አል-ኢዕቲካፍ

ሼር ያድርጉ
491 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1/ የቃላት ፍቺ፡-

ኢዕቲካፍ ማለት ቀጥተኛ ፍቺው፡- ራስን በአንድ ነገር ላይ መልካምም ሆነ መጥፎ ማድረግ/ማዘውተር ማለት ነው፡፡ ሸሪዓዊ ፍቺው ደግሞ፡- ሶላቱል ጀማዓህ በሚሰገድባቸው የአላህ ቤቶች/ መስጂድ ውስጥ ወደ አላህ በመልካም ሥራ ለመቃረብና ኃጢአትን ለማስሰረዝ ከልብ በመነየት/በመወሰን የተወሰነ ጊዜ (ለደቂቃ፣ ለሰዓታት፣ ለቀናት፣ ለሳምንታት) ቆይታ ማድረግ ማለት ነው፡፡

2/ የድርጊቱ ሸሪዓዊነት፡-

በአላህ ቤቶች ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ፡ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች፡ በቅዱስ ቁርኣንና በሐዲሥ የተደገፈ ሸሪዓዊ መሠረት ያለው ተግባር ነው፡፡ የአላህ ቃል በአላህ ቤቶች ውስጥ ኢዕቲካፍን ያደረገ አንድ ሙስሊም ከባለቤቱ ጋር የግብረ-ሥጋ ግኑኝነት መፈጸም እንደሌለበት ሲያስተምር፡ እግረ-መንገዱንም ኢዕቲካፍ የሚባል ነገር መኖሩን ጠቁሞናል፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

“…وَلَا تُبَاشِرُوهُنَّ وَأَنْتُمْ عَاكِفُونَ فِي الْمَسَاجِدِ…” سورة البقرة 187
“…እናንተም በመስጊዶች ተቀማጮች ስትኾኑ አትገናኙዋቸው…” (ሱረቱል በቀራህ 2፡187)፡፡

عَنْ عَائِشَةَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهَا، – زَوْجِ النَّبِيِّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ -: «أَنَّ النَّبِيَّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ، كَانَ يَعْتَكِفُ العَشْرَ الأَوَاخِرَ مِنْ رَمَضَانَ حَتَّى تَوَفَّاهُ اللَّهُ، ثُمَّ اعْتَكَفَ أَزْوَاجُهُ مِنْ بَعْدِهِ» رواه البخاري 2026 ومسلم 2841
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ ትላለች፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይህችን ዱንያ እስኪሰናበቱ ድረስ የረመዷንን የመጨረሻዎቹን አሥርት ቀናት ኢዕቲካፍ ያደርጉ ነበር፡፡ ከሳቸው ዱንያን መሰናበት በኋላም ባለተቤቶቻቸው (የምእመናን እናት ረዲየላሁ ዐንሁንነ) ኢዕቲካፍ አድርገዋል” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

3/ ቅድመ-ዝግጅቱ (መሟላት ያለበት መስፈርት)፡-

ኢዕቲካፍ ለማድረግ የወሰነ ሙስሊም የአላህ ባሪያ፡ ኢዕቲካፍ ከማድረጉ በፊት፡ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

ሀ/ ዐቅል ያለው (አእምሮው ያልተዛባ) መሆን፡- ጤናማ አእምሮ ያለው ሊሆን ግድ ነው፡፡ የአእምሮ ህመምተኛ የኾነ ሰው በሕክምና ቦታ ሊታከም ይገባዋል እንጂ፡ የአላህ ቤት መጥቶ አማኞችን ማስቸገር የለበትም፡፡

ለ/ ጡሀራ መሆን፡- ይህ ማለት፡ ከጀናባ፣ ከሐይድ (ከሐይድ ቀን ውጭ የሚፈሰውን የኢስቲሓዷ (የበሽታ ደም) አያካትትም) እና ከኒፋስ (የወሊድ ደም) የጠሩ መሆን አለባቸው፡፡

