እውን ክርስቲያናዊው መጽሐፍ ለመለኮታዊ መረጃነት በቂ ነውን? ክፍል -2

ሼር ያድርጉ
324 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

ክፍል ኹለት

በኣላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያ ዘመን የመጨረሻ ነብይ ኾነው በተላኩት ሙሐመድ ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን ቀጠልን፡፡
ሐዋርያት ለኢየሱስ (ዐ.ሰ) የተወረደለትን ኢንጂል በጽሑፍ እንዲያቆዩ ከኢየሱስ (ዐ.ሰ) ኣደበት የተላለፈ በኣራቱም “ወንጌላት” ምንም ዓይነት ትዕዛዝ እንደሌለ ልብ ይሏል፡፡ ራሱ ኢየሱስም ኣንዴ ብቻ መሬት ላይ የኾነ ነገር ጫር ጫር እንዳደረገ ከሚተርክ ነጥላ ታሪክ ውጪ (ዩሐ 8/6-8)፣ ጽሑፍ የጻፈበት ኣጋጣሚ የለም፡፡ ዛሬ “ወንጌላት” የሚባሉት የኢየሱስ በግርድፉ የሦስት ዓመታት የሰበካ ጊዜን የሚተርኩ ጽሑፎች እንጂ ሙሉ በሙሉ ከኣምላክ ለኢየሱስ (ዐ.ሰ) የተወረዱ ቃላት ኣይደሉም፡፡ ለኣብነት ያህል፡-

“ ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር” ሉቃ 3/18

ይህ ታሪክ ገና ኢየሱስ በመጥምቁ ሳይጠመቅ መጥምቁ ዮሐንስ ስላደረገው የሚተርክ ነው፡፡ ጥቅሱ ለመጥምቁ ዮሐንስ ከተሰጠ፣ ገና ኢየሱስ ወንጌልን መስበክ ሳይጀምር እርሱ ወንጌልን ከየት ሰምቶና አውቆ ሰበከ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከጥያቄው ባሻገር ከወንጌል ምን ጠቅሶ እንዳስተማራቸውም የተነገረ ነገር የለም፡፡ ታሪኩ በራሱ ግን ወንጌል እንዳልኾነ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ ኣንድ መምሕር ተማሪዎቹን ሰብስቦ እንግሊዘኛ ኣስተማራቸው የሚል ዘገባ ቢኖር፣ ተማሪዎቹ በጥቅል እንግሊዘኛ እንደተማሩ ብናውቅም፣ከእንግሊዘኛ ውስጥ በትክክል ምን እንደተማሩ ግን የምናውቀው ነገር የለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጥቅሱ ዮሐንስ ከወንጌል ያስተማረው የኾነ ነገር እንደነበረ በዘጋቢ መልኩ ቢናገርም፣ ምን አስተማረ የሚለውን ግን ከጥቅሱ መረዳት ኣንችልም፡፡
ሌላ ምሳሌ፡-
“ አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና…” ሉቃ 20/1
ኣሁንም እዚህ ጋር ኢየሱስ ከወንጌል ምንድር ነበር የሰበካቸው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ “ወንጌል” ማለት የኢየሱስ የሕይወት ታሪክና ብስራት ነው ከተባለም፣ ኢየሱስ የሕወት ታሪኩንና ገድሉን ሰባካቸው ማለት ትርጉም ኣልባ ሲኾን፤ ብስራቱን ኣሳወቃቸው ከተባለ ደግሞ ያ ብስራት ምንድር ነበር የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከነዚህና መሰል ታሪኮች በመነሳት ብቻ ዛሬ ወንጌል የተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሰዎች ዘጋቢ ቃላትና ትረካዎች እንዳሉበት፣ ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ የተወረደው ወንጌል እንዳልኾነም መረዳት ኣያዳግትም፡፡

