ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ለምን ብዙ ሚስት አገቡ?

ሼር ያድርጉ
1,000 Views

ጸረ-ኢስላም ሃይላት ሕዝቡ በኢስላም ላይ ጥላቻ እንዲኖረው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ፡፡ የሃይማኖቱ መምህር በሆኑት ነብዩ “ﷺ” ላይ በርካታ ውንጀላዎች አቅርበዋል፡፡ በዚህ ላይ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሚሆኑት ኦሬንታሊስቶችና ሚሽነሪዎች ናቸው፡፡መጀመሪያ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የ25ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር በአስራ አምስት አመት የምትበልጣቸውን፤ ሁለት ጊዜ አግብታ የፈታችውን ከድጃን ያገቡት፡፡ ሕይወቷ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሌላ ሚስት ሳያገቡ ከርሷ ጋር ለ25 ዓመታት አብረው ኖሩ፡፡ የተወሰነ ጊዜ በብቸኝነት ቆዩ፡፡ ለ25 ዓመታት አብረዋቸው ቆይታ በ65 ዓመት እድሜዋ በሞት የተለየቻቸው ከድጃ ሞት ኀዘን ጥሎባቸዋል፡፡ አቡ ጣሊብና ከድጃ በሞት ስለተለዩዋቸው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እጅግ አዘኑ ፡፡ ያ ዓመት በኢስላም ታሪክ ‹‹የሃዘን ዓመት›› ተብሎ ይታወቃል፡፡እነ‹‹ሐመረ ተዋህዶ እና መሰሎቻቸው››እንደሚወንጅላቸው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ሴሰኛ›› ቢሆኑ ኖሮ በወጣትነታቸው ከአሮጊት ሴት ጋር ብቻ ተወስነው ይቆዩ ነበርን? ‹‹ሴሰኛ›› ቢሆኑ ኖሮ ሌላ አማርጠው እንዳያገቡ አስራ የያዛቻቸው ሴት በመሞቷ (ያውም በ65 ዓመቷ) ያዝኑ ነበርን? ወይስ ወድያውኑ ድንግል ያገቡ ነበር? መጀመሪያውኑ ፈቅደውና ወደውስ አይደል በእድሜ የምትበልጣቸውን ሴት ያገቡት?

ከድጃ(ረ.ዐ) ከሞተች በኋላ ብቻቸውን ሳሉ ኸውላ ቢንት ሐኪም መጥታ እንዲያገቡ ጠየቀቻቸው ፡፡እንዲህ ተዘግቧል፡- ‹‹ከዓኢሻ እንደተላለፈው ፡-ከድጃ በሞተች ጊዜየዑስማን ቢን መዝዑን ሚስት ኸውላ ቢንት ሐኪም ቢን አል-ቀውስ በመካ ሳሉ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ አያገቡምን?›› አለች፡፡ ‹‹ማንን?›› አሏት፡፡‹‹ከፈለጉ ድንግልን፤ ከፈለጉም ያገባች ሴት›› አለች፡፡ ‹‹ማንናት አግብታ የፈታችው?›› አሏት፡፡ ‹‹ሰውድ ቢንት ዘመዓ በእርግጥ በርሶ አመነች ፤ እርሶም ያሉበትን እምነት ተከተለች ›› አለች፡፡ ሂጅና(ለጋብቻ እንደምፈልጋት) ንገሪያት አሏት፡፡ ወደ ሰውዳ ቤት ሄደችና ‹‹ሰውዳ ሆይ!(የምስራች) እንዲህ ካለ መባረክና መልካም ነገር ይበልጥ የናንተ ቤት ገባ ምን (የምስራች) አለ?አለቻት፡፡ ‹‹ምንድነው? ስትል ጠየቀቻት፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሰላምና ሰላት በሳቸው ላይ ይሁንና አንቺን ለጋብቻ እጠይቀሽ ዘንድ ላኩኝ፡፡›› አለቻት፡፡ ‹‹ወደድኩ (ተቀበልኩ)፡፡ ግቢና ለአባቴ ንገሪው፤….‹‹የአላህ መልእክተኛ ሰላምና ሰላት በሳቸው ላይ ይሁንና ሰውዳን አገቧት፡፡››(አልሙዕጀም አል-ከቢር፤ ጥራዝ 24፤ ገጽ 30)

ከዚህ ዘገባ የምንረዳው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ድንግል ወይስ አግብታ የፈታች?›› የሚል ምርጫ ሲቀርብላቸው ዳግም የመረጡት አግብታ የፈታችውን ሴት ነው፡፡ በጋብቻ ምክኒያት ሊወነጅላቸው የሚሯሯጡትን ወገኖችን የምጠይቀው ‹‹ሴሰኛ›› የሚባል ሰው አግብታ የፈታች ሴትን(ከዲጃም ሆነ ሰውዳን) ይመርጣል ወይስ ድንግልን?ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ግን በሃምሳ ዓመታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ያገቡት ፈትና የሐምሳ ዓመቷን ወይዘሮ ሰውዳን ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ለኢስላም መጠናከር ሲሉ በተለያየ መልኩ ጋብቻዎችን ፈጽመዋል (ሁሉንም የጋብቻ ዓይነቶች የፈጸሙበትን አጋጣሚዎች እና ምክኒያቶች በአላህ ፍቃድ በዝርዝር እናያቸዋለን፡፡ ሐመረ ተዋህዶ በልዩ እትም መጽሐፍ ገጽ 155 ላይ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ወንጅሏል “ሴሰኛ” ሲል ተሳድበዋል፡፡ ነገር ግን የሳቸውን ታሪክ በጥሞና ብናጤነው እንዲህ አይነት ሰው እንዳልነበሩ እንረዳለን፡፡ በስተርጅና ለሃይማኖቱ መስፋፍያ በስልትነት ለመጠቀም ማግባታቸው “ሴሰኛ” ያሰኛቸዋልን? እነ ሐመርና መሰሎቻቸው እንደሚሉት ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ግለሰብ ነበሩ? ይህንን እኔ ከምመልሰው ባለቤታቸውአዒሻ(ረ.ዐ) ስለ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ›ዐ›ወ) የሰጣችው ምስክርነት፡-

“አንዳችሁም የወሲብ ስሜታችሁን ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንደሞቆጣጠሩት መቆጣጠር አትችሉም፡፡” የሚል ነው (ሰሂህ ሙስሊም፤ ጥራዝ 006፤ ቁጥር 2439)

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለምን ብዙ ሚስት አገቡ?

