ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ቢሳሳቱ የሚጐዳው ማነው?

1,107 Views

ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ቢሳሳቱ የሚጐዳው ማነው?

“ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡” ቁርዓን 34፡50

ቁርአንን አስመልክቶ ከሚቀርቡ ግጭቶች መካከል ይህ ከላይ ያስቀመጥነው አንቀፅ አንዱ ነው። የእንግሊዝኛ ዌብሳይቶች የግጭት ዝርዝር ውስጥ በተለምዶ የመጀመሪያ ተደርጎ ተቀምጧል። ከዚያው ድህረ ገፅ በመተርጎም “60 ግጭት አገኘን” ያሉ የኛው ተርጓሚዎችም ተራ ቁጥር ቀይረው አስቀምጠውታል። አንድ ዜሮ በመጨመር 10ኛ ተራ ቁጥር ላይ አስቀምጠውታል፤ ከድህረ ገፁ አልወሰድንም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑ ነው። ለነገሩ ባይጠቅሱትም ይታወቃል፤ የድህረ ገፃቸው ሰፊ ክፍል ከዚሁ ድህረ ገፅ በሚተረጎሙ አርቲክሎች የተሞላ ነው። ከሞላ ጎደል እያንዳንዱን አርቲክል ይዘን ወደዚህ ድህረገፅ ብንገባ ቀድሞውኑ በእንግሊዝኛ የተቀመጠ ነው። ሙሉ ድህረ ገፅ መተርጎምን ስራው ያደረገ አካል ሀሳብን ወደጎን በማድረግ ሰዎችን በትርጉምና መሠል ክሶች በመተቸት ለመደበቅ ሲሞክር ማየት ደግሞ ይበልጥ አስቂኝ ነው። ለማንኛውም ክሱን በመጠኑ ጠቅሸ ወደ ምላሹ ልግባ፦
በዚህ አንቀፅ ላይ የክርስቲያን ሚሽነሪዎች ጥያቄ ግልፅ ነው። ነብዩ ”ﷺ” ቢሳሳቱ እሳቸው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሙስሊም ይጎዳል፤ ስለዚህ ብሳሳት የምጎዳው እኔ ብቻ ነኝ በሚል የተገለፀው ቃል ትክክል አይደለም የሚል ነው። በዚህ ጥያቄ ውስጥ ጠያቂዎቹ በእውቀት ማነስ ሳቢያ የፈጸሟቸው መጠነኛ ስህተቶች አሉና እነሱን በማረም ልጀምር።

1- ነብዩ ”ﷺ” ቀጥታ እያናገሩ በሚመስል መልኩ የተቀመጡ የቁርአን አንቀፆች ሁሌም እሳቸውን ብቻ የሚገልፁ አይደሉም። እነዚህ የቁርአን አንቀፆች በተለዩ ጊዜያት ለሚተላለፉ መልዕክቶች ቀጥታ እሳቸውን የሚያነሱ እንዳሉ ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ እሳቸውን እንደማሳያ (እንደ ምሳሌ) በማንሳት ለሁሉም ሙስሊም ዑማ መልዕክትን የሚያስተላልፉም የተለዩ አንቀፆችም ነበሩ። ስለዚህም እሳቸውን የሚጠቅሱ አንቀፆች ሁለት አይነት ናቸው ማለት ነው። ለዚህ ብዙ የቁርአን አንቀፆችን እንደማስረጃ መጥቀስ ቢቻልም ጥቂቶቹን ለአብነት ሰጥቸ ልለፍ፦

يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ جَاهِدِ الْكُفَّارَ وَالْمُنَافِقِينَ وَاغْلُظْ عَلَيْهِمْ ۚ وَمَأْوَاهُمْ جَهَنَّمُ ۖ وَبِئْسَ الْمَصِيرُ
(ሱረቱ አል-ተውባህ – 73)
አንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡
—–
يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ اتَّقِ اللَّهَ وَلَا تُطِعِ الْكَافِرِينَ وَالْمُنَافِقِينَ ۗ إِنَّ اللَّهَ كَانَ عَلِيمًا حَكِيمًا
(ሱረቱ አል- አሕዛብ – 1)
አንተ ነቢዩ ሆይ! አላህን ፍራ፡፡ ከሓዲዎችንና መናፍቃንንም አትታዘዝ፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
——–
يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُل لِّأَزْوَاجِكَ وَبَنَاتِكَ وَنِسَاءِ الْمُؤْمِنِينَ يُدْنِينَ عَلَيْهِنَّ مِن جَلَابِيبِهِنَّ ۚ ذَٰلِكَ أَدْنَىٰ أَن يُعْرَفْنَ فَلَا يُؤْذَيْنَ ۗ وَكَانَ اللَّهُ غَفُورًا رَّحِيمًا
(ሱረቱ አል- አሕዛብ – 59)
አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶቸህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው፡፡ ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

እነዚህን ለአብነት ጠቀስናቸው እንጅ መሠል የቁርአን አንቀፆች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ስለዚህም ነብዩን አስመልክቶ ቀጥታ የተነገረን ቃል ሁሌም ለሳቸው ብቻ አድርጎ ጥያቄ ማንሳት መሠረታዊ የእስልምና እውቀት ላይ ያለን ክፍተት የሚያሳይ ነው።

2- ነብዩን ”ﷺ” ብቻ የሚመለከት ትዕዛዝስ የለምን?

