አላህን የምናመልከው ለምንድነው?

ሼር ያድርጉ
367 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

በሁላችንም ዘንድ እንደሚታወቀው፡ እኛ ሰዎች የተፈጠርንበትና በዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ዋና ዓላማ፡- የፈጠረንና ያስገኘንን፡ አምላካችን አላህን በብቸኝነት እንድንገዛው ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣንም ይህን ዓላማ ግልፅ በሆነ መልኩ ያስረዳል፡-

“وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنْسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ ” سورة الذاريات 56
“ጋኔንንና ሰውን ሊገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።” ሱረቱ-ዛሪያት 56

ዒባዳህ (አምልኮ) አላህ በባሮቹ ላይ ካሉት መብቶቹ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው፡፡ እኛም የዚህ ባለ-ዕዳዎች ነን፡፡ እዳችንን ባግባቡ መክፈል ደግሞ ግዳጃችን ነው፡፡ተከታዩ ሐዲሥ ይህን ያብራራል፡-

وعن معاذ بن جبل رضي الله عنه قال: كنت رديف النبيِّ – صلى الله عليه وسلم – على حمار فقال لي: «يا معاذ أتدري ما حقّ الله على العباد، وما حقّ العباد على الله»؟ قلت: الله ورسوله أعلم. قال: «حقّ الله على العباد أن يعبدوه ولا يشركوا به شيئًا، وحقّ العباد على الله أن لا يعذب من لا يشرك به شيئاً». قلت: يا رسول الله! أفلا أبشر الناس؟ قال: «لا تبشرهم فيتكلوا» أخرجاه في ((الصحيحين((.
ሙዐዝ ኢብኑ ጀበል (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- ” አንድ ቀን ከአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጋር ከአህያ ኃላ ተቀምጬ ሳለ፡ ሙዐዝ ሆይ! አላህ በባሮቹ ላይ ያለውን መብት፡ ባሮችም በአላህ ላይ ያላቸውን ድርሻ ታውቃለህን? አሉኝ፡፡ እኔም፡- አላህና መልክተኛው የበለጠ ዐዋቂ ናቸው ብዬ መለስኩ፡፡ እሳቸውም፡- አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት ምንም ሳያጋሩበት ብቻውን ሊያመልኩት ሲሆን፡ ባሮች ደግሞ አላህ ዘንድ ያላቸው ድርሻ ምንም ካላጋሩበት በእሳት ላይቀጣቸው መሆኑ ነው አሉኝ፡፡ታዲያ ሰዎቹን በዚህ ላበስራቸው እንዴ? ስላቸው፡ እሳቸውም፡- (ሌሎች ህግጋትትን በመርሳት በሷ ላይ ብቻ በመጽናት) ይሳነፋሉና አታበስራቸው አሉኝ፡፡” ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት፡፡

በዒባዳህ ሰው የተፈጠረለትን ዓላማ ያሳካል፣ አምላካዊ ግዳጁንም ይወጣል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ያለ ዒባዳህ መኖር ማለት የሕይወት አላማና ግብ ሳይኖራቸው በደመ-ነፍስ እንደሚኖሩት እንሰሳ መሆን ማለት ነው፡፡እነሱ እንደሚበሉት ይበላል ይጠጣል፤ እንደሚተኙት ይተኛል፤ እንደሚሞቱትም ይሞታል፡፡

“إِنَّ اللَّهَ يُدْخِلُ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ جَنَّاتٍ تَجْرِي مِنْ تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ وَالَّذِينَ كَفَرُوا يَتَمَتَّعُونَ وَيَأْكُلُونَ كَمَا تَأْكُلُ الْأَنْعَامُ وَالنَّارُ مَثْوًى لَهُمْ ” سورة محمد 12
“አላህ እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችን የሠሩትን፣ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ያገባቸዋል፤ እነዚያም የካዱት (በቅርቢቱ ዓለም) ይጣቀማሉ፤ እንሰሳዎችም እንደሚበሉ ይበላሉ፤ እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት።” (ሱረቱ ሙሐመድ 12)፡፡

በዒባዳህ ደስተኛና ጣፋጭ የሆነ፡ የቀልብ መረጋጋት ያለበት ሕይወት ይኖራል፡፡ያለ ዒባዳህ የሚኖር ሰው ህይወት ጥጠበዋለች፤ ተስፋ-ቢስ ሁኖ ይኖራል፡፡

