እውን ቁርዓን ይጋጫልን? መግቢያ

1,073 Views

ቁርአን ከአምላካችን አላህ (سبحانه وتعالى ) የተሰጠን መለኮታዊ መፅሀፍ በመሆኑ በውስጡ ምንም አይነት የርስበርስ ግጭት እንደሌለበት እኛ ሙስሊሞች እናምናለን። አንድ “መለኮታዊ” የተሰኘ መፅሀፍ ውስጡ ከእርስ በርስ መጣረስ የፀዳ ሊሆን እንደሚገባ ሁሉም ሰው ይጠብቃል። የእርስ በርስ ግጭት ስንል ከሀሳብ ግጭት ጀምሮ የቁጥር፣ የጊዜ፣ የቦታ ወዘተ ግጭቶችን ያካትታል። መነሻ ላይ የተናገረውን መድረሻ ላይ በተቃራኒ ቃል የሚያፈርስ መፅሀፍ አይደለም የአምላክ ቃል ሊሆን ይቅርና የአስተዋሽ ደራሲ ውጤትም ሊሆን አይችልም።
ከዚህ በመነሳት እኛ ሙስሊሞች መፅሀፍ ቅዱስ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ስንሰነዝር ቆይተናል። መፅሀፍ ቅዱስ አያሌ የእርስ በርስ ግጭቶችን በውስጡ አቅፎ የያዘ መፅሀፍ እንደሆነ የሚገልፁ የተለያዩ ድርሳናት በተለያዩ ቋንቋዎች ለዘመናት ሲቀርቡ ኑረዋል። ለሀገራችን አንባቢያን እንዲጠቅም በማሰብም ከዚህ በፊት “ስቲሮት” በሚል ርዕስ መፅሀፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ በቁጥር ከመቶ በላይ የሚሆኑ ግጭቶችን በማጠናቀር በአማርኛ ቋንቋ መጠነኛ መፅሀፍ አዘጋጅቼ ነበር። ሌሎች ወንድሞችም በተመሳሳይ በራሳቸው መንገድ ከመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኟቸውን መጣረሶች በተለያዩ ጊዜያት አስነብበዋል፤ጠይቀዋል።
ነገር ግን እነዚህን መጣረሶች አስመልክቶ በክርስቲያኖች ዘንድ የተሰጡ ምላሾች እምብዛም የሚባሉ ናቸው። በዚህ ዘርፍ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ጥቂት የክርስቲያን ፀሀፍትን ስራዎች ብንመለከት “ምላሽ” ተብለው የቀረቡ ሀሳቦች ከነ አካቴው ሊያስገርሟችሁ ሁሉ ይችላሉ። የአንዳንዶቹ መልስ “ቢጋጭ ምን ችግር አለው?” ወይንም “የቁጥርና መሠል ግጭት መኖሩ እምነታችን ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ የለውም” የሚሉ “ምላሾች” ነበሩ። ዳንኤል ተሾመ የተሰኘ የክርስቲያን ፀሀፊ “ይኸውና መልሴ” በሚል ርዕስ ምላሽ ለመስጠት በሞከረበት መጽሀፉ ላይ የመፅሀፍ ቅዱስ ስህተቶችን አስመልክቶ የሚከተለውን ይላል፦

” ….. በአንፃሩ ደግሞ ቅዱሳን ሰዎች በጊዜና በቦታ ውስን ስለሆኑ፣ ሁሉንም አይነት እውቀት ለምሳሌም መልክዓ ምድራዊ፣ ሥነ ቋንቋዊ፣ የሥነ ጹሁፍ፣ ልዩ ልዩ መረጃዎች .. ወዘተ ስለማያውቁ (በከፊል ካልሆነ በቀር) በሥነ ጹሁፋቸው ውስጥ እንደ መረጃ ስሕተት፣ የጊዜ አቆጣጠር መዛባት፣ እንደ ታሪካዊ ቅንብር ያለ ጉድለት ሊኖር ግድ ነው”
(ዳንኤል ተሾመ – “ይኸውና መልሴ” ገጽ 10 በተጨማሪም ዳንኤል ተሾመ፣ ስለ መፅሀፍ ቅዱስ … ገፅ 6)
በሌላ ቦታ እነዚህን የስምና የአሀዝ ግጭቶች አስመልክቶ ፀሀፊው ሲናገርም እንዲህ ይላል፦

“.. ስለዚህ የቦታ፣ የስምና የአሃዛት ልዩነት መከሰቱ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ጸሀፊዎቹ የተሰጣቸውን መለኮታዊ መልዕክት በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሥነ ጹሁፍ በኩል ስለሚያስተላልፉ፣ በዚያም ዘመን መረጃዎችን እንደ ልብ የማግኘትም ሆነ ወዲያው የመዘገብ ሁኔታ ስለሌለ፣ እስኪዘገብም ድረስ በትውስታ መልኩ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ስለሚተላለፍ፣ መዘገብ በሚጀመርበት ጊዜ የቦታ፣ የስምና የአሃዛት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል” (ዳንኤል ተሾመ – “ይኸውና መልሴ” ገጽ 84)

