ቁርዓን የማን ቃል ነው?

1,037 Views

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው

እሱ፡- ቁርኣን የማን ቃል ነው?
እኔ፡- ቁርኣን የአላህ ቃል ነው፡፡
እሱ፡- ምን ማስረጃ ይኖርሀል?
እኔ፡- ቁርኣን ራሱ የአላህ ቃል መሆኑን ይናገራል!፡፡
እሱ፡- የቱ ጋር?
እኔ በሱረቱ ተውባህ ምእ 9 ቁ 6 ላይ ‹‹ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፡፡ ከዚያም ወደ መጠበቂያው ስፍራ አድርሰው፡፡ ይህ እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው ነው፡፡›› በማለት ቁርኣን የአላህ ንግግር መሆኑን ይገልጻል!፡፡
እሱ፡- እንደዛ ከሆነ ቁርኣን ከራሱ ሀሳብ ጋር ይጋጫል ማለት ነዋ!
እኔ፡- ቁርኣን በሱረቱ-ኒሳእ ምእ 4 ቁ 82 ላይ ‹‹ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡›› በማለት፡ ከአላህ ዘንድ የመጣ የአላህ ቃል መሆኑን ይገልጽና፡ በዛውም ከሀሳብ ግጭት የጸዳ መለኮታዊ መጽሐፍ መሆኑን ያውጃል፡፡
እሱ፡- በሱረቱ 81፡19 ላይ ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው የሚል ተጽፏል እኮ!
እኔ፡- በቁርኣን ውስጥ ቁርኣንን አስመልክቶ ‹‹የጂብሪል ቃል›› ነው የሚል አንድም ቦታ አልተጻፈም፡፡ ይህ ቅጥፈት ነው፡፡
እሱ፡- ሱረቱ 81፡19 አውጣና አንብብልኝ እሺ!
እኔ፡- ሱረቱ-ተክዊር ምዕ 81 ቁ 19 ‹‹እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡›› ይላል፡፡ የታለ የጂብሪል ቃል ነው የሚለው?
እሱ፡- ይኸው ቁርኣን የክቡር መልክተኛ ቃል ነው እያለ የምን መከራከር ነው?
እኔ፡- ያቀረብኩልህ ጥያቄ ‹የጂብሪል ቃል ነው› የሚለውን አውጥተህ እንድታሳየኝ ነው ወዳጄ!
እሱ፡- መልክተኛ የተባለው ጂብሪል እኮ ነው! ከዚህ በላይ ምን ላሳይህ?
እኔ፡- መልክተኛ የተባለው ማን እንደሆነ የምነግርህ እኔ ነኝ እንጂ አንተ አይደለህም፡፡ ከዛ በፊት ግን በቃሉ ላይ የሰፈረውን እንደተጻፈው አንብበህ ነው መጠየቅ ያለብህ እንጂ፡ አንተ የምትፈልገውን ትርጉም ከሰጠህ በኋላ አይደለም!፡፡
እሱ፡- አሁን ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
እኔ፡- ለማለት የፈለግሁትማ ቁርኣን ‹‹የክቡር መልክተኛ ቃል ነው›› ይላል እንጂ ቁርኣን ‹‹የጂብሪል ቃል ነው›› እንደማይል ላረጋግጥልህ መውደዴን ነው፡፡
እሱ፡- እሺ መልክተኛ የተባለው ማነው?
እኔ፡- እንደዚህ ስትጠይቅ ነው የሚያምርብህ፡፡ ለማወቅ ከፈለግህ ጠያቂ እንጂ ደረቅ ተከራካሪ አትሁን፡፡
እሱ፡- እሺ አሁን ጥያቄዬን መልስልኝ ወደሌላ አታስቀይስ፡፡
እኔ፡- በስርአት ተወያየኝ ወዳጄ!፡፡ ወደየትም አላስቀይስም፡፡ መልክተኛ የተባለው ማነው? ላልከው፡ በዚህ ሱራ ሱረቱ-ተክዊር ምዕ 81፡19 ላይ የተጠቀሰው መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ነው፡፡
እሱ፡- እኮ! ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው በለኛ ታዲያ! እኔስ መጀመሪያ ምን አልኩህና?
እኔ፡- ትንሽ ተረጋጋ አትውረግረግ፡፡ አሁንም ቃሉ የሚለው ቁርኣን የክቡር መልክተኛ ቃል ነው በማለት እንጂ የጂብሪል ቃል ነው በማለት አይደለም!፡፡ መልክተኛ የተባለው ጂብሪል ስለሆነ ‹የክቡር መልክተኛ ቃል ማለት› የጂብሪል ቃል ማለት ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ልንይዝ አይገባንም፡፡
እሱ፡- ቁርኣን የክቡር መልክተኛ ቃል ነው ማለት እና የጂብሪል ቃል ነው ማለት ምን ልዩነት አለው?
እኔ፡- ትልቅ ልዩነት አለው!
እሱ፡- እኮ ምን? ንገረኛ!
እኔ፡- መልካም! ልዩነቱን ለመረዳት መልክተኛ የሚለው ቃል ላይ ትኩረት እናድርግ፡፡ አንተን የምጠይቅህ ‹‹መልክተኛ›› ማለት ምን ማለት ነው?
እሱ፡- የተላከ ማለት ነው፡፡
እኔ፡- ምን የተላከ?
እሱ፡- ማንኛውንም መልእክት እንዲያደርስ የተላከ ማለት ነው፡፡
እኔ፡- በጣም ጥሩ!፡፡ ስለዚህ መልክተኛ ማለት ወደ አንድ ስፍራ መልእክትን እንዲያደርስ የተላከ ማለት ከሆነ፡ በዚህ ‹‹መልክተኛ›› በሚለው ቃል ውስጥ ሁለት በሥም ያልተጠቀሱ ነገራት አሉ ማለት ነው፡፡ ገባህ?
እሱ፡- ምን እና ምን?
እኔ፡- ላኪ እና መልእክት!፡፡ ላኪ ሳይኖር መልክተኛ አይኖርም!፡፡ መልክተኛም ያለ መልእክት አይመጣም፡፡ እንትና መልክተኛ ነው ማለት፡ እሱን የላከው ላኪና እንዲያደርስ የተሰጠው መልእክት አልለ ማለት ነው፡፡ ትስማማለህ በዚህ?
እሱ፡- ግልጽ ነው እስማማለሁ፡፡