——————————————————
በቅድሚያ በሁለት አበይት ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ የኢስላም ጠላቶች በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የጋብቻ ህይወት ላይ የሚነዙትን ትችቶችና አሉባልታዎች ከንቱነት ለማሳየት እንሞክራለን፡፡ ከዓኢሻ በስተቀር ያገቧቸው ሴቶች ሁሉ ባሎቻው የሞቱባቸው ወይም አግብተው የፈቱ ነበሩ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከአንድ በላይ ማግባት የጀመሩት የሽምግልና እድሜ ውስጥ ከገቡ በኋላ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ያገቧቸው ሴቶች ደግሞ በእድሜ የገፉ የወለዱና የከበዱ ነበሩ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ብዙ ሚስት ያገቡት የኢስላም ጠላቶች እንደሚሉት ስጋዊ ስሜታቸውን ለማርካት ቢሆን ኖሮ ልጃገረዶችንና ኮረዳዎችን በዓይነት ባገቡ ነበር፡፡ አንጋፋ ተከታያቸው ጃቢር ኢብን አብደላህ(ረ.ዐ) በአንድ ወቅት ሙሽራ መስሎ መጣ ‹‹አገባህ እንዴ?›› ካሉት በኋላ ‹‹ልጃገረድ ወይስ አግብታ የፈታች››አሉት፤ ጃቢርም አግብታ የፈታች እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ነብዩም ‹‹የምታጫውትህ የምታጫውታት፤ የምታስቅህ የምታስቃት፤ ልጃገረድ አታገባም ነበር›› በማለት ሐሳብ መሰዘራቸው ይታወሳል፡፡ይህም አባባላቸው የሚጠቁመን ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከልጃገረድ የሚገኘውን ደስታ ሳይረዱት ቀርተው አለመሆኑን ነው፡፡ ታዲያ እኒህ ነቢይ ልጃረዶችን ትተው አግብተው የፈቱ ሴቶችን ማግባታቸው ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ነው ለማለት ያስችለናልን? እንዲሁም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በወጣትነታቸው በአንድ ሴት ተወስነው ሲኖሩ ቆይተው ከ50 ዓመት በኋላ ከአንድ በላይ ማግባታቸው የስሜታዊነት መገለጫ ይሆን?የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቀደምት ተከታዮች(አስሐቦች) ንብረታቸውንም ሆነ ህይወታቸውን ለመሪያቸው ሲሉ አሳልፈው የሰጡ እና ለመስጠትም ዝግጁ የነበሩ መሆናቸው አሌ የሚባል አይደለም፡፡በመሆኑም ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) በሴት ልጅ ውበት የመቀናጣት ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ እያንዳንዱን አስሐባ ውብ ልጃገረዶች የሆኑ ልጆቹን ለነብያት ቁንጮ ለሆኑት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከመዳር ወደ ኋላ ባላሉ ነበር፡፡ ሴቶችም እንዲሁ ከነብያቸው ጋር የመጎዳኘትን ታላቅ እድል የሚቀበሉት በከፍተኛ ደስታ ነበር ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) 50 ዓመት ከሆናቸው በኋላ በእድሜ እጅግ የገፉ ሴቶችን ማግባታቸው ‹‹ሙሐመድ ስሜታዊና ሴሰኛ ነበር›› የሚለው ትችት ከእውነት የራቀ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ የእኝህ ታላቅ ነብይ ከአንድ በላይ የማግባት ምስጢር ልብ ወለድና ስሜትን ከመከተል እጅግ የራቀ ነው፡፡

ከአንድ በላይ እስከ አራት ሚስት ማግባት ለምን አስፈለገ?——————————————————

እንደ እውነቱ ከሆነ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ምክኒያት ማፈላለግ አያስፈልግም ፡፡ አንድ ሰው ለምን አንድ ሚስት አገባህ፤ አስረዳ ተብሎ አይጠየቅም ፡፡ ከአንድ በላይ ሲያገባ ምክኒያት እንዲደረድር ይገደዳል? ችግራችን አንድ ማግባት ሕጋዊና የጥሩ ስብእና መገለጫ ከዚያም በላይ መጨመርን ደግሞ የስጋዊነትንና የእኩይነት ምልክት አድርገን ስለምናየው ነው፡፡ ይህ ግን ሳይንሳዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እሳቤ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ምክኒያቱ የሚፈይዳቸው ስለሚኖሩ እንጠቁም፡፡ ነብዩ ሙሐመድ ከአራት በላይ ማግባታቸው ምክኒያቶች በዛ ያሉ ቢሆኑም በአራት ዋና ዋና ክፍሎችልንመድባቸው እንችላለን፡፡