“مَنْ عَمِلَ صَالِحًا مِنْ ذَكَرٍ أَوْ أُنْثَى وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَلَنُحْيِيَنَّهُ حَيَاةً طَيِّبَةً وَلَنَجْزِيَنَّهُمْ أَجْرَهُمْ بِأَحْسَنِ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ ” سورة النحل 97
“ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።” (ሱረቱ-ነሕል 97)፡፡

“وَمَنْ أَعْرَضَ عَنْ ذِكْرِي فَإِنَّ لَهُ مَعِيشَةً ضَنْكًا وَنَحْشُرُهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ أَعْمَى” سورة طه 124
” ከግሳፄየም የዞረ ሰው፣ ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤ በትንሳኤም ቀን ዕውር ሆኖ እንቀሰቅሰዋለን።” (ሱረቱ ጣሀ 124)፡፡

በዒባዳህ ከጀሐነም እሳት በመትረፍ ጀነትን መጎናጸፍ ይቻላል፡፡ያለ ዒባዳህ ግን ትርፉ ለጀሐነም እሳት ማገዶ መሆን ነው (አላህ ይጠብቀን)፡፡

“تِلْكَ الْجَنَّةُ الَّتِي نُورِثُ مِنْ عِبَادِنَا مَنْ كَانَ تَقِيًّا ” سورة مريم 63
“ይህች ያቺ ከባሮቻቸን ጥንቁቆች ለኾኑት፣ የምናወርሳት ገነት ናት።” (ሱረቱ መርየም 63)፡፡

“وَقَالَ رَبُّكُمُ ادْعُونِي أَسْتَجِبْ لَكُمْ إِنَّ الَّذِينَ يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِي سَيَدْخُلُونَ جَهَنَّمَ دَاخِرِينَ ” سورة غافر 60
“ጌታችሁም አለ፦ ለምኑኑኝ እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያም እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ።” (ሱረቱ ጋፊር 60)፡፡

በዒባዳህ ሰው መሰል ብጤውን ሰውን ከማምለክ ከባርነት ቀንበር ነጻ ይወጣል፡፡ለአላህ እንጂ ለማንም የማይዋደቅ፤ አላህን እንጂ ሌላን የማይፈራ በመሆኑ ውስጣዊ ሃሴትና የበላይነት ይሰማዋል፡፡

ስለ ዒባዳህ ለመግቢያ ያህል ይህን ካነሳን፡ ወደ ጀመርነው ርእስ እንመለስና፡ አላህን የምናመልከው ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ፡ ቅዱስ ቁርኣን የሚሰጠንን ምላሽ እንከታተል፡-

1. ብቻውን ፈጣሪ ስለሆነ

“يَا أَيُّهَا النَّاسُ اعْبُدُوا رَبَّكُمْ الَّذِي خَلَقَكُمْ وَالَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ* الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ فِرَاشًا وَالسَّمَاءَ بِنَاءً وَأَنْزَلَ مِنَ السَّمَاءِ مَاءً فَأَخْرَجَ بِهِ مِنَ الثَّمَرَاتِ رِزْقًا لَكُمْ فَلَا تَجْعَلُوا لِلَّهِ أَنْدَادًا وَأَنْتُمْ تَعْلَمُونَ ” سورة البقرة:22-21
“እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ (እርሱ) ያ ለናንተ ምድርን ምንጣፍ ሰማይንም ጣራ ያደረገ ነው፤ ከሰማይም (ከደመና) ውሃን ያወረደ በርሱም ከፍሬዎች ለናንተ ሲሳይን ያወጣ ነው፡፡ እናንተም (ፈጣሪነቱን) የምታውቁ ስትኾኑ ለአላህ ባላንጣዎችን አታድርጉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 21-22)፡፡

