“አል-ሐምዱ ሊላህ” ማለትን እናብዛ!

ሼር ያድርጉ
333 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1/ ትርጉም፡- “አል-ሐምዱ ሊላህ” ማለት፡- ፍጹም የኾነ ልባዊ ምሥጋና ለአላህ ብቻ የተገባ ነው ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህን ስናመሰግነው በሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛ፡- በማንነቱ ፍጹም የኾነ የምሉእ ባሕሪያት ባለቤት በመኾኑ፣ እንከንና ጉድለት ፈጽሞ የሌለበት በመኾኑ ብቻ ይመሰገናል፡፡ ከፍጡራን ምሥጋና በፊትም እራሱን ያመሰገነና ያወደሰ አምላክ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ፡- ክፍያንና ወሮታን ሳይጠይቅ ለባሪያዎቹ የሚለግስ ደግ አምላክ በመኾኑ፣ ለለመኑትና ለተማጸኑት ደግሞ ፈጥኖ ደራሽ በመኾኑ ስለ-ጸጋዎቹ ይመሰገናል፡፡ አላህ በራሱ በማንነቱም ኾነ በጸጋዎቹ የሚመሰገን ጌታ ነውና፡፡

2/ ‹‹ሐምድ›› እና ‹‹ሹክር›› የተሰኙ ቃላቶች፡ ሁለቱም ምሥጋናን ያዘሉ ከመኾናቸው ጋር፡ የኢስላም ሊቃውንት በመሐከላቸው ልዩነት መኖሩን ይጠቁማሉ፡፡ እሱም፡- ‹‹ሐምድ›› በምላስ በመናገር የሚገለጽ የምሥጋና አይነት ሲኾን፡ ‹‹ሹክር›› ደግሞ፡ በልብ፣ በመላስና በአካልም የሚገለጽ የምሥጋና አይነት ነው፡፡ አንድ ሙስሊም አላህ የሰጠውን የጤንነት ጸጋ በማስተዋል፡ ጌታውን በአንደበቱ ካመሰገነ፡ ይህ ‹‹ሐምድ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በተጨማሪም በተሰጠው ጤንነት፡ ለጌታው ከሰገደና መልካምንም ከሠራበት፡ ይህ ደግሞ ‹‹ሹክር›› ይሰኛል ማለት ነው፡፡ በቀላሉ፡ የአንደበት ምሥጋና ‹‹ሐምድ›› ሲሰኝ፡ የልብ፣ የአንደበትና የአካል ምሥጋና ደግሞ ‹‹ሹክር›› ይሰኛል ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ካየነው፡ ‹‹ሐምድ›› ራሱ ‹‹ሹክር›› ውስጥ ይካተታል ማለት ነው፡፡

ሌላው ልዩነት ደግሞ፡- ‹‹ሐምድ›› ከአላህ ዘንድ ጸጋ ለኛ ከመሰጠቱ በፊትም ኾነ ከተሰጠ በኋላ ሊቀርብ የሚችል የምሥጋና አይነት ሲኾን፡ ‹‹ሹክር›› የሚባለው ደግሞ፡ ከኒዕማ በኋላ የሚገለጽ የምሥጋና አይነት ነው፡፡ ይህ ማለት፡- አላህን ምንም ጸጋውን ባይልክልንም እንኳ በፍጹም መለኮታዊ ባሕሪው ብቻ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ›› በማለት የሚመሰገን ሲኾን፡ ጸጋውንም ከላከልንም በኋላ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ›› በማለት እናመሰግነዋለን፡፡ ‹‹ሹክር›› ግን ከጸጋ በኋላ ብቻ የሚቀርበውን የምሥጋና አይነት የሚወክል ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ መልክ ካየነው ደግሞ፡ ‹‹ሐምድ›› ከጸጋ በፊትም ኾነ በኋላ ያለውን ምሥጋና የሚወክል ቃል በመኾኑ በውስጡ ‹‹ሹክር››ንም ያቅፋል ማለት ነው፡፡ ወላሁ አዕለም (ተፍሲር ኢብኑ ከሢር 1/32፣ ኢብኑል-ቀይዪም፡ መዳሪጁ-ሳሊኪን 2/246)፡፡