1) ለትምህርት ስርጭት

2) ጎጂ ባህሎችን ለማስወገድ

3) ለማህበራዊ ዋስትና

4) ለፖለቲካዊ እርቅ፤

=========

1) ለትምህርት ስርጭት
——————————–

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ያስፈለገበት መሰረታዊ ምክኒያት ሴቶችን ሊያስተምሩ፤ ሊያነቁና ሊያንቀሳቅሱ የሚችሉ መምህራትን ለማደራጀት ነበር፡፡ እንደ ኢስላም እምነት ሴቶች የአንድ ህብረተሰብ ግማሽ አካል ናቸው ፡፡ ለወንዶች የተደነገጉ ሕግጋትና ግዴታዎች ሴቶችንም በፍትሃዊና እኩል ደረጃይመለከታሉ፡፡ ብዙ ሴቶች ነብዩ ሴቶችን የሚመለቱ በተለይ ግለሰባዊ ጉዳዮች ለመጠየቅ ያፍሩ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ስለወር አበባ፤ የወሊድ ደም፤ በግብረ ስጋ ግንኙነትና በመሳሰሉት ዙሪያ ስለሚነሱ ጉዳዮች ፤ ከወስብ በኋላ ስለሚደረጉ ትጥበቶች ፤እንዲሁም ስለ ጋብቻ ሕይወት ነፃ ሆኖ ለመጠየቅ ሴቶች የሃፍረት ካባቸውን ለመጣል ይቸገሩ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እንኳ ከ1400 ዓመታት በፊት ለነበሩ ደርባባ ሴቶች፤ ከፍተኛ የጾታ ቅልቅልና ትርምስ ለሚታይበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴቶች በአብዛኛው ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮቻቸውን እንደሚናገሩት ከፍተኛ ትህትና የተላበሱና በጫጉላ ቤት ከምትገኝ ሙሽራ የበለጠ ዓይን አፋር ነበሩ፡፡ በመሆኑም የአላ መልእክተኛ ሴቶች ለሚያነሱት ጾታዊ ጥያቄዎች በጣም ግልጽ በሆነ መልኩ ከመመለስ ይልቅ በአሽሙር መናሩን ይመርጡ ነበር፡፡ በሽሙር የሚናገራቸው ነጥቦች ደግሞ ለታዳሚው(ለጠያቂው) ግልጽ የማይሆንበት አጋጣሚ ስላለ አለመግባት ይፈጠር ነበር፡፡ ዓኢሻ (የነብዩ ባልተቤት) (ረ.ዐ) ያስተላለፈችውን ሐዲስ ለአብነት እንጠቅሳለን፡-‹‹በአንድ ወቅት አንዲት የመዲና ሴት የወር አባባ ከቆመላት በኋላ እንዴት እንደምትታጠብ አስረዷት፡፡ ንግግራቸውን ለመቋጨት ‹‹ከዚያም በመቀጠል ሽቶ ቢጤ የተርከፈከፈበትን ቁራጭ ጨርቅ ካዘጋጀሽ በኋላ አጽጂው››አሏት ‹‹ወይጉድ እንዴት ነው የማጸዳው›?›› ብላ ጠየቀች፡፡ ነብዩም በድጋሚ‹‹አጽጂው›› አሏት፡፡ እርሷም ‹‹ወይ ጉድ እንዴት ነው የማጸዳው›?››ስትል ደግሞ ጠየቀች፡፡ ነብዩም ‹‹ሱብሃነአላህ ፈተጧሀሪ ቢሃ (አጽጂው)›› አሉና ዝም አሉ፡፡ በዚህ ወቅት የነብዩ ባለቤት ዓኢሻ (ረ.ዐ) የጠያቂዋን እጅ ለቀም አደረገችና ይህን ይህን ቦታ በጥጡ ጥረጊ ከደሙ ያልጸዱ ክፍሎችን ጥረጊ ነው የሚሉሽ በማለት ብልቷን በሚስክ(ሽቶ) በተርከፈከፈበት ጥጥ(ጨርቅ) መጥረግ እንዳለባት በግልጽ አስረዳቻት ፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ግን እንደ ዓኢሻ ግልጽሆነው ለማናገር ያፍሩ ነበር፡፡ እንዲሁም ያለምንም ማመንታት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለማቅረብ የሚነሳሱ ሴቶች ጥቂቶች ባይሆኑም በርካታ አልነበሩም ፡፡ ኡሙ ሱለይም የተባለች የአቡ ጦልሃ ባልተቤት ወደ ነብዩ በመቅረብ እንዲህ ስትል ነበር ጥያቄ ያቀረበችው፡- ‹‹አንቱ የአላህ መልእክተኛ አላህ እውነትን ከመግለጽ እንድናፍር አያዝም፡፡ በመሆኑም የሚከተለውን ጥያቄ አቀርባለሁ…አንዲት ሴት በህልም የግብረ ስጋ ግንኙነት ብታደርግ ሰውነቷን መተጣጠብ ይኖርባታልን?›› ነብዩ ሙሐመድ ‹‹ፈሳሽ ነገር ካየች መታጠብ ይኖርባታል፡፡››አሏት ኡሙ ሱለይምም ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ ! ሴት ልጅ ደግሞ ዘር ይፈሳታልን?›› አለች፡፡ ነብዩም‹‹ሴት ልጅ ዘር የምታፈስ ባይሆን ኖሮ እንዴት መሰሏን ትወልዳለች?›› በማለት ጥያቄዋን በጥያቄ መለሱላት፡፡(ኢማሙ አህመድ ዘግበውታል)

ይህ መልስ ለጠያቂቱ ምን ያህል አደናጋሪ እንደሆነ መገንዘብ እንችላላን፡፡ ነብዩ ለማለት የፈለጉት ሽል የሚፈጥረው ከወንዱና ከሴቱ ዘር ቅንጅት በመሆኑ ልጅ እናቱን የመመስል ሁኔታ ይታይበታል ለማለት ነው፡፡ የዚህን ጭብጥ እውነታ በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ) በቁርአን እንዲህ ብሏል፡- “እኛ ሰውን ቅልቅል ከሆነ ፍትወት ጠብታ ፈጠርነው ሰሚ ተመልካች ም አደረግነው ፡፡››(ሱረቱ አል-ደህር 2)

ኢብን ከሲር በመባል የሚታወቁት ታላቅ የቁርአን ተንታኝ ‹‹አምሻጂን››የሚለውንና በዚህ አንቀጽ የተጠቀሰውን ቃል ‹‹የተቀላቀለ (ቅልቅል) ውህድ›› ማለት ነው ሲሉ አብደላህ ኢብን አባስ የተባለው የነብዩ የቅርብ አገልጋይም ‹‹አምሻጂን›› የሚባለው የወንድ ዘር (Sperm) እና የሴቲቱን ዘር(Egg) በአንድ ላይ ሲገናኙ ሲዋሃዱ የሚገኘው አካ መሆኑን ገልጸዋል፡፡እኝህና የመሳሰሉትና ቤተሰባዊ ጥያቄዎች የማስተማሩን ኋላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተወጡት የነብዩ ባልተቤቶች (ረ.ዐ) ነበሩ፡፡ ለዚህ ነው ዓኢሻ እንዲህ ያሉት ፡- ‹‹የመዲና ሴቶች አላህ ይዘንላቸው ሃይማኖታቸውን ከማወቅና ከመረዳት ዓይነ አፋርነት አልገደባቸውም፡፡››(ቡዃሪ ኪታቡ አል-ኢልም ባብ አል-ሃያ ፊ አል-ኢልም በሚለው ዘግበውታል ) በማለት የመዲና ሴቶች ወደ ነብዩና የነብዩ ባልተቤቶች በመምጣት የሚጠይቁትን ጥያቄዎች በማድነቅ ተናግራለች፡፡