እኔ፡- ወደ ቁርኣኑ አንቀጽ ስንመለስ፡ መልክተኛ ተብሎ የተጠቀሰው መልአኩ ጂብሪል ነው በሚለው ሀሳብ ከላይ ተስማምነተናል አይደል?
እሱ፡- በሚገባ!
እኔ፡- አሁን መልክተኛውን መልአኩ ጂብሪል መሆኑን ካወቅን፡ የላከውን እና የተላከውን መልእክት ደግሞ ማወቅ ስለሚገባን፡ ማነው ላኪው የተላከው መልእክትስ ምንድነው ትላለህ?
እሱ፡- ላኪው አላህ ነው፡፤ የተሰጠው መልእክት ደግሞ ቁርኣን ነው፡፡
እኔ፡- በጣም ጥሩ፡፡ ስለዚህ መልእክት ባለቤትነቱ ለላኪው ነው ወይስ ለመልክተኛው?
እሱ፡- የላኪው ነው የሚሆነው!፡፡
እኔ፡- መልካም፡፡ ላኪው ደግሞ ጌታ አላህ ከሆነና መልእክቱ ደግሞ ቁርኣን ከሆነ፡ ቁርኣን የአላህ እንጂ የመልክተኛው የጂብሪል አይሆንም ማለት ነው፡፡ አሁን የተግባባን መሰለኝ?
እሱ፡- ታዲያ ቁርኣኑ ‹‹እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡›› ለምን አለ?
እኔ፡- ቁርኣኑ እንደዛ ያለውማ፡ መልክተኛው እንዲያደርስ የተሰጠው መልእክት መሆኑን ለመግለጽ ነዋ፡!
እሱ፡- እንዲያደርስ የተሰጠው የሚለው እኮ ቁርኣን ውስጥ የለም፡፡ ቁርኣኑ ላይ የተጻፈው ‹‹የክቡር መልክተኛ ቃል ነው›› የሚል ነው፡፡
እኔ፡- ላንተ ጊዜ ሲሆን ነው ቁርኣኑ ላይ አልተጻፈም የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ የምታነሳው? ቅድም ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው ይላል ብለህ ያልተጻፈ ስታነብ አልነበረም? ባንድ ራስ ሁለት ምላስ!፡፡
እሱ፡- አሁን ገተታህን ተወውና መልስልኝ፡፡
እኔ፡- ምኑን ልመልስልህ?
እሱ፡- በቁርኣኑ ውስጥ ‹እንዲያደርስ የተሰጠው› የሚለው ቁርኣን ውስጥ የለም፡፡ ቁርኣኑ ላይ የተጻፈው የክቡር መልክተኛ ቃል ነው›› የሚል ነው፡፡ ከየት አምጥተህ ነው አንተ እንዲያደርስ የተሰጠው ያልከው?
እኔ፡- መልክተኛ ማለት አንድን መልእክት ወደ አንድ ስፍራ እንዲያደርስ የተላከ ነው በሚል ፍቺ ከላይ አልተስማማንም እንዴ?
እሱ፡- እሱን ተስማምተናል፡፡
እኔ፡- ስለዚህ የክቡር መልክተኛ ቃል ነው በሚለው ውስጥ፡ ‹መልክተኛ› የሚለው ኃይለ-ቃል መልእክትን ወደታዘዘበት ስፍራ እንዲያደርስ የተላከ የሚል ፍቺን ስለያዘ፡ የክቡር መልክተኛው ቃል ነው ማለቱ ወደ ተላከበት ስፍራ እንዲያደርስ የተሰጠው ማለት እንጂ፡ ከገዛ ሀሳቡ ያፈለቀው የራሱ ንግግር የኾነ ቃል ማለት አይደለም፡፡ በአንዲት ቃል ‹‹መልክተኛ›› በሚለው ውስጥ መልእክትን እንዲያደርስ የተላከ የሚለው ሁሉ መካተቱን ልብ በል፡፡ አሁንስ?
እሱ፡- አላሳመነኝም ምንም፡፡
እኔ፡- እንድታምን እኔ በተራዬ ልጠይቅሃ?
እሱ፡- እሺ፡፡
እኔ፡- ቃሉ የራሱ የጂብሪል ከሆነ ለምን ጂብሪል መልክተኛ ተብሎ ተጠራ እንግዲያውስ?
እሱ፡- መልክተኛ የተባለውማ ከአላህ ዘንድ ስለተላከ ነዋ!
እኔ፡- ምንድነው የተላከው?
እሱ፡- ቁርኣንን እንዲሰጥ፡፡
እኔ፡- በተላከው ነገር ላይ የመልክተኛ ሚናና ድርሻ ምንድነው?
እሱ፡- መልክቱን በታማኝነት ማድረስ!
እኔ፡- የማንን መልእክት?
እሱ፡- የላኪውን፡፡
እኔ፡- ስለዚህ ቁርኣን የላኪው የአላህ መልእክት እንጂ፡ የመልክተኛው የጂብሪል ቃል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው ከማለት ይልቅ የክቡር መልክተኛ ቃል ነው የተባለው፡፡ የጂብሪል ቃል ነው ቢል ኖሮ፡ እራሱ ጂብሪል ከገዛ ሀሳቡ ያፈለቀው ወይስ ምን? የሚል ጥያቄን ያስነሳ ነበር፡፡ በጂብሪል ቦታ መልክተኛ የሚለው ቃል መጠቀሱ፡ የጂብሪል ሚና መልእክት ማድረስ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ለመጠቆም ነው፡፡ በተለይ ይህን ጉዳይ በሌላ የቁርኣን ክፍል ላይ እንዲህ ይገልጸዋል፡-
‹‹ለጂብሪል (ለገብርኤል) ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው፡፡ እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና፡፡›› (ሱረቱል በቀራህ 2፡97)
‹‹እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት ሙስሊሞቹንም ለመምራትና ለማብሰር (ቁርኣንን) ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው፡፡›› (ሱረቱ-ነሕል 16፡102
‹‹እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡ እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤ ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡ ግልጽ በኾነ ዐረብኛ ቋንቋ፡፡›› (ሱረቱ-ሹዐራእ 26፡192-195)፡፡
ማጠቃለያ፡-