በዚህ አንቀጽ መሰረት አላህ የሰዎች ሁሉ ፈጣሪና አስገኚ፡ እንዲሁም በዝናብ አማካይነት ሲሳይን ሰጪና መጋቢ በመሆኑ፡ አምልኮ የሚገባው ለሱ ብቻ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ምድርንም ምንጣፍ ያደረገልን እርሱ ነው፡፡ ምድር ለሰው የምትስማማ ምቹ ምንጣፍ ነች፡፡ ማንንም አትጎረብጥም፡፡ ሰማይም ከበላያችን ያለ-ምሰሶ የተዘረጋች ጣሪያ ነች፡፡ አንድ ቀንም ቢሆን ትወድቅብን ይሆን? ብለን ሰግተን አናውቅም፡፡ የቤትታችን ግድገዳ ግን ገና በተወሰነ አመታት ውስጥ መሰንጠቅ ሲጀምር፡ ዛሬ ነገ ይፈርሳል በሚል ስጋት እናሳድሰዋለን፡፡ የጥበበኛው ስራ ግን ያለ እድሳት ዘመናትን ይሻገራል፡፡ታዲያ እንዲህ አይነቱ ፈጣሪ እንዴት አይመለክ? ደግሞስ የሚፈጥር እንደማይፈጥር ነውን?

“أَفَمَنْ يَخْلُقُ كَمَنْ لَا يَخْلُقُ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ ” سورة النحل 17
“የሚፈጥር፣ እንደማይፈጥር ነውን? አትገሡጹምን?” (ሱረቱ-ነሕል 17)፡፡

2. ብቻውን ሲሳይ ሰጪ በመሆኑ

“إِنَّمَا تَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ أَوْثَانًا وَتَخْلُقُونَ إِفْكًا إِنَّ الَّذِينَ تَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ لَا يَمْلِكُونَ لَكُمْ رِزْقًا فَابْتَغُوا عِنْدَ اللَّهِ الرِّزْقَ وَاعْبُدُوهُ وَاشْكُرُوا لَهُ إِلَيْهِ تُرْجَعُونَ ” سورة العنكبوت 17
“ከአላህ ሌላ የምትግገዙት ጣዖታትን ብቻ ነው፤ ውሸትንም ትቀጣጥፋላችሁ፤ እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትግገዙዋችው ለናንተ ሲሳይን ሊሰጧችሁ አይችሉም፤ ስለዚህ ሲሳይን ከአላህ ዘንድ ብቻ ፈልጉ፤ ተገዙትም፤ ለርሱም አመስግኑ፤ ወደርሱ ትመለሳላችሁ።” (ሱረቱል ዐንከቡት 17)፡፡

“وَيَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ مَا لَا يَمْلِكُ لَهُمْ رِزْقًا مِنَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ شَيْئًا وَلَا يَسْتَطِيعُونَ ” سورة النحل 73
“ከአላህም ሌላ ከሰማያትም ከምድርም ምንንም ሲሳይ የማይሰጧቸውን፣ (ምንንም) የማይችሉትንም ይግገዛሉ።” (ሱረቱ-ነሕል 73)፡፡

አምላካችን አላህ ብቻውን ሲሳይ ሰጪ ነው፡፡ ከአረንጓዴ እጽዋት ለሰዎችም ለእንሰሳትም በሕይወት ለመቆየት ሰበብ የሆነውን ምግብ በችሎታው ማዘጋጀት የቻለ አምላክ!!፡፡ ሲያዘጋጀውም በልዩ ልዩ መልክና ሽታ እንዲሁም ጥፍጥና የታጀቡ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፡፡ታዲያ ለዚህ አምላክ እንዴት ብጤ ይደረግበታል?፡፡

3. ጥቅምና ጉዳት እሱ ዘንድ ብቻ ስለሆነ

“قُلْ أَتَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ مَا لَا يَمْلِكُ لَكُمْ ضَرًّا وَلَا نَفْعًا وَاللَّهُ هُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ ” سورة المائدة 76
“ከአላህ ሌላ ለናንተ መጉዳትንና መጥቀምን የማይችልን ትግገዛላችሁን? በላቸው፤ አላህም እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነው።” (ሱረቱል ማኢዳህ 76)፡፡

በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ሰውን ለመጥቀም ሰበብ መሆን የሚችሉ ነገሮች በጠቅላላ አላህ የፈጠራቸውና ያዘጋጃቸው ናቸው፡፡ ህይወት፣ ጤና እና የመሳሰሉት ማለት ነው፡፡ በዛው ተቃራኒ በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ሰውን ለመጉዳት ሰበብ መሆን የሚችሉ ነገሮች ሞት በሽታ እና የመሳሰሉት ሁሉ እሱ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ለሚፈልገው ህዝብና ሃገር ሲሳዩን አስፍቶ ጤናውን አሟልቶ በቸርነቱ መሰረት ይለግሳል፡፡ ሌላውንም እንደዚሁ በጥበቡ ሲሳዩን በማጥበብ በበሽታና በሰላም እጦት ይፈትናል፡፡ ከሱ ውጪ ይህን ሊያደርግ የሚችል አንድም ኃይል የለም፡፡

