ክርስትና ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዴት ገባ?

ሼር ያድርጉ
1,777 Views

ብዙ ክርስቲያን ወገኖቻችን እምነታቸው ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ኢትዮጵያ የነሱ ብቻ ርስት እንደሆነች እና የሌላው እምነት ተከታይ መጤና ስደተኛ ነው የሚል አመለካከት አላቸው።ይህ አመለካከት ስር ሰድዶ በአንዳንድ የሀይማኖት መምህራኖቻቸው ሳይቀር በአደባባይ ሲነገር ደጋግመን ሰምተነዋል። እንደነ ዲያቆን አባይነህ ካሴ ያሉ የቤተ ክርስቲያኗ መምህሮች ደግሞ ከነአካቴው ክርስትና መሠረቱ ኢትዮጵያ ነው ብለው ሳይቀር እንደሚያምኑ ሲናገሩ ሰምተናቸዋል (ብዝሀ ሀይማኖት አንድ ሀገር – በኢትዮጵያ ሬዲዬና ቴሌቭዥን ጣቢያ የተዘጋጀ ዶክመንትሪ) ይህ አመለካከት እውነት በማስረጃ የተደገፈ ነው? ወይንስ በአፈታሪክ የተላለፈና በመደጋገሙ ምክንያት ከጊዜ በኃላ እውነት ተደርጎ የተወሰደ አመለካከት ነው? የሚለውን አስመልክቶ ከዚህ በታች በተወሰነ መልኩ የምንመለከተው ይሆናል።

ክርስትና ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መቸ ገባ? የሚለውን ከማየታችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ ብሎ ሚጠራት አሁን ባለንበት ዘመን ኢትዮጵያ ተብላ ምትጠራውን አገር ነውን? የሚለውን እውነት በመጠኑ መፈተሹ መልካም ነው።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ200 ዓ.ዓ አካባቢ ብሉይ ኪዳን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተረጎመ። ይህም ትርጉም ሰፕቱጀንት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ትርጉም ‹‹ኩሽ›› የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው የግሪኩ ትርጉም ተካው።›› (ቲም ፌሎስ፣ ገፅ 14)። በአጭሩ ብሉይ ኪዳን መጀመሪያ በተፃፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ አንድም ስፍራ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል ቃል የሌለ ሲሆን ያለው በግሪኩ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ከግብፅ በስተደቡብ በዛሬዋ ሱዳን የነበረችውን ‹‹የኩሽ መንግስት›› ጥቁሮች ስለነበሩ ግሪካውያን ጥቁርነታቸውን ለመግለጽ (ፊታቸው በፀሐይ ተቃጥሎ የጠቆረ ለማለት) በቋንቋቸው ‹‹ኢትዮጵያውያን›› አሏቸው።

« ኩሽ፤የካም መጀመሪያ ልጅ፤ ዘፍ. 19፥6-8፤ 1ኛ ዜ,መ 1፥8-10። ኩሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል አገርን ሲያመለክት «ኢትዮጵያ» ተብሎ ተተርጕሟል፤ ዘፍ. 2፥13 » (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 191)

« ኢትዮጵያ፤የቃሉ ትርጕም ጥቁር ማለት ነው፤ ኤር. 13፥23። በግሪክና በመ.ቅ. ጸሓፊዎች አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ከግብጽ በስተደቡብ ጥቁር አባይና ነጭ አባይ እስከሚገናኙበት የነበረ አገርና መንግሥት ነው በመቅ. ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። »
( ያለፈው ምንጭ ገጽ 163 )

ከዚህ በላይ እንዳየነው ዛሬ ባለው ካርታ ላይ ኢትዮጵያ ተብላ የተለገጸችውና መጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያ ብሎ ሚጠራት ኢትዮጵያ የተለያዩ መሆናቸውን ነው።

ቀጥለን “ክርስትና በሐዋርያት ዘመን ገባ” የሚለውን የክርስቲያን ወገኖቻችን አመለካከት እስኪ እንፈትሸው። ለዚህ የተሳሳተ አመለካከት የዳረጋቸውን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 27 ላይ እናገኛዋለን፤ « ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ » ። ይህን ታሪክ ጫፉን በመያዝ አገራችን ላይ ያሉ ክርስቲያን ወገኖች ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ዘመን ነው የሚል ሙግት ያነሳሉ እስኪ ታሪኩን በመረጃ እንፈትሸው፦

