የሀሰተኛ ነብያትን የፈውስ ድራማ በተመለከተ

ሼር ያድርጉ
420 Views

እናንት ጎረምሶች እንባችኹን ባደፈ እጃችኹ ማበሳችኹ አይቀርም!!!

ኢሊያህ ማህሙድ

በኣላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀሞቀሚያው (መጨረሻው)ነብይ ሙሐመድ የኣለህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን እንቀጥላለን
ወዳጄ እንደምን ከረሙ…ክረምቱ ገብቶ ሳይጨፍን፣ጉልበታችንም በቅዝቃዜው ሳይቀነበብ (ሳይጨመደድ) ሳሰላስለው የከረምኹትን ላካፍሎ ፈለግኹ፡፡ ወዳጄ እርሶም እንደታዘቡት ታሪክ ነጋሪዎችም ጻፎችም ኣንድ ወቅት ሑሴን ጅብሪል የሚባል ትንቢተኛ ከኣጼዎች ደጅ እንደነበር፣ ብዙ ተንብዮም የኣጼዎቹን ክፍለ ዘመን በትንቢት እንደተሻገረ ነግረውናል፡፡ በርግጥ የሰውዬው ነው የተባሉ ትንቢቶች ኹሉ ከርሱ ስለመኾናቸው ሰንሰለታዊ መረጃ የለንም፡፡ ጻፎችም ቢኾኑ እረኞች፣አዛውንቶችና አዛውንታት፣በአፈ-ታሪክና ነቢብ የሑሴን ጅብሪል ነው እያሉ የሚመላለሷቸውን ስንኞች ነው አሰባስበው ለሰውዬው ያደረጓቸው፡፡ ያም ቢኾን እኛን አይመለከትም!!! ምክንያቱም ኢስላም ለግለሰቦች ትንቢት ምንም ቦታ የለውም፤ የነብያት ትንቢት ራዕይ ነው፤ እኛን የሚያድነን ደግሞ እምነትና ተግባር ብቻ ስለኾነ…አይመለከተንም፡፡

ስለ ትንቢት ሲነሳ መቼም ኖስትራዳማስ ከፊት ለፊት ተሰላፊ ነው፡፡ ሰውዬው ኮከብ ቆጣሪ እንደነበር በርሱ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ዛሬ በኃያ ኣንደኛው ክ.ዘ. ትንቢት እንደወትሮው በግለሰቦች አፍ ተነግሮ የሚቀባበል ሳይኾን፣ በአየር ላይ ለዓለም የሚሰራጭ ዜና ኾኗል፡፡ ወዳጄ በሐገራችን ተነገሩ ተተነበዩ የተባሉ ኹሉም ትንቢቶችና መላምቶች፣ለድሓይቷ ሐገራችን ምን ፋይዳ ነበራቸው ብለው ቢጠይቁ…መልሱ ግለሰቦቹ መኖሪያቸውን አደላደሉበት እንጂ ለኛስ የረባ ነገር የለውም ነው፡፡

ባለንበት ዘመን ጎረምሶች ከትንቢት አልፈው በአደባባይ ያለምንም ስጋትና ማቅማማት ታየን ተገለጸልን በሚል ስሜት በዓለም ፊት ሲዋሹ እያየን ነው፡፡ የኣምላክ እጅ ነን በሚል አጓጉል ትምከትም ፈወስን እያሉ ሲደባብሱ እያየን ነው፡፡ ስለነዚህ ኹሉም ግለሰቦች ኹለት ነጥቦችን አንሰተን ወጋችንን እንቋጭ፡-

[ግልጠታችሁ ለምን እዚህ ላይ ብቻ ተገደበ]