ነብዩ ”ﷺ” በህይወት በነበሩበት ጊዜ እሳቸውና ምዕመንን ለመምራት የወረዱ የቁርአን አንቀፆች ነበሩ። እነዚህ የቁርአን አንቀፆች ጊዜና ቦታውን በዋጀ መልኩ በቀጥታ እሳቸውን የሚያናግሩ ነበሩ። ለአብነት ጥቂቱን ለመጥቀስ ያክል፦

يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُل لِّأَزْوَاجِكَ إِن كُنتُنَّ تُرِدْنَ الْحَيَاةَ الدُّنْيَا وَزِينَتَهَا فَتَعَالَيْنَ أُمَتِّعْكُنَّ وَأُسَرِّحْكُنَّ سَرَاحًا جَمِيلًا
(ሱረቱ አል- አሕዛብ – 28)

አንተ ነቢይ ሆይ! ለሚስቶችህ (እንዲህ) በላቸው «ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጧን የምትፈልጉ እንደ ሆናችሁ ኑ፤ አጣቅማችኋለሁና፡፡ መልካምንም ማሰማራት (በመፍታት) አሰማራችኋለሁና፡፡
—–
يَا نِسَاءَ النَّبِيِّ مَن يَأْتِ مِنكُنَّ بِفَاحِشَةٍ مُّبَيِّنَةٍ يُضَاعَفْ لَهَا الْعَذَابُ ضِعْفَيْنِ ۚ وَكَانَ ذَٰلِكَ عَلَى اللَّهِ يَسِيرًا
(ሱረቱ አል- አሕዛብ – 30)
—-
وَإِذْ أَسَرَّ النَّبِيُّ إِلَىٰ بَعْضِ أَزْوَاجِهِ حَدِيثًا فَلَمَّا نَبَّأَتْ بِهِ وَأَظْهَرَهُ اللَّهُ عَلَيْهِ عَرَّفَ بَعْضَهُ وَأَعْرَضَ عَن بَعْضٍ ۖ فَلَمَّا نَبَّأَهَا بِهِ قَالَتْ مَنْ أَنبَأَكَ هَـٰذَا ۖ قَالَ نَبَّأَنِيَ الْعَلِيمُ الْخَبِيرُ
(አል- ተሕሪም – 3)
ነቢዩ ከሚስቶቹ ወደ አንዷ ወሬን በመሰጠረ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ እርሱንም በነገረችና አላህ እርሱን (ማውራትዋን) ባሳወቀው ጊዜ ከፊሉን አስታወቀ፡፡ ከፊሉንም ተወ፡፡ በእርሱም ባወራት ጊዜ «ይህን ማን ነገረህ?» አለች፡፡ «ዐዋቂው ውስጠ ዐዋቂው ነገረኝ» አላት፤
——
እነዚህ ከላይ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ የጠቀስናቸው የቁርአን አንቀፆች በልዩ ሁኔታ የሚመለከቱት ነብዩ ”ﷺ” ብቻ ሲሆን የአንቀፆችን ሰበበ ኑዙል/የአወራረድ ምክንያት/ ስንመለከትም የሚጠቁሙን ይህንኑ ነው (በያኑል ቁርአን – ለሱራዎቹ የተሰጡትን ትንታኔዎች ይመልከቱ)
ከላይ ያለውን እንደ መግቢያ ያስቀመጥኩበት ምክንያት አንድ ሰው ቁርአን ላይ ነብዩን ”ﷺ” አስመልክቶ ቀጥታ የሚናገሩ አንቀፆችን በተመለከተ ያለው መረዳት መታረም ስለሚኖርበት ነው። በትችት መልኩ የቀረበውን የቁርአን አንቀፅ ስንመለከትም ጠያቂው ይህንን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ሳቢያ የተፈጠረ እንደሆነ እንረዳለን። እንደ ጠያቂው እሳቤ መሠረት ነብዩን ”ﷺ” ጠቅሶ የሚገለፅ ቃል ሁሉ እሳቸውን ብቻ የሚመለከት ነው ማለት ነው። ይህ ለቁርአን ባይተዋር የሆነ ሰው የሚፈጽመው ስህተት ነው።