ብዙ ሴቶች በውድቅት ጨለማ ስለ አንዳንድ ግላዊ ሕግጋ ለመጠየቅ ወደ ዓኢሻ (ረ.ዐ) ቤት ጎራ ይሉ ነበር፡፡ እሷም በሚገባ ታስተናግዳቸው ነበር፡፡ የነብዩ ባልተቤቶች በተለይ ለእንስት ሙስሊሞች አስተማሪና መመሪያ አስተላላፊ ነበሩ፡፡ አያሌ ሴቶች የአላህን ሃይማኖት ከነርሱ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ(ሱና) የሚባለውን የርሳቸውን ንግግር ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን እና ሌሎች የተናገሩትን ወይም የሰሩትን ያልተቃወሙትን ወይም ያጸደቁትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የመሪውን ቃል ተግባርና ያፀደቁትን ሆነ ያልተቃወሙትን ሁሉ የመከተል ግዴታ አለበት፡፡ እናም የነብዩን የግል ህይወትና ከማህበረሰቡ ተገንጥለው በሚቆዩበት ወቅት የሚናገሩትን ሆነ የሚሰሩትን ለሕዝበ ሙስሊሙ በማስተላላፍ ረገድ የተጫወቱት ሚና ቀላ አይደለም፡፡ በወፁአት(ጧሂራት)የሆኑ የነብዩ ባልተቤቶች የመልእክተኛው የቤት ውስጥ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ለሕዝቡ በማድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ ድረሳነ ታካቸው ህያው ምስክር ነው፡፡ ከፊሎቹ ይበልጥ ምሁራዊ ግልጋሎት ሲሰጡ ቀሪዎቹ ደግሞ የትዳና የማህበራዊ ሕይወት ተምሳሌት መሆን ችለዋል፡፡

2.ጎጂ ባህሎችን ለማስወገድ
————————–

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከአንድ በላይ ሚስት እንዲያገቡ ካስፈለገበት ምክኒያት ሁለተኛው መጥፎ ባህልን በመደምሰሰስ በምትኩ ኢስላማዊ የሆነ(ደንብ)ስርአት (ሸሪዓ) ለመመስረት ሲባል ነበር፡፡ ይህም በጨለማ ዘመን ሰዎች ሲሰሩት የነበሩት ጎጂ ባህሎች ከናካቴው ለማጥፋት ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ ነው፡፡ ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር ይበልጥ ቀረቤታ ያለውና ዐረቦች ከኢስላም በፊት ሲሰሩት ከነበሩት አፍራሽ ባህሎች አንዱን ለአብነት እናቅርብ፡፡ ይኸውም አንድ ሰው ከአብራኩ ያልወጣን ልጅ ‹‹አንተ ልጄ ነህ፤ እወርስሃለሁ ትወርሰኛለህ›› በማለት ይዋዋላል፡፡ የማደጎ ልጅ ያደርገዋል፡፡ ለቤተሰቡና ለአከባቢው ሰው በማሳደግ ይጀምራል፡፡ ይህም የማደጎ ልጅ ከአብራኩ ከተወለዱ ልጆች ጋር እኩል መብት ይሰጠዋል፡፡ ይኸውም አሳዳጊው (አባት ተብዬው ) ቢሞት ይወርሰዋል፤ እርሱም ከአሳዳጊው ይወርሳል፡፡ የአሳዳጊውን ልጅ እንዲያገባ አይፈቀድለትም፡፡ አሳዳጊውም የማደጎ ልጁን ሴት ልጅም ሆነ እርሱ የፈታትን ሴት ማግባት እርም ይሆንበታል፡፡ የማደጎ ልጅ ወላጅ አባት ስምም በአሳዳጊው ይተካ፡፡ ይህ ባል በግርድፉ ስናየው መጥፎ ላይመስለን ይችላል፡፡ በእርግጥ ማንም ግለሰብ አሳዳጊ የሌላቸውን ልጆች ሆነ የሌላ ሰው ልጅበራ ተነሳሽነት ቢያሳድግና ለደረጃ ቢያበቃ ኢስላም አይከለክልም፡፡ ነገር ግን ህጋዊ ልጅ ያልሆነውን ሰውልጄ ነው በማለት የአባቱን ስም ቀይሮየሥጋዊ ልጁ ካልሆነ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ግኑኝነት ጋር ማስተሳሰር ቁርአን አይቀበለውም፡፡ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ግኑኝነት ስንል የማደጎ ልጅ እንዲወርስና በአሳዳጊውም እንዲወረስ ማድረግና ከጋብቻ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን ለመጠቆም ነው፡፡ የማደጎ አሳዳጊውን መውረስ ወይም መወረስ እንዲሁም እንደ ስጋ ዘመድ ተቆጥሮ የተለያዩ የጋብቻ ማነቆዎች መፈጠራቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውዝግብና ማህበራዊ ቀውስ ፈጥሮ ነበር፡፡

1ኛ) ለምሳሌ አሳዳጊ ሲሞት የስጋ ልጆች ውርስ በሚቀርበበት ወቅት የማደጎ ልጅም ወራሽ ነኝ ብሎ ስለሚቀርብ ሽኩቻ መፍጠሩ እሙን ነው፡፡

2ኛ) የማደጎ ልጅ በሚሞትበት ጊዜ አሳዳጊወራሽ ነኝ በማለት ሲመጣ የማደጎ ልጅ ሚስት የስጋ ወላጅ፤ ልጆችና ሌሎችም ለውርስ ይቀርባሉ፡፡ ግና የማደጎ ልጅ ባህል ሚስት ባሏን እና ልጇና ልጅም አባቱንወዘተ….እዳይወርስ ያግዳዋል፡፡ አልያም ሊያገኙ የሚገባቸውን ትክክለኛ ድርሻ ይነፈጋሉ፡፡

3ኛ) የማደጎ ልጅ በስጋ አባቱ ስም መጠራት ሲገባው የወላጅ አባቱ ስም ተቀይሮ በአሳዳጊው ስም መጠራት የአባትነትን ተፈጥሮአዊ ፀጋና ማንነት እንደመፋቅ ይቆጠራል፡፡ የማደጎ ልጅ ሲባል በአገራችን እንደሚጣወቀው ከመንገድ ዳ ወይም ከተስፋ ተቋማት ወይም ከድሃ ቤተ ዘመዶች ተቀብለን ልጄነህ ወላጅህ ነኝ ትወርሰኛለህ እወርስሃለሁ በማለት ቃል የምንገባቸውን ሰዎችና በዚህ መስክ የምናሳድጋቸውን ልጆች ብቻ ሳይሆን የሚመለከተው በቂ መጠለያ ቤተሰብና መተዳደሪያ ያላቸውን ልጆችንም እንደ ስጋ ልጅ መቁጠርን የሚጠቁም መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