“مَا يَفْتَحْ اللَّهُ لِلنَّاسِ مِنْ رَحْمَةٍ فَلَا مُمْسِكَ لَهَا وَمَا يُمْسِكْ فَلَا مُرْسِلَ لَهُ مِنْ بَعْدِهِ وَهُوَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ ” فاطر2
“አላህ ለሰዎች ከችሮታ የሚከፍታት ለርሷ ምንም አጋጅ የላትም፤ የሚያግደውም ከርሱ በኋላ ለርሱ ምንም ለቃቂ የለውም፤ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው ” (ሱረቱ ፋጢር 2)፡፡

“وَإِنْ يَمْسَسْكَ اللَّهُ بِضُرٍّ فَلَا كَاشِفَ لَهُ إِلَّا هُوَ وَإِنْ يُرِدْكَ بِخَيْرٍ فَلَا رَادَّ لِفَضْلِهِ يُصِيبُ بِهِ مَنْ يَشَاءُ مِنْ عِبَادِهِ وَهُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ ” سورة يونس 107
” አላህም ጉዳትን ቢያደርስብህ ከእርሱ ሌላ ለእርሱ ገላጭ የለውም፡፡ በጎንም ነገር ቢሻልህ ለችሮታው መላሽ የለም፡፡ ከባሮቹ የሚሻውን በእርሱ ይለይበታል፡፡ እርሱም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 107)፡፡

عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ قَالَ كُنْتُ خَلْفَ رَسُولِ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم يَوْمًا فَقَالَ « يَا غُلاَمُ إِنِّى أُعَلِّمُكَ كَلِمَاتٍ احْفَظِ اللَّهَ يَحْفَظْكَ احْفَظِ اللَّهَ تَجِدْهُ تُجَاهَكَ إِذَا سَأَلْتَ فَاسْأَلِ اللَّهَ وَإِذَا اسْتَعَنْتَ فَاسْتَعِنْ بِاللَّهِ وَاعْلَمْ أَنَّ الأمَّةَ لَوْ اجْتَمَعَتْ عَلَى أَنْ يَنْفَعُوكَ بِشَيْءٍ لَمْ يَنْفَعُوكَ إِلاَّ بِشَيْءٍ قَدْ كَتَبَهُ اللَّهُ لَكَ وَلَوْ اجْتَمَعُوا عَلَى أَنْ يَضُرُّوكَ بِشَيْءٍ لَمْ يَضُرُّوكَ إِلاَّ بِشَيْءٍ قَدْ كَتَبَهُ اللَّهُ عَلَيْكَ… » رواه الترمذي 2706
ከዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው፡- አንድ ቀን ከአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ኃላ ሁኜ ሳለ “አንተ ታዳጊ ወጣት! እንዚህን ቃላቶች አስተምርሃለሁ፡- አላህን (ህጉን) ጠብቅ፤እርሱም ይጠብቅሀልና፣ አላህን (ህጉን) ጠብቅ፤ ፊት-ለፊትህ ታገኘዋለህ፣ስትለምን አላህን ለምን፣ እርዳታ ስትሻ በአላህ ታገዝ፣ ሕዝቦች ተሰብስበው አንተን ለመጥቀም ቢፈልጉ፤ አላህ ቀድሞ የጻፈልህን ካልሆነ በቀር በምንም ሊጠቅሙህ እንደማይችሉ እወቅ፣ ሕዝቦች ተሰብስበው አንተን ለመጉዳት ቢፈልጉ፤ አላህ ቀድሞ የጻፈብህን ካልሆነ በቀር በምንም ሊጎዱህ እንደማይችሉ እወቅ…አሉኝ” (ቲርሚዚይ 2706)፡፡

4. የሰማያትና ምድር ብቸኛ ፈጣሪና አስተናባሪ በመኾኑ

“إِنَّ رَبَّكُمُ اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ ثُمَّ اسْتَوَى عَلَى الْعَرْشِ يُدَبِّرُ الْأَمْرَ مَا مِنْ شَفِيعٍ إِلَّا مِنْ بَعْدِ إِذْنِهِ ذَلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ فَاعْبُدُوهُ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ ” سورة يونس 3
“ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠረ፥ በዐርሹም ላይ ራሱን ያደላደለ (አምላክ) ነው። ነገሮችን (ሁሉ) ያስተናብራል፥ ይመራል። ከርሱ ፈቃድ በኋላ ካልሆነ በቀር (የሚያማልድ) አንድም አማላጅ የለም። ጌታችሁ አላህ ይህ ነው። ስለሆነም (በብቸኝነት) አምልኩት።አትገሰፁምን?” (ሱረቱ ዩኑስ 3)፡፡

