እውን ጥቁር ሰው ይጠላልን?

ሼር ያድርጉ
371 Views

ለምን ይዋሻል?

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

የኢስላም ጠላቶች ኢስላምን በመረጃ መርታት ቢያቅታቸው፡ የሚኖራቸው አማራጭ የሀሰት ወሬዎችን በኢስላም ላይ መንዛት ነው፡፡ የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ታሪክ ላነበበ ሰው የካፊሮችን ሴራ ለመረዳት ብዙም አይከብደውም፡፡ ከሀሰት ቅጥፈቶቻቸው አንዱ፡- አላህና መልክተኛው ያላሉትን ብለዋል ብሎ መዋሸት፡ አልያም የተነገረውን ነገር ሀሳቡንና መልእክቱን እንዲስት፡ ከፊትም ሆነ ከኋላ ወይም ከመሀል ቃላትን በመቁረጥ ማቅረብ ነው፡፡ ያ አልሳካም ያለ ጊዜ ደግሞ ትርጉሙን ቀይሮ የዋሁን ህዝብ ማምታታት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-

” فَوَيْلٌ لِلْمُصَلِّينَ ” سورة الماعون 4
“ወዮላቸው ለሰጋጆች” (ሱረቱል ማዑን 4)፡፡

በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ከቆምን ግራ እንጋባለን፡፡ አምላካችን አላህ ለሱ የሚሰግዱለትን መልካም ባሮች ‹‹ወዮላቸው›› በማለት ካስፈራራ፡ እንግዲያውስ ሶላት ለምኔ? የሚል ሀሳብ ይነሳል፡፡ ቃሉን በመቀጠል ካነበበው ግን ‹‹ለነዚያ እነሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)።›› በማለት ያብራራለታል፡፡ አዎ! ወዮላቸው በማለት የተዛተባቸው እነዚህ ሰጋጆች ‹‹ዘንጊዎች›› የሆኑት ናቸው፡፡ እነሱም አንዳንዴ የሚያቋርጡ፣ ወይም ያለምንም ሸሪዐዊ ምክንያት አንድን ሶላት ከወቅቱ አውጥተው ከሌላ ሶላት ጋር ደርበው የሚሰግዱትን ነው፡፡ አንቀጹ ከፊትና ከኋላ ያለው ሲነበብ ሀሳቡ የተሟላ ይሆናል፡፡

ዛሬ የማስነብባችሁ ደግሞ፡ ከነዚህ ከማያባሩት የክርስቲያን ወገኖች ቅጥፈት ውስጥ አንዱን ነው፡፡

የዚህ ‹‹ጆሮ ያለው ይስማ›› የሚል አካውንት ባለቤት በ ‹ተሃድሶ ለኦርቶዶክስ› የፌስቡክ ግሩፕ ላይ ይህንን ሀሰት ለወዳጆቹ አካፍሏል፡፡ ከወዳጆቹም በሀሳብ መስጫው (comment) ላይ ቢያንስ እንኳ ዐረብኛውን ካልቻለ እንግሊዘኛውን ሙሉ ቃል ይለጥፍላቸው ዘንድ የጠየቀው አንድም የለም፡፡ ነገሩ ‹birds of the same feather flock together› እንደተባለው ነውና በማንም አንፈርድም፡፡ አላህ ማስተዋሉን ይስጣቸው፡፡

ይህ ወገንም እራሱ በተረጎመው (ወይም በተነገረው) አማርኛ ‹ጥቁር ሰው› አላህ ዘንድ በእጅጉ የተጠላ መሆኑን በመግለጽ ኢስላም ለጥቁሮች ቦታ እንደሌለው ለማሳየት ሞክሯል፡፡