4ኛ) እንደ አሳዳጊ የማደጎ ልጁን ልጆቹንም ሆነ የቀድሞ ሚስት(የተፈታችውን) እንዲያገባ ቅርብ ዘመድ (እህት አክስት) የዐረቦች ባህል አይፈቅድም ነበር፡፡ በመሆኑም በማህበረሰቡ የጋብቻ ህይወት ላይ ነቀርሳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ ችግሮችን ለመፍታትና ኢስላም ከማሀይማን የተወረሱ ጎጂ ባህሎችን ለመፍታትና ኢስላም ከመሐይማን የተወረሱ ጎጂ ባህሎችን ለማጥፋ ሲል አስደናቂ ፀረ-ጎጂ ባህል እርምጃ ወስዷል፡፡ ጥበበኛው አላህ(ሱ.ወ) ከላይ የተጠቀሰውን ጎጂ የሕይወት ገጠመኝ መዋጋት ፍላጎቱ ነበርና ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የነብይነት ማዕረግ ከማግኘታቸው በፊት ከላይ በጠቀስነው የዐረቦች ባህላዊ ህይወት ውስጥ እንዲያልፉ አደረገ፡፡ ይኸውም ዘይድ ኢብን ሃሪሳን የማደጎ ልጅነት እውቅና ሰጡት፡፡

በምን አይነት ሁኔታ ነብዩ ዘይድን ልጃቸው ሊያደርጉት እንደበቁ የታሪክ ሰዎችና የቁርአን ተንታኞች በሰፊው የገለጽት ጣፋጭ ታሪክ አለ፡፡ ለጊዜው ወደ ታሪኩ አንገባም፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት መስጠት የምንሻው ራሳቸው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዘይድ ኢብን ሀሪስን(ልጅ) አድርገው መያዛቸውንናየዚህ ልጅ ስምም ዘይድ ኢብን ሀሪስ መባሉ ቀርቶ ዘይድ ኢብኑ ሙሐመድ እየተባለ መጠራቱ ነው፡፡ አብደላ ኢብን ዑመር (ረ.ዐ) የተባለው የነብዩ አስሃባ(ባልደረባ) እንዲህ ይገልጸዋል፡- ‹‹ዘይድ ኢብ ሀሪስን ዘይድ ኢብን ሙሐመድ ብለን ነበር የምንጠራው፡፡ የኋላ ኋላ ግን አላህ (ሱ.ወ) ፡- (ሱረቱ አል-አህዛብ፡5) አንቀጽ ሲያወርድ ነብዩ ‹‹አንተ ዘይድ ከእግዲህ ዘይድ ኢብን ሀሪስ ኢብን ሹረይሂል ተብለህ ነው የምትጠራው፡፡››አሉት፡፡ እኛም በዚሁ(በመጀመሪያው) ስሙ እንጠራው ጀመርን ፡፡(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ዘይነብ ቢንት ጃህሽ አል-አሰዲይ በመባል የምትታወቀውን የአክስታቸውን ልጅ ለዘይድ ድረውለት ነበር፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ዘይድና ዘይነብ አብረው መኖር ቢችሉም በመሃከላቸው ያለው ግኑኝነት ከቀን ወደ ቀን እየሻከረ መጥቶ ለፍች ተዳረሱ፡፡ የውዝግቡ ምንጭ ዘይነብ ከሉዕላን ቤተሰብ የተወለደችና በዘር ሐረጓና በዕውቀቷ የምትኩራራ ስለነበረች ትላንትና ባሪያ የነበረውን ዘይድ አቻዬ ነው የሚል እምነት አልነበራትም፡፡ በመጨረሻም ዘይድ አሰናበታት፡፡ የኋላ ኋላ አላህ(ሱ.ወ) የማደጎ ልጅ ሥርዓትን በኢስላማዊ ባል መተካተ መለኮታዊ እቅዱ ሆነና የነብዩ ሙሐመድን(ሰ.ዐ.ወ) የማደጎ ልጃቸው(ዘይድ) የፈታትን ሴት ማለትም ዘይነብ ቢንት ጀህሽን እንዲያገቡ በቁርአን ታዘዙ ፡፡ ነገር ግን የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መናፍቃንን እና የሐሜተኛችን ምላስ በመፍራት ዘይነብን የትዳር ጓደኛቸው ለማድረግ እያንገራገሩ ባሉበት ወቅት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መልአኩ ጅብሪል ይዞ ከተፍ አለ፡፡

وَتَخْشَى النَّاسَ وَاللَّهُ أَحَقُّ أَن تَخْشَاهُ ۖ فَلَمَّا قَضَىٰ زَيْدٌ مِّنْهَا وَطَرًا زَوَّجْنَاكَهَا لِكَيْ لَا يَكُونَ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ حَرَجٌ فِي أَزْوَاجِ أَدْعِيَائِهِمْ إِذَا قَضَوْا مِنْهُنَّ وَطَرًا ۚ وَكَانَ أَمْرُ اللَّهِ مَفْعُولًا[٣٣:٣٧] مَّا كَانَ عَلَى النَّبِيِّ مِنْ حَرَجٍ فِيمَا فَرَضَ اللَّهُ لَهُ ۖ سُنَّةَ اللَّهِ فِي الَّذِينَ خَلَوْا مِن قَبْلُ ۚ وَكَانَ أَمْرُ اللَّهِ قَدَرًا مَّقْدُورًا [٣٣:٣٨“……

አላህን ልትፈራው ይልቅ የተገባው ሲሆን፤ ሰዎችን የምትፈራ ሆንክ……….ዘይድም ከርሷ ጉዳይን በፈጸመ ጊዜ ፍላጎቱን አርክቶ በፈታትና ዒዳዋን በጨረሰች ጊዜ) በምዕመናኖች ላይ ልጅ አድርገው ባስጠጋቸው (ሰዎች) ሚስቶች፤ ከነርሱ ጉዳይን በፈጸሙ ጊዜ (በማግባት) ችግር እንዳይኖሩባቸው፤እርሷን አጋባንህ፤ የአላህም ትእዛዝ ተፈጻሚ ነው፡፡››(ሱረቱ አል-አህዛብ 33፡37)

ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ዘይነብን ከቤታቸው አስገቡ፡፡ የማደጎ ልጅ ጥንታዊ ወግም በነብዩ አርዓያነት ተሸረ፡፡

مَّا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَا أَحَدٍ مِّن رِّجَالِكُمْ وَلَٰكِن رَّسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ ۗ وَكَانَ اللَّهُ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا [٣٣:٤٠]

“ሙሐመድ፤ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም ፤ ግን የአላህ መልእክተኛና የነብያት መደምደሚያ ነው፤ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡”(ሱረቱ አል-አህዛብ 40)