እናንት በ”ፈጣሪ” ሥም እየማላችኹ ተገለጠልን፣ታየን የምትሉ ሆዳችሁ የገደላችሁ፣በሌላው ቀብር ላይ ቆማችሁ ሰርጋችሁን የምትበሉ፣ፈጽሞ ርህራሄ ኣልባ የሂትለርና ስታሊን አለታማ ልብ “የታደላችሁ” ጎረምሶች ሆይ!!! “እየታያችኹ” እና “እየተገለጠላችኹ” ያለው ነገር ስልምን ነው በሰይጣንና በጠንቋይ ላይ ብቻ የቀረው!!!! ኹላችኹም በምልዓት ታየን ምትሉት ወይ ሰይጣን ነው፤ ወይም ጠንቋይ እያሴረብህ ነው የሚል ነው፤ ወይም የኣባትህ ስም እገሌ ነው…ስልክ ቁጥርህ እንዲያ ነው…ከሚስትህ ጋር ተኳርፈኃል፣ስራ አልተሳካልህም..ወዘተና አከተ የሚል ብቻ የኾነው ስለምን ነው!!!፡፡ ስለምን ነው “የገለጠላችኹ” ኣካል ከነዚህ አሰሰ ገሰሶች ውጪ መግለጥ ያልቻለው…

እኛ በዓለም የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉ ሐገራት ውስጥ የመጀመሪያ ነን፡፡ የነበረን የሶስት ሺም የስድስት ሺም….የትኛውም ታሪክ ዛሬ ያተረፈልን ድህነት ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ገላጩ ኣካል ስልምነው ከድህነት እንድንወጣ፣ የቱ ጋር ነዳጅ እንዳለ፣ የቱ ጋር አሉሚኒየም፣ የቱ ጋር ዚንክ፣ የቱ ጋር ወርቅና ብር…እንዳለን የማይነግራችኹ… እሺ ምናልባት እነዚህ ውድ ነገሮች ስለኾኑ ሊከብደው ለራሱም ላይገለጥለት ከቻለ፣ ስለምን ነው የቱ ጋር የከርሰ ምድር ውኃ እንኳ እንዳለን መናገር ያልቻለው…ወይም እሺ ጥያቄኣችንን ቀለል እናድርገውና የኾነ ቀመር (ፎርሙላ) ለምን አይገልጥላችኹም…ለምሳሌ የዚህ ዓይነት fX = 21x+g
21 = ኃያ ኣንደኛው ክፍለ ዘመን ለማለት ነው፤ x = ውሸታም ነብያት ናቸው፤ g = በመሬት ስበት ፍጥነት ኢትዬጵያን ገደል እንዳይከቷት ያሰጋል፡፡

ወዳጄ ይህንን ኹሉ የለፋኹት “ለገላጩ” አካል ቀለል ላድረግለት በሚል ወገናዊነት ብቻ ነው!!!! ገላጩ የኾነ ቀመር ቢያስቀምጥልንና ቀመሯን ተጠቅመን እኛም ወዲያው እንደነጮቹ ሐብታም እንኾን ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው ገላጫችኹ ግን ይህን ማድረግ ተሳነው…ነጋ ጠባ ሰይጣንና ጠንቋይ ብቻ እያሳየ ገደላችኹ፡፡

የኣዳም እግር አሻራ የተባለችውንና እጆቿን ወደ ሰማይ ታነሳለች የተባለላት ሐገራችን ይህን ያህል ምስቅልቅሏ ሲወጣ፣ “ገላጫችኹ” ስለምነው ዝም ያለው!!! ሰዎች ሲራቡና ሲታረዙ፣ሲገደሉና ሲሞቱ “ገላጩ” የኾነ መፍትሔ እንዴት ሹክ አላላችኹም…ያን ያህል ቅንባ ሙሉ ወሬ ስታወሩ ኣንድስ እንኳ ፍንጭ እንዴት ሳይሰጣችኹ ቀረ….

