ከመጽሀፍ ቅዱስ አስገራሚ ይዘቶች መካከል

ሼር ያድርጉ
454 Views

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

በዚህ ክፍል የምንመለከታቸው አንቀፆች ብዙውን ጊዜ ስናነባቸው ፈገግ የሚያደርጉን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አሳዛኝ የሆኑ አልፎም አስደንጋጭ የሆኑ የባይብል አንቀፆችን ነው፡፡ እነዚህ አንቀፆች ቅዱስ በተሰኘ መጽሀፍ ውስጥ ሊኖሩ የማይገቡና ፈጽሞ የመለኮታዊ ቃልነትን ካባ ያልተላበሱ ናቸው።

1. ታላቁ ገዳይ

እንደ መጽሀፍ ቅዱስ መሠረት አምላክ በሆነ ወቅት ደስ ካላለው “ለምን ይሄን አያችሁ?” ብሎ ሳይቀር ህዝብ በመደዳ ጨፍጭፎ ሊያስለቅስ ይችላል፡፡

” ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ።”
(መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 6:19)

የሚገርመው የእንግሊዝኛው ንጉስ ጀምስ ቅጅ የሚለው Fifty thousand (አምሳ ሺህ) ሲሆን ወደ አማርኛ ሲተረጎም ግን አምስት ሺህ ሁኗል፤ የቱ ነው ትክክል? ለማመሳከር እንዲያግዝ የእንግሊዝኛውን አንቀጽ ከታች አስቀምጣለሁ፡፡

“And he smote the men of Beth-shemesh, because they had looked into the ark of the LORD, even he smote of the people fifty thousand and threescore and ten men: and the people lamented, because the LORD had smitten [many] of the people with a great slaughter.” (1Samuel 6:19)

2. ብልት መንካት እጅ ያስቆርጣል

እንደ መጽሀፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት የአንድን ወንድ ብልት አንዲት ሴት በጠብ መሀል ከጨበጠች እጇ ይቆረጣል። ይህ አስቂኝ ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳን መጽሀፍት ውስጥ ሊገኝ የማይገባው ቁምነገር አልባ ተራ ዝባዝንኬ ነው።

“ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ፥ እጅዋን ቍረጥ፥ ዓይንህም አትራራላት። ”
(ኦሪት ዘዳግም ምዕ. 25፥11-12)

3. ባርነትን አሜን ብለህ መቀበል አለብህ

መጽሀፍ ቅዱስ ባርነትን አስመልክቶ ያለው አስተምህሮ እጅግ ኃላቀር ነው። የባርነትን አስከፊ ስርአት ለማስወገድ ያስቀመጣቸው ቆራጥም ሆነ ሒደታዊ መፍትሔዎች የሉም። በተቃራኒው ግን ባሪያ ለሎሌው ተገዥ እንዲሆንና እድሜ ልኩን በባርነት ቀንበር እንዲማቅቅ በግልጽ ይመክራል።

” ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ።”
(1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2:18)

4. የወሲብ ባርነት ይበረታታል ካስፈለገህ ሴት ልጅህንም መሸጥ እንደምትችል ይገልፃል፡፡

ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ። ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም። (ኦሪት ዘጸአት ምዕ. 21፥7-8)

ይህንን አይነት መመሪያ “የፍቅር አምላክ” የተባለ አካል በአንድ ወቅት ህግ አድርጎት ነበር ብሎ ማሰብ ህሊና ይቀበለዋልን?

5. ሰው በሊታ ስለሆኑ ሰዎች በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ 🙂

መጽሀፍ ቅዱስ ከያዛቸው ቁምነገር አልባ ትርክቶች መካከል አንዱ ስለሰው በሊታ ሰዎች ተዘግቦ የምናገኘው ታሪክ አንዱ ነው። እንደሚከተለው ይነበባል፦

ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት፤ እርስዋም። ይህች ሴት። ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ። ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም። እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው ብላ መለሰችለት።
(መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕ. 6፥28-29)

አምላክ በዚህ ተረት በመሠለ ታሪክ ውስጥ ለአማኙ ምን ሊያስተላልፍ እንዳሰበ ግልጽ አይደለም። ትርክቱስ ምን ሊፈይድ ነው በቅዱሳን መጽሀፍ ውስጥ የተቀመጠው?

6. የአካል ጉዳተኞችን ስብዕና ዝቅ ያደረገ

አካል ጉዳተኛ የሆነ ግለሰብ እኩል መብት እንደሌለው መጽሀፍ ቅዱስ በማያሻማ መልኩ ይነግረናል። አካል ጉዳተኞችንም በግልፅ ቋንቋ “ነውረኛ” ሲል ይገልፃቸዋል።

“ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም ትርፍ አካል ያለው፥ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥ ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።”
ዘሌዋውያን 21፥18-21

በተመሳሳይ ብልትህ ወይንም የመራቢያ አካልህ የተጎዳ ከሆነ ሲያምርህ ይቀራል እንጅ የእግዚአብሔር ጉባኤ ውስጥ አትገባትም..!

” ቍላው የተቀጠቀጠ ብልቱም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ”
(ኦሪት ዘዳግም 23:1)

7. እግዚአብሄር እዝነተ ቢስ ከመሆኑ አንፃር ሴቶች ህፃናት ከብቶች ሳይቀሩ በጅምላ ቢጨፈጨፉ ግድ አይሰጠውም እንዴውም ትዕዛዝ አስተላልፎ ሳይቀር ያስጨፈጭፋል፡፡

” አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል። ”
(መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:3)

ታዲያ ይህንን በውስጡ ያካተተ መጽሀፍ የአምላክ ቃል ነው ብለው ያምኑበታል?

—————-💦

ተጨማሪ ንጽጽራዊ ትምህርቶችን ለመከታተል

በቴሌግራም

በፌስቡክ

በድህረ ገጽ