4/ የኢዕቲካፍ ማእዘናት፡-

አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ኢዕቲካፍ እንዲሆንለት የሚፈልግ አንድ ሙስሊም፡ በኢዕቲካፍ ወቅት ቀጥሎ ያሉትን ማእዘናት ሊፈፅም ግድ ይለዋል፡፡ እነሱም፡-

ሀ/ ኒይያ (ቁርጠኛ ውሳኔ)፡- እራሱን በመስጂድ ውስጥ በመገደብ ኢዕቲካፍ የሚያደርገው፡ ወደ አላህ ለመቃረብ እንጂ፡ ቤት መተኛት ስላስጠላው፡ ወይም የቤት ውስጥ ጭቅጭቅ ስለሰለቸው መሆን የለበትም፡፡ ያ ከሆነ ምክንያቱ ኒይያው ተቀይሯል ማለት ነው፡፡ ኢዕቲካፍን የሚነይት የአላህ ባሪያ ዓላማው፡ ብዙ መልካም ነገራትን በማድረግ፡ ኃጢአትንም በመራቅ ወደ አላህ እቃረብበታለሁ ብሎ መሆን አለበት፡፡ ሥራ በጠቅላላ ተቀባይነቱ በኒይያ ነውና፡፡ ለአላህ ብሎ የኢስላምን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ ጠላትን የታገለ ሙስሊምም ሆነ፡ ሥምና ዝናን ለማትረፍ፡ በጀግንነት እንዲወሳ የፈለገ ሙስሊም፡ ሁለቱም በጦር ሜዳ ላይ ቢገደሉ ‹‹ሸሂድ›› የሚል የጋራ ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ ግን አላህ ዘንድ ተጠቃሚውና ባለ-ምንዳ የሚሆነው ኒያውን አስተካክሎ በኢኽላስ የሰራው ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ኒያው የተበላሸ በመሆኑ፡ አላህ ይቅር ካላለው በስተቀር የሚጠብቀው ሽልማት ሳይሆን ቅጣትና ቁጣ ነው፡፡

ለ/ ቦታው መስጂድ መሆኑ፡- የኢዕቲካፍ ስፍራ መስጂድ ብቻ ነው፡፡ በተለይ ጁምዓ ጭምር የሚሰገድበት (ጃሚዕ) ቢሆን ይመረጣል፡፡ ወንዶች ሶላቱል ጀመዓህ እና ጁምዓ ስለሚወጅብባቸው፡ የጁምዓ መስጂድ ፍለጋ እንዳይቸገሩ ይረዳቸዋልና፡፡ ያ ከመሆኑ ጋር እሱ ያለበት መስጂድ ጁምዓህ ባይሰገድበትም ‹‹መስጂድ›› ተብሎ እስከተጠራ ድረስ ግን ኢዕቲካፍ ሊያደርግበት ይችላል፡፡ የቁርኣኑም አንቀጽ ከላይ የተናገረው ‹‹በመስጂድ ውስጥ›› በማለት ነውና፡፡

5/ ኢዕቲካፍ አዳቦች/ስርኣቶች፡-

አጅሩ የተሟላ እንዲሆንለትና ይበልጥ ወደ አላህ ቤት የመጣበትን ዓላማ ከግብ ለማሳካት የሚፈልግ ሙስሊም፡ ቀጥሎ ያሉትን አዳቦች ማሟላት ይገባዋል፡-

ሀ/ የዒባዳህ ተግባራትን ማብዛት፡- ሶላት (ሱንናዎችን ጭምር)፣ ቁርኣን ማንበብ፣ ዚክር፣ ኢስቲግፋር፣ ዱዓእ የመሳሰለውን፡፡

ለ/ ከሐሜትና ነገር ማዋሰድ፣ ከጭቅጭቅና ጉንጭ አልፋ ክርክር፣ ጥቅም አልባ ከሆነ ወሬ እራስን ማግለልና በዒባዳህ ተግባር መወጠር፡፡

ሐ/ ኢዕቲካፍ የሚያደርግበትን የመስጂዱን አንድ የተለየ ስፍራ በመምረጥ፡ ኢዕቲካፉን እስኪጨርስ ድረስ፡ ከቻለ በዛ ቦታ ላይ መሆን፡፡

