል (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወደ መዲናህ ከተሰዱ ከአሥራ ስድስት/አሥራ ሰባት ዓመት በኋላ (ማለትም እሳቸው ከሞቱ ከስድስት/ሰባት ዓመት በኋላ) በዑመር ኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የኺላፋነት (ዘመነ-ንግሥና) ጊዜ ነው፡፡

4ኛ/ ኢማሙ-ሱሀይሊ (ረሒመሁላህ) ‹‹ረውዱል-ኡንፍ›› በተሰኘው ኪታባቸው ላይ እንደገለጹት፡ ሶሓቦች (ረዲየላሁ ዐንሁም) ይህን የሂጅራን ቀን የዘመን መቁጠሪያ አድርገው መጠቀምን የመረጡት እንዲህ ከሚለው የአላህ ቃል በመነሳት ነው፡-

” لَا تَقُمْ فِيهِ أَبَدًا لَمَسْجِدٌ أُسِّسَ عَلَى التَّقْوَى مِنْ أَوَّلِ يَوْمٍ أَحَقُّ أَنْ تَقُومَ فِيهِ فِيهِ رِجَالٌ يُحِبُّونَ أَنْ يَتَطَهَّرُوا وَاللَّهُ يُحِبُّ الْمُطَّهِّرِينَ ” سورة التوبة 108
“በእርሱ ውስጥ በፍጹም አትስገድ፡፡ ከመጀመሪያ ቀን ይዞ በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሠረተው (የቁባ) መስጊድ በውስጡ ልትሰግድበት ይልቅ የተገባው ነው፡፡ በእሱ ውስጥ መጥራራትን የሚወዱ ወንዶች አልሉ፡፡ አላህም ተጥራሪዎችን ይወዳል፡፡” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡108)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹‹ከመጀመሪያ ቀን›› የሚል ቃል አልለ፡፡ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው፡ በአንጻራዊነት ካልኾነ በስተቀር፡ በልቁ የመጀመሪያ ቀን ተብሎ የሚጠራ ነገር የለም፡፡ (ከሱ በፊትም ሌሎች ቀናት ስለሚኖሩ ማለት ነው)፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ ግን ‹‹የመጀመሪያ ቀን›› የሚለው የተጠቀሰው፡ ኢስላም በግልጽ ይፋ የወጣበት፡ አላህን በነጻነት ያለ-ምንም ስጋት መዲናህ በሚገኘው መስጂድ ቁባእ ውስጥ ማምለክ ስለተቻለበት፡ እንዲሁም መስጂድ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተገነባበት፡ ይህን ቀን የመጀመሪያ ብሎ ሰየመው፡፡ በዛው መልኩ ሶሓቦችም በስምምነት ከዚህ ጊዜ በመነሳት የዘመን አቆጣጠርንም ጀመሩ ማለት ነው፡፡ (አር-ረውዱል ኡንፍ 4/255)፡፡ (በመክተበቱ-ሻሚላህ ላይ ደግሞ 2/331 ይመልከቱ)፡፡

5ኛ/ ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ የሂጅራን ታሪካዊ አጀማመር ምክንያት ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ፡- ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠርን ከምን እንጀምር? ለሚለው ሀሳብ፡ አራት ዋና ዋና የተስማሙባቸው ምክንያቶች ቀርበው ነበር፡፡ እነሱም፡- የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የልደት ቀን፣ ነቢይ ኾነው የተመረጡበትን ቀን፣ ወደ የሥሪብ (የአሁኗ መዲና) ያደረጉትን የስደት ቀን እና የሞቱበትን ቀን፡፡ ከዛም የሂጅራ ቀን ይሁን! የሚለው በላጭ ሀሳብ ሆኖ ተገኘ፡፡ ምክንያቱም፡- የልደታቸውና ነቢይ ኾነው የተመረጡበትን ቀን በተመለከተ፡ በኢስላም ሊቃውንት ዘንድ መቼ ነበር ቀኑ? የሚለው ኺላፍ (የሃሳብ ልዩነት) ያለበት በመኾኑ፡ ከክርክር የሚወገድ ሀሳብ አይሆንም ማለት ነው፡፡ የሞቱበት ቀን ደግሞ እንዳይኾን፡ ቀኑን ማስታወሱ በራሱ ሐዘንን ያወርሳል በማለት ተዉት፡፡ ስለዚህ የቀረው ሂጅራህ ያደረጉበት ቀን ኾነ ማለት ነው፡፡

6ኛ/ የአላህ መልክተኛ ወደ የሥሪብ (ወዲናህ) የገቡት በሶስተኛው ወር በረቢዑል-አወል ነበር፡፡ ታዲያ የዓመቱ አቆጣጠር ለምን ከሙሐረም ተጀመረ? ለሚለው የተሰጠው ምላሽ፡- ለሂጅራ ስደት ሀሳቡና ውሳኔው ተላልፎ የነበረው በወርኃ ሙሐረም ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ በይዓህ (ቃል-መጋባት) የተከናወነው፡ በዙል-ሒጃህ (ከሙሐረም በፊት ያለው ወር) ላይ ነበር፡፡ ከበይዓው በኋላ የቀጣዩ ወር (የሙሐረም) ጨረቃ ብቅ አለ፡፡ በሙሐረም ወርም የስደቱ ውሳኔ ተከናወነ፡፡ ስለዚህም የዓመቱ አቆጣጠር ጅማሬ ከዚህ ወር እንዲሆን ተወሰነ ማለት ነው፡፡ (ወላሁ አዕለም)፡፡