ከላይ የጠቀስነው ታሪክ የምንረዳው ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ)› ዘይነብን ያገቡት በራሳቸው ፍላጎት ሳይሆን በአላህ ትእዛዝ መሆኑን እና ጋብቻው የተፈጸመውም ለከፍተኛ ዓላማ መሆኑ ነው ፡፡ አላህም ነብዩን ይህችን ሴትእንዲያገቡ ያስገደደበት ምክኒያት በምዕመናኖች ላይ ማህበራዊ ችግር እንዳይፈጥር መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ዓኢሻ(ረ.ዐ) የተባለችው የነብዩ ባለቤትም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከአምላክ የሚተላለፍላቸውን መልእክት የሚሸሽጉ ቢሆን ኖሮ ይህን አንቀጽ ሳይነግሩን ይቀሩ ነበር በማለት ዘይነብ ጋር በመጋባት የአከባቢውን ባህል መዋጋ ለነብዩ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁማለች፡፡ኢማ አል-ቡኻሪ እንደዘገቡትም ዘይነብ(ረ.ዐ) የተቀሩትን የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሴቶች(ሚስቶች ‹‹እናንተ በወላጆቻችሁ አማካኝነት ነብዩ ጋር ስትጋ እኔን ግን የዳሩኝ ወላጆቼ ሳይሆኑ ከሰባት ሰማያት በላይ ያለው አላህ(ሱ.ወ) ነው፡፡›› በማለት ትፎክርባቸው ነበር፡፡በጥቅሉ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ዘይነብን ያገቡት የዐረቦችን ባህል ለመቃወም፤ ሸሪዓ (ህገ-ኢስላም) ለመመስረት መሆኑን ነው፡፡ አላህም እነሆ ምን አይነት ጥበብ በዚህ ረገድእንደተጠቀመ መመልከት እንችላለን፡፡ ፡፡ የሰው ልጅ ያለው እውቀትም የአላህን ፍላጎት ጥበብ ሙሉ በሙሉ ሊደርስበት አይችልም፡፡ ለዚህም ነው የተከበረው ቁርአን

፡-وَمَا أُوتِيتُم مِّنَ الْعِلْمِ إِلَّا قَلِيلًا [١٧:٨٥]

“ከዕውቀት ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም፤በላቸው”(ሱረቱ አል-ኢስራእ 17፡85) ሲል ያሳሰበው፡፡

3) ለማህበራዊ ዋስትና

——————————
ለማህበራዊ ዋስትና መሻሻልና ማደግ ሲሉ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የቀውጢ ቀን ጋደኞቸውን እና የመጀመሪያውን ኸሊፋ (አቡበከር) ልጅ ሲያገቡ ከሌሎች ተሰሚነት ከነበራቸው የቁረይሽ ነገድ አባላት ጋር በአማችነትና በስጋ ተሳስረዋል፡፡ በመሆኑም ጎጠኛ የአረብ ጎሳዎች ጋር ለመተሳሰርና ልባቸውን ለነብዩ እንዲሰጡ ለማድረግ እንዲሁም ለአንድ አላማእንዲሰለፉና የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ማንነት እንዲገነዘቡ አድርጋቸዋል፡፡አቡበከር(ረ.ዐ) የነብዩ የቅርብ ወዳችና አይዞህ ባይ ነበሩ፡፡ ነብዩም በበኩላቸው እንደ አቡበከር የሚወዱት ሰው አልነበረም፡፡ አቡበከር በጣት ይቆጠሩ ከነበሩት ከመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች አንዱና አንጋፋው ነበሩ፡፡ በቲርሚዙ እንደተዘገበው ነብዩ ስለ አቡበከር እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ውለታ የዋለልኝን ሁሉ አጸፋውን መልሼለታለሁ-አቡበከር ሲቀር፡፡ እርሱን አላህ(ሱ.ወ) በዕለተ ትንሳዬ ውለታውን ይመልስለት ፡፡ እንደ አቡበከር ገንዘብ የጠቀመኝ የማንም ገንዘብ የለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው የኢስላም ጥሪ ሳስተዋውቀው መጀመሪያ ላይ ከብዶታል (አንገራግሯል)፡፡ አቡበከር ሲቀር-አላንገራገረም፡፡(ከአላህ ሌላ) ቅርብ ወዳጅ (ኸሊል) መያዝ ቢፈቀድ ኖሮ አቡበከርን ወዳጅ አድርጌ እይዝ ነበር፡፡ አዋጅ! አላህወዳጅ ኸሊል አድርጎኛል፡፡››(ቲርሚዚ ዘግበውታል)አቡበከር ለነብዩና አጠቃላይ ለኢስላ ለዋሉት ከፍተኛ ውለታ በዚህ ዓለም ሊመለስላቸው የሚችል ውለታ ባይኖርም ልጃቸውን ዓኢሻን በማግባት ከጋደኝነት ባሻገር በብርቅዬ የአማችነት ገመድ መተሳሰር ተገቢ መሆን የተረዱ ነብይ ዓኢሻን በማግባት የአቡበከርን አይን አሳረፉ(አስደሰቱ)፡፡ ትስስራቸው ይበልጥ ጸና ፡፡ ሁለተኛ ኸሊፋ (የፖለቲካና የአስተዳደር ምትክ)ዑመር በቆራጥነታቸው በሃቀኝነታቸውና ለዚህ ዲን በመዋደቃቸው ከፍተኛ ከበሬታና አድናቆት ያተረፉ ጀግናና ብርቅዬ ሰው ነበሩ፡፡ አላህ(ሱ.ወ) ኢስላምና ሙስሊሞችን በዑመር አማካኝነት ክብር እዲጎናጸፉ አድርጓል፡፡ታዲያ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ዑመር እጅግ ይወዷት የነበረችውን ልጅ ሀፍሷን ማግባታቸው የዑመርን ክብር ለመጠበቅ ጓደኘረነቱን ለማጠናከር የተጠቀሙበት አስገራሚ ስልት ነበር፡፡ባለውለታ ለመሆንም ነበር፡፡ በርግጥ የሀፍሷን መብትና ክብር ማስጠበቅም የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነ መስታወስ አለበት፡፡በሌላ በኩል ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ለዑስማንና ለዓሊይ (ረ.ዐ) ያላቸውን አንድነትና ክብር ለመግለጽ ልጆቻቸውን ዳሩላቸው፡፡ ይኸውም ለዑስማን ሩቂያንና ዑሙ ኩልሱምን(ረ.ዐ) ለዓሊይ ደግሞ ፋጡማን (ረ.ዐ) ሰጥተው ነበር፡፡ በዚህ አድራጎታቸው የነብዩን ብልህነት በግልጽ ማየት የቻልን ይመስለናል፡፡ ምክኒያቱም የኢስላምን ሃይማኖት በማስፋፋት የታወቁትን አቡበክርን እና ዑመርን(ረ.ዐ) ልጆቻቸውን በማግባት ወዳችነታቸውን ሲገልጹ ዑስማንና ዓሊን ደግሞ ልጆቻቸው በመዳር በአንድነት ላይ አንድነት በፍቅር ላይ ፍቅርን እንዲጨምሩ አድርገዋል፡፡ አቡበክር፤ዑመር፤ ኡስማንና ዓሊ (ረ.ዐ) ከነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ዕረፍት በፊትም ሆነ በኋላ የኢስላምን ባንዲራ በስፋት እንዲውለበለብ ያስቻሉ ከፍተኛ የኢማን መሰረት የጣሉና ፋና ወጊ ታጋዮች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ኸሊፋ የተባሉትም ለዚሁ ነው፡፡ ይኸውም ነብዩ ይህችን ዓለም ሲሰናበቱ ኢስላምም አብሮ ይከስማል ብለው የሚያስቡ መናፍቃን በጊዜው ነበሩ፡፡ ነገሩ የተገላቦጦሽ ሆኖ በነዚህ ሰዎች ስልጣን ዘመን የቁርአንና የሐዲስ ትምህርት ይበልጥ ተስፋፋ፡፡ እነሆ ኢስላም በአሁኑ ወቅት የቀለምና የብሄር እንዲሁም የቋንቋና የመሬት ልዩነት ሳያግደው በዓለም ላይ ሊሰራጭ የቻለው ከአላህ እርዳታ ጋር በነብዩ ጥበብ ፀባይና ሃቀኝነት ተማርከው ለማንም ምድራዊ ኃይል አንበረከክም በማለት ቁርአንን እና ኢስላምን በዚሁ ዓለም ከማንም በላይ ከፍ አድረገው በሚያዩት አስሐባዎች ተጋድሎ መሆኑን ይታወቃል፡፡ ለዚህ መጠነ ሰፊ ትግልም የአቡበክርና የዑመር የዑስማንና የዓሊ ግንባር ቀደም ሚና ተጠቃሽ ነው፡፡ አዎ! ለዚህ ነበር ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ዓኢሻንና የዑመርን ልጅ ሃፍሷን ያገቡት፡፡ ለወሲባዊ ጥማት ሳይሆን ከላይ ለዘረዘርነው ኢስላማዊ ማህበራዊ ግብ!

