ከእስልምና ስለወጡ ሰዎች/Apostasy/ የኢስላም ህግጋት

1,421 Views

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

1- መግቢያ

ይህንን አርዕስት አስመልክቶ በምዕራባውያንና ክርስትያን ሚሽነሪዎች ከፍተኛ ክሶች ሲደመጡ ይስተዋላል፡፡ የዚህ ጉዳይ ትችት በነኝህ ክፍሎች ብቻ የሚቆም አይደለም ይልቅስ በኤቲየስቶችና/አምላክ የለም ብለው የሚያምኑ/ እንዲሁም በነጻነት ስም ነጋሪ ለሚጎስሙ ጥቂት የሌላ እምነት አማኞችም ጭምር ነው፡፡ ወደ መልሱ ከመግባታችን በፊት ክርስቲያኖች ነጥቡን የሚያነሱበትን አስገራሚ ምክንያት በመጠየቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስትና በዚህ ዙሪያ ግልጽና የማያወላዳ አቋም እንዳለው ብሉይ ኪዳን ይመሰክራልና፡፡
መጽሀፍ ‹‹ቅዱስ›› በኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 13፡6-9 እንዲህ ይላል፡፡

የእናትህ ልጅ ወንድምህ ወይም ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ ወይም በብብትህ ያለች ሚስትህ ወይም እንደ ነፍስህ ያለ ወዳጅህ በስውር። ና፥ ሄደን ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ወደ አንተ የቀረቡት ከአንተም የራቁት አንተን ከብበውህ ያሉ አሕዛብ ከሚያመልኩአቸው አማልክት፥ አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን ሌሎች አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ፥ እሺ አትበለው፥ አትስማውም፤ ዓይንህም አይራራለት፥ እትማረውም፥ አትሸሽገውም፤ ነገር ግን ፈጽመህ ግደለው፤ እርሱን ለመግደል በፊት የአንተ እጅ፥ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ በላዩ ትሁን።  ኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 13፡6-9

በተጨማሪም

አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከአገርህ ደጆች በማንኛይቱም ውስጥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ቃል ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፋት የሠራ ቢገኝ፥ ሄዶም ሌሎች አማልክትን ያመለከ፥ እኔ ላላዘዝኋቸው ለፀሐይና ለጨረቃ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የሰገደ ቢገኝ፥ ቢያወሩልህም ብትሰማም፥ ያንን ፈጽመህ መርምር፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ በእስራኤልም መካከል እንዲህ ያለ ርኵሰት እንደ ተሠራ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥ ይህን ክፉ ነገር የሠሩትን ያን ወንድ ወይም ያችን ሴት ወደ በርህ ታመጣቸዋለህ፥ እስኪሞቱም ድረስ በድንጋይ ትወግራቸዋለህ። (ኦሪት ዘዳግም ምዕ. 17፡ 2-5)

አሁን ወደ መልሱ እንግባ

2- እስልምናን ያለመረዳት ምንጭ

አንድ ሰው ከኢስላም ስለወጣ መገደል እንዳለበት የሚገልጸውን ጽንሰሀሳብ አስመልክቶ ብዙ ሰዎች ጥያቄ የሚፈጥርባቸው የእስልምናን ሀይማኖት ስረ-መሰረት ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ ኢስላም ምንድን ነው? እስልምና ማለት ልክ እንደየትኛውም ሀይማኖት ክርስትና ሂንዱይዝም ሀይማኖት ብቻ ነውን? በጭራሽ ኢስላም ከዚህም የመጠቀ ነው…! አስልምና ሀይማኖት ብቻ ሳይሆን የተሟላ የሀይወት መመሪያ ጭምርም ነው፡፡ ይህ መመሪያ ኢስላማዊ ግዛትንም ጭምር የማስተዳደርን የተሟላ የህግ ማዕቀፍ የያዘ ነው፡፡ ኢስላም በነዚህ ኢስላማዊ ወርቃማ የኺላፋ ጊዜያት አንጸባራቂ ታሪክን ትቶልን አልፏል፡፡

