እግዚአብሔር እና ኢየሱስ

ሼር ያድርጉ
546 Views

መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሆነ ፈጣሪ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት እንዲሰግዱለት ያስፈልጋል።

“እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” ዮሐንስ 4፥24

በሌላ አነጋገር አምላክ ማንነቱ “መንፈስ” እንደሆነ በቀጥታ እየተነገረን ነው። ከዚህ ገለፃ ተነስተን ኢየሱስ ታዲያ እግዚአብሔር ነውን? ብለን ከጠየቅን መልሱ አይደለም የሚል ይሆናል። የዚህን መልስ እራሱ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይሰጠናል፦

“እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ #መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።” ሉቃስ 24፥39

በዚህ አንቀጽ ኢየሱስ እንደሚነግረን መንፈስ በባህሪው ስጋና አጥንት የለውም። እርሱ ግን በተቃሪኒው በመሆኑ ምክንያት ስጋና አጥንት አለው። ደቀመዛሙርቱም ይህንን ቀርበው ማረጋገጥ እንዲችሉ አካሉን እየጠቆመ እንዲዳስሱት ይጋብዛቸው ነበር። በዚህ አንቀጽ ኢየሱስ በግልጽ የሚነግረን እርሱ “መንፈስ” እንዳልሆነ ነው።

መንፈስ ካልሆነ ደግሞ ፈጣሪ አይደለም..! ምክንያቱም ፈጣሪ እግዚአብሔር መንፈስ እንጅ ስጋ የለበሰ ደካማ አካል እንዳልሆነ ከላይ ተነግሮናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ምናልባት አንዳንድ ክርስቲያኖች “ዮሐንስ የገለጸው አብን እንጅ ወልድን አይደለም፤ ምክንያቱም ወልድ ስጋ ለባሽ መሆኑ ይታወቃል” የሚል መከራከሪያ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ይህ መከራከሪያ ግን በሁለት መንገዶች የሚያስኬድ አይደለም።

፩- እዚህ ጋ ልብ ልንለው የሚገባው ቁምነገር አንቀጹ በደፈናው “እግዚአብሔር” አለንጅ ክርስቲያኖች እንደሚያስቡት የሥላሴ አካላትን ከፋፍሎ አልገለጸም። እግዚአብሔር ከተባለ ደግሞ እንደ ክርስቲያኖች እሳቤ መሠረት ሁሉም (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) እንጅ አንዱን ብቻ ነጥሎ አይጠቁምም። ሁሉም እኩል ስልጣን አላቸው ተብሎ ይታመናልና።

፪- አንቀፁ ይህንን ሲናገር “ወልድን አያካትትም” ካልን “ወልድ እግዚአብሔር አይደለም” ማለት ነው። ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽነው እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ወልድ ደግሞ መንፈስ አይደለም። ስለዚህም ወልድ አምላክ አይደለም ማለት ነው።

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)