4) ለፖለቲካዊ እርቅ
————————–
የክርስቲያን ምሁራን ጥበብ የተቸረው ጠቢቡ ሰለሞን 700 ሚስቶችና 300 እቁባቶች እንደነበሩትበመጽሐፍ ቅዱስ ስለተጠቀሰው ሲያብራሩ፡- ‹‹ሰለሞን ብዙ ሴቶች አገባ፡፡ የአብዛኛው ጋብቻ ዓላማ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የፖለቲካ ስምምነት ለማድረግ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰለሞን 700 ሚስቶች 300 እቁባቶች እንደነበሩት ይናገራል፡፡……..ሰለሞን በርካታ ሚስቶች ይህ ለመሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለውም፡፡›› (ቲም ፌሎስ፤ የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፤ 1ኛ መጽሐፍ፤ ገጽ 503)

ሰለሞን ከሺ ሴቶች ጋር ለፖለቲካዊ እርቅ ሲል መጣመሩን የሚቀበሉት ክርስቲያን ምሁራን የነብዩ ሙሐመድን በጣት የሚቆጠሩ ጋብቻ ሊቀበሉ ፈጽሞ አይሹም፡፡ ተቀበሉም አልተቀበልም ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ለፖለቲካዊ እርቅ መመቻቸት ሲሉ ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ይኸውም የዘመኑ ህብረተሰብ በነገድና በጎሳ ወይም ቤተሰብ ጋር በሚጋባበት ጊዜ የአማችነት ስሜት ስለሚፈጥር መቀራረብና መከባበር ይሰፍናል፡፡ ይህ አጋጣሚ ሰዎችን ወደ ኢስላም ለመጥራትና ለተልዕኮውም መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ነበር፡፡ ከዚህ መንፈስ ጋር በተያያዘ መልኩ ነብዩ(ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ምሳሌዎች እነሆ

ሀ. ጁወይሪያ ቢንት ሓሪስ
——————————
በኒ ሙስጠሊቅ የተባለ ጎሳ መሪ ልጅ ነበረች፡፡ ከቤተሰብዋና ተከታዮችዋ ጋር ትማረካለች፡፡ በምርኮንነት እንዳለች ራሷን ነፃ ለማውጣት የምትችልበትን ሁኔታ ለመነጋገር ወደ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መጣች ገንዘብ ከፍላ ነፃ እንድትሆን ስትጠይቅ ነብዩ ካሣውን ራሳቸው እንደሚከፍሉላትና የትዳር ጓደኛም ሊያደርጓት እንደፈለጉ ሲገልጹላት በደስታ ተቀበለች፡፡ አገቧትም፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ የሙስሊሙ ሠራዊት የነብዩ አማኞች በእኛ ሥር በምርኮኝነት ሊቆዩ አይገባም በማለት በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን ምርከኞች ሁሉ ነፃ አወጡ፡፡ በዚህ ታላቅ ውለታ በተቸሩት ክብርና ሞገስ የበኒ ሙስጠሊቅ ብሄረሰብ አባላት እጅግ ተደሰቱ፡፡ በቀል ሳይሆን ማርታ እስር ሳይሆን ነፃነት ያጎናፀፏቸውን ነብይም ለመከተል ቃል ገቡ፡፡ ሙስሊም ሆኑ፡፡ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ይህችን የጎሳ መሪ ልጅ ማግባታቸው ለወይዘሮዋና ለተከታዮችዋ ትልቅ ተስፋና ረድኤት ነበር፡፡ ምክኒያቱም ወደ ኢስላም ለመግባትና ከባርነት (ከምርኮኝነት)ነፃ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ በውጤቱም የቁርአን ተልኮ መጠነ ሰፊ ዕድል ሊያጋጥመው ችሏል፡፡