ከተወሰኑ አመታት በፊት በአንድ የፓልቶክ ግሩፕ የቀጥታ የድምጽ ውይይት ላይ አንድ ግብጻዊ ሙስሊም ወንድማችን የገጠውን እንዲህ ሲያጫውተን ያዳመጥሁትን ላካፍላችሁ፡-

…የሆነ የክርስቲያን ዐረቦች ግሩፕ ላይ ከአንዱ ጋር ስለ ቁርኣን ምንነት እየተወያየሁ ሳለ፡ ክርስቲያኑ፡- ቁርኣን የጂብሪል ቃል እንጂ የአላህ ቃል አይደለም! ብሎ ተከራከረኝ፡፡ እኔም በተራዬ ማይክ ያዝኩና፡- ቁርኣን የአላህ ቃል መሆኑን አምነህ ባትቀበልም፡ ባላወቅኸው መንገድ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ መልክተኛና ነቢይ መሆናቸውን መስክረሀል አልኩት፡፡ እሱም እንዴት? ሲለኝ፡ እኔም፡- ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው ብለህ ከተናገርክ፡ መልአኩ ጂብሪል አይዋሽምና፡ የጂብሪል ቃል ነው ባልከው ቁርኣን ውስጥ ‹‹ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፡፡ ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡›› (ሱረቱል አሕዛብ 33፡40 የሚል ቃል ስለተቀመጠ፡ መልአኩ ጂብሪል እንኳ የአላህ ነቢይና መልክተኛ መሆናቸውን ስለመሰከረላቸው፡ አንተም መልአኩን ተከትለህ በሳቸው ነቢይነት ማመን፡ ወይንም መልአኩን ሀሰተኛ ነው ብለህ በውሸት መክሰስ እና የሳቸውምን ነቢይነት መካድ ነው ያለህ ምርጫ ስለው፡ መውጪያ ቀዳዳ በማጣቱ ከግሩፑ ባውንስ አደረገኝ፡፡ የካፊር መጨረሻው ይኸው ነው፡፡ አላህ ይምራችሁ፡፡

ፊ አማኒላህ

አቡ ሐይደር