ኢስላም ላይ የሚቀርቡ ትችቶችን እንዴት በቀላሉ መመለስ እንችላለን?

መግቢያ

ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች ኢስላምን አስመልክቶ የተለያዩ የተሳሳቱ ምልከታዎች እንዳሏቸው እሙን ነው፡፡ ለዚህ የተለያዩ ተጠቃሽ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን የሚዲያ ተፅእኖ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡አብዛኛው የሚዲያ ተቋማት ለኢስላም ከፍተኛ ጥላቻ ባላቸው /Islamophobia/ ግለሰቦች የሚመሩ መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ የነዚህ ክስተቶች ትስስር አብዛኛው ሙስሊም ያልሆነ ወገን ኢስላምን አስመልክቶ ያለው አመለካከት የተንሸዋረረ እንዲሆን የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ከዚህ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ጋር አብሮ የሚያያዘው የህትመት ሚዲያ ተፅዕኖም እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ የህትመት ሚዲያ አሁን ላይ መልኩን በትንሹ ቀይሮ የኢንተርኔት ፁሁፎችን ያካተተ ሆኗል፡፡ ፀረ ኢስላም ፁሁፎችና ይህንን የሚያስተላልፉ ቋሚ ድህረገፆች አሁን ላይ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ብዙዎቹ የክርስቲያን ሚሽነሪዎችና ጥንተ ነገር አጥኝዎች/Orientalist’s/ ሲሆኑ ኢስላም ላይ የለየላቸው ቅጥፈቶችን ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ የዚህ አነስተኛ ፁሁፍ ዋና አላማም እነኝህን የተጠኑ የማጭበርበሪያ መንገዶችን በማጋለጥ እውነታውን እንዴት ማወቅ እንደምንችል ማሳየት ነው፡፡

ከዚህ በታች የሚጠቀሟቸውን ደካማ አካሄዶች በነጥብ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

1- አንድን የቁርዓን ወይም የሀዲስ አንቀፅ ከሙሉ ኢስላማዊ እሳቤው ነጥሎ በማቅረብ፡፡

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ምሳሌ የሚሆነው የሱረቱ ተውባ ምዕራፍ 9 ቁጥር 5 አንቀፅን አስመልክቶ የሚቀርቡ ትችቶች ናቸው፡፡ የቁርዓን አንቀፁን ካለአውዱ ብቻውን በማስቀመጥ ጉዳዩን ለማጮህ እልህ አስጨራሽ ሲደረግ ይስተዋላል፡፡

“… አጋሪዎችን ባገኛችኋቸው ስፍራ ሁሉ ግደሏቸው”

2- አንድን ሀዲስ ከታሪካዊ ዳራው/Context/ ውጭ ማቅረብ፡፡

3- ደኢፍ/ደካማ/ ሀዲሶችን ሆን ብሎ በመጠቀምና እነሱን ሰሂህ/አስተማማኝ/ ሀዲስ አስመስሎ በማቅረብ፡፡

4- ኢስላማዊ የታሪክ መፅሀፍትን (እንደ ኢብን ኢስሀቅ፣ አጦበሪ፣ ኢብኑ ሰዓድ) የመሳሰሉትን ልክ እንደ አስተማማኝ ምንጭ አድርጎ በማቅረብ፡፡

እነዚህ ታላላቅ የታሪክ ሰዎች ደካማ መረጃዎችን ወደ ጥራዞቻቸው ላለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ቢታወቅም የሠው ልጆች እንደመሆናቸው ስህተት ላይ ከመውደቅ አይቀሩም፡፡

5- የአረብኛ ቋንቋ የሠዋሠው ፍሰትና የቃላት ፍችዎችን ጠንቅቆ ባለመረዳት

6- በ21ኛው ክፍለ ዘመን መነፅር የ7ተኛውን ከፍለ ዘመን የአረብያ ማህበረሰብ መመልከት፡፡

ይሄ ይበልጥ በነብዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) ህይወት ዙሪያ ሲመጣ ሚዛናቸው የመጋደል ድክመት፡፡