አላህ የሰማያትና ምድር ፈጣሪና አስተናባሪ በመሆኑ ልናመልከው እንደሚገባ እየነገረን ነው፡፡ ነገም ሁሉም ነገር የሚመለሰው ወደሱ ነው፡፡ የፍጥረታት ጀማሪና አስገኚ እንዲሁም መላሽና ብቸኛ ወራሽ ነው፡፡

“وَلِلَّهِ غَيْبُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَإِلَيْهِ يُرْجَعُ الْأَمْرُ كُلُّهُ فَاعْبُدْهُ وَتَوَكَّلْ عَلَيْهِ وَمَا رَبُّكَ بِغَافِلٍ عَمَّا تَعْمَلُونَ ” سورة هود 123
“በሰማያትና በምድርም ያለው ምስጢር ሁሉ፣ የአላህ ነው፤ ነገሩ ሁሉም ወደርሱ ይመለሳል፤ ስለዚህ ተገዛው፤ በርሱም ላይ ተጠጋ፤ ጌታህም ከሚሠሩት ሁሉ ዘንጊ አይደለም።” (ሱረቱ ሁድ 123)፡፡

“رَبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا فَاعْبُدْهُ وَاصْطَبِرْ لِعِبَادَتِهِ هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا ” سورة مريم 65
“(እርሱ) የሰማያትና የምድር፣ በሁለቱም መካካል ላለዉ ሁሉ ጌታ ነዉና ተገዛዉ፤ እርሱን በመግገዛትም ላይ ታገሥ፤ ለርሱ ሞክሼን ታዉቃለህን?” ሱረቱ መርየም 65

5. ሕይወትና ሞት በእጁ በመሆኑ

” قُلْ يَاأَيُّهَا النَّاسُ إِنْ كُنْتُمْ فِي شَكٍّ مِنْ دِينِي فَلَا أَعْبُدُ الَّذِينَ تَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ وَلَكِنْ أَعْبُدُ اللَّهَ الَّذِي يَتَوَفَّاكُمْ وَأُمِرْتُ أَنْ أَكُونَ مِنْ الْمُؤْمِنِينَ ” سورة يونس 104
“እናንተ ሰዎች ሆይ! ከእኔ ሃይማኖት በመጠራጠር ውስጥ ብትሆኑ እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትገዟቸውን አልገዛም፡፡ ግን ያንን የሚገድላችሁን አላህን እገዛለሁ፡፡ ከምእምናን እንድሆንም ታዝዣለሁ» በላቸው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 104)፡፡

በሕይወትና በሞት ላይ ስልጣን ያለው ( ሊገድልም ሆነ ህያው ሊያደርግ) እርሱ በርግጥ መመለክ አለበት፡፡ ልቦች በፍርሃትና በተስፋ እንዲሁም በፍቅር ሊንጠለጠሉበት የሚገባ ነው፡፡

” كَيْفَ تَكْفُرُونَ بِاللَّهِ وَكُنتُمْ أَمْوَاتًا فَأَحْيَاكُمْ ثُمَّ يُمِيتُكُمْ ثُمَّ يُحْيِيكُمْ ثُمَّ إِلَيْهِ تُرْجَعُونَ ” سورة البقرة 28
“ሙታን የነበራችሁ ስትኾኑ ሕያው ያደረጋችሁ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ሕያው የሚያደርጋችሁ ሲኾን ከዚያም ወደርሱ የምትመለሱ ስትኾኑ በአላህ እንዴት ትክዳለችሁ!” (ሱረቱል በቀራህ 28)::

በህይወት ዘመናቸው አላህን ብቻ ተገዝተው፡ ሙስሊም ሆነው ከሚሞቱ ባሮቹ ያድርገን፡፡በህይወት ዘመናቸው አላህን ብቻ ተገዝተው፡ ሙስሊም ሆነው ከሚሞቱ ባሮቹ ያድርገን፡፡

Shortlink http://q.gs/ExaUN