3/ ከጌታ አላህ መለኮታዊ ሥሞች አንዱ ‹‹አል-ሐሚድ›› የሚለው ነው፡፡ ይህ መለኮታዊ ሥም ትርጉሙ፡- ፍጹም ተመስጋኝ ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህ በህልናውም ሆነ በባሕሪው በራሱ የተብቃቃ የምሉእ ባሕሪ ባለቤት በመሆኑ “አል-ሐሚድ” ይባላል፡፡ ጌታ አላህ ለባሮቹ ሊቆጠር የማይችልን ጸጋ በመለገሱ አምሳያ የሌለው በመሆኑ “አል-ሐሚድ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታ አላህ ሁሌም ካመሰገኑትና ከተማጸኑት ከጸጋው የሚጨምር አምላክ በመሆኑ “አል-ሐሚድ” ይባላል፡፡ ዓለማቱን በጠቅላላ ብቻውን ፈጥሮ (አል-አንዓም 6፡103)፣ ለእያንዳንዱ ነገር የሚያስፈልገውን ነገር ብቻውን ሰጥቶና አሟልቶ (ጣሀ 20፡50)፣ አማኝ ባሪያዎቹን ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወትን በጸጋ ጀነቶች ሊያኖራቸው ቃል ገብቶ (ዩኑስ 10፡9) ሳለ እንዴትስ አይመስገን? ለጸጋው ገደብ እንደሌለው ሁላ ለመመስገኑም ገደብ የለውም፡፡ ማንኛውም አይነት የምስጋና መገለጫዎች ሁሉ የሚግገቡት ለሱ ነውና፡፡ የዓለማት ጌታ በመሆኑ ብቻ ምስጋና ይገባዋል፡፡-

ይህ “አል-ሐሚድ” የሚለው መለኮታዊ ስም በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ አስራ ሰባት ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ (ሱረቱል በቀራህ 2፡267፣ አን-ኒሳእ 4፡131፣ ሁድ 11፡73፣ ኢብራሂም 14፡1፣ ኢብራሂም 14፡8፣ አል-ሐጅ 22፡24፣ አል-ሐጅ 22፡64፣ ሉቅማን 31፡12፣ ሉቅማን 31፡26፣ ሰበእ 34፡6፣ ፋጢር 35፡15፣ ፉሲለት 41፡42፣ አሽ-ሹራ 42፡28፣ አል-ሐዲድ 57፡24፣ አል-ሙምተሒናህ 60፡6፣ አት-ተጋቡን 64፡6፣ አል-ቡሩጅ 85፡8)፡፡

4/ አላህ በመላእክት ዘንድም የሚመሰገን አምላክ ነው!፡- መላእክት ከብርሀን የተፈጠሩ፣ ከኃጢአትና ከስጋዊ ስሜት የራቁ፣ ሁሌም አላህን በማምለክ ተግባር ላይ የተሰማሩ መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው፡፡ ጌታቸውን አላህን ከጎዶሎ ባሕሪያት የጠራ መኾኑን በመግለጽ ሁሌም ያመሰግኑታል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤» ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ እነርሱም) «እኛ #ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» አሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡30)፡፡

“(ከአላህ ፍራቻ) ሰማያት ከበላያቸው ሊቀደዱ ይቀርባሉ፡፡ መላእክትም ጌታቸውን #እያመሰገኑ ያወድሳሉ፡፡ በምድርም ላለው ፍጡር ምሕረትን ይለምናሉ፡፡ ንቁ! አላህ እርሱ መሓሪው አዛኙ ነው፡፡” (ሱረቱ-ሹራ 42፡5)፡፡

5/ አምላካችን አላህ ከባሪያዎቹ ምሥጋናን ይወዳል፡፡ የሰጣቸውን ፀጋ በአግባቡ ተጠቅመውበት፡ እሱንም ያመሰግኑት ዘንድ ይወዳል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

“ጌታችሁም «ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ ብትክዱም (እቀጣችኋለሁ) ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና» በማለት ባስታወቀ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡” (ሱረቱ ኢብራሂም 14፡7)፡፡

“ብትክዱ አላህ ከእናንተ የተብቃቃ ነው፡፡ ለባሪያዎቹም ከህደትን አይወድም፡፡ ብታመሰግኑም፤ እርሱን ይወድላችኋል፡፡” (ሱረቱ-ዙመር 39፡7)፡፡
ከአነስ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ ከባሪያው ምግብን እንዲመገብና በሱም እንዲያመሰግነው፡ ወይንም ሐላል መጠጥን ጠጥቶ በሱም እንዲመሰግነው ይወዳል” (ሙስሊም 2734)፡፡