ሐዲሡ የሚናገው ስለ ኸዋሪጆች ወደፊት መነሳት በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የተነገረ ትንቢት መኖሩን ነው፡፡ በትንቢቱ ውስጥም የነሱን ባሕሪ ሲገልጹ፡- ‹‹በአንደበቶቻቸው እውነትን የሚናገሩ፡ ግና ከጉሮሮአቸው አልፎ ወደ ልቦናቸው የማይዘልቅ ›› የሆኑ እንደሆኑና፡ ከመሀከላቸው ደግሞ አላህ ዘንድ ከፍጡራኑ እጅግ የተጠላ አንድ ጥቁር ሰው መኖሩንና ይህም ሰው አንደኛው እጁ የበግ/ፍየል ጡት የሚመስል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እስኪ ወደ ሐዲሡ እንግባ፡-

عَنْ عُبَيْدِ اللهِ بْنِ أَبِي رَافِعٍ، مَوْلَى رَسُولِ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أَنَّ الْحَرُورِيَّةَ لَمَّا خَرَجَتْ، وَهُوَ مَعَ عَلِيِّ بْنِ أَبِي طَالِبٍ رَضِيَ اللهُ عَنْهُ، قَالُوا: لَا حُكْمَ إِلَّا لِلَّهِ، قَالَ عَلِيٌّ: كَلِمَةُ حَقٍّ أُرِيدَ بِهَا بَاطِلٌ، إِنَّ رَسُولَ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ وَصَفَ نَاسًا، إِنِّي لَأَعْرِفُ صِفَتَهُمْ فِي هَؤُلَاءِ، «يَقُولُونَ الْحَقَّ بِأَلْسِنَتِهِمْ لَا يَجُوزُ هَذَا، مِنْهُمْ، – وَأَشَارَ إِلَى حَلْقِهِ – مِنْ أَبْغَضِ خَلْقِ اللهِ إِلَيْهِ مِنْهُمْ أَسْوَدُ، إِحْدَى يَدَيْهِ طُبْيُ شَاةٍ أَوْ حَلَمَةُ ثَدْيٍ… مسلم 1066

‘Ubaidullah b. Abu Rafi’, the freed slave of the Messenger of Allah (ﷺ), said:
When Haruria (the Khwarij) set out and as he was with ‘Ali b. Abu Talib (Allah be pleased with him) they said,” There is no command but that of Allah.” Upon this ‘Ali said: The statement is true but it is intentionally applied (to support) a wrong (cause). The Messenger of Allah (may peace be upon him described their characteristics and I found these characteristics in them. They state the truth with their tongue, but it does not go beyond this part of their bodies (and the narrator pointed towards his throat). The most hateful among the creation of Allah us one black man among them (Khwarij). One of his hand is like the teat of a goat or the nipple of the breast. (Muslim The Book of Zakat Book 5, Hadith 2334).

ዑበይዲላህ ኢብኒ አቢ-ራፊዕ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ከዐሊይ ኢብኒ አቢ ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ጋር ሆኖ ሳለ እንዲህ አለ፡- ሐሩሪያዎች (ኸዋሪጆች) ብቅ ባሉ ጊዜ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ፍርድ የአላህ እንጂ የማንም አይደለም››፡፡ ዐሊይም (ረዲየላሁ ዐንሁ)፡- ‹‹ሀሰት የተፈለገባት እውነተኛ ንግግር!›› ናት አላቸው፡፡ ቀጠለና፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሰዎቹን (ባሕሪያቸውን) ገልጸውልናል፡፡ እኔም በነዚህ ሰዎች ላይ ይህን ባሕሪ አግኝቻለሁ፡፡ በአንደበቶቻቸው እውነትን የሚናገሩ፡ ግና ከዚህ (ከጉሮሮአቸው አልፎ ወደ ልቦናቸው) የማይዘልቅ የሆኑ ናቸው፡፡ ከነሱ መካከል አላህ ዘንድ ከፍጥረታቱ እጅግ የተጠላው አንድ ጥቁር ሰው አለ፡፡ ይህም ሰው አንደኛው እጁ የበግ/ፍየል ጡት የሚመስል ነው…›› በማለት ገለጻቸው፡፡ (ሙስሊም 1066)፡፡

1ኛ. በሐዲሡ ውስጥ የተነገረው ስለ አንድ ሰው ሆኖ ሳለ (እሱም ለምልክትነት)፡ ለምን ‹‹አላህ ዘንድ የተጠላው ጥቁር ሰው ነው!›› በማለት ጉዳዩን ወደ ጥቁሮች በጠቅላላ ለማለት ነው የሚል ትርጉም መስጠት አስፈለገ? በውሸት የራስን ሃይማኖት ማስወደድና የሌሎቹን እንዲጠላ ማድረግ ይቻላልን? ውሸት እስከመቼ?

