እርሱ ጌታዬ አላህ ነው!

1,013 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

ከአንዳንድ ክርስቲያኖች የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ እሱም፡- ሙስሊሞች አምላካችን የምትሉት አላህ ማነው? ምንድነው? አካል አለው ወይስ የለውም? አይነት ጥያቄ! (አስተግፊሩላህ)፡፡ ሰው ፈጣሪ አምላኩን እንዴት ማምለክ እንዳለበት፡ ህጉንና ትእዛዙን እንዴት መጠበቅ እንደሚገባው፡ ማሰብና መጨነቅ ሲኖርበት፡ ይህ አምላክ ምን አይነት ነው? አካልስ አለው ወይስ የለውም? የሚል ጥያቄ ማንሳት የጤና አይመስልም፡፡ በዚህ ምድር ላይ አምላክ በአይነ-ሥጋ የሚታይ ሳይኾን፡ በአይነ-ልቦና የሚታወቅና በልብ የሚታመን፣ በምልክቶችና በተአምራት ማንነቱ የሚገለጥ፣ በፍጥረታት ሥራዎቹ ስሙና ባሕሪው የሚነገር ነው፡፡ ግን አምላክ ስጋ ለበሰ፣ እንደኛ ሰው ሁኖ ተወለደ፣ እኛን መስሎ ኖረ ብሎ ያመነ ጭንቅላት፡ ከሌሎችም ይህንኑ አይነት ነገር ካልኾነ በቀር ወጣ ያለ ነገር ለመስማትና ለመቀበል ይከብደዋል፡፡

‹‹ኢለለዚ ሰአለ አይነላህ?›› በሚለው ኪታብ ላይ እንደተቀመጠው፡ በአንድ ወቅት በአምላክ መኖር የማያምኑ ሙልሒዶች (እምነት አልባዎች) የወቅቱ የኢስላም ሊቅና ኢማም የነበሩት አቡ ሓኒፋህ (80-150 ሂጅ.) ረሒመሁላህ ዘንድ ይመጡና፡- እስኪ ስለ ጌታህ ዛት (ሀልዎት፣ ህልውና) ምንነት ንገረን፡፡ እሱ እንደ ብረት ጠጣር ነውን? ወይስ እንደ ውሀ ፈሳሽ ነውን? ወይስ እንደ ጭስና እጣን ትነት ነገር ነው? በማለት ጠየቁ (አስተግፊሩላህ)፡፡ ኢማሙም፡- ሊሞት የተቃረበ ህመምተኛ ሰው ዘንድ ተቀምጣችሁ ታውቃላችሁን? አሏቸው፡፡ እነሱም ‹‹አዎን!›› በማለት መለሱ፡፡ ኢማሙም፡- ይህ ሰው ከሞተ በኋላ አናግሯችሁ ነበርን? ሲሏቸው፡ በፍፁም! በማለት መለሱ፡፡ ኢማሙም፡- ከሞት በፊት ሰውየው ይናገር ነበር፡ ከሞት በኋላ ግን የማይናገር የማይንቀሳቀስ በድን ሆነ! ይህን ሁኔታውን የቀየረው ነገር ምንድነው? አሏቸው፡፡ ሰዎቹም፡- ከሰውነቱ ሩሑ (መንፈሱ) በመለየቷ ነው! ብለው መለሱ፡፡ ኢማሙም ‹‹እውነት ሩሑ ወጥታ ነውን?›› ሲሏቸው፡ እነሱም በድጋሚ ‹‹አዎን!›› አሉ፡፡ ኢማሙም፡- በሉ እንግዲህ ይህቺን ሩሕ ምንነቷን ግለጹልኝ፡፡ እሷ እንደ ብረት ጠጣር ነችን? ወይስ እንደ ውሀ ፈሳሽ ነችን? ወይስ እንደ ጭስና እጣን ትነት ነገር ነች? አሏቸው፡፡ ሰዎቹም ስለሷ ዝርዝር ሁኔታ የምናውቀው ነገር የለም! አሉ፡፡ ኢማሙም፡- ሩሕ ፍጥረትና ግኝት ከመኾኗ ጋር ምንነቷን በቅጡና በወጉ ማወቅ ከተሳናችሁ፡ እንዴት ደካማና ውስን በኾነው ሰዋዊ ዕውቀት የሩሕ ፈጣሪና አስገኚ የኾነውን አምላክ፡ ስለ ህልውናው ምንነት እንዳብራራላችሁ ለመጠየቅ ደፈራችሁ? እሱ አላህ ፡- ‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡›› (ሱረቱ-ሹራ 42፡11)፡፡ አሏቸው፡፡