ከሷሊሖች አንዱ፡ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ ወ አስተግፊሩላህ›› የሚለውን ቃል ብቻ በመደጋገም ሌላ ሳይጨምር ይዘክር ነበር፡፡ ከዚም ለምን ይህን እንደመረጠ ሲጠየቅ፡- ‹‹የኔ ሁኔታ ከሁለት ነገር አይወጣም፡፡ ወይ የተሟላ ጸጋ ላይ ነኝ፡፡ ወይንም በኃጢአት ውስጥ ነኝ፡፡ ለጸጋው አል-ሐምዱ ሊላህ፣ ለኃጢአቴ ደግሞ አስተግፊሩላህ እላለሁ በማለት መለሰ›› (ነዘሯት ፊ-መዓኒይ አስ-ሶላት፡ ገጽ 62)፡፡

6/ አላህን ማመስገን ተቆጥሮ የማይዘለቅ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከነዚህም ጥቅሞቹ ውስጥ፡-

ሀ/ አላህ ዘንድ ከተመረጡት መልካም ንግግሮች አንዱ ነው፡- ከአቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ ከንንግግሮች አራቱን መረጠ፡፡ እነሱም፡- ሱብሐነላህ፣ አልሐምዱ ሊላህ፣ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ፣ አላሁ አክበር የሚሉት ናቸው፡፡” (ነሳኢይ፡ ሱነኑል ኩብራ 10676፣ ሶሒሑል-ጃሚዕ 1718)፡፡

ለ/ ከዱዓዎች ሁሉ በላጭ ነው፡- ጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከዚክሮች ሁሉ በላጩ ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ የሚለው ነው፡፡ ከዱዓዎች ሁሉ በላጩ አል-ሐምዱ ሊላህ የሚለው ነው” (ኢብኑ ማጀህ 3932፣ ቲርሚዚይ 3711)፡፡

ሐ/ ጀነትን ያሸልማል፡- ከአቢ ሙሳ አል-አሽዐሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አንድ የአላህ ባሪያ ልጅ በሚሞትበት ጊዜ፡ አላህ ለመላእክቱ ‹‹የባሪያዬን ልጅ ወሰዳችሁበትን?›› ሲላቸው፡ መላእክቱም፡ ‹‹አዎን ጌታችን ሆይ!›› ይላሉ፡፡ እሱም፡ ‹‹የልቡን ፍሬ (የገዛ ልጁን) ወሰዳችሁበትን?›› ሲላቸው፡ እነሱም ‹‹አዎን ጌታችን ሆይ!›› ይላሉ፡፡ አላህም፡- ‹‹ባሪያዬ ምን አለ ታዲያ?›› ሲላቸው፡ እነሱም፡ ‹‹አንተን አመሰገነህ፡ ሁሉም የአንተ መኾኑን እና ወደ አንተም ተመላሽ መኾኑን ገለጸ›› ይላሉ፡፡ አላህም ‹‹ለባሪያዬ በጀነት ውስጥ ቤትን ገንቡለት፡ ቤቱንም በይቱል-ሐምድ ብላችሁ ሰይሙት›› ይላቸዋል” (ሲልሲለቱ-ሶሒሓህ 1408)፡፡

7/ ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ሁኔታዎች እና ምክንያቶች አላህን ማመስገን ይበልጥ የተወደደ ይኾናል፡-

ሀ/ ከመኝታ ሲነሱ፡- ሑዘይፈተ ኢብኑል-የማን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተናገረው፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ‹አል-ሐምዱ ሊላህ፡ አለዚ አሕያና በዕደ ማ-አማተና፡ ወኢለይሂ-ኑሹር› ይሉ ነበር›› (ቡኻሪይ 6312፣ ሙስሊም 7062)፡፡ ትርጉሙም፡- ትንሹን ሞት (እንቅልፍ) እንድንሞት ካደረገን በኋላ ሕያው ላደረገን (ለቀሰቀሰን) አላህ ምሥጋና የተገባ ነው! ማለት ነው፡፡
ከአቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በተላለፈው ሐዲሥ ደግሞ፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ከናንተ አንዳችሁ በነቃ ጊዜ፡- ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ፡ አለዚ ዐፋኒ ፊ-ጀሰዲ፣ ወረደ ዐለይየ ሩሒ፣ ወአዚነ ሊ ቢዚክሪሂ›› ይበል” (ቲርሚዚይ 3729)፡፡ ትርጉሙም፡- ሰውነቴን ጤናማ ላደረገ፣ ሩሔንም ወደኔ መልሶ እሱን እንዳወድሰው ለፈቀደልኝ አላህ ምሥጋና ተገባ ይሁን! ማለት ነው፡፡