ኢብኑ ሐጀር (ረሒመሁላህ) በኪታባቸው ‹‹ፈትሑል-ባሪይ›› ላይ እንደገለጹት፡- አባ ሙሳ አል-አሽዐሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ለዑመር ኢብኑል-ኸጥጧብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ከአንተ ዘንድ ዘመኑ ያልተጻፈበት (ያልተገለጸበት) መጽሐፍ እየመጣልን ነው ሲለው፡ ዑመርም ሰዎችን ሰበሰበና በጉዳዩ ዙሪያ አማከራቸው፡፡ ከፊሎቹ፡- እሳቸው ነቢይ ሆነው በተመረጡበት ቀን ይሁን ሲሉ፡ ከፊሉ ደግሞ፡- በሂጅራው ቀን ይሁን አሉ፡፡ ዑመርም ረዲየላሁ ዐንሁ፡ ሂጅራህ እውነትን ከሐሰት የለየች ቀን በመሆኗ በሷ ዘመንን ቁጠሩ! አለ፡፡ ይህም አሥራ ሰባተኛው ዓመት ላይ ነበር፡፡ እነሱም በሂጅራው ቀን መሆኑን ከተስማሙ በኋላ፡ ከፊሎቹ የወሩ መጀመሪያ ረመዷን ይሁን ሲሉ፡ ዑመርም፡- ሙሐረም ነው መሆን ያለበት፡፡ እሱ (ሙሐረም) ሰዎች የሐጅ ስርኣታቸውን ፈጽመው የሚመለሱበት ነውና አለ፡፡ ከዚያም በሙሐረም የመጀመሪያ ወርነት ተስማሙ፡፡ (ፈትሑል-ባሪይ፡ 7/268)፡፡ በሌሎች ዘገባዎችም፡ ይህ የሂጅራህ ቀን፡ የዘመን መቁጠሪያ ጅማሬ እንዲሆን ሐሳብ ያቀረበው ሶሓቢዩ ዐሊይ ኢብኑ አቢ-ጧሊብ ረዲየላሁ ዐንሁ ነው፡፡ ዑመርም ረዲየላሁ አንሁ ይህን ሀሳብ ተቀበለው የሚልም አልለ፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡

7ኛ/ ቀኑን እንደ ዒድ መያዝ፡- በዚህ አዲስ አመት ላይ የ‹‹እንኳን አደረሰህ›› የመልካም ምኞት መግለጫን፡ ሙስሊሙ ለሌላው ሙስሊም ወንድሙ መስጠቱ ይበቃል ወይስ አይበቃም? ለሚለው፡ ሁለት ወይም ሶስት የኢስላም ሊቃውንት ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ አቀርበዋለሁ፡-

ሀ/ ኢብኑ ዑሠይሚን (ረሒመሁላህ)፡- አንድ ሰው ወደ አንተ በመምጣት ‹‹እንኳን አደረሰህ!›› ካለህ፡ አንተም በዛው አምሳያ መልስለት፡፡ ግን አንተ በዚህ (የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ) ጀማሪ አትሁን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሻለው ሀሳብ ይህ ነው፡፡ አንድ ሰው እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ! በማለት፡ የመልካም ምኞት መግለጫውን ቢሰጥህ፡ አንተም፡- አላህ አንተንም በመልካም ያበስርህ! ዓመቱንም የበረካና የመልካም ሥራ ዓመት ያድርገው በለው፡፡ ሆኖም አንተ ሰዎችን በዚህ ሰላምታ ጀማሪ አትሁን፡፡ እኔ ይህ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሰህ! ሰላምታ ከሰለፎች ለመገኘቱ የማውቀው ነገር የለም፡፡

እንደውም ሰለፎች (ሶሓቦች) ሙሐረምን በዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ የኸሊፋነት ጊዜ እንጂ፡ ከዛ በፊት የዓመቱ መጀመሪያ አድርገው ይዘው እንደማያውቁ ዕወቁ፡፡ (ሊቃእ ባቡል-መፍቱሕ ጥያቄ ቁ 835)፡፡ የድምጽ ማስረጃ ለፈለገ ደግሞ ይህንን ያዳምጥ

ለ/ ኢብኑ ባዝ (ረሒመሁላህ)፡- በየአዲስ ዓመቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት መለዋወጥ ከሰለፉ-ሷሊሕ የተገኘ መሰረት ያለው መኾኑን የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ከቁርኣንም ሆነ ከሱንና ሸሪዓዊ መሠረት እንዳለውም የሚያሳይ ነገር አይታወቅም፡፡ ሆኖም፡ በእንኳን አደረሰህ ቀድሞ የጀመረህን ሰው፡ ላንተም እንኳን አደረሰህ! ብለህ መመለሱ ችግር የለውም፡፡ ቀድሞ የሰላምታው ጀማሪ መሆን ላይ ግን ምን መሠረት እንዳለው አላውቅም፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡ (የድምጽ ማስረጃ)

ጠቅለል ለማድረግ፡- የሂጅራን ዓመታዊ አቆጣጠር አስመልክቶ፡ የእንኳን አደረሳችሁ! መልእክት መለዋወጡ፡ ከሰለፎች ያልተገኘ፡ ኢስላማዊ መሠረት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ሆኖም አንድ ሰው አንተን ቀድሞ ‹‹እንኳን ለሂጅራ አዲሡ ዓመት አደረሰህ!›› ቢልህ፡ ድርጊቱን አታውግዘው፡፡ ኃጢአት አልሰራምና የሚል ነው፡፤ ወላሁ አዕለም፡፡

ምንጭ፡- አቡ ዐብደላህ አዝ-ዘሀቢይ