የዐይን ምስክሮች  ስለ ኢየሱስ ምን ኣሉ
የዓይን ምስክሮች ስለ ኢየሱስ (ዐ.ሰ.) ያዩትንና የሰሙትን ትክክለኛውን ታሪክ ዛሬ ላይ እያነበብን እንዳልኾነ አስቀድመን ኣይተናል፡፡ በጥቅሉ የበኩር ጽሑፎች ዛሬ እኛ ዘንድ የሉም፡፡ ይህ ባለበት ኹኔታ ስለ ዓይን ምስክሮች መናገር ስላልተጻፈ ድርሰት እንደመተረክ ይቆጠራል፡፡ በኣራቱ “ወንጌሎች” መካከል የታሪክ መጣረስ መኖሩ ደግሞ የዓይን ምስክሮች የተባለውን ሙሉ በሙሉ ውሸት ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ኹሉም ጸሐፍት እንደሚባለው ያዩትን ወይም ካዩት የሰሙትን ወይም ደግሞ በመንፈስ ተመርተው ጽፈው ከነበር፣ በ”ወንጌላቱ” መካከል ኣንድ ዓይነት ታሪክ እናነባለን እንጂ በጭራሽ እርስ በርስ የሚጣረሱ ነገሮች ባልነበሩ ነበር፡፡ ዛሬ ወንጌላት በሚባሉ መጽሐፎች መካከል ብዙ መጣረሶች እንዳሉ እርግጠኛ ለመኾን መጽሐፎቹን በማነጻጸር ማንበብ በቂ ይኾናል፡፡ ለኣብነት ያህል፡-
“ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ..” ማቴ 2/1
“ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ።ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ።ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።” ሉቃ 2/2-7
በማቴዎስ ዘገባ መሰረት ኢየሱስ በንጉስ ሄሮድስ ዘመን ተወለደ፤ በሉቃስ ዘገባ መሰረት ደግሞ ቄሬኔዎስ አገረ ገዥ በነበረበት ዘመን ማለትም ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ተወለደ፡፡ መሰል መጣረሶች በወንጌላቱ መካከል መኖሩ፣ ወንጌላቱ በኋላ ላይ ከአፈ-ታሪክ በመነሳት የተዘጋጁ እንደኾነ ግልጽ መረጃ ነው፡፡
“ወንጌላቱ” በትክክል በነማን ተጻፉ? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከማርቆስ ወንጌል ጀምረን እስከ ዮሐንስ ድረስ የዘርፉ ልሂቃን የደረሱበትን ማጠቃለያ አጠር ኣድርገን እንቃኛለን፡፡

የማርቆስ ወንጌል (70 ዓ.ል.)
ልሂቃኑ ይህንን መጽሐፍ በትክክል ማን እንደጻፈው እንደማይታወቅ ይልቁንም የኾነ ከፍልስጤም ውጪ ይኖር የነበረ ግሪክኛ ተናገሪ ግለሰብ እንደጻፈው ይናገራሉ፡፡
“ We do not know who the author was, only that he was a Greek-speaking Christian, presumably living outside
of Palestine, who had heard a number of stories about Jesus.” The New Testament p 91
“ ደራሲው ከፍልስጤም ውጪ ይኖር የነበረ ስለ ኢየሱስ በርካታ ታሪኮችን የሰማ ግሪከኛ ተናጋሪ ክርስቲያን እንደነበረ ከመረዳት ባሻገር ማን እንደኾነ ኣናውቅም፡፡”
ይህ “ወንጌል” በእድሜ ከሌሎቹ ቀደም ያለ ስለነበር ፣ በርካታ የዘርፉ ልሂቃን ከኋላ የመጡ “ወንጌሎች” (ማቴዎስና ሉቃስ) በዋቢነት እንደተጠቀሙበት ይስማማሉ፡፡
የማቴዎስ ወንጌል (80-90 ዓ.ል.)
የማቴዎስ ወንጌል በሚባል የሚታወቀው መጽሐፍ ከኣዲስ ኪዳን መጽሐፎች የመጀመሪያው ነው፡፡ ምንም እንኳ የማርቆስ “ወንጌል” በኣጻጻፍ ታሪክ የቀደም ቢኾንም፣ የማቴዎስ “ወንጌል” ግን የመጀመሪያው የኣዲስ ኪዳን መጽሐፍ እንዲኾን ተወስኗል፡፡ ይህ የኾነበት ምክንያት እንደ ኣንዳንድ ምሁራን አመለካከት፣ ወንጌሉ በርካታ የብሉይ ትንቢቶችን ስላቀፈ፣ በብሉይ የተነገሩ ትንቢቶች በኣዲስ ኪዳን ስለ መፈጸማቸው ማሳያ ይኾን ዘንድ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ባርት እንዲህ ይላል፡-