ለ/ አዲስ ልብስ ሲለብሱ፡- ከአቢ-ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው እንዲህ አለ፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አዲስ ልብስ ሲለብሱ፡- ‹‹አልላሁመ ለከል-ሐምዱ አንተ ከሰውተኒህ፣ አስአሉከ ሚን-ኸይሪሂ ወኸይሪ ማሱኒዐ ለህ፣ ወአዑዙ ቢከ ሚን-ሸርሪሂ ወሸርሪ ማሱኒዐ ለህ›› ይሉ ነበር” (አቡ ዳዉድ 4022፣ ቲርሚዚይ 1873)፡፡ ትርጉሙም፡- አምላኬ አላህ ሆይ! ይህን አዲስ ልብስ ስላለበስከኝ ምሥጋና ላንተ ነው፡፡ የዚህን ልብስ ጥሩነትና ይህ ልብስ የተሰራበትን መልካም ነገር እማጸንሀለሁ፡፡ የዚህን ልብስ መጥፎነትና ከተሰራበት መጥፎ ነገር ባንተ እጠበቃለሁ! ማለት ነው፡፡

እንዲሁም ማንኛውንም ልብስ በሚለበስበት ጊዜ፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዳስተማሩት፡- “ልብስን የለበሰና ከዛም፡- ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ፡ አለዚ ከሳኒ ሀዘ-ሠውበ፣ ወረዘቀኒሂ ሚን ገይሪ ሐውሊን ወላ-ቁውወተ ሚንኒ›› ያለ ሰው ከዚህ በፊት የፈጸመው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል” (አቡ ዳዉድ 4025)፡፡ ትርጉሙም፡- ይህን ልብስ ላለበሰኝና ያለ-ምንም አቅሜና ብልሀቴ ለሰጠኝ አላህ ምሥጋና የተገባ ነው! ማለት ነው፡፡

ሐ/ የሚያስደስተውንና የሚያስከፋውን ነገር በተመለከተ ጊዜ፡- ከእናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንደተላለፈው፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሚያስደስታቸውን ነገር ሲመለከቱ፡ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ፡ አለዚ ቢኒዕመቲሂ ተቲሙ-ሷሊሓት›› ይሉ ነበር፡፡ የሚያስከፋቸውን ነገር ሲመለከቱ ደግሞ፡ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ ዐላ-ኩልሊ ሓል›› ይላሉ፡፡ (ኢብኑ ማጀህ 3935)፡፡

መ/ ባስነጠሰው ጊዜ፡- አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከናንተ አንዳችሁ ካስነጠሰ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ›› ይበል…” (ቡኻሪይ 6224፣ ሙስሊም 7679፣ አቡ ዳዉድ 5033፣ ኢብኑ ማጀህ 3715፣ ቲርሚዚይ 2740)፡፡

ሠ/ ምግብን ተመግቦ ሲያጠናቅቅ፡- የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ፡- “ምግብን በልቶ ከዚያም፡ ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ፣ አለዚ አጥዐመኒ ሀዘ-ጠዓም፣ ወረዘቀኒሂ ሚን-ገይሪ ሐውሊን ሚንኒ ወላ-ቁውዋህ›› ያለ ሰው፡ ከዚህ በፊት የሰራው ጥፋት ይቅር ይባላል” (አቡ ዳዉድ 4025፣ ኢብኑ ማጀህ 3285፣ ቲርሚዚይ 3458)፡፡