“ተነሥቶም ሄደ እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤”— ሐዋርያት 8፥27

በሐዋርያት ሥራ 8፡27 ላይ ‹‹እነሆ የኢትዮጵያ (ኩሽ) ንግሥት የህንዳኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ›› ይላል ይህ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ እየሩሳሌምን ሊሳለም እንደሄደ ተጠቅሷል ይህ ክስተት እ.ኤ.አ በ37 የተፈጸመ ነበር። ይህ የአይሁድ እምነት ተከታይ ኩሻዊ ግለሰብ ለጸሎት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በዚያ በኢየሱስ ተከታይ በተሰበከበት ጊዜ የአክሱም ስርወ መንግስት ክርስትናን ልትቀበል ኢትዮጵያ ገና ሦስት መቶ (300) ዓመታት ይቀራት ነበር፤ የአይሁድ እምነትም በአክሱም አልነበረም። አክሱማውያን ጣኦት አምላኪዎች ነበሩ ይህን በራሳቸው በአክሱማውያን መሪዎች የተጻፉ በርካታ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ያረጋግጣሉ።

«የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥና አምላክ አርዌ የተባለ እባብ እንደ ነበር በአፈ ታሪክ ይነገራል እርሱን ለማረጋጋት ሕዝቡ አዘወትረው ልጃገረዶችን፣ ፍየሎችን፣ በጎችኝና ወተት በመሥዋዕት ያቀርቡለት ነበር ከዕለታት አንድ ቀን ግብሶ ወይም አንጋባ የተባለው ስው ተነሥቶ አርዌን ገደለው ከዚያም የአርዌን እኅት አግብቶ ንጉሥ ሆነ ይህ አፈ ታሪክ አቬስታ ከተባለው የፋርስ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኝ፣ የመጣው ከዚያ ሳይሆን አይቀርም። ዋና ዋናዎቹ የደቡብ ዐረቢያ አምላኮች የሰማይ አምላክ፣ አስታር፣ የጨረቃ አምላከ ሲንና የደቡብ ዐረቢያኝ አልሙጋህ ነበሩ። ኢዛና ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት እነዚህ ጣዖታት በአክሱም መንግሥት ውስጥ አንደ ተመለኩ የሚጠቁሙ ቤተ መቅደሶች ተገኝተዋል የአክሱም ሕዝብም የጦርነት አምላክ የሆነውን ማሕሪምን፣ ምድርንና ባሕርን በድምሩ ሦስት ጣዖታት አምልከዋል እነዚህ ሦስቱ ከዚያ አካባቢ ባሕል ጋር የተያያዙ ስለሆነ፣ በሌላ ቦታ በየትም አልተመለከም »
(ስሜ ታደሰ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 215 )

ከኢዛና መንገስ እና ከፍሬምናጦስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በፊት አክሱሞች ዘንድ የነበረው ሃይማኖት ምንድን ነበር? የሚለውን በተጨማሪ ማስረጃዎች እንመልከት፦

«ክብረ ነገሥታችን እንደሚለው ቀዳማዊ ምኒልክ አባቱ ሰለሞን ዘንድ ሄዶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ታቦተ ጽዮንና የኦሪትን ካህናት ይህ መጥቶ ስለ ነበረ የኦሪት ካህናት ባስተማሩት መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከክርስትና በፊት በኦሪትና በእውነተኛው ኣምላክ እያመለኩ መኖራቸውን ይገልጽልናል። ነገር ግን እንደ እውነቱ የሆነ እንደሆነ እነዚያው ከኢየሩሳሌም የመጡት ወገኖች ወይም የነሱን ሃይማኖት የተቀበለው ፩ዱ ግን በእውነተኛው እግዚአብርና በኦሪት ያምኑ እንደሆነ ነው እንጂ የቀረው ልዩ ልዩ ነገድ በልዩ ልዩ ጣዖትና አማልክት ያመልክ እንደነበረ የታወቀ ነው ይኸንንም ታሪከ ነገሥቱ ሳይቀር « …… ወመጽአ አባ ሰላማ ምስስ አይኑ ሕዝበ ኢትዮጵያል እለ ሀለዉ በሕገ ኦሪት ወ እለ ነበሩ እንዘ ያመልኩ በአርዌ ፡ » …… እያለ ባጭሩ ከኦሪት በቀር ሉች በባብ የሚያመልኩ እንደኔበሩ ይገልጽልናል

(የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ዛጕዬ እስከ ዐፄ ይኵኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በተክለ ጻድቅ መኹሪያ ገጽ 239)

ስለዚህ እነዚህን መረጃዎች መሠረት አድርገን ሐዋርያት ስራ ላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ስናስተውለው የአገራችን ክርስቲያኖች እንደሚሉት ክርስትና በሐዋርያት ዘመን ገባ የሚለው ንግግር ተራ ምኞት ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን በሐዋርያት ሥራ 8፡27 የተጠቀሰችው ሕንዳኬ (ክንዳኬ) የሜሮዌ ንግስት መሆኗን በርካታ ምሁራን ገልጸዋል መጽሐፍ ቅዱስ ገና ተፅፎ ከመሠራጨቱ በፊት እ.ኤ.አ በ79 (ሰባ ዘጠኝ) የሞተው ፕሊኒ (Pliny) ክንዳኬ የተባለችው የሱዳኗ ሜሮዌ ንግስት እንደነበረች ጽፏል። (The Dictionary of Ethiopian Biography, from early times to the end of Zagwe Dynasty, C. 1270 AD., Institute of Ethiopian Studies, Addis Ababa University, 1975, volume one, PAGE 43)

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ መቸ ገባ?

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባባት ወቅት አነጋጋሪ ቢመስልም ግልጽና ቁርጥ ያለ የዘመን ስሌትና ታሪክ እንዳለው በአሁኑ ጊዜ ተረጋግጧል ኢትዮጵያ በ4ኛው ክፍለ ዘመን (330-335 )ክክርስትና እምነት ጋር ተዋወቀች፤ በዘመኑም ዒዛና በመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበረበት ወቅት ነው ይህ ጊዜ ክርስትና እርሾውን እንዳኖረ ከሚገልጹት የማረጋገጫ ምልክቶች ውስጥ ፦

ሀ) አስቀድሞ የአረመኔ ምልክት ያላቸው ገንዘቦች፣ ኋላ ላይ ደግሞ የክርስትና ምልክት ያለው ገንዘብ በገዛ ዘመኑ መቅረጹ፣

ለ) ዒዛና በዘመኑ የፈጸመውን የጦርነት ገድል «ክርስትናቀመስ ባሕርይ ታይቶ መገኘቱ፡» (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰሜ ታደሰ ክፍል አንድ ገጽ 194 )

«ከ330 ዓም በፊትም የክርስትና እምነት በአክሱም ግዛት ውስጥ ስለ መከስቱ ምንም ፍንጭ አይገኝም » ( ያለፈው ምንጭ ገጽ 208 )

የዘመንን ቅደም ተከተል ትተን፣ የአሁኑ ታሪካዊ መረጃችን ክርስትና ከ330 ዓ.ም በፊት በአክሱም ውስጥ አለመኖሩን መጥቀስ ያስፈልገናል «በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ውስጥ ከስፈሩ መረጃዎች በመነሣት ይህ ድርጊት ከ40 ዓ.ም በፊት መፈጸሙ ግልጽ ነው የተጠቆመው ጃንደረባ አይሁድ ስፍረውበት ከነበረው ከግብፅ ስሜናዊ ግዛት ኣካባቢ-ከኤሌፋንታይል ሳይመጣ አልቀረም ከዚህ የተነሣ፣ ህንደኬ የተባለችው ንግሥት ባለ ሥልጣን ምንም ነገር ቢያደርግም አንኳ የወንጌልን የምስራች ቃል ወደ ኣክሱም ግዛት ይዞ አልመጣም የግሪክ የመልክዓ ምድር ተመራማሪዎች ይህ የመንግሥት ባለ ሥልጣን የመጣበት ግዛት ከመጀመሪያው የአስዋን ፏፏቴ አንሥቶ ወደ ደቡብ አስከ ዘመናዊቷ ሱዳን ያለውን ክፍል እንደሚያጠቃልል ይጠቁማል
(ያለፈው ምንጭ ገጽ 209 )

«ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 የሰበሰብነው ታሪክ እፈ-ታሪክ ባይሆንም፣ ክርስትና በአዲሲቱ ኢትዮጵያ ለሚለው እውቀታችን ምንም አስተዋጽኦ እንደማይኖረው ግልጽ ነው የእክሱም ግዛት በ330 ዓ.ም የተቀበለው የክርስትና እምነት ኑቢያን ከመሳሰሉት ምዕራባዊ ኣገሮች የክርስትና እምነት ጋር ግንኙነት ይኑረው እይኑረው ታሪክ የመዘገበው ነገር አይገኝም፡፡ » ( ያለፈው ምንጭ ገጽ 210 )

«ኢላ አሚዳ በ፫፻፴ ዓ.ም. ገደማ በኢትዮጵያ ነገሠ በዚህ ዘመን አንድ የሶሪያ ነጋዴ በቀይ ባሕር ላይ ወደ ሕንድ ሲያልፍ ዘመዶቹ የሆኑና ያስተምራቸው የነበሩ ፪ ክርስቲያን ልጆች ከርሱ ጋር ነበሩ መርከቢቱን ለምግብ አቁመዋት ሳሉ ሁለቱ ልጆች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹ ተገደሉ እነዚህ ልጆችም ፍሬምናጦስና
አኤደስየስ ነበሩ። እነዚህ ልጆች በአንድ ዛፍ ሥር ተቀምጠው ትምህርታቸውን ሲያጠኑ ተገኝተው ወደ ንጉሥ ኤላ አሚዳ አክሱም ተወሰዱ፤ በዚያም በጥበብ እያደጉ ሄዱ ንጉሡ ፍሬምናጦስንና አኤደስየስን በቤተ መንግሥቱ ኃላፊ አደረጋቸው ንጉሡ ኤላ አሚዳ ሲሞት ልጁ ኢዛና ገና ልጅ ስለነበር ንግሥቲቱ ልጅዋ እስኪያግድ ፍሬምናጦስንና አኤደስየስን በመንግሥቱ አስተዳደር እንዲረደት ጠየቀቻቸው። ንጉሥ ኢዛና መንግሥቱን ለማስተዳደር ዕድሜው ሲፈቅድ ፍሬምናጦስንና ኣኤደስየስን እርዳታቸውን እንዲቀጥሉ ደግሞ ጠይቋቸዋል። ኢዛና የድል ሰው በመሆኑ በጦርነት ከኤርትራ ፤ ከሱዳን ፤ ከየመንና ከሌሎችም አገሮች ግዛት እየቆረሰ ወደ አክሱም ግዛቱ ጨምሮአል እስከ ጊዜው ድረስ በግዛት ስፋት ኢዛና የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ነበር በሰላም ጊዜም መንግሥቱን በማስተዋል አስተዳድሯል ፍሬምናጦስም ለንጉሡ ከውጭ ነጋዴዎችን ፤ ግንበኞችንና ሌሎችን ሠራተኞችንም ወደ አክሱም እንዲያስመጣ ምክር ሰጥቶታል እነዚህም ሞያተኞች አክሱምንና ጠቅላላ ግዛቱን በማሻሻል ንጉሡን ለመርዳት የመጡት ከሮም ከግሪክና ከሶሪያ ነበር ።

ፍሬምናጦስና አኤደስዩስ በነርሱ በኩል የክርስቲያን ሃይማኖት ወደ ኢትጵያ ሊገባ የቻለባቸው እና ለብዙ ሕዝብም ወንጌልን የሰበኩ ክርስቲያኖች ነበሩ።
ንጉሡም መንግሥቱን በደህና ሲመራ ሳለ ምንም እንኳን እንዳይሄዱ ቢጠይቃቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ ፈልገው ነበርና ሄዱ ።

አኤደስዩስ ቤተሰቡን ለማየት ሶሪያ ሄዶ እዚያው ቄስ ሆነ፤ ታሪኩን ሁሉ ለሩፋይነስ ስለነገረው በታሪክ መጽሐፍ ውስጥ አስገብቶ ጽፎታል ፍሬምናጦስ ደግሞ ለፓትርያርኩ ለአትናትዮስ ስለ ኢትዮጵያውያን ክርስትና ሊናገር ወደ እስክንድርያ ሔዶ ፤ በአክሱም የሚገኙትን ክርስቲያኖች የሚረዳ ጳጳስም እንዲልክ አክሱም ንጉሥ የተጻፉ ነበር። ንጉሡ በዚህ ጽሑፍ ስለ ራሱ ድል አድራጊነትና ብዙ ሐገሮችን መያዝ አትቷል ። ከነዚህም አገሮች የዘመኑ ቤጌምድር ክፍል ፤ ደንከል ፤ትግሬ እና ሰሜን ኤርትራ ናቸው እንደዚሁም ከሱዳን ክፍልና ቀይ ባሕር ተሻግሮ`የደቡብ ምዕራብ ዐረብን ቆርሶ ለመውሰድ እንደሔደ ገልጿል ።