[ፈውሳችኹ ስለምንስ ከመድረክ ላይ በቻ ኾነ]

ነብያትና ቅዱሳን በየትኛውም ስፍራ ተዓምራትንና ፈውሶችን እንዳስፈላጊነቱ እንደፈጸሙ የናንተው መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ታዲያ የናንተው ተዓምርና ፈውስ ስለምነው ከመድረክ ብቻ የቀረው…እውነት ነው፤እያሳያችኹን ያለው ከኣጫጭር ተውኔት የሚመደብ መጨረሻው ቀድሞ የሚታወቅ ትርዒት ነው፡፡ ያም ቢኾን አልፎ አልፎ ለበዓሉ ድመቀትና ውበት ሲባል ከአኪም ቤትም ጎራ እያላችኹ የከፈላችኹትን ሰው ስትፈውሱ ብታሳዩን መልካም ነበር፡፡ ኹሉም ያው እከክልኝ ልከክልህ ቢኾንም፣ ቢያንስ ለተመልካች አይሰለችም፡፡ “ፈውሳችኹ” እና ዘይት ልቅለቃው ከመድረክ ብቻ መኾኑ ዘረኛ፣ ጎጠኛና ጨለምተኛ እንድትባሉ ምክንያት እንዳይኾን ያሰጋል፡፡ በእውን ዳሳችኹ ወይም ዘይት ቀብታችኹ መፈወስ ሚቻላችኹ ከኾነ፣ ከሐኪም ቤት ኑና ፈጽሙት፣ያኔ እናንተ ምትፈልጉትን ምታስቡትንና ምትዋሹለትን ሐብት ከመቅጽበት ታገኙታላችኹ፡፡ ቀናት ሳይገሰግሱ በሀብት ላይ ሐብት ትጎናጸፋላችኹ፡፡ ኅልቆ-መሳፍርት፣ የባሕር አሸዋ ብርና ወርቅ ይኖራችኋል!!!

[መንግስት ቢያስብበት]

ወዳጄ በአሸዋ ላይ የተካበ ጎጆ እንደማያከርም ግልጽ ነው፡፡ ከዝናብ በፊት በሚነፍስ ትንሽ ነፋስ ይወድቃል፡፡ ጎረምሶቹም የነርሱ ይህ ኹሉ ቁና ውሸት ኣንድ ወቅት እንደሚቦል ያውቁታል፡፡ እስከዚያ ግን በውሸት ቁና ሰውን እያጫኑና ቀቢጸ-ተስፋ እያስጨበጡ “በል በለው የሐሙሱን ፈረስ…” ይጋልቡታል…፡፡ ይሄ ከኣእምሮ የተጣላ ብኩን ሕዝብ ከፊት ለፊቱ በትንቢትና ግልጠት ስም ሲዋሹ እንኳ ፈጽሞ መረዳት አልቻለም፡፡ ከነጭ ኪሱና መሐረቡ እየፈታ ለጎረምሶቹ ግንብ ይክባል፤እርሱ በባዶ እግሩ እየሄደ፣እነርሱን በሪቮ ያንፈላስሳል፡፡ ሕዝቡ ይህን ያህል በኣንድ ሌሊት ሶስቴ እንደተዘረፈ ሰው በድን ከኾነ፣ መንግስት ስለምንድንነው እነዚህን ግለሰቦች በዝምታ እያለፈ ያለው…!!! በፈውስ ስም ግለሰቦች እየሞቱ፣ አካለ ስንኩላንም እየኾኑ፣የድሀው ገንዘብ ግን በአጓጉል ተስፋ ወደ ግለሰቦች ሒሳብ ሲጋጋዝ፣ መንግስት “ጆሮ ዳባ ልበስ፤ ዓይንም ሰብሰብ በል” ማለቱ ስለምንድር ነው…!!! ጉዳዩ መንግስታችንን አጓጉል እንድንጠረጥር እያደረገን ስለኾነ፣ ጥርጣሬያችንን ሊያጸዳ ይገባዋል፡፡ ሌቦችም ፍርዳቸውን ሊያገኙ፣ ጀሌውና ፋኖው ተከታይም በትክክል ወደ ራሱ ሊመለስ ይገባዋል፡፡ ያ ካልኾነ ግን እኔ እንደተገለጠልኝ ከኾነ፣ ሕዝብ በራሱ የነቃ ለት… ሚኾን ይመስለኛል!!!

ቸር እንሰንብት

Shortlink http://q.gs/Eye3t