ከዚያ በኋላ የተተኩ ‹‹ሰው ሰራሽ›› ስርዐቶችና የኢምፔሪያሊዝም አገዛዞች ለሰው ልጅ እልቂትና ዘግናኝ አገዛዞች አሳልፈው ሰጥተውታል፡፡ ያንን አንጸባራቂ ዘመን በታሪክ ሰነዳቸው የቃኙ ህዝቦች ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ደጋግመው ናፍቀዋል፡፡ በአጭሩ ኢስላም የተለመደ የሀይማኖት ቀኖና ስብስብ ሳይሆን አገዛዝን ጨምሮ ሙሉ የህይወት መመሪያን ያቀፈ ነው፡፡

3- የኢስላማዊ ግዛት መኖር አስፈላጊነት

አንድ ግዛት ማካተት ከሚኖርባቸው ጉዳዮች አንዱ አበይት የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎች ናቸው፡፡ እነኝህ አበይት የህግ ማዕቀፎች ደግሞ በሌሎች ተያያዥ ህጎች እየተተነተኑ /Define/ በሀገሪቱ ውስጥ በህግ ደረጃ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ አስልምና ታዲያ ከነኝህ ግዛቶች የሚለይበት መሰረታዊ ነጥብ አለ፡፡የኢማም አሸይባኒን ‹‹ኪታብ አሲያር አሰጊርን›› ወደ እንግሊዝኛ የተረጎሙት ዶ/ር ማህሙድ አህመድ አልጋዚ በመግቢያቸው እንዲህ ይሉናል፡፡

‹‹በተለመደው ስርዓት አንድ ህግ የሚረቀቀውና እውቅና የሚሰጠው በፖለቲካው መስክ ስልጣኑ ባላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ለዚህም ነው ህግ የፖለቲካው አለም ሰዎች ውጤት ነው የሚባለው፡፡ነገር ግን በኢስላማዊው እሳቤ ግን ጉዳዩ ይገለበጣል፡፡ ይህም ግዛቱና የፖለቲካው ሰዎች የህጉ ውጤቶች ናቸው፡፡›› Kitab Al-Siyar Al- saghir- The shorter book on muslim international law, Islamic Research Institute, Islamabad, 1998, p. 18

በዚህም ኢስላማዊው ግዛት ምንጩ የግለሰቦች የ‹‹ይሆናል ሀሳብ›› ሳይሆን መለኮታዊ መመሪያ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ግልጽ በሆነ መንገድ ኢስላም ከሌሎች ሰው ሰራሽ የአገዛዝ ስርዐቶች ይለያል፡፡

የነዚህን ስርዐቶች ከኢስላማዊው ስርዐት ያላቸውን ልዩነት ኢብን ኹልዱን (808 ዓ.ሂ የሞተ) ሲገልጸው

‹‹ ሰው ሰራሹ ህግ ምንም ባማረ አእምሮና በበሰለ ጭንቅላት ቢሰራም የመጨረሻ ግቡ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ተቋም ብቻ ነው፡፡ ነግር ግን በአምላክ ህግ አውጭነት የተመሰረተ ግዛት ግን በዚህም ዓለም ይሁን በመጨረሻውም አለም ይበልጡኑ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡›› Muqaddima, Translated by Franz Rosenthal,Chapter III, section 23

ኢስላማዊው የአስተዳደር ተቋም እንደሆነ የተገለጸው የኺላፋው አስተዳደር ነው፡፡ ኢስላማዊው ግዛት ከሌሎች ሴኩላር አስተዳደሮች የሚለየው የሰውን ልጅ ፍላጎት በማሟላት ረገድ በዚህም በመጨረሻውም ዓለም የተዋጣለት መሆኑ ነው፡፡ በኢስላም የመዳን መንገድ አምላካችን አላህ (ሱ.ወ) ያስቀመጠለንንና የደነገገልንን ህግጋት መታዘዝ ነው፡፡ የዚህ ኢስላማዊ ግዛት ዋነኛ ግብ አስመልክቶ ቁርዓን እንዲህ ይለናል፡፡