ምንም እንኳን ስሙ በእርግጥ ባይታወቅም ይህ ንጉሥ በ፫ኛው መቶ ዓ.ም. የአክሱም ንጉሥ የነበረው (አፊላስ) ነው ተብሎ ይታመናል ይህ ንጉሥ የአክሱምን መንግሥት ከማስፋፋቱ ሌላ የጥንታዊቱ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መስራች ተብሏል።

ፍሬምናጦስ ጳጳስ ሆኖ አክሱም ከመጣ በኋላ ኢዛና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክርስቲያን ንጉሥ ሆነ ፤ በጦርነት ላደረገለት እርዳታ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሰጠ ፤ ክርስቲያንነቱንም ለማሳወቅ በኣክሱም ገንዘቦች ላይ የመስቀል ምልክት መረጠ የክርስትናም ሃይማኖት እያደገ ሄደ ቤተክርስቲያናትም ይታነጽ ጀመር ከነዚህም ዝነኛው የአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው ።

_፬፻ ዓመታት ከፍሬምናጦስ በኋላ በ፬፻፪ ዓም. ገደማ ፱ ሰዎች ከሶሪያ ወደ ኣክሱም መጡ ፤ እነርሱም በኋላ ፱ኙ (ተሰዐቱ) ቅዱሳን ተብለው የተጠሩት መነኮሳት ነበሩ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ግእዝኛ በመተርጐም ክርስቲያኖችን ኣስተማሩ ገዳማትን ማሠራት ጀመሩ። ቤተ ክርስቲያናትን በማቋቋም ረዱ የእስክንድርያው ፓትሪያርክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን የአክሱምን ጳጳሳት የሚመድብ እርሱ ነበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ቀን አቆጣጠር ፤ በዓመት ለ 30 ቀናት ፲፪ ወራትና በመጨረሻው ተጨማሪ ቀናት ይጠቀሙ ጀመር በተጨማሪም የግብጻውያን በዓላት እና የክብረ በዓላት ወጋቸውንም ይጠብቁ ነበር ።

በጥንታዊት ኢትዮጵያ በዐረቦች ሴማውያን የመጣው ሳባውያን ሥልጣኔ ዝነኛ ሆኖ ሳለ በ፮ት መቶኛው ዓመት ከበጥሎሜዎች ፫፻ ዓ. ዓለም እስከ ንጉሥ ኢዛና ፫፻ ዓ.ም. እ. ኤ. አ. ገደማ ድረስ የግሪክ ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ተዛመተ ከኢዛናም በኋላ ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ ግሪክኛ እየተረሳ ግእዝ ግን በብዛት እየተሰራ በት ይሄድ ጀመር በ፳፻ ዓ.ም. ግሪክኛ ፈጽሞ በመቅረት ግእዝኛ የአክሱም መንግሥት ዋና ቋንቋ ሆነ ። »

(የኢትዮጵያ ታሪክ በሐሪ አትክንስ ገጽ 4— 6)

➧ ማጠቃለያ

ክርስትና ሀገር በቀል ሀይማኖት ተደርጎ እንዲታመን ለዘመናት ብዙ አፈታሪኮች ተፈጥረው ተሰራጭተዋል። ኢየሱስ ትምህርቱን የሰበከው ፍልስጤም ምድር ሳይሆን ጎጃምና ጎንደር እስኪመስለው ድረስ አማኙ ላይ የተዛነፈ ቀኖና ተጭኖበት ኑሯል። ይህ አመለካከቱም “ክርስትና ሀገር በቀል ሌላው ሁሉ ደግሞ መጤ ነው” የሚል እይታ እንዲኖረው አድርጓል። ይህ ፈጽሞ ስህተት የሆነና መታረም የሚኖርበት አመለካከት ሲሆን ክርስትና እንደ ሌሎች እምነቶች ሁሉ ከውጭ የመጣ ሲሆን ምንጩም መካከለኛው ምስራቅ ነው። ይህ እውነት በፍጹም ተዛብቶ መቅረብ አይኖርበትም።

Shortlink http://q.gs/F4aVb