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቅል በሆነ መልኩ የመፅሀፍ ቅዱስን ይዘትና የፀሀፊዎችን ማንነት አስመልክቶ ያለውን ግራ መጋባት መምህር ያሬድ ሽፈራው “የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥ” በተሰኘው መፅሀፉ የመጀመሪያው ቅጽ (ቅጽ ፩) ላይ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፦
“በዘመናችን አንድ መጽሀፍ የመጽሀፉን ርእስ፣ የጸሀፊውን ስም፣ የተጻፈበትን ቀን፣ የታተመበትን ማተሚያ ቤትና ሀገር እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች መረጃዎችን ስለሚይዝ ስለመፅሀፉ ለመናገር ይቻላል። ሆኖም ቅዱሳን መፅሀፍት በተጻፉበት ወቅት ይህንን ዘመናዊውን የመረጃ አሰጣጥ መንገድ ተከትለው ስላልተፃፉ የተፃፉበትን ጊዜ በርግጠኝነት ለማወቅና በማን እንደተፃፉ ለመረዳት እጅግ አዳጋች ሊሆን ችሏል”
(ያሬድ ሽፈራው ፤ የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥ ቅጽ ፩ ገፅ 7)

በዚህ ዘርፍ የረባ መልስ የሌላቸው ተስፋ የቆረጡ አካላት የተሻለ መስሎ የታያቸው አካሄድ በተቃራኒው “ቁርአን ውስጥም ግጭት አለ” የሚል መከራከሪያ በማንሳት ጥያቄውን በአፀፋ ለመመለስ መሞከር ነው። በዚህም “መፅሀፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ቁርአንም ይጋጫልና ብዙ አይገርምም” የሚልን መልዕክት በቀላሉ ለማስተላለፍ የታለመ ነው። ነገር ግን ይህንን አስመልክቶ “በእውነት ቁርአን ይጋጫልን?” የሚለውን ጥያቄ አንስተን በጥልቀት ካየን መልሱ “በፍፁም” የሚል ነው። ይህንን አስመልክቶ ከምንም በፊት እራሱ ቁርአን ማስተማመኛውን እንዲህ ሲል ይሰጠናል፦
أَفَلَا يَتَدَبَّرُونَ الْقُرْآنَ ۚ وَلَوْ كَانَ مِنْ عِندِ غَيْرِ اللَّهِ لَوَجَدُوا فِيهِ اخْتِلَافًا كَثِيرًا
(ሱረቱ አል-ኒሳእ – 82)
ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡
የዚህን የቁርአን አገላለፅ አስመልክቶ የምንመረምርበት ሁለት መንገድ አለ። አንደኛው መንገድ ቁርአንን ሙሉ ለሙሉ በማጥናት የሚጋጩ አንቀፆች እንደሌሉ ማረጋገጥ ነው። ይህኛው ትንሽ አድካሚና ጊዜ የሚወስድ ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛው አካሄድ ደግሞ እራሱ ይህንን የቁርአን አንቀፅ ብቻ በመመልከት ረቂቅ በሆነ መልኩ የምናረጋግጥበት ሌላኛው መንገድ ነው። ይህንን በሚከተለው ምሳሌ ግልፅ ለማድረግ ልሞክር፦

❐ አበበ በሶ ይወዳል
❐ አበበ የሚለው ቃል ሶስት ፊደል አለው

በመጀመሪያው አረፍተ ነገር ላይ ያወራነው አበበ ስለሚባለው ግለሰብ ሲሆን በሁለተኛው አረፍተ ነገር ላይ ያወራነው ግን አበበ ስለሚለው ቃል ነው። የቁርአን አንቀፁን በዚህ መልኩ መፃፍና መመልከት እንችላለን፦

“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ “ኢኽቲላፈን ከሲረን” ባገኙ ነበር፡፡”

ወይንም

“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን “ኢኽቲላፈን” ባገኙ ነበር፡፡”
ቃላቶቹን መልሰን ስንሰድራቸው የሚከተለውን አረፍተ ነገር እናገኛለን፦
“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን “ኢኽቲላፈን” ባገኙ ነበር፡፡”
ይህንን ያስተዋለ ጎበዝ ምክንያታዊ ሰው ቀጥታ የሚያደርገው ተግባር “ኢኽቲላፈን” የሚለውን ቃል ትርጉሙን ለጊዜው አቆይቶ ቃሉን ሌጣውን በሙሉ ቁርአን ውስጥ መፈለግ ነው። በዚህም በቀላሉ የቁርአን ፀሀፊ አንድን ቃል በ”መጠቀም” እና እንዲሁ በ “ማንሳት” መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ የተረዳ እንደሆነ ማወቅ ይችላል። ያ ብልህ ምክንያታዊ ሰውም ኢኽቲላፈን የሚለው ቃል ቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው ብዙ ጊዜ ሳይሆን አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ በቀላሉ ይረዳል ማለት ነው (Muhammad Fu’ad `Abd al-Baqi, Al-Mu`ahjam al-Mufahris li al-Fadh al-Qur’anal-Karim, 1997, Dar al-Fikr, Beirut (Lebanon), p. 305.)

