ዙል–ሒጃና አሥርቱ ቀናቶቹ!!

ሼር ያድርጉ
362 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

እንግዲሕ በአላህ ፈቃድ ካላንደር እንደሚያሳየው የፊታችን ጁምዓ/ቅዳሜ የዙል-ሒጃ ወር ይጀምራል፡፡ ዛሬ ዙል–ቂዕዳህ 28 ነው። ዙል-ሒጃ በእስልምና ወር አቆጣጠር አስራ ሁለተኛው (የመጨረሻው) ወር ነው፡፡ በዚህ ወር ውስጥ ካሉት 29/30 ቀናት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት እጅግ የተከበሩ ቀናቶች ናቸው፡፡ መከበራቸውን ከሚያመላክቱት ውስጥ:–

ሀ. አላህ የማለባቸው መሆኑ:–

” በጎህ እምላለሁ።በዐሥር ሌሊቶችም።” (ሱረቱል ፈጅር 1-2)።
ታላቅ የሆነው ጌታችን አላህ የሚምለውም ታላቅ በሆነ ነገር ስለሆነ የቀኑን ክብደት ይገልጽልናል፡፡ እነዚህ አሥር ሌሊቶች የተባሉት የዙል-ሒጃ የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት እንደሆኑ አብዝሓኞቹ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

ለ. እኔን አስታውሱባቸው ማለቱ:–

” ለነሱ የሆኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ፣ በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከማለዳ እንሰሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ፣ (ይመጡሃል)፤ ከርሷም ብሉ፤ ችግረኛ ድኻንም አብሉ።” (ሱረቱል-ሐጅ 28)።

” የታወቁ ቀኖች ” የተባሉት እነዚሁ አሥርቱ ቀናት እንደሆኑ ሙፈሲሮች ያስረዳሉ፡፡ ታዲያ አላህን በማንኛውም ጊዜ ማውሳትና ማወደስ ከመቻሉ ጋር በነዚህ ቀኖች አወድሱት ብሎ ቀኖቹን ለይቶ መጥቀሱ የተለየ ደረጃና ክብር እንዳላቸው ይጠቁማል፡፡

ሐ. ከዱንያ ቀናት ሁሉ በላጭ መሆናቸው:–

ከጃቢር ኢብኒ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በተላለፈው ሐዲሥ ረሱላችን (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡-” ከዱንያ ቀናቶች ሁሉ በላጩ (የዙል-ሒጃ) አሥሩ ቀናት ናቸው ” (ሶሒሕ አል-ጃሚዑ ሰጊር 1133)፡፡
በዚህ መሰረት እነዚህ አስርት ቀናቶች ልዩ ክብር የሚሰጣቸው ናቸው፡፡

ምን እንስራባቸው?

ዐብደላህ ኢብኑ አባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “መልካም ሥራ ከዙል-ሒጃ አሥርቱ ቀናት በልጦ አላህ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነበት ቀናት የለም፡፡” ሶሓባዎችም፡- በአላህ መንገድ ጂሐድ ማድረግም (ጠላትን መታገልም) ቢሆን? ሲሉ፡ እሳቸውም፡- አዎ ጂሐድም ቢሆን! ሰውየው ከነፍሱና ከንብረቱ ጋር በዛው ሳይመለስ የቀረ ካልሆነ በስተቀር አይበልጥም ” (ቡኻሪይ)።

ታዲያ ያለምንም የመግቢያ ክፍያ እንዲህ ዐይነት ታላቅ ኤግዚቢሽን ከተዘጋጀልን እኛስ ለመሳተፍ ምን ያህል ወስነናል?፡፡ ጠላታችን ሸይጣን እንዳንጠቀምበት ደፋ ቀና ማለቱ አይቀርምና እኛም አላህን ይዘን እሱን ድል በመምታት ቀኑን እንጠቀምበት፡፡ ከሚሰሩ መልካም ስራዎች ውስጥ፡-

1. ሐጅና ዑምራህ:–

” ዑምራህ ቀጣዩ አመት ዑምራ እስኪመጣ ድረስ (በመሃል ለተፈጸሙ ጥቃቅን ኃጢአት) ማስተሰረያ ነው፣ ትክክለኛ ሐጅ ደግሞ ከጀነት ውጪ ክፍያ የለውም” (ቡኻሪና ሙስሊም)።