The most hateful among the creation of Allah us one black man among them ማለት ትርጉሙ፡- አላህ ዘንድ እጅግ በጣም የተጠላ ሰው ማለት ጥቁር ሰው ነው ማለት ነውን? ምን አይነት የአማርኛ ትርጉም ብትጠቀሙ ነው ለዚህ ስህተት የዳረጋችሁ? one black man among them የሚለውን እንኳ መረዳት አቅቷችሁ ነው?

2ኛ. ጌታ አላህ በቅዱስ ቁርኣኑ ላይ በሚገርም ሁኔታ የሚነግረን፡ የኛ የሰዎች መልክ መለያየት (ጥቁር፣ ቀይ፣ ነጭ…) ለሱ ከአስደናቂ ምልክቶቹና ከአምላካዊ መገለጫ ባሕሪያቱ እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ መልኩ አድርጎ የሰራን እሱ ነውና፡-

“ሰማያትንና ምድርንም መፍጠሩ፥ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤ በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ታምራቶች አሉበት።” (ሱረቱ-ሩም 22)፡፡ ታዲያ እንዴት ብለን ተመልሰን ጌታ አላህ ጥቁር አድርጎ የፈጠረውን ፍጥረት በጣም ይጠላዋል እንላለን?
3ኛ. ቅዱስ ቁርኣን እንደሚያስተምረው አላህ ዘንድ የተጠሉት ከነጭም ሆነ ከጥቁር ሰው ወይም ቀይ ከሆነ ሰው የሚገኙ ክፉ ተግባራት እንጂ፡ ቀይ ወይም ጥቁር መልክ ያለው ሰው አይደለም፡፡ ቀጣዮቹም አንቀጾች ይህን ይገልጻሉ፡-

“ልጆቻችሁንም ድኽነትን በመፍራት አትግደሉ፤ እኛ እንመግባቸዋለን፣ (እናንተንም እንመግባለን)፤ እነሱን መግደል ኃጢአት ነውና። ዝሙትንም አትቅረቡ፤ እርሱ በእርግጥ መጥፎ ሥራ ነውና፤ መንገድነቱም ከፋ! ያቺንም አላህ ያወገዛትን ነፍስ ያለ ሕግ አትግደሉ፤ የተበደለም ሆኖ የተገደለ ሰው፣ ለዘመዱ (በገዳዩ ላይ) በእርግጥ ስልጣንን አድርገናል፤ በመግደልም ወሰንን አይለፍ፤ እርሱ የተረዳ ነውና። የየቲምንም ገንዘብ፣ የብርታቱን ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በሆነች ሁኔታ እንጂ አትቅረቡ፤ በኪዳናችሁም ምሉ፤ ኪዳን የሚጠየቁበት ነውና። በሰፈራችሁም ጊዜ ስፍርን ሙሉ፤ በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ፤ ይህ መልካም ነገር ነው፤ መጨረሻውም ያማረ ነው። ለአንተም በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፤ መስሚያ፣ ማያም፣ ልብም፣ እነዚህ ሁሉ (ባለቤታቸው) ከነሱ ተጠያቂ ነውና። በምድርም ላይ የተንበጣረርክ ሆነህ አትኺድ፤ አንተ ፈጽሞ ምድርን አትሰረጉድምና፣ በርዝመትም ፈጽሞ ጋራዎችን አትደርስምና። ይህ ሁሉ መጥፎው እጌታህ ዘንድ #የተጠላ ነው።” (ሱረቱል ኢስራእ 31-38)፡፡

