እውን ቁርአን ይጋጫልን? ክፍል -2

ሼር ያድርጉ
368 Views

የመላዒካዎች ስግደት ለማን?

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

ለአላህ ብቻ፡– ሱራ 7፡206 “እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት (መላዕክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም ያወድሱታልም ለርሱ ብቻ ይሰግዳሉ፡፡”

ለሰው ሰግደዋል፡–ሱራ 2፡34 “ለመላዕክት ለአደም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ) ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ ኢብሊስ (ዲያቢሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ  ኮራም ከከሐዲዎቹም ሆነ፡፡” በተጨማሪም ሱራ 17፡61፤ 15፡30

ክርስቲያኖች እነዚህን ሁለቱን የቁርአን አንቀፆች በማስቀመጥ እንደሚጋጩ ሊገልፁልን ይሞክራሉ። አያይዘውም ስግደት የሚገባው ለአንድ አምላክ ብቻ እንጅ እንዴት ለሰው ይሰገዳል? ሲሉም ይጠይቃሉ።

ምላሽ -1

ይህንን አስመልክቶ ግራ የሚጋባ አካል ከመነሻው የእስልምና አስተምህሮ ላይ ያለው እውቀት ውስን የሆነ ብቻ ነው። ለአላህ የሚገባው ስግደትና አላህ ራሱ ለመላዕክት ያዘዘው ስግደት ሁለቱ የተለያዩ ስግደቶች ናቸው። ለአላህ ﷻ የሚገባው የአምልኮ ስግደት በቀደምት የነብያት ህዝቦች ሸሪዓ ውስጥ ሲተገበር ከነበረው የአክብሮት ስግደት ጋር የሚገናኝ አይደለም። በሱረቱል በቀራህ የተገለፀው ስግደት የአክብሮት ስግደት እንጅ አምልኮን ያለመ ስግደት አይደለም። በቀደምት ነብያት ዘንድ መሠል ስግደቶች ከአምልኮ ውጭ የራሳቸው ትርጉም ነበራቸው።

ስግደቱ የክብር ሰላምታ ከመስጠት የተለየ አልነበረም። ይህንን አስመልክቶ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነን የዩሱፍ ወንድሞች ለዩሱፍ የሰገዱለት ተግባር ነው።

وَرَفَعَ أَبَوَيْهِ عَلَى الْعَرْشِ وَخَرُّوا لَهُ سُجَّدًا ۖ وَقَالَ يَا أَبَتِ هَـٰذَا تَأْوِيلُ رُؤْيَايَ مِن قَبْلُ قَدْ جَعَلَهَا رَبِّي حَقًّا ۖ وَقَدْ أَحْسَنَ بِي إِذْ أَخْرَجَنِي مِنَ السِّجْنِ وَجَاءَ بِكُم مِّنَ الْبَدْوِ مِن بَعْدِ أَن نَّزَغَ الشَّيْطَانُ بَيْنِي وَبَيْنَ إِخْوَتِي ۚ إِنَّ رَبِّي لَطِيفٌ لِّمَا يَشَاءُ ۚ إِنَّهُ هُوَ الْعَلِيمُ الْحَكِيمُ

ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፡፡ ለእርሱም ሰጋጆች ኾነው ወረዱለት፡፡ «አባቴም ሆይ! ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፡፡ ጌታ በእርግጥ እውነት አደረጋት፡፡ ከወህኒ ቤትም ባወጣኝና ሰይጣንም በእኔና በወንድሞቼ መካከል ከአበላሸ በኋላ እናንተን ከገጠር ባመጣችሁ ጊዜ በእርግጥ ለኔ መልካም ዋለልኝ፡፡ ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው፡፡ እነሆ እሱ ዐዋቂው ጥበበኛው ነው» አለ፡፡
(ሱረቱ ዩሱፍ – 100)

በቁርአን እንደተገለፀልን የዩሱፍ ወንድሞች አባቱን ጨምሮ ለዩሱፍ ስግደት ፈጽመዋል። ታዲያ እንደ ክርስቲያኖች እሳቤ መሠረት የያዕቆብ ልጆችና ያዕቆብ ዩሱፍን ያመለኩ ነበር ማለት ነው? በፍጹም..! ይህ ስግደት ልቅናና አክብሮትን ለመግለጽ በጥንት ህዝቦች ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው። ልክ በአሁኑ ዘመን አንድ የተከበረ ሰው ሲመጣ ከመቀመጫችን ብድግ እንደምንለው እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ትከሻንና ግንባርን የመሳም ተግባር ለሚከበር ሰው እንደሚደረገው ማለት ነው። ይህንን በተመለከተ ሙፍቲህ ጣቂ ዑስማኒ “ማዕሪፉል ቁርአን” በተሰኘው የተፍሲር ኪታባቸው የሱረቱል በቀራህን ቁጥር 34 ሲተነትኑ በሰፊው አብራርተውታል። በተጨማሪም ኢማም አል-ጀሳስ “አህካሙል ቁርአን” በተሰኘው ጥራዛቸው በሰፊው ዳሰውታል።