2. ጾም:–

የፈለገ ሙሉውን ዘጠኝ ቀን: ካልሆነም የቻለውን ያክል መጾም ይችላል፡፡ዐብደላ ኢብኑ አባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዳስተላለፉት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “መልካም ስራ ከዙል-ሒጃ አስርቱ ቀናት በልጦ አላህ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነበት ቀናት የለም፡፡” በዚህ ሐዲሥ መሠረት ጾም “መልካም ሥራ” የተባለው ሐዲሥ ውስጥ ስለሚካተት በጾሙ የቻለውን ያክል መበርታት ይችላል፡፡

3. አላህን ማውሳት:–

” ለነሱ የሆኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ፣ በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከማለዳ እንሰሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ፣ (ይመጡሃል)፤ ከርሷም ብሉ፤ ችግረኛ ድኻንም አብሉ።” (ሱረቱል-ሐጅ 28)።

ይህ ቅዱስ አንቀጽ አላህን በነዚህ ቀናት ማውሳት: መዘከር እንዳለብን ይነግረናል፡፡ ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ባስተላለፉት ሐዲሥ ላይ ነቢዩ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ ብለዋል፡- “በነዚህ ቀናት ውስጥ ተህሊል (ላ ኢላሀ ኢልለሏህ)፤ተክቢር (አላሁ አክበር)፤ተሕሚድ (አል-ሐምዱ ሊላህ) ማለትን አብዙ” (አህመድ 7/224)

ዐብዱላህ ኢብኑ ኡመር እና አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁም) ወደ ገበያ በመውጣት በተክቢራ ሲያሞቁት ሰዎቹም እነሱን ተከትለው ተክቢራ ይሉ ነበር (ኢርዋዑል-ገሊል: አልባኒይ 651)።

4. ተውበት ማብዛት:–

“…ምእምናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ።” (ሱረቱል አሕዛብ 31)።

5. መልካም ሥራዎችን ማብዛት:–

በኢስላም የመልካም ሥራ በሮች ብዙ ናቸው፡፡ ተቆጥረው አይዘለቁም፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ስራው ላይ ተሳታፊ መሆን ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምረን እሰከ ሩቅ ሰው ድረስ አቅማችን የቻለውን ያህል በመርዳት ወደ አላህ እንቃረብ፡፡

6. በዒባዳህ መጠናከር:–

ከፈርድ ሶላት ቀጥሎ ያሉትን ሱንና ሶላቶችን ማብዛት፤ቁርኣንን ማንበብና ማዳመጥ፡፡

7. ከሐራም መቆጠብ:–

ከላይ የተጠቀሱት መልካም ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የአላህን ተውፊቅ ያላገኘ ሰው ቢያንስ ከሱ እጅና ምላስ ሌሎች ሰላም እንዲሆኑ እራሱን ማቀብ፡፡እሱም ትልቅ ተውፊቅ ነውና፡፡
አላህ ተጠቃሚ ያርገን

#የኡድሑይያህ እርድ

1/ ኡድሑይያህ ማለት:– በዙል ሒጃህ ወር ከአሥረኛው ቀን አንስቶ እስከ አያመ–ተሽሪቅ (አስራ ሶስተኛው ቀን ድረስ) ወደ አላህ ለመቃረብ ሲባል ከቤት እንሰሳት (ግመል፣ ከብት፣ ፍየል/በግ) አንዳቸውን በመምረጥ የማረድ ስርአት ማለት ነው።

2/ የኡድሑይያህ ስርአት በጣም ጠንካራ ሱንና ከሆኑ የአምልኮ ዘርፎች ይመደባል። የአላህ ቃልም:– “ለጌታህም ስገድ፣ በስሙም እረድ” (አል–ከውሠር 3)። ባለው መሠረት በአላህ ሥም ይታረዳል።

3/ የኡድሑይያህ የእርድ ስርአት ሱንና ነው። ዋጂብ አይደለም። የተወው ሰው በኃጢአት አይከሰስም። ሲታረድም ለአላህ ተብሎና በአላህ ሥም ነው የሚታረደው።