ስለዚህም ቁርአን ከአላህ ሌላ የነበረ ቢሆን ኖሮ በውስጡ ብዙ “ኢኽቲላፈን” ይገኝበት ነበር። ቁርአን ስለፅንሰ ሀሳብ እያወራ ቃል ሲጠቅስም መልዕክቶችን አዝሎ ነው። ምናልባት አንድ ሰው ይህንን ሲመለከት ድንገታዊ ግጥምጥሞሽ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ሊሰነዝር ይችላል። መልሱ ግን “አይደለም” የሚል ነው። ምክንያቱም እንዲህ አይነት አስደናቂ አንቀፆች በዚህ አንቀፅ ብቻ የተገደቡ አይደሉም። ቁርአንን ያጠና ሰው መሠል አንቀፆችን ያስተውላል..! አንድ እንጨምር፦
“ዋሂዳን” ወይንም “አንድ” የሚለው ቃል ቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው በሚከተለው አንቀፅ ላይ ነው።
ذَرْنِي وَمَنْ خَلَقْتُ وَحِيدًا
(አል ሙደሢር – 11)
አንድ ኾኖ ከፈጠርኩት ሰው ጋር ተዎኝ (እኔ እበቃሃለሁ)፡፡
ይህ አንድ የሚለውን ቃል የሚጠቁመው “ዋሂዳን” የተሰኘ ቃል በቁርአን ውስጥ ስንት ጊዜ የተጠቀሰ ይመስልዎታል? መልሱ ቀላል ነው፤ አንድ ጊዜ ብቻ..!

መሠል የቁርአን መልዕክቶች ጥልቀት ባለው መልኩ ጥናት የሚያስፈልጋቸውና ከተራ ትርጉም በዘለለ የግል ጥረትንም የሚጠይቁ ናቸው። ቁርአን ተጋጭቷል በሚል በአላዋቂ ሚሽነሪዎች የሚቀርቡ ሀተታዎችን አስተውሎ ለተመለከተ ሰው አይደለም መሠል ጥናት ውስጥ ሊያልፉ ይቅርና አንቀፆች በአርምሞት እንዳልተመለከቷቸው ሳይቀር ይረዳል።

በአንድ መፅሀፍ ውስጥ “በለጠ ወደ አዲስ አበባ ሔደ” የሚል አረፍተ ነገርና በሌላ ቦታ ደግሞ “በለጠ ወደ ጎንደር ሔደ” የሚል ሌላ አረፍተ ነገር ቢያገኙ ለነዚህ ሰዎች ምናልባት ግጭት ተደርጎ ታይቷቸው ሊያስገርሟችሁ ይችላሉ። ለነሱ በለጠ አንዴ አዲስ አበባ ከሔደ ሌላ የትም ቦታ ሊሄድ የማይችል ሚስኪን ግለሰብ ነው። በዚህ የተወላገደ አረዳዳቸው ፈረንጆቹ የከተቧቸውን ፁሁፎች የኛው ተርጓሚዎችም ወደ አማርኛ አምጥተው ሲቀላውጡበት ባይ ጊዜ በመጠኑ ምላሽ መሰጠት እንዳለበት አሰብኩ። ከዛ በፊት ግን ወንድሜ ወሒድ ቀድሞኝ ለሁሉም ምላሽ ሰጥቷል፤ የሱን ምላሾች በሚከተለው አድራሻ ያገኙታል) የኛዎቹ ግጭቶቹን ቀናንሰው “60” ብቻ አድርገዋቸዋል። ምናልባት ሌላው ክፍል ሲተረጉሙ አላሳመናቸው ይሆናል የተውት። ባይሆን በቁጥር ተርታቸው ላለመተርጎም ቅደም ተከተላቸውን ቀያይረውታል፤ ከዛ ውጭ የተለየ ነገር በሀሳብ ደረጃ እንኳን ለመጨመር አልሞከሩም። የራሳቸው ነገር ለሌላቸው ሰዎች ቦታ ሰጥቶ ጊዜ ከማባከን ይልቅ ከኦርጅናል የትርጉም ምንጫቸው (አንሰሪንግ ኢስላም) ቀጥታ በመውሰድ መመለሱ ይሻላልና የመልስ ቅደምተከተሌ እርሱን ብቻ የተከተለ ይሆናል።

እነሆ ከዚህ በኃላ በሚቀርበው ተከታታይ ፁሁፍ እያንዳንዳቸውን ቁርአን ላይ የሚቀርቡ የግጭት ክሶች ምላሽ የምንሰጥ ይሆናል። በዚህ ዘርፍ እስካሁን ያለውን ጥያቄ በአላህ ፍቃድ በተቻለ መጠን በዚህ ተከታታይ ፁሁፍ ዘርዝረን የምናጠናቅቀው ይሆናል።

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)