እናንተ ንስሐ ያስፈልጋችኋል!!!

ሼር ያድርጉ
379 Views
ኢሊያህ ማህሙድ በኣላህ ስም እጅግ ኣዛኝ እጀግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን በተላኩ የመጨረሻው የኣላህ መልክተኛ ላይ ሰላም ይሁን ብለን ቀጠልን፡፡ ወዳጄ ዛሬ ማወጋዎ ከሰሞኑን ከተጣድኹበት ጉባኤ የተነሱ በርካት ነጥቦች ሲያብሰለስሉኝ ብቻዬንም እንደ ወፈፌ ሲያስወጉኝ (ሲያስቀባጥሩኝ) ከነበሩት ውስጥ ጥቂቱን ይኾናል፡፡ እውነት እውነት እሎታለሁ! እዚህ ግድግዳ ላይ መሰል ወጎችን ላለመጻፍ ወስኜ ነበር፡፡ ምክንያቱም ብዙኃኑ ቋንቋው እንደራቀበት እየተረዳኝም እንዳልኾነ ስለተረዳኹ፤ኣንባቢ ካልተረዳኝ ለማንስ ነው ምጽፈው ብዬ ከመሰል ጽሑፎች ታቅቤ ከረምኹ፡፡ አሁን ከምሽቱ 3፡21 ላይ እገኛለሁ መንፈሴ ከትላንት ጀምሮ ርብሽ እንዳለ ነው፡፡ መጽሐፍት ቤቴ ውስጥ ቁኝ ብዬ በወንበሬ እየተሸከረከርኹ ከራሴ ጋር ብዙ ለፈለፍኹ፤…በስተመጨረሻም እነሆ ከራሴ ጋር ያወጋኹትን ጉዳይ እጅግ አሳጥሬው ላካፍሎ መልካም መስሎ ታየኝ ፡- [በመጀመሪያ] ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በየመድረኩ ማስተማር ሳይኾን ወደ ራሳቸው አቋምና ተቋም ብሎም ወደ ራሳቸው አዋቂነትና ጠቢብነት ይጎትቱን የነበሩ የያኔው ኮበሌዎች ከጉባኤው ተከስተው አየኹ፡፡ ማጉያውን ይዘው ስለመቻቻልና ስለኣንድነት የማር ወለላ በተቀቡ ቃላት ዓርፍተ ነገርን ከነገር እያጋጩ ሲያወሩ ጆሬዬ ሰምቶ ዓይኔም አይቶ ማመን ከበደኝ፡፡ ንግግራቸውን እያደምጥኹ በምናብ ጥቂት አስርት ዓመታትን ወደ ኋላ ነጎድኹና ገና ብላቴና እያለን ከነርሱ ፊት ተቀምጠን ስለመቧደን፣ የ“ከኛ ውጪ ላሳር” ዜማን ሲዘምሩን፣ ሰቅጣጭ ሆሳእ ቃላት ከአንደበታቸው ያለምንም ርህራሄ እየተፈተለከ ግለሰቦችን ሲሰድቡና ሲያዋድቁ፤ እነርሱን የተደባለቀ ብቻ ፍፁም ትክክለኛ ፍኖት ውስጥ እንዳለ ሲነግሩን፤ በሰው እያፌዙ ሲያሽካኩን ታየኝ፡፡ ከቅቤ ክር ሚመዘው (ነውር ፈላጊ) ምላሳቸው ጠብታውን ውቅያኖስ አድርጎ በንቄት ታንኳ ሲያስቀዝፈን፤እኑስ (ጥቂት) ችግሩን ተራራ አስመስሎ ሽቅብ በትችት ኮቴ ሲያስፈነጥረን…ያ የወጠጤ ደፋር ኣንደበታቸው ታወሰኝ፡፡ ሙስሊሙን በምልዓት ከኣንድ ጎራ መድበው ራሳቸውን ደግሞ ካኣንድ ሩቅ ካለ ሃሳባዊ ጎራ ሰንቅረው የሌሎች ጠንካራ ጎንና ልፋት እንዳይታየን ከቀጭን አየር ላይ “እብቅ” እያፈሱ በብላቴናው ዓይናችን ውስጥ ሲረጩት ታወሰኝ፡፡ “ጥቁር” እንጂ “ነጭ” የማይታየው ዓይናቸው ፍንትው ባለ ሰማይ ጭጋግ እየፈለገ ሲጠቁመንና ሲያመላክተን ታየኝ፡፡ ስለመከፋፈል፣ መቆራረጥና መለያየት ብቻ ኣላሚ የሚመስለው “ብሩህ” ኣእምሮአቸው ኡማውን በቀበሌ፣ በጎጥና ቅሬ (እድር) ከፋፍሎ እንደቅርጫ ሲያቃርጠን፤መስጂዶቻችን በማንም ውርጋጥ በየጊዜው ሲደፈሩ እነሱን እያየኹና እያዳምጥኹ የያኔው ምግባራቸው ትዝ አለኝ፡፡ ወደየትምህርት ተቋማቱ እነሱ በረጩት ዲዲቲ መርዝ እየተመረዘ የሚቀላቀለው የኔ ብጤው ወጣት ኹሉም በየፊናው ጥጉን ይዞ የነርሱን “ነጠላ የጨረባ ዜማ “ሲያንቆረቁር”ና “ሲውረገረግ” በነሱ ንግግር ውስጥ መጣብኝ፡፡ ዛፍ በፍሬው ይለያል ነውና ምስጢሩ፣እነሱ የተከሉት ዛፍ እነሆ አፍርቶና ጎምርቶ መርጋጋና ጎፍናና ፍሬ ሰጥቷል፡፡ ሰብስበው አይበሉት እማይቻል ሆነባቸው፤ እንዳይነቅሉት ስር መስደዱ ጡንቻን የሚጠይቅ ኾነ፡፡ አጥልቀው የተከሉት እነርሱ ኾነው፣ሌላው ነው አጥልቆ የተከለው ማለታች ደግሞ ያስተዛዝባል፡፡ያኔ አርቀው ሲተክሉት “ይቅር ተዉ …ይህ ለኹላችንም አይበጅም” ሲባሉ አንገተ ደንዳና ኾነው አሻፈረን ብለዋል፡፡ ዛሬ አፋቸውን ጠርገው ተባብረን ይህንን ዛፍ እንንቀለው ለኣንድነታችን ሳንካ ሆኗል …ማለታቸው ደግሞ ይበልጥ ያስተዛዝባል፡፡ ልብም ይነካል፡፡ [ከበመጨረሻው በፊት] ወደ ዛሬ ከተመለስኹ በኋላ እንዲህ አልኹ፡-
እነሱ ያኔ በጠጡት “የልዩነት ካቲካላ” ዛሬ እኛ እየተንገዳገድን ነው፡፡ እነርሱ ያኔ በሳሉት ፈንዜ (ሰይፍ) እኛ ዛሬ እየተመታተርን (መቆራረጥ) ነው፡፡ እነርሱ ባጤሱት አጤፋሪስ እኛ እየነሆለልን ነው፡፡ እውነት ነው በነርሱ ውስጥ ተውሒድን፣ቢድዓንና ኣንድነት አውቀናል፤ ይህን መልካም ጎናቸውን ግን በዜሮ የሚያባዛ የስራይ ስሪት (የሴጣን ሥራ) አሳልፈዋል፡፡ ስለዛም ትውልድ ኹሉ ይወቅሳቸዋል፡፡ [በስተመጨረሻም] እናንተ የያኔው ኮበሌዎች የዛሬው የኣንድነት ሐዋሪያት ሆይ! በምልዓት ንሰሐ ግቡ…ወሬያችኹ ኹሉ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” አይሁን፤የኣንድነት የጋራ ዶሴ (ፋይል) እንክፈት ብላችሁ በተከፈተው ዶሴ ውስጥ ሌላ የራሳችሁን ንዑስ ዶሴ እየከፈታችሁ ኣንድነቱን ከኣንገት በላይ አታድርጉት፡፡ ለተፈጠረው መገፋፋት እናንት የኣንበሳውን ድርሻ እንደምትይዙ እወቁ፡፡ በልባችሁም ያዙ፡፡ ታላቅ ሸፈጥና በደል ፈጽማችኋልና ወደ ኣላህም ህዝቡም ዳግሞ ትመለሱ ዘንድ የመጨረሻውን ንስሐ ግቡ፡፡ኣላህ ይቀበላችሁ!!!