እምነት ማለት፡- በሚታይና በሚዳሰስ ነገር ላይ ብቻ ተመርኩዞ፡ የጉዳዩን መኖር ማጽደቅ አይደለም፡፡ ይህንንማ ሰው የተባለ በጠቅላላ በጋራ የሚቀበለው ነገር ነው፡፡ የዛኔም አንዱ አማኝ ሌላው ከሀዲ የሚል ክፍፍል አይኖርም፡፡ እምነት ግን ከዚህ በዘለለም መልኩ፡- በመለኮታዊ ምሪት በመታገዝ፡ በአይን ያልታዩና ከስሜት ህዋሳት የራቁ የኾኑ ነገራትን በጠቅላላ አምኖ መቀበል ነው፡፡ መላእክት የሚባሉ ፍጥረታት መኖራቸውን፡ ሙስሊሞች አይሁዶችና ክርስቲኖች ያምናሉ፡፡ በተጨማሪም እነዚህ መላእክት ክንፍ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን፡- ይህ ክንፍ ምን አይነት ነው? ከምን የተሰራ ነው? በአይን እንደምናየው የዶሮና የአእዋፋት ክንፍ አይነት ነው ወይስ ምን? ቢባል፡ ምንድነው መልሱ የሚኾነው? ባልተጻፈ እና ባላየነው ነገር ላይ ምንም መናገር ስለማንችል፡ የፈጠራቸው አምላክ እሱ ምንነታቸውን ይወቀው ከማለት ውጭ ምንም የምንለው የለንም፡፡ ታዲያ የነሱ ፈጣሪ የኾነውስ አላህ ምን አይነት ነው? አካል አለው ወይስ የለውም? ደግሞስ ምን አይነት አካል? ብለን ለመጠየቅ እንዴት ደፈርን? አላህ ይቅር ይበለን፡፡

ፈጣሪ አምላካችን አላህ በሰጠንና በለገሰን አዕምሮ ስለሱ ማንነት በአቅማችን ልክ እናውቀውና እንረዳው ዘንድ ከራሱ ጋር አስተዋውቆናል፡፡ ከፊል ባሕሪያቱንና ማንነቱንም በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል፡፡ በፍጥረታት ሥራው እና በምልክቶቹም እሱ ማን እንደኾነ ነግሮናል፡፡ እኛም ከፍጥረታት ሥራዎቹ፣ ከምልክቶቹ፣ እንዲሁም ከቃሉ በመነሳት ስለሱ ማንነት ያወቅነውንና ያመንነውን እንዲህ እንናገራለን፡-

1/ እሱ ፍጹም አንድ የኾነ አምላክ ነው፡- ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር፣ ቀንና ሌሊትን በማፈራረቅ፣ ጸሀይና ጨረቃን በተመደበላቸው ሰአት ብቅ እያሉ ለሰው ብርሀን እንዲሰጡ በማድረግ፣ ፍጥረተ ዓለሙን በጠቅላላ ምንም ሳይዛነፍ፣ የተፈጥሮ ስርአት አንድም ቀን እክል ሳይገጥመው ለዘመናት በማስተዳደር ብቻውን ያለ አንድ ጌታ፣ ንጉስ፣ አምላክ መኾኑን ይነግረናል፡፡
ከርሱ ጋር አብሮት ያለ ዋና ሰራተኛ፣ መሀንዲስ፣ አማካሪ የሚባል ሌላ ኃይል የለም፡፡ ይህ ነገር ቢኖር ኖሮ፡ የሀሳብ ልዩነት ይፈጠርና ሁሉም ከፍጥረቱ ላይ የራሱን ድርሻ ይዞ በተገለለ ነበር፡፡ ከዚያም ከፊሉ በከፊሉ ላይ የበላይ ለመኾን ሲል አንዱ የሰራውን ሌላው ሲያጠፋበት ፍጥረተ ዓለሙ በተናጋ ነበር፡፡ ይህ በኛው ሕይወት በተጨባጭ የምናየው ነገር ነው፡፡ ሀገር በአንድ መሪ እንጂ አትመራም፡፡ ቤት በአንድ አባወራ እንጂ አልቆመም፡፡ ፋብሪካ በአንድ ማናጀር እንጂ በሁለት ማናጀር አይቆምም፡፡ እነዚህን እውነታዎች የአላህ ቃል እንዲህ ይገልጻቸዋል፡-

“አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፡፡ ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፡፡ ከፊላቸውም በከፊሉ ለይ በላቀ ነበር፡፡ አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ፡፡” (ሱረቱል ሙእሚኑን 23፡91)፡፡

“በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፡፡ የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ፡፡” (ሱረቱል አንቢእ 21፡22)፡፡

“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡163)፡፡

“ለእናንተም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም ገራላችሁ፡፡ ከዋክብትም በፈቃዱ የተገሩ ናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ ለሚያውቁ ሕዝቦች በእርግጥ ተዓምራቶች አልሉ፡፡” (ሱረቱ-ነሕል 16፡12)፡፡

2/ እሱ እጅግ በጣም ሩኅሩህና አዛኝ ነው፡- ጌታ አላህ ለባሪያዎቹ ከነፍሳቸው በላይ ያዝናል ይራራል፣ ከቁጣው ትእግስቱ፣ ከቅጣቱ ምሕረቱና ይቅር ባይነቱ የቀደመ አምላክ ነው፡፡ እስካሁንም በሕይወት ያለነው በቸርነቱ ብዛት እንጂ፡ በመልካም ሥራችን ትሩፋት አይደለም፡፡ ልክ እንደ ምድራዊ ስርአት ህግን በተላለፍን ቅጽበት ወዲያው የሚቀጣን ቢኾን ኖሮ፡ በምድር ወለል ላይ አንድም ተንቀሳቃሽ እንደማይኖር ሲገልጽ እንዲህ ይለናል፡-

“አላህም ሰዎችን በሠሩት ኀጢአት ቢይዝ ኖሮ በወለሏ (በምድር) ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ ባልተወ ነበር፡፡ ግን እተወሰነ ጊዜ ድረስ ያቆያቸዋል፡፡ ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት (በኀጢአታቸው ይቀጣቸዋል)፡፡ አላህ በባሮቹ (ኹኔታ) ተመልካች ነውና፡፡

” (ሱረቱ ፋጢር 35፡45)፡፡

“ጌታህም በጣም መሃሪው የእዝነት ባለቤቱ ነው፡፡ በሠሩት ሥራ ቢይዛቸው ኖሮ ቅጣቱን ለእነሱ ባስቸኮለባቸው ነበር፡፡ ግን ለእነሱ ከእርሱ ሌላ መጠጊያን ፈጽሞ የማያገኙበት ቀጠሮ አላቸው፡፡” (ሱረቱል ከህፍ 18፡58)፡፡

በዚህ አንቀጽ መሠረት አላህ ለቅጣት የማይቸኩል፡ ባሮቹን ኃጢአት ሲፈጽሙ እየተመለከተና እየሰማ ግን የተወሰነ ጊዜ ድረስ የሚያቆይ አምላክ መኾኑን እንረዳለን፡፡ ያም የተወሰነ ግዜ ተውበት አድርገው ወደሱ የሚመለሱበት የኾነ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ኃጢአተኛ መኾናቸውን አምነው ወደ አላህ በተጸጸተ ልብ ከተመለሱ ደግሞ፡ አላህ ኃጢአትን በጠቅላላ የሚምር እና ይቅር የሚል አምላክ መኾኑን እንዲህ ይነግራቸዋል፡-

“በላቸው «እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፡፡ አላህ ኃጢኣቶችን በመላ ይምራልና፡፡ እነሆ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነውና፡፡” (ሱረቱ-ዙመር 39፡53)፡፡

“ባሮቼን እኔ መሓሪው አዛኙ እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡ ቅጣቴም እርሱ አሳማሚ ቅጣት መኾኑን (ንገራቸው)፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 49-50)፡፡

