እግዚአብሔርና እውቀቱ

ሼር ያድርጉ
511 Views

በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ….

እግዚአብሔር ግብፃውያንን ሊያጠፋ አሰበ። እንግዲህ እግዚአብሔር ሲያጠፋ ሴት ወንድ አይልም፤ አዋቂ እንስሳም አይመርጥም፤ ሲገል ሁሉንም ነው የሚገለው። በዛ ወቅትም እንደተለመደው እግዚአብሔር ግብፃውያንን ሊገድልና አማልክታቸውንም ሊያጠፋ ወሰነ።

“እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
ዘጸአት 12፥12

ግብፃውያን ሲገደሉ እንዲሞቱ የተፈረደባው ነዋሪዎቿ ብቻ አይደሉም። የሚያገለግሏቸው እንስሳትም ጭምር ከእግዚአብሔር ግድያ አያመልጡም። በዚህ የእግዚአብሄር እቅድ ውስጥ ግን አንድ ችግር ገጠመው። እስራኤላውያንና ግብፃውያን የሚኖሩት ተቀላቅለው ስለነበር እንዴት ለይቶ ግብፃውያንን ብቻ መርጦ እንደሚገድላቸው ግራ ገባው። በዚህም ምክንያት ዘዴ ይኖር ከሆነ በሚል ማሰብ ጀመረ፤ እንዳሰበ አልቀረም ተሳካለት። እቅዱ እንደሚከተለው ነበር።

“ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም።” ዘጸአት 12፥13

ይኸውም ለእስራኤላውያን ምን አላቸው? መጀመሪያ ጠቦት እረዱ አላቸው፤ ከዚያም ካረዳችሁት ጠቦት የሚፈሰውን ደም ወስዳችሁ በቤታችሁ በር ላይ ምልክት እንዲሆን ቀቡት አላቸው። ከዚያ እግዚአብሄር ግብፃውያንን ሊገል ሲመጣ የትኛው የግበጻውያን የትኛው ደግሞ የእስራኤላውያን ቤት መሆኑን በቀላሉ ለየው ማለት አይደል? ቢንጎ አሁን ጥሩ መንገድ ነው። በዚህም መንገድ እግዚአብሔር አላማውን አሳካ።

በዚህ ታሪክ ውስጥ አብዛኛዎቻችሁ የሚከተሉት ጥያቄዎች ውስጣችሁ ላይ መፈጠራችሁ አይቀርም።

፩- እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይሁን ግዴለም በጥፋታቸው ምክንያት ቀጣቸው እንበል። ምንም የማያውቁ ህፃናትን ጨምሮ እንስሳት ምን አጥፍተህ ይሆን እነሱም የዚህ ሰለባ የሆኑት? እግዚአብሔር ለህፃናት የሚራራ ልብ የለውምን?

፪- እግዚአብሔርስ የእስራኤላውያንንና የግብፃውያንን ቤት ለመለየት ተስኖት የደም ምልክት ካስፈለገው እንዴት ሁሉን አዋቂ ሀያል አምላክ ነው ማለት ይቻለናል?

እነዚህ ሀሳቦች ምናልባት በእኔ ብቻ ህሊና ውስጥ ተመላልሰው ይሆናል። ምናልባትም በናንተም ልብ ውስጥ ድንገት ውልብ ይልባችሁ ይሆናል። ክርስቲያን ወገኖቼ ሆይ ከዚህ ጥያቄ እንዴት ራሳችሁን ታስታርቁታላችሁ?

የአምላክን እውቀት በተመለከተ ቁርዓን ምን ይለናል? የሚለውን አንድ አንቀፅ ብቻ ለንፅፅር አስቀምጨ ፁሁፌን ላጠናቅ።

“የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በየብስና በባሕር ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ከቅጠልም አንዲትም አትረግፍም የሚያውቃት ቢኾን እንጅ፡፡ ከቅንጣትም በመሬት ጨለማዎች ውስጥ የለም ከእርጥብም ከደረቅም አንድም የለም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውስጥ (የተመዘገበ) ቢኾን እንጅ፡፡”
[ ሱረቱ አል-አንዓም፣ – 59 ]

አምላካችን አላህ ﷻ ያለው እውቀት እስራኤላውያንንና ግብፃውያንን መለየት እንኳን የማያስችል አይደለም። በዚህ አለም ላይ የሚገኙ ዛፎች ከያዟቸው እልፍ ቅጠላት መካከል አንዷም እንኳ ያለእሱ እውቀት አትረግፍም..!

የትኛውን አምላክ ይመርጣሉ..?!

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

Shortlink http://q.gs/F2Yfn