“ We do not know the name of its author: the title found in our English versions (“The Gospel according to Matthew”) was added long after the document’s original composition…For one thing, the author never identifies himself as Matthew, either in 9:9 or anywhere else. Also, certain features of this Gospel make it difficult to believe that this Matthew could have been the author. The New Testament P. 115

“ የመጽሐፉ ደራሲ ማን እንደኾነ ኣናውቅም፡፡ በእንግሊዘኛ እትሞቻችን ውስጥ የሚገኘው “የማቴዎስ ወንጌል” የሚለው ስያሜ ሰነዱ ከተዘጋጀ ከረዥም ጊዜ በኋላ የተጨመረ ነው፡፡ ደራሲው ከማይታወቅባቸው ምክንያቶች ኣንዱ በወንጌሉ ምዕራፍ 9/9 ላይና ሌላም ቦታ ላይ ራሱን ማቴዎስ ነኝ ብሎ ኣለማስተዋወቁ ነው፡፡”

በ”ወንጌሉ” ምዕራፍ 9 ቁጥር 9 ላይ “ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና፦ ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው” የሚለው ታሪክ መጽሐፉ በሌላ ኹለተኛ ወገን ስለተተረከ፣ የ”ወንጌሉ” ጸሓፊ ራሱ ቀራጩ ማቴዎስ አለመኾኑን ያሳየናል፡፡

ቀደም ብለን እንዳየነው የዘርፉ ልሂቃን ከሚያነሷቸው ነጥቦች ማቴዎስና ሉቃስ ከራሳቸው ማጣቀሻዎች ባሻገር (በቅደም ተከተል M እና L ይባላሉ) የማርቆስን ወንጌል እንደዋቢ ተጠቅመዋል፡፡ ማቴዎስ በትክክለ የዓይን ምስክር ከነበር ስለምንድር ነው የማርቆስን ማጣቀስ ያስፈለገው

“ Why, for example, would someone who had spent so much time with Jesus rely on another author (Mark) for nearly two-thirds of his stories, often repeating them word for word …And why would he never authenticate his account by indicating that he himself had seen these things take place? ” The New Testament P. 115

“ ኣንድ ከኢየሱስ ጋር ረዥም ጊዜ ያሳለፈ ግለሰብ ስለምንድር ነው ኹለት ሦስተኛ ታሪኩን ሌላ ማርቆስ ከሚባል ደራሲ ስራ መውሰድ ያስፈለገው ኣብዛኛው ቦታ ላይ ታሪኮችን ቃል በቃል ይደግማቸዋል…እሱ ራሱ ኹኔታዎች ሲከናወኑ በዓይኑ እንዳየ ኣድርጎ ኃላፉነቱን ስለምን ኣልወሰደም  ”

የሉቃስ ወንጌል (80-90 ዓ.ል)

ሉቃስ መጽሐፉን ገና ሲጀምር ራሱ የዓይን ምስክር እንዳልነበረና የዓይን ምስክሮች እንዳስተላለፉለት ትክክለኛውን ተከትሎ እንደጻፈ ይናገራል፡፡ ስለነዚህ ምሥክሮች ማንነት ግን ምንም ያለው የለም፡፡ የዘርፉ ልሂቃን ምስክሮቹ የማርቆስ ወንጌልና ሌላ Q የሚባል ሰነድ በተጨማሪም እርሱ ራሱ ያነጋገራቸው ግለሰቦችም ጭምር ሳይኾኑ እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡

የዩሐንስ ወንጌል (90-100 ዓ.ል.)
የዩሐንስ ወንጌል ከሌሎች ሦስት ወንጌሎች በኣጻጻፍ ስልቱና በታሪክ ይዘቱ ይለያል፡፡ በታሪክ ከሌሎች ዘግይቶ ብቅ ማለቱ በሦስቱ ወንጌሎች ውስጥ ያልተተረኩ በርካታ ታሪኮቹ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ኾኗል፡፡ ሆርኔ ሲናገር ፡-
Its authenticity has been questioned by Erasmus,Calvin,Beza,Grotius, Le Clerc, Wetstein, Semler, Schulze, Morus, Heanlein, Paulus, Schmidt, and various other writers who are mentioned by Wolfius and by Koecher“ (Introduction to the Scriptures,Baker, 1970, Horne)
“ ኢራስመስ፣ካለቪን፣ቤዛ፣ግሮቲዮስ፣ሊ ክሌርክ፣ዌስቴን፣ሴምለር፣እስቹልዝ፣ሞረስ፣ሄንሌን፣ፓውለስ፣እስቺምት እና ሌሎችም
በርካታ ጸሐፍት በወንጌሉ ተዓማኒነት ላይ ጥያቄ ምልክት እንዳደረጉ ዎልፊየስ እና ኮቸር ገልጸዋል”

በዮሐንስ ወንጌል ዙሪያ ያሉትን ጭቅጭቆች በጥቅሉ “ተዓማኒ ነው” “ኣይ ተዓማኒ ኣይደለም” በሚል በኹለት ጎራ የተከፈለ እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡ ተዓማኒ ነው የሚለውን ጎራ ባሸናፊነት ብንቀብል እንኳ፣ ስልምንድር ነው በኣጻጻፍ ታሪክ ከቀደሙት “ወንጌሎች” የተለየ ዘገባ የያዘው? ስለምንስ ከሌሎች ጋር ተጣረሰ? እነዚህ ጥያቄዎች “ወንጌሉ” በትክክል በሐዋርያው ዮሐንስ ሳይኾን ተመሳሳይ ስም ባለው በሌላ ግለሰብ እንደተጻፈ ያሳብቃሉ፡፡ ለኣብነት ያህል እንዚህ ጥቅሶች ያመሳክሯል፡-

“ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው” ማር 1/12
በዚህ ዘገባ መሰረት ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ በመንፈስ ወዲያው ወደ ምድረ በዳ ተወስዷል፡፡ በበረሃም ኣርባ ቀንና ለሊት በሰይጣን እየተፈተነ ቆየ፡፡በዮሐንስ ዘገባ ግን ከጥምቀቱ ማግስት ወደ በረሓ ኣለመወሰዱን በግልጽ እናነባለን፡፡
“…በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር” ዮሐ 1/35

መሰል መጣረሶችን በሰፊው ለማንበብ Jesus interrupted ከሚለው የፕሮፌሰር ባርት መጽሐፉ ምዕራፍ ኹለት a world of contradiction የሚለውን በጥልቅ ማንበብ፣በተጨማሪም ኣራቱንም ወንጌሎች በማነጻጸር ማንበብ በቂ ነው፡፡
በዚህ ወንጌል ላይ የተለያዩ ጸሐፍት እጃቸውን እንዳሰፈሩበት ፕሮፌሰር ባርት እንዲህ ሲል ይናገራል፡-
“ወንጌሉን ያነበበ ሰው ምዕራፍ 20/31 ኛው ጥቅስ ላይ መጠናቀቁን ይረዳል፡፡ ስለኾነም በምዕራፍ 21 ላይ ያሉት ክስተቶች በኋላ ላይ የታሰቡና የክርስቶስን የትንሳኤ ገጽታ ለማስቃኘት፣ በተጨማሪም በወንጌሉ ያሉትን ትረካዎች ለማብራራት፣ ኀላፊነት የተጣለበት የ”ተወዳጁ ሐዋርያ” ያልተጠበቀ አሟሟትም ምን ይመስል እንደነበር ለማብራራት የተጨመሩ ናቸው” (21/22-23)፡፡ ማን በረዘው/ 75
ይህንን ርዕስ ስናጠቃልል፡-

ኣራቱም የኢየሱስን ታሪክ ዘግበናል የሚሉ “ወንጌላት” ራሳቸው በዓይናቸው ያዩትን አልመዘገቡም፤ወይም ደግሞ በትክክል በዓይን ካዩ ሰዎች ሰምተው ኣልጻፉም፡፡ መጽሐፎቹ በኋላ ላይ አፈ-ታሪክን መሰረት ኣድርገው በግል ተነሳሽነት የጻፉ ግለሰቦች ሥራ ነው፡፡ መጽሐፎቹ ሥያሜኣቸውንም ያገኙት በኋላ ላይ እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡

Shortlink http://q.gs/Eydtg