الَّذِينَ إِن مَّكَّنَّاهُمْ فِي الْأَرْضِ أَقَامُوا الصَّلَاةَ وَآتَوُا الزَّكَاةَ وَأَمَرُوا بِالْمَعْرُوفِ وَنَهَوْا عَنِ الْمُنكَرِ ۗ وَلِلَّهِ عَاقِبَةُ الْأُمُورِ [٢٢:٤١]

‹‹(እነርሱም) እነዚያ በምድር ላይ ብናስመቻቸው ሶላትን እንደሚገባ የሚያስተካክሉ፣ ዘካንም የሚሰጡ፣ በደግ ነገርም የሚያዝዙ፣ ከመጥፎ ነገርም የሚከለክሉ ናቸው፡፡ የነገሮቹም ሁሉ መጨረሻ ወደ አላህ ነው፡፡›› 22፡41

በዚህም ሲጠቃለል ኢስላማዊው ግዛት አበይት አላማው መልካሙን መጠቆም ከመጥፎ ነገርም መከልከል ነው፡፡ (ይህንን አስመልክቶ የጦበሪን ተፍሲር መመለክት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ሰሂህ ሙስሊም 1/79)

4- ከእስልምና የወጣን ሰው/ሙርተድነት/ አስመልክቶ ኢስላም እንዴት ይመለከተዋል፡፡

4.1 ልክ እንደ አመጽ ተግባር /Act of rebellion/

እስልምና ሙርተድነትን የሚመለከተው ልክ እንደ አመጻ ነው፡፡ ዶ/ር ሙሀመድ ሀሚዱላህ ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲህ ያስቀምጡታል፡፡

‹‹.. ይህ ተግባር/ሙርተድነት/ ከግዛቱ መክዳትንና ማፈንገጥንና ከማካተቱ አንጻር ይህ የግድያ ህግ መተግበሩ የሚደገፍ ነው፡፡›› Muslim Conduct of State Sh. Muhammad Ashraf Publishers, Lahore 1945 p.161)

እንደሚታወቀው ደግሞ ይህ የሀገር ክህደት ወንጀል /Treason/ በአብዛኛው ሀገራት የሚጠብቀው ፍርድ ሞት ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ይህ ነገር ላይዋጥለት ይችላል፡፡ ይህ ግን የሚያመጣውን መዘዝ ካለመረዳት ነው፡፡ አንድ ሰው የሚኖርበትን ሀገር ከዳ ማለት ለየትኛውም የሀገሪቱ ጥፋት የሚጀመሪያውን እርምጃ ተራምዷል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ህልውና ከማጥፋት ጀምሮ የዜጎቿንም ደህንነት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡ በሀገራዊ ጉዳይና በህዝቦቿ ደህነነት ረገድ ወግ አጥባቂነት /fanaticism/ ይመከራል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዶ/ር ሙሀመድ ኢቅባል ኢንዲህ ይላሉ፦