ምላሽ -2

በርግጥ የአምልኮ ስግደት የሚገባው ለአንድ አምላክ ብቻ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ከላይ የተጠቀሰው የመላዕክት ስግደት ምንን የተመለከተ እንደሆነ አብራርተናል።ከዚህ ጋ በተያያዘ ግን እንደሚታወቀው አንድ ክርስቲያን “ስግደት የሚገባው ለአምላክ ብቻ ነው” ሲል አስተምህሮቱ መጽሀፍ ቅዱሳዊ እንዲሆንም አያይዘን እንጠብቃለን። ይህንን አስተምህሮ አስመልክቶ በክርስቲያን አማኞች ዘንድ የተለያየ አመለካከት እንደሚገኝ እሙን ነው። በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ስግደት ለአምላክ ብቻ የሚሰጥ ተግባር አይደለም። ቅዱሳንም የክብር ስግደት ይገባቸዋል። ብጹዕ አቡነ ገብርኤል በ1990 በታተመውና “ክብረ ቅዱሳን” በሚለው መጽሀፋቸው ውስጥ ስግደት ለቅዱሳንም ጭምር የሚገባ እንደሆነ ብሉይና ሀዲስን አጣቅሰው ይሟገታሉ። ከዚህ በታች ጥቂት የመጽሀፍ ቅዱስ አንቀጾችን ለአብነት ላካፍላችሁ፦

❐ ለመላዕክት ስገደት

የበለአም ስግደት ለመላእክት፦
“እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ።”  ዘኍልቁ 22፥31

ሎጥ ለመላዕክት ሰግዷል፦
“ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም፦”
ዘፍጥረት 19፥1

የኢያሱ ስግደት፦
“እርሱም፦ አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፦ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው።” ኢያሱ 5፥14

❐  ለሰዎች የተፈጸመ ስግደት

የዮሴፍ ወንድሞች ለዮሴፍ ሰግደዋል፦

“ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ በግምባራቸው ሰገዱለት።” ዘፍጥረት 42፥6

ኦርና ለነብዩ ዳዊት ሰግዷል፦

“ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ተመልክቶ ዳዊትን አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፋ።” 1 ዜና 21፥21

ሲጠቃለል

ከላይ እንዳብራራነው ቁርአን ውስጥ ስግደትን በተመለከተ የቀረበው ገለፃ ሁለት መልክ ያለው ነበር። በቀደምት ነብያት ሸሪአ ዘንድ ስግደት ከአምልኮ በተጨማሪ ለክብርም አገልግሎት ላይ ይውል ነበር። ይህ አስተምህሮ ለነብዩ ሙሀመድ “ﷺ” በተሰጣቸው ሸሪዓ ውስጥ ስግደት አንድ መልክ ይኖረው ዘንድ ቢደነገግም በቀደምት ነብያት አስተምህሮ ዘንድ ግን ለክብር የሚሰጥ ተግባር ተደርጎም አገልግሎት ላይ ይውል ነበር። ይህን የኢስላማዊ አስተምህሮ ትውፊት ላልተረዳ ሰው ከላይ የመጣው ጥያቄ ውዥንብር ቢፈጥርበት ብዙም አይገርምም። ሀሳቡ ግን ቀላልና ለጥያቄም የሚቀርብ አይደለም..!

❐ ማጣቀሻ/Reference/
—————-
1- معارف القرآن 34
2- احكام القرآن 34
3- ክብረ ቅዱሳን – ብጽዕ አቡነ ገብርኤል
4- የኢት/ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን እምነት ስርአተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት – በ1988 የተዘጋጀ ሲሆን በስርአተ ስግደት ክፍሉ ውስጥ ይህንን ይተነትናል።

ይቀጥላል…
____

ተጨማሪ ንጽጽራዊ ትምህርቶችን ለመከታተል

❐  በዩቲዩብ – http://bit.ly/2ZPzYTI

❐ በቴሌግራም – t.me/yahya5

❐ በፌስቡክ- facebook.com/yahyanuhe/

❐ በድህረ ገጽ- www.ethio-islamic.org

Shortlink http://q.gs/EybZv