ኢየሱስ መቼ ተወለደ?

1,004 Views

የኢየሱስን የልደት ዓመት በተመለከተ ሁለት ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አለ። የማቴዎስና የሉቃስ ዘገባ። ማቴዎስ ኢየሱስ የተወለደው በይሁዳ የሮማው ተጠሪ ታላቁ ‹‹ሄሮድስ›› በንግስና በነበረበት ጊዜ ነው ይላል።

‹‹ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን ተወለደ።››
(ማቴ 2፡1-2)

ሉቃስ ደግሞ ኢየሱስ የተወለደው ‹‹ቄሬኔዎስ›› የሶርያ አገረ ገዥ በነበረበት ጊዜ ነው የሚል ለየት ያለ ዘገባ አስፍሯል።

‹‹ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ።…ዮሴፍም…ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ የበኵር ልጅዋንም ወለደች።››
(ሉቃ 2፡2-7)

ሁለቱ ገዥዎች ሄሮድስና በቄሬኔዎስ ደግሞ በተለያየ ጊዜ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን የታሪክ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ዘመናዊ የታሪክ አጥኝዎች እንደሚሉት ንጉስ ሄሮድስ የኖረው በአውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር ከኢየሱስ ልደት በፊት ከ73-4 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ኢየሱስም ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ከእናቱና ጋር በስደት ግብፅ አገር እንደነበረ ማቴዎስ 2፡14 ላይ ተገልጿል።

‹‹ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።››

ሉቃስ ግን ኢየሱስ የተወለደው በመጀመሪያው የቄሬኔዎስ ህዝብ ቆጠራ ጊዜ ሲሆን ታዋቂው የአይሁድ የታሪክ ተመራማሪ ጆሲፈስ እንደዘገበው ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ የሆነው ታላቁ ሄሮድስ ከሞተ በኋላና በምትኩ የተተካው ልጁ ከንግስናው በወረደበት ከ6-7 C.E ውስጥ ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው።

ከዚህ በመነሳት ንጉስ ሄሮድስ በሞተበትና ቄሬኔዎስ አገረ ገዥ ሆኖ የህዝብ ቆጠራ ባካሄደበት መካከል የ7 ዓመታት ልዩነት ሲኖር ኢየሱስ ደግሞ ሄሮድስ ሲሞት የ3 ዓመት ልጅ እንደነበረ ስለሚታመን በድምሩ የ‹‹10›› ዓመታት ልዩነት በማቴዎስና በሉቃስ መካከል እናገኛለን።

አንዳንድ ሰዎች ቄሬኔዎስ ያካሄደው የህዝብ ቆጠራ በ7 C.E ከተካሄደው የህዝብ ቆጠራ በፊት የተደረገ ሲሆን ሄሮድስ በሞተበትና ቄሬኔዎስ ወደ ንግስና በመጣበት ዘመን የተደረገ ነው በማለት ዓመታቱን ለማጠጋጋት ይሞክራሉ።

እርግጥ ነው ከቄሬኔዎስ በፊት በርካታ የህዝብ ቆጠራዎች ተካሂደዋል። ነገር ግን ቄሬኔዎስ ‹‹አገረ ገዥ›› የሆነው ከሄሮድስ ሞት በኋላ በመሆኑ እንደ ሉቃስ ዘገባ ቆጠራው የተካሄደው ከ6-7ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው። በተጨማሪም ሉቃስ ‹‹ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ›› በማለት የህዝብ ቆጠራው ቄሬኔዎስ ‹‹አገረ ገዥ›› ሲሆን ያካሄደው የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎችም የኢየሱስን ልደት በተመለከተ በማቴዎስና በሉቃስ መካከል የጊዜ ልዩነት የሚታይ ሲሆን ሄሮድስና ቄሬኔዎስ በአንድ ዘመን ያልነበሩ ሰዎች ናቸው ሲሉ ፅፈዋል።

ሁሉም አብያተክርስቲያናትም ይህንኑ ሀሳብ በመጋራት የኢየሱስ የልደት ቀን በትክክል እንደማይታወቅ የሚስማሙ ሲሆን ካቶሊካዊቷ ቤተክርስቲያን በምታዘጋጀው ዘኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እውነታውን ገልፃዋለች።
አስገራሚው ነገር ታዲያ ኢየሱስ የተወለደበት ቀን ቀርቶ ዓመቱ እንኳን ባልታወቀበት ሁኔታ ዛሬም የዓለም አብያተክርስቲያናት የኢየሱስ የልደት ቀን ታህሳስ 25 ነው በማለት ገናን ያከብራሉ። የልደት ቀኑ ባልታወቀበት ሁኔታ ለምን ታህሳስ 25 (በእኛ 29) የልደቱ ቀን ተደርጎ ተመረጠ ለሚለው ጥያቄ ኢንሳይክሎፒዲያ ብርታኒካ ‹‹ምናልባት የሮም አረማውያን ከሚያመልኩት የፀሐይ አምላክ (Unconquered Sun) የልደት ቀን ጋር ለማዛመድ ተፈልጎ ይሆናል›› ሲል አስነብቧል። ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካናም በተመሳሳዩ ‹‹ክርስትና ለሮም አረማውያን ትርጉም እንዲሰጥ በማሰብ የተደረገ ነው›› የሚል አስተያየት በምሁራኑ ዘንድ እንዳለ ገልጿል።

ሰልማን

Shortlink