‹‹ወግ አጥባቂነት ለሀይማኖት አርበኝነት ሲሆን ለሀገር ደግሞ እመርታ ነው›› Stray Reflection, No. 18 p.33

4.2 የግዛት መቃወስ

ይህ ጽንሰ-ሀሳብ ከላይኛው ጋር ተመሳሳይ ቢመስልም በትንሹ ለየት ይላል፡፡ በኢስላማዊው ግዛት ውስጥ የተረጋጋ ህይወት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ህዝቡ ኢስላማዊ ህግጋትን ካለማንም ማስገደድ መከተል ሲችሉና በኢስላማዊው ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችም እምነታቸው ተጠብቆ በሰላም መተግበር ሲችሉ ነው፡፡ ይህ ከኢስላም የወጣ ሰው ግን ለነዚህ ሀገራዊ ህግጋት ተገዥ መሆን እንደማይፈልግ በራሱ ጊዜ ይፋ አድርጓል፡፡ ሲያሻው ከጠላት ጋር በማበር ካልሆነም እምነትን ሳይቀር መጫወቻ በማድረግ ጠዋት ላይ አማኝነቱን ተናግሮ ማታ ላይ ደግሞ ከሀዲነቱን በመግለጽ በግልጽ የኢስላማዊው ህግጋትን ለጠላት ክፍተት በሚያመች መልኩ ሲጥስ ይገኛል፡፡ ይህን አስመልክቶ ቁርዓንን እንዲህ ይላል፡-

وَقَالَت طَّائِفَةٌ مِّنْ أَهْلِ الْكِتَابِ آمِنُوا بِالَّذِي أُنزِلَ عَلَى الَّذِينَ آمَنُوا وَجْهَ النَّهَارِ وَاكْفُرُوا آخِرَهُ لَعَلَّهُمْ يَرْجِعُونَ [٣:٧٢]

‹‹ከመጽሐፉ ባለቤቶች የኾኑ ጭፍሮችም አሉ፡- «በነዚያ በአመኑት ላይ በተወረደው (ቁርኣን) በቀኑ መጀመሪያ ላይ እመኑበት፡፡ በመጨረሻውም ካዱት፡፡ እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና፡፡» 3፡72

በዚህም ዘመን ሳይቀር እንዲህ አይነት አሳፋሪ ሽወዳዎች ሲከሰቱ እንመለከታለን፡፡ አንዳንዴም ወደ ኢስላማዊ መንግስታት አማኝ መስሎ በመግባትና የውስጥ መዋቅሩን በመሰለል ለጠላት ተጋልጦ በመስጠቱ ብዙ ክስረትን ሲያመጣ ተመልክተናል፡፡

ኢስላማዊው ግዛትም ሀገሪቱንና ህዝቦቿን/ሙስሊምም ሆነ ሙስሊም ያልሆኑ/ ለመጠበቅና ማንኛውንም መጥፎ ተግባርን ለማስወገድ ከስርዓቱ የሚጠበቀውን ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ ይጠበቃል፡፡

የኢስላማዊው ህግጋትን /አህካሙ ሸሪአ/ በጥልቀት ላጠና ሰው ኢስላም የህዝቦችን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር የህግጋቱን አስፈላጊነት /መቃሲዱ ሸሪዓ/ የቀረጸበት መንገድ ምክንያታዊና አሳማኝ እንደሆነ ይረዳል፡፡እንዴውም እንደ ኢማም አል-ገዛሊ (505 ዓ.ሂ) እንዲሁም አልኣሚዲ ባሉ ታላላቅ ሙስሊም ምሁራን ይህ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ተግባር ነው፡፡( አል ሙስጠፋ 1/173 እንዲሁም አል አህካም ፊ ኡሱሊል አህካም 3/274 መመልከት ይችላሉ)

በተጨማሪም አዝርከሺ (794 ዓ.ሂ) በእውቁ መጽሀፋቸው አል-በህር አል ሙሂጥ ፊኡሱሉል ፊቂህ 7/266 ጉዳዩን ዘርዘር አድርገው ጠቅሰውታል፡፡

በዚህ ዙሪያ ጉዳዩን በስፋት የሚተነትነው የአቡል ሀሰን አልሙዋሪዲ (450 ዓ.ሂ) ‹‹አህካሙ ሱልጣኒያህ›› ጥራዝ ውስጥ ራሱን በቻለ ርዕስ ‹‹አል ዊላያህ አላ አል-መሳሂህ ፊል ዊላያህ ኣላ ዓለል ሀርብ›› በተሰኘ ክፍል ይህ ግድያ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ግዛቱ የክልሉን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻርና የሚመጣውን አስከፊ ጉዳት ከማስወገድ አንጻር ካመነበት እንደሆነ መረጃዎቸን በማጣቀስ ያስረዳል፡፡

እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ይህ ውሳኔ የሚሰጠው በኢስላማዊ ግዛት ውስጥ ባሉ ኢስላማዊ ፍርድ ቤቶች በሚሰጠው ውሳኔ ተመርኩዞ የሀገሪቱ መንግስት የሚተገብረው እንጅ ማንኛውም ሰው በግሉ የሚወስደው እርምጃ አይደለም፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ዙሪያ ገባውን የቃኘ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው የኢስላማዊው ፍርድ ቤት ቃዲ ውሳኔ እንጅ የማንም ሰው ሀላፊነት አይደለም፡፡

5- ከሀይማኖት ነጻነት ጋር ያለው እይታ

ኢስላም በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን አስመልክቶ ግልጽና የጠሩ ህግጋቶች አሉት፡፡ የጥበቃው ሀላፊነት የኢስላማዊው ግዛት ላይ የሚጣል ሲሆን ሙሉ መብታቸው ይከበር ዘንድ ኢስላም አጽንኦት ሰጥቶ ያበክራል፡፡ (መብቶቻቸውንና እነሱን የተመለከቱ ህግጋትን አስመልክቶ ወደ ፊት በአላህ ፍቃድ በሌላ ጹሁፍ እመለስበታለሁ)

ነገር ግን ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችንና ከእስልምና የሚወጡ ሰዎቸን አስመልክቶ ኢስላም ግልጽ የሆነ ልዩነትን አስቀምጧል፡፡ ይህም ከላይ እንደጠቀስነው በዚህ ሰበብ የሚመጡ አፍራሽ መዘዞችን ግዛቱ ላይ ከማስወገድና የህዝቡን ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር ነው፡፡

6- ማጠቃለያ

☞ እስልምና ልክ ሌሎች እምነቶችን እንደምናይበት እምነት ብቻ ሳይሆን የተሟላ ስርዓትም ጭምር ነው፡፡ እናም ኢስላም ይህንን ድንጋጌ ሲደነግግ ግዛታዊ እሴቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

☞ ይህ ሰው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ከማምራቱ በፊት እስልምናን የለቀቀበት መንገድ ተጠይቆና የከፈረበት ምክንያት በመደናገርና ባለማወቅ ከሆነ ያልገባው ነገር ተጠይቆ ከዚያም ግልፅ በሆነ ማስረጃ ተጠይቆ እንዲመለስ ተደጋግሞ ይጋበዛል፡፡

☞ እስልምና አንድን ነገር ‹‹መጥፎ›› ነው ወይንም ‹‹ጥሩ›› ነው የሚልበት ራሱን የቻለ የሞራል እሴት አለው፡፡ የግለሰቦችን ነጻነት ኢስላም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያበረታታ ቢሆንም የሀገሪቱን ስጋት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ላይ ግን ገደብ ይጥላል፡፡ እንደሚታወቀው በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን ፍጹም ነጻነት/Absolute freedom/ የለም፡፡

☞ ግድያውን ወስኖ መፈጸም የሚችለው ማንኛውም ሰው ሳይሆን የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሶቹን መርምሮ ተገቢ እንደሆነ ካመነ ራሱ ግዛቱ ብቻ ነው፡፡

☞ እምነትን አሽቀንጥሮ በመጣል ግዛትን አደጋ ውስጥ በሚጥል ሁኔታ የሚንቀሳቅን ሰው አስመለክቶ ያለውን ይህንን ድንጋጌ አስመልክቶ እስልማና ብቻ ሳይሆን ከላይ እንዳየነው ክረስትናና የአይሁድ እምነትም የሚጋሩት ነው፡፡

ወሏሁ ዐዕለም !!!!

Shortlink