እኛ የምናነበው ጽሑፍ ግልባጭ ነን

ሼር ያድርጉ
348 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

ወዳጄ ኣንተ ዙኃኑ የሚያደርገውን በማድረግህ፣ ትክክለኛ ለመኾንህ ወይም የዘመን ተሻጋሪ ፍልስፍና ባለቤት ስለመኾንህ ዋስትና ኣይሰጥህም፡፡ የተግባርህን ትክክለኛነት ብዙኃኑ የተቀበሉት አመለካከት ሳይኾን ሚዛን ኾኖ ሚያረጋግጥልህ፣ ኣንተንም ፍልስፍናህንም ህልውና እንዲኖራችሁ ያደረገው ኣምላክ ኣለህ ያስቀመጠው መለኪያ ብቻ ነው፡፡

ወዳጄ ብዙ ለስጋም ለመንፈስም የማይጠቅሙ ጽሑፎችን በማንበብና ምንም ባለማንበብ መካከል ልዩነትም ኣንድነትም እንዳለ ልብ ይሏል፡፡ የማየረቡ ጽሑፎች የማይረባ እንቶፈንቶ ፍልስፍናን እንደ ነቀርሳ በሒደት ያበቅላሉ፡፡ ነቅርሳውም ሥር ሰዶ የማይፈወስ በሺታ ይኾናል፡፡ ካለማንበብ ጋር ያለውም ኣንድነት እዚህ ጋር ነው፡፡ ያለማንበብ ወና ኣእምሮ ከመፍጠር ባሻገር ለማንኛውም ዓይነት በሺታ ያጋልጣል፡፡ እማያነብ ኣእምሮ ወዴት መሄድ እንዳለበት ትልም ስለሌለው፣የትኛውም መንገድ ይዞት ይነጉዳል፤ መንገዶች ኹሉ መዳረሻ እንዳላቸው ስለሚያምን፣ መንገዶች ኹሉ ኣልማዝና ዕንቁ ኾነውበት ለምርጫ ፈጽሞ ይቸገራል፡፡ መታመም ማለት ታዲያ ይኸው ነው፡፡ ፍኖተ-ሕይወት ማጣትና መዋለል!!!

ልዩነታቸው ተራ ጽሑፎችን የሚያነብ ነራሱ ብዙ ኣንባቢ እንደኾነ መንገር፣ለሌሎችም በመለከት መንፋትና ማወጅ ይከጅለዋል፡፡ ያነበበው ኹሉ ሲከፍቱት ተልባ መኾኑን ስለሚዘነጋ፣ በባዶ ጣሳ (ኣእምሮ) ውስጥ እንደተበተነ ጥቂት ጠጠር (እውቀት) ብጤ ነው፡፡ ጣሳው ሰፊ ስለኾነ ኹለት ሦስት ጠጠሮች በትንህ ብትነቀንቀው ይንጫጫል፡፡ ጣሳውን በጠጠር ብትሞላውና ብትነቀንቀው ግን ምንም ድምጽ ኣይሰጥህም፡፡ ይሕ ጠቃሚ መጽሐፍትን ያነበቡ ሰዎች ምሳሌ ሲኾን፣ በማይረባ ጽሑፍ ከሕይወቱ በርካታ ጊዜያትን ያቃጠለው ግን በየሔደበት ልክ እንደሚንጫጫው ጣሳ ስለለፈለፈ ብዙ ኣድማጭ ያለው ኣዋቂ እንደኾነ ይሰማዋል፡፡

Shortlink http://q.gs/Eye4A