4ኛ. በኢስላም ውስጥ የአላህን አምላክነትና ብጨኛ ተመላኪነት፡ እንዲሁም የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት ከመመስከር በኋላ የሚከተለው ሁለተኛው የኢስላም ማእዘን ‹ሶላት› ነው፡፡ ሶላት ደግሞ ወቅቱ መግባቱን ለማረጋገጥና አማኞችን ወደ አላህ ቤት ለመጥራት የሚደረገው ጥርሪ ‹አዛን› ነው፡፡ ይህንን አዛን ለመጀመሪያ ጊዜ በካዕባ አናት ላይ በመውጣት እንዲያሰማ የተፈቀደለት፡ የጥቁሮችና የሀበሾች ኩራት የሆነው ‹ቢላል ኢብኑ-ረባሕ› (ረዲየላሁ ዐንሁ) ነው፡፡ ኢስላም ጥቁሮችን ማግለልና አላህ ዘንድ የተጠሉ አድርጎ ማቅረቡ እምነቱ ቢሆን ኖሮ፡ ለቢላል ይህ ሁሉ ቦታ ባልተሰጠው ነበር፡፡

5ኛ. ዛሬም ላይ በተጨባጩ ዓለም የምናየው እውነታ ይህንን ሐቅ ይመሰክራል፡፡ በነጮቹ ሀገር (አውሮፓና አሜሪካ) ስንት ጥቁር ሙስሊሞች የኢማምነትን (መሪነት) ቦታ ይዘው ነጮችን ከኋላቸው አሰልፈው ሰግደዋል! ስንትና ስንት ጥቁሮችስ ከነጮቹ ጋር በመቀላለቀል በእኩልነት በመቆም በአላህ ቤት እና በዳዕዋ መድረኮች ላይ አብሮ በመቀመጥ አሳልፈዋል!! ታዲያ ይህ እኩልነት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማራቸው ነውን? ለእኩልነቱስ ከሐጅ ስነ-ስርአት የበለጠ ምን አይነት አስረጂ እንዲመጣ ትፈልጋላችሁ? እውነት በነጮቹ ቤተክርስቲያን ላይ ከጥቁሮች ጋር በአንድነት በመቀላቀል ‹አምላክ› የሚሉትን በጋራ ያመልካሉን? ነጮቹን የሚመራ ጥቁር ሰባኪ አለን? ለምን ቅድሚያ የራስን ጉድፍ ማጥራቱ ላይ ትኩረት ተነፈገው?

6ኛ. እኛም ተጠይቀንና መልስ ሰጥተን ብቻ አንቀርምና፡ እስኪ በተራችን ስለ እምነታችሁ አንድ ጥያቄ እንጠይቃችሁ፡-

“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው። ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥ ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥ ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። የቅዱሱንና የቅዱስ ቅዱሳኑን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤ ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገረ።” (ኦሪት ዘሌዋውያን ምእ 21፡ ቁ 16-24)፡፡

ጥያቄ፡- ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥ ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥ ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ ለምን ተባለ? እነሱስ የሱ ፍጥረት አይደሉምን? ከሆኑስ ለምን ለአምላካቸው መስዋትን ያቀርቡ ዘንድ ወደ መቅደሱ መቅረብን ለምን ተከለከሉ?

7ኛ. በመጨረሻም ክርስቲያን ወገኖች ሆይ! በውሸት ፕሮፖጋንዳ እውነትን ልትደበቅ አትችልምና ይህን እወቁ፡፡ እናንተ የምትናገሩት እውነት ከሌላችሁ፡ ኑ ወደ ኢስላም፡፡ እዚህ ተነግሮ የማያልቅ እውነት አለና፡፡

” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَكُونُوا مَعَ الصَّادِقِينَ ” سورة التوبة 119
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከዉነተኞቹም ጋር ሁኑ።” (ሱረቱ-ተውባህ 119)፡፡

Shortlink http://q.gs/ExaTx