ወደ ጥያቄው ስንመለስ

እንደ መግቢያ ይሆነን ዘንድ ከላይ ትንሽ ካልን በአጭሩ ወደ መልሱ እንዝለቅ።
የዚህን የቁርአን አንቀፅ ምንነት አስመልክቶ ያለው ማብራሪያ ጠያቂው ካነሳው ሀሳብ ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም። አንቀፁ የሚያወራው ስለመለኮታዊ ራዕይ ወይንም ስለ አስተምህሮ መዛነፍ ሳይሆን እንደ ሰው በነበራቸው የግል ህይወት ዙሪያ ስለሚፈጠሩ ስህተቶች ነው። አንቀጹ “ብሳሳት” ብሎ የሚገልፀው የሳቸውን ሰብአዊ ባህሪይ ነው። ነብዩ ”ﷺ” መለኮታዊ ራዕይ የሚወርድላቸው ነብይ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ማንኛውም ሰው የግል ህይወት ያላቸው ሰውም ነበሩ። እንደሚታወቀው ደግሞ ነብያት ሰውኛ ባህሪያትንም የተጎናፀፉ ግለሰቦች እንጅ ከስህተት የተጠበቁ መላዕክት አይደሉም። በዚህም ሳቢያ በዕለትተዕለት ህይወታቸው ዙሪያ እንደማንኛውም ሰው ግላዊ ስህተቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ። ያ ስህተት ከሀይማኖታዊ እይታ አንፃር ሳይሆን ከግላዊ ስህተት አኳያ ብቻ ሊታይ እንደሚገባ ቁርአን በዚህ ክፍሉ ይነግረናል። ከኢማም ኢብን ከሲር ጀምረን የተለያዩ የተፍሲር ሊቃውንትን ስራ ብንመለከት ከዚህ ውጭ የተለየ ፍችን ሰጥተው አናገኝም።
ነብያት በግል ህይወታቸው ዙሪያ ከልምድ ማነስ ሳቢያ የሚፈጽሟቸው ስህተቶች ጉዳት ካመጡ የሚጎዱት እራሳቸውን እንጅ ማንንም አይደለም። የሰው ልጅ ያለው ነፃ ምርጫ እነሱንም ይመለከቷቸዋልና “ቢሆን ይሻላል” ብለው የሚመርጧቸው ግላዊ ውሳኔዎች የሚወሰዱት እንደግላዊ ምልከታዎች ነው።

❐ ኢየሱስን እንደ ንፅፅር

በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ መሠል ነብያት የፈጸሟቸው ስህተቶችና ከእውቀት ማነስ የተገበሯቸው ተግባራት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እነዚህ ተግባራት በተደጋጋሚ የተነገሩ ስለሆነ መደጋገሙ ፁሁፍ ማርዘም ነው። እነሱን ወደጎን አስቀምጠን ለአብነት ኢየሱስ ባለማወቅ የፈጸመውን ስህተት እንመልከት፦
❝ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።❞ ማርቆስ 11: 13
ኢየሱስ ወደ በለሲቱ መጥቶ የነበረው ምናልባት በለስ ካገኘባት በማሰብ ነበር፤ ነገር ግን የበለስ ወራት እንደነበር አላወቀም ነበርና ስህተት ውስጥ ወደቀ። ውጤቱም እንደጠበቀው ሳይሆን በተቃራኒው ሆነ..! የዚህ ክስተት ባለቤት እንደ ክርስቲያኖች እምነት መሠረት “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ” ነው። አምላክ እንዴት የበለስ ወራትን ማወቅ ተሳነው? የሚለው ወደጎን እንተወውና በግለሰብ ደረጃ ይህ ስህተቱ ግን ከያዘው አስተምህሮት ወይንም ከመለኮታዊ ራዕዩ ጋር የሚገናኝ አይደለም። እንደ ግለሰብ የሚኖረውን ህይወት አስመልክቶ ወንጌላት የእርሱን የህይወት ጉዞዎች ሲዘግቡ የመዘገቡት ታሪኩ ነው። እንደ ግለሰብ ይህንንን አለማወቁን እንዲሁም ስህተቱን መላው ክርስቲያን የጠመመበት ስህተት አድርጎ መሳል ግን ትክክል ያልሆነና አለፍ ሲልም አስቂኝ ነው።

❐ ሲጠቃለል

የአምላክ መልዕክት ወደነሱ የሚመጣላቸው ቅዱሳን ሰዎች በግላዊ የምርጫ ውሳኔዎቻቸው ዙሪያ መሠል ስህተቶችን ማስተናገዳቸው የማይቀር ነው። ይህም እነኝህ ሰዎች ከስህተት የተጠበቁ መላዕክት ወይንም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ባለመሆናቸው ሳቢያ ነው። ይህንን ስህተት ከመለኮታዊ አስተምህሮ ጋር ማገናኘት የግልብ ግንዛቤ ውጤት ነው። ምክንያቱም መለኮታዊ መመሪያን አስመልክቶ አንቀፁ ራሱ ቀጠል አድርጎ ያብራራዋልና፦

“…… ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡”
በርግጥም የአምላክ መመሪያ የሚወስደው ወደ መመራት ነው። የእርሱ መመሪያ ቅናቻን የሚጠቁም እንጅ ከስህተት ጋር የተጋነኘ አይደለም። በ”ግጭት” ደረጃ የተነሳው ሀሳብ እንደተመለከትነው ውሉን የሳተና ከግንዛቤ እጥረት የተፈጠረ ነው። ቀጣዩን በአላህ ፍቃድ በሁለተኛው ክፍላችን እንዳስሰዋለን።

ወሏሁ አዕለም..!
(የሕያ ኢብኑ ኑህ)