ረ/ ሰበቡል-ሂዳያ ስትኾን፡- አላህ ባንተ ዳዕዋ (ዱዓ) ሰበብ፡ አንድን ሰው ከኩፍር ጨለማ ወደ ኢስላም ብርሀን ቢመራልህ፡ አንተም ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ›› በል፡፡ አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈው፡ እንዲህ ይላል፡- “ረሱልን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሚኻድማቸው አንድ አይሁዳዊ ነበር፡፡ ኋላም ይታመምና የአላህ ነቢይም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሊጠይቁት ይመጣሉ፡፡ በአናቱ አጠገብ ይቀመጡና ‹‹ስለም›› ይሉታል፡፡ እሱም ወደ አባቱ ይመለከታል፡፡ አባቱም ‹‹አበል-ቃሲምን ታዘዛቸው!›› ሲለው፡ ልጁም ሸሀደተይንን በመመስከር ይሰልማል፡፡ የአላህ መልክተኛም ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ፡ አለዚ አንቀዘሁ ሚነ-ናር›› እያሉ ከቤቱ ወጡ” (ቡኻሪይ 1356)፡፡

ሰ/ በጤናው የተፈተነን ሰው ሲያይ፡- ከዑመር ኢብኑል-ኸጥጧብ እና ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁም) እንደተላለፈው፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በጤናው የተፈተነን ሰው ያየና ከዚያም ‹‹አል-ሐምዱ ሊላህ፡ አለዚ ዐፋኒ ሚመ-ብተላከ ቢህ፣ ወፈደለኒ ዓላ-ከሢሪን ሚን-መን ኸለቀ ተፍዲላ›› ያለ ሰው፡ ይህ በላእ(ፈተና) እሱን አያገኘውም” (ኢብኑ ማጀህ 3892፣ ቲርሚዚይ 3432)፡፡

• ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ አላህ፡-

“ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለኾነው” (ሱረቱል-ፋቲሓህ 1፡2)፡፡
“በመልክተኞቹም ላይ ሰላም ይኹኑ፤ ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን፡፡” (ሱረቱ-ሷፍፋት 37፡181-182)፡፡
“መላእክትንም በጌታቸው ምስጋና ቀላቅለው የሚያጠሩ ሲኾኑ በዐርሹ ዙሪያ ከባቢዎች ኾነው ታያለህ፡፡ በመካከላቸው በእውነት ይፈረዳል፡፡ ይባላልም፤ «ምስጋና ለአላህ ለዓለማት ጌታ ይገባው፡፡” (ሱረቱ-ዙመር 39፡75)፡፡

• ምሥጋና ሰማያትና ምድርን ለፈጠረው አላህ፡-

“ምስጋና ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው ጨለማዎችንና ብርሃንንም ላደረገው ለአላህ የተገባ ነው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡1)፡፡
“ምስጋና ለዚያ በሰማያትም ያለ በምድርም ያለ ሁሉ የርሱ ለኾነው ለአላህ ይገባው፡፡ በመጨረሻይቱም ዓለም ምስጋና ለእርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ብልሃተኛው ውስጠ ዐዋቂው ነው፡፡” (ሱረቱ ሰበእ 34፡1)፡፡
“ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሶስት ሶስትም፣ ባለ አራት አራትም ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው፡፡” (ሱረቱ ፋጢር 35፡1)፡፡
“ምስጋናም ለአላህ ለሰማያት ጌታ ለምድርም ጌታ ለዓለማት ጌታ የተገባው ነው፡፡ (36) ኩራትም በሰማያትም በምድርም ለእርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም አሸነፊው ጥበበኛው ነው፡፡” (ሱረቱል ጃሲያህ 45፡36-37)፡፡

• ምሥጋና ቁርኣንን ላወረደው አላህ፡-

“ምስጋና ለአላህ ለዚያ መጽሐፉን በውስጡ መጣመምን ያላደረገበት ሲሆን በባሪያው ላይ ላወረደው ይገባው፡፡” (ሱረቱል ከህፍ 18፡1)፡፡

• ምስጋና ልጅን ከመያዝ ለጠራው ጌታ አላህ፡-

“ምስጋና ለአላህ ለዚያ ልጅን ላልያዘው፣ ለእርሱም በንግሥናው ተጋሪ ለሌለው፣ ለእርሱም ከውርደት ረዳት ለሌለው ይገባው በልም፡፡ ማክበርንም አክብረው፡፡” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡111)፡፡

Shortlink http://q.gs/Ey5yk