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ምሳሌ የሚሆነው የነብዩ (ሰዐወ) እና የዓዒሻ ጋብቻ ጉዳይ ሲሆን የዘመናችን ሚሽነሪዎች በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተቀመጠውን የጋብቻ የተለመደ አሰራር ከዛሬ 1400 አመት በፊት ለነበረ ማህበረሰብ ሊጠቀሙበት ይዳዳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ወቅቱንና ጊዜውን ያላማከለ ፍርደ ገምድል ክስ ነው፡፡

7- የአረብኛውን ኦርጅናል የቁርዓንና የሀዲስ መልዕክት ሳይሆን የትርጉም ስራዎችን መሠረት አድርጎ ለፍርጃ መጣደፍ፡፡

በየትኛውም የትርጉም ስራዎች ውስጥ ከአገላለፅ ግድፈት ጀምሮ ስህተቶች አይጠፉም፤ ያ ማለት ግን ኦሪጅናሉ ተሳስቷል ማለት አይደለም፡፡

8- ለአመለካከታቸው የገጠመውን የአንድን ዑለማ/ሙስሊም ሊቃውንት/ ትንታኔ ብቻ በመያዝ ሌላው አሳማኝ ቢሆን እንኳን ከሀሳባቸው ጋር ስለማይገጥም ሆን ብሎ ያለመቀበል፡፡

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ተፍሲሮችን አስመልክቶ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ናቸው

9- ኢስላምን በግለሠቦች ስራ መመዘን..!

ይሄ እጅግ የተሳሳተ አመለካከት ሲሆን ከነብዩ (ሰዐወ) ውጭ ማንም ሰው የሚሰራው ስራ መቶ በመቶ በሚባል መልኩ ኢስላምን አይወክልም፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ተሳሳች ነውና ከኢስላም አስተምህሮ ውጭ የሆኑ ስራዎችን ሊሠራ ይችላል፡፡ ስለዚህ በሰውየው ስራ ኢስላም ተጠያቂ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ምሳሌ የሚሆነው “ሽብርተኝነትን” አስመልክቶ የሚመጡ ትችቶችና የግለሰብ ጥቃቶችን አስመልክቶ የሚመጡ ወቀሳዎች ናቸው፡፡ በኢስላም ስም የሚፈፀም ግድያ ሁሉ ኢስላማዊ ነው አይባልም በተመሳሳይ ሙስሊሞች የሚፈፅሟቸው ግለሠባዊ ጥቃቶችም እንደ ኢስላማዊ ተግባራት አይወሰዱም፡፡ ለፈፀመው ጥፋት ግለሠቡ እንጅ ኢስላም ተጠያቂ የሚሆንበት ምንም አይነት አመክኗአዊ መሠረት የለም፡፡ ስለዚህም በዚህ ረገድ አማኙንና እምነቱን ለያይቶ የማስቀመጥ ጉልህ ክፍተት አለ፡፡

10- አንድን ውሸት ደጋግሞ በማስተጋባት እውነት እንዲመስል መጣር

“ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” እንደሚበለው ሚሽነሪዎች አንድን አጀንዳ እውነት ለማስመሠል ደጋግመው ማጮኽ የተለመደ ስራቸው ነው፡፡በዚህ ረገድ የተለመደው ውሸት ኢስላም ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን በመግደል ፃድቅ መሆንን ያስተምራል የሚለው ተራ ፈጠራ ነው፡፡ ይህ አባባል በዘመናት ሂደት ተደጋግሞ ከመተረቱ አንፃር ብዙ ሰዎች ሳይቀሩ እውነት እየመሰላቸው በቁምነገር ሲጠይቁት፣ ሲያነሱት ተስተውሏል፡፡

ማጠቃለያ

የሚሽነሪዎች የማታለያ ስልቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ከላይ የቀረቡት በተደጋጋሚ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ ችግርን ማወቅ መፍትሄ ያስተምራልና ህዝበ ሙስሊሙም የማታለያ መንገዶቹን ማወቁ በቀላሉ መልሶቻቸውን ለማዘጋጀት ስለሚያግዘው ከላይ የቀረቡትን ነጥቦች በጥሞና መቃኘቱ መልካም ነው እላለሁ፡፡

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

ሼር ያድርጉ
  • 40
    Shares