“እኔም ለተጸጸተ፣ ላመነም፣ መልካምንም ለሠራ፣ ከዚያም ለተመራ ሰው በእርግጥ መሓሪ ነኝ፡፡” (ሱረቱ ጣሀ 20፡82)፡፡

“..ጌታችሁን ምሕረትን ለምኑት፡፡ እርሱ በጣም መሐሪ ነውና፡፡” (ሱረቱ ኑሕ 70፡10)፡፡

3/ እሱ አላህ ፈጽሞ አምሳያ የሌለው ነው፡- አላህ ፈጣሪና ጌታ ነው፡፡ ከሱ ውጭ ያለው በጠቅላላ ፍጥረትና ባሪያ ነው፡፡ አላህ ፍጡሩን አይመስልም፡፡ ፍጡራንም አላህን አይመስሉም፡፡ ሰው የሚያየውም ሆነ በህሊናው የሚያስበው ነገር በጠቅላላ ፍጥረታዊ ነው፡፡ አላህ ደግሞ የዛ ተቃራኒ ነው፡፡ ስለዚህ የአላህን ፍጹማዊ የጌትነት ባሕሪውን ከማጽደቅ ውጭ (ሰሚ፣ ተመልካች፣ የሚናገር፣ የሚራራ ወዘተ መኾኑን) ከፍጡራን ውስናዊና ጊዜያዊ ባሕሪ ጋር አናመሳስለውም፡፡ እሱ ጌታችን ቢያይ ፍጥረቱን በመላ፡ እኛ ብንመለከት ከፊታችን ያለውንና በተወሰነ ሜትር ርቀት ያለውን ብቻ፣ እሱ ጌታችን ቢሰማ የፍጥረቱን ቋንቃ በጠቅላላ፡ እኛ ብንሰማ ውስን ቋንቋ በውስን ርቀት ብቻ ወዘተ ነውና አላህን የሚመስል የለም!፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“ለአላህም አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡ አላህ (መሳይ እንደሌለው) ያውቃል፡፡” (ሱረቱ-ነሕል 16፡74)፡፡

“(እርሱ) የሰማያትና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው፡፡ እርሱን በመገዛትም ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን?” (ሱረቱ መርየም 19፡65)፡፡

“ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ነው፡፡ ከነፍሶቻችሁ ሴቶችን ከቤት እንስሳዎችም ዓይነቶችን (ወንዶችና ሴቶችን) ለእናንተ አደረገላችሁ፡፡ በእርሱ ያበዛችኋል፡፡ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡” (ሱረቱ-ሹራ 42፡11)፡፡

“ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም፡፡” (ሱረቱል ኢኽላስ 112፡4)፡፡

4/ እሱ አላህ አል-ሙጂብ (የባሮቹን ልመና) ተቀባይ ነው፡- ጌታ አላህን በአይነ ስጋችን ሳናየው፡ በልባችን አምነን ተቀብለነው በችግር ጊዜ እጃችንን ወደላይ በማንሳት፡ ልብ ከመላስ ጋር በመጣመር ‹ያረብ!› ስንለው ምላሽ የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ስንትና ስንት ሚሊዮኖች በደረሰባቸው ችግር፣ ጭንቀትና መከራ አላህን ተማጽነው ምላሽን አግኝተዋል!፡፡ ሁሉም ራሱን ይጠይቅ፡፡ አላህ ለባሮቹ ቅርብ እንጂ ሩቅ ያልኾነ፣ ዱዓን ሰሚና ተቀባይ እንጂ መላሽ ያልኾነ አምላክ መኾኑን እንዲህ ይነግረናል፡-

“ጌታችሁም አለ «ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና፡፡ እነዚያ እኔን ከመግገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ኾነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ፡፡” (ሱረቱ ጋፊር 40፡60)፡፡

“ባሮቼም ስለእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፡፡ ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡186)፡፡

“«ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው፡፡ ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡ እርሱ ሰሚ ቅርብ ነውና» በላቸው፡፡” (ሱረቱ ሰበእ 34፡50)፡፡

ለዛሬ ጽሑፍ ላለማስረዘም በዚህ ላብቃ፡፡ አላህ ምንድነው? ብላችሁ የጠየቃችሁን ወገኖቻችን ሆይ! ስለ አምላካችሁ የተወሰነ ነገር እንዳወቃችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አላህ ቅኑን ጎዳና ይምራችሁ፡፡

“…እርሱ (አልረሕማን) ጌታዬ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ በርሱ ላይ ተጠጋሁ፡፡ መመለሻየም ወደርሱ ብቻ ነው» በላቸው፡፡” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡30)፡፡

“እርሱ አላህ ነው፤ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ የኾነ ነው፡፡ እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ ነው፡፡ እርሱ አላህ ነው፡፡ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ፣ ንጉሡ ከጉድለት ሁሉ የጠራው፣ የሰላም ባለቤቱ፣ ጸጥታን ሰጪው፣ ባሮቹን ጠባቂው፣ አሸናፊው፣ ኀያሉ፣ ኩሩው ነው፡፡ አላህ ከሚያጋሩት ሁሉ ጠራ፡፡ እርሱ አላህ ፈጣሪው (ከኢምንት) አስገኚው፣ ቅርጽን አሳማሪው ነው፡፡ ለእርሱ መልካሞች ስሞች አልሉት፡፡ በሰማያትና በምድርም ያለው ሁሉ ለእርሱ ያሞግሳል፡፡ እርሱም አሸናፊውና ጥበበኛው ነው፡፡” (ሱረቱል ሐሽር 59፡22-24)፡፡