መ/ ኢዕቲካፍ ማለት እራስን ከቤተሰብና ከጓደኞች አግልሎ በአላህ ቤት ማኖር ማለት ስለሆነ፡ አሁንም ከተቻለ ከማንም ጋር ሳይቀላቀል ብቻውን ጉዳዩን እስኪፈጽም ድረስ ገለል ማለት (ለብቻ መሆን)፡፡

6/ የኢዕቲካፍ የጊዜ ገደቡ፡-

ኢዕቲካፍ ማድረግ የፈለገ ሰው በማንኛው ጊዜ (በቀንም ሆነ በለሊት) የፈለገውን ሰዓት ያህል (ለደቂቃም ሆነ ለሰዓት፣ ለቀናትም ሆነ ለሳምንታት) መነየት ይችላል፡፡ የተገደበ ወቅትና መጠን የለውም፡፡ ከሁሉም የተሻለው ግን የረመዷን ወር የመጨረሻው አሥርት ቀናትን መጠቀሙ ነው፡፡ ይህም የረመዷን 20ኛው የፆም ቀን ከመጠናቀቁ (መግሪብ መግባት) ቀደም ብሎ መስጂድ በመግባት፡ ነገ ዒድ ነው እስኪባል ድረስ (የረመዷን 29/30ኛ ቀን ተጠናቅቆ መግሪብ እስኪሰገድ ድረስ) መቆየት ማለት ነው፡፡

7/ የተፈቀዱ ተግባራት፡-

ሀ/ የመስጂዱን ንጽህና ከመጠበቅ ጋር፡ መብላት መጠጣት እንዲሁም መተኛት፡፡

ለ/ ለንጽህና ተግባር (ሽንት ቤት) መውጣት እና የዉዱእ ስፍራ መገኘት፡፡

ሐ/ አስገዳጅ ለሆነ ተግባር ከመስጂዱ ክልል መውጣትና፡ ጉዳዩን በፍጥነት አስተካክሎ መመለስ፡፡

መ/ ፀጉርን ማበጠር፣ የእጅና የእግር ጥፍርን ማስተካከል፣ ገላን መታጠብና ሽቶ መቀባት፡ እንዲሁም ልብስን መቀየር፡፡

ሠ/ ባል ሚስቱን፡ ወይም ሚስት ባሏን ሰላምታ ማቅረብና መነጋገር፡፡ እና ሌሎችም፡፡

8/ ኢዕቲካፍን የሚያበላሹ ነገራት፡-

ሀ/ ከባለቤቱ ጋር የግብረ-ስጋ ግኑኝነት መፈፀም፡፡

ለ/ ከትዳር አጋሩ ጋር የፍቅር ጨዋታ እየተጫወተ የዘር ፈሳሽ ማውጣት፡፡

ሐ/ የወር አበባ ወይም የወሊድ ደም መከሰት፡፡

መ/ ያለ ምንም ዑዝር ከመስጂዱ መውጣት፡፡

9/ በመጨረሻም፡-

አላህ ወፍቆአችሁ ኢዕቲካፍ የምትገቡ የአላህ ባሮች ሆይ! አላህ ኢዕቲካፋችሁን ይቀበላችሁ፡፡ በአኼራ መልካም ሥራ ሚዛን ላይ ያድርግላችሁ፡፡ እናንተም ሙስሊም ወንድሞቻችሁን (በተለይ ከሀገራችን ጀምሮ በዓለም ላይ በፍትሕ እጦት ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ የሚሰቃዩትን) ከልባችሁ በዱዓ እንዳትረሷቸው፡፡ የአንዳችሁ ዱዓ ተቀባይነትን አግኝቶ ቅፅበታዊ ምላሽን ሊያመጣ ይችላልና፡፡ የሚለመነው ጌታ ደግሞ ተስፋ የሚቆረጥበት አይደለምና!!

መልካም ዒባዳህ!፡፡

Shortlink http://q.gs/Ewil9