4/ የኡድሑይያህ የእርድ ቀናት ከዒዱ ቀን ሶላት መጠናቀቅ ጀምሮ (የውሙ–ነሕር 10ኛው ቀን ማለት ነው) እስከ አያሙ–ተሽሪቅ የመጨረሻው ቀን (11፣ 12 እና 13ኛው ቀን ፀሀይ መግባት ድረስ) የሚቆይ ይሆናል። በጥቅሉ አራት ቀናት ይኾናል ማለት ነው። 10ኛው ሶላቱል ዒድ የሚሰገድበት ቀን (የውሙ–ነሕር)፣ 11ኛው ቀን፣ 12ኛው ቀን፣ 13ኛው ቀን።

5/ በዋጋ ጠንከር ያለ፣ ስጋው በዛና ሞላ ያለ፣ ከነውር የፀዳ፣ የእርድ አይነት መግዛቱ በላጭ ይኾናል። ኡድሑይያህ የነየተውም አካል: ከእርዱ ላይ እራሱም ሊበላ፣ ቤተሰቡንም ሊያበላ፣ ዘመድና ወዳጆቹንም ሊጋብዝ፣ ለምስኪኖችም ሊያከፋፍል ይወደድለታል።

6/ የሚታረደው የእርድ አይነት ግመል ከሆነ አምስት አመት የሞላው፣ ከብት (በሬ/ላም) ከሆነ ሁለት አመት የሞላው፣ ፍየል ከሆነ አመት የሞላው፣ በግ ከኾነ ስድስት ወር ያለፈው ከኾነ ለእርድ የበቃ ይኾናል።

7/ የእርዱ አይነት እውር ወይም አንካሳ ወይም በሽተኛ ከሆነ አይበቃም። ጆሮው ወይም ጭራው የተቆረጠ፣ ጥርሶቹ በመላ የረገፉ ከኾነ ደግሞ እሱን ለእርድ ማቅረብ የተጠላ ይኾናል።

8/ የዒዱል አድሓን እርድ ለመፈጸም የነየተ የአላህ ባሪያ (ወንድም ሆነ ሴት) ወሩ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፡- የሰውነት ጸጉሩን መላጨትም ሆነ መቀነስ፣ የእጁንም ሆነ የእግሩን ጥፍር ማስተካከል፣ ከገላው ላይ የተወሰነ ቆዳንም ቢሆን ቆርጦ ማንሳት አይፈቀድለትም፡፡ ይህ ብይን የሚመለከተው የዒዱን እርድ በራሱ ወጪ ለማረድ የነየተውን ግለሰብ ብቻ ነው፡፡ ቤተሰቦቹን ብይኑ አይመለከታቸውም፡፡

ሰውየው በቀጥታ እራሱም አራጅ ሆነ፡ ወይም በወኪል ቢያሳርድ ኃላፊው እሱ እስከሆነ ድረስ ብይኑ ይመለከተዋል፡፡ ወኪል ሆኖ የሚያርደውን ሰው ግን ብይኑ አይመለከተውም፡፡

ኡሙ ሰለማህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንደነገረችን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የዙል-ሒጃህን ጨረቃ ካያችሁና አንዳችሁም ኡድሑያን (እርድን) ከነየተ፡ ጸጉሩንና ጥፍሩን (ከመቀነስ) ይቆጠብ” (ሙስሊም 1977)፡፡

በሌላ ዘገባ ላይ ደግሞ ‹‹ከጸጉሩና ከሰውነቱ (ቆዳው) ይቆጠብ›› ይላል።

ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ነገር፡ እርዱን የነየተ ሰው፡ በዙል-ሒጃህ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ጸጉሩን ወይም ጥፍሩን ቢቀንስ፡ ከፋራው ‹ካሳው› ተውበትና ኢስቲግፋር ብቻ ነው በማለት ዑለሞች ፈትዋ ሰጥተዋል (ኢብኑ ቁዳማህ፡ አል-ሙግኒይ 9/346)፡፡
አላህ ተጠቃሚ ያድርገን።

Shortlink http://q.gs/Ewigl