ለ. ሶፊያ ቢንት ሁየይ
————————-
በተመሳሳይ ሁኔታ ሶፍያ ቢንት ሁየይ ኢብን አኽጣብ የተባለች ሴትም ጋር ፖለቲካዊ ጋብቻ ፈጽመዋል ንብዩ፡፡ ሲፊያ (ረ.ዐ) ‹‹በኸይበር›› ጦርነት ባሏከተገደለ በኋላ ተማረከች፡፡ በቁርአን ህግ መሰረት በኢስላማዊ ጦርነት የተማረከ ማንኛውም ነገር አንድ አምስተኛው ያህል ለማዕከላዊ መንግስት ገቢ ከተደረገ በኋላ ቀሪው ለሰራዊቱ እንዲከፋፈልይደረጋል፡፡ የምርኮ ክፍፍልም ሲደረግ ሶፊያ በተወሰኑ ሙስሊሞች እጅ ወደቀች፡፡ ሽማግሌዎች በበኑ ቁረይዛ እመቤት የሆነች ሴት በነብዩ እንጂ በሌላ ሰውቁጥጥር ሥር መሆን የለባትም በማለት አስተያየት ስለሰጡ ጉዳዩን ነብዩ እንዲወሰኑበት ተደረገ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ሶፊያን ከጠሩ በኋላ ሁለት ምርጫዎችን አቀረቡላት፡፡

1. ነፃ ካደረጓት በኋላ የርሳቸው የትዳር አጋር መሆን
2. ምንም ካሣ ሳትከፍል በነፃነት ወደቤተሰብዋ መቀላቀል

የነብዩን ማንነትና ሰው አክባሪነት በመረዳቷ ከምርኮኝነት ነፃ አውጥጠው ቢያገቧት ፈቃደኛ እንደምትሆን ገለጠች፡፡ ሶፊያ ወደ ኢስላም ሃይማኖት ያለ ምንም ማፈግፈግ ገባች፡፡ እሷም በመስለምዋ ብዙ ሰዎች ለመስለም በቁ፡፡ ነገሩን ግልጽ ለማድረግ የሚከተለውን ቃለ ምልልስ ይመልከቱ፡፡በሐዲስ እንደተዘገበው ሶፊያ ነብዩን ለማነጋገር ወደ መኖሪያ ቤታቸው ገባች፡፡ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሏት፡- ‹‹አባትሽ አላህ እስከገደለው ቀን ድረስ ከአይሁዳውያን ሁሉ ቀደኛ ጠላቴ ነበር፡፡››ሶፊያም፡- አንተ የአላህ መልእክተኛአላህ በቁርአን ‹‹……ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም…››አላለምን?! በማለት የመከላከያ መልስ ሰጣች፡፡ነብዩም፡- ‹‹ምርጫው ያንቺ ነው ኢስላምን ከመረጥሽ አገባሻለሁ፡፡ አይሁድነትን የምትመርጪ ከሆነ ደግሞ ነፃ አውጥቼ ወደ ሕዝቦችሽ እንድትሄጂ አደርጋለሁ፡፡›› አሏት፡፡ሶፊያ ፡- ‹‹አንተ አላህ መልእክተኛ እኔ ወደ ኢስላም ዝንባሌ አድሮብኛል፡፡ የአንተን እውተኝነትም ወዳንተ ማረፊያ እንድመጣ ከመጠራቴ በፊት ነው የተከነዘብኩት፡፡ ከአይሁድ እንግዲህ ምንም የቀራኝ ነገር የለም፡፡ ዘባቴም ሆነ ወንድሜ የሉም፡፡ ወደ ቤተሰቦቼ ከመሄድ ይልቅ ነጻነቴን ተጎናጽፌ አላህና መልእክተኛውን እመርጣለሁ እወዳለሁ፡፡›› አለች፡፡ ነብዩ ምርጫን ጠበቁላትና አገቧት፡፡

ሐ. ረምላ ቢንት አቡ ሱፍያን
——————————–
አባቱዋ የጣዖት አምላኪው የቁረይሽ ሕዝብ ዓላማ አራማጅና የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ግንባር ቀደም ጠላት ነበር፡፡ መበካ ከተማም ተሰሚነት ካላቸው ቱጃሮችና መሪዎች የሚጠቀስ ሰው ነበር፡፡ በመካ ከተማም ተሰሚነት ካላቸው ቱጃሮችና መሪዎችም የሚጠቀስ ሰው ነበር ፡፡ ከዚህ ግለሰብ አብራክ ግን ረምላ ቢንት አቡ ፉፍያን (ኡሙ ሃቢባ) የምትባል ቅን ሴት ወጣች፡፡ ይህችም እመቤት በመካ ውስጥ በቀዳሚነት ከሰለሙት ሰዎች አንዷ ስትሆን በመስለሟ ምክኒያት ከአከባቢዋ ሰዎች የሚደርስባት ስቃይና መከራ እየከፋ ሲመጣ ከባልዋ ጋር ወደ ሀበሻመሰዳዳ ይታወሳል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በሀበሻ(ኢትዮጲያ) እንዳለች ባለቤትዋ ከፍሮ በመሞቱ ያለረዳትና አይዞሽ ባይ ለብቻዋ ቀራች፡፡ ይህ ዜና በመካ ለነበሩት ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ደረሳቸው፡፡ እሳቸው ሰምተው ዝም አላሉም፡፡ ነጃሺ የተባለው የወቅቱ የሐበሻ ንጉስ ልጂቱን (ረምላን) እንዲድርላቸው ጠየቁት፡፡ ንጉስ ነጃሺም ይህን ሁኔታ ለረምላ (ረ.ዐ) ነገራት፡፡ ከመጠን በላይ ተደሰተች፡፡ምክኒያቱም ወደ ከበርቴው አባትዋና ቤተሰቦቻ ብትመለስ ከኢስላም ሃይማት እንድትወጣና ወደ ጣዖት አምልኮ እንድትመለስ እንደሚያስገድዷት ወይም እንደተለመደው ብርቱ ቅጣት እንደሚጠብቃት እውን ነበርና፡፡ ነጃሺም አራት መቶ ዲናር ወርቅ በጥሎሽ መልክ ከሰጣትና ሌሎች ስጦታ ካበረከተላት ወደ መዲና ላካት፡፡ መዲና በገባች ጊዜም ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ጋር መኖር ጀመረች፡፡ ይህ ክስተት ለአቡ ሱፍያን ደረሰው፡፡ የነብዩ ሙሐመድን አማችነት ውድቅ ማድረግ አልተቻለውም፡፡ ጋብቻውን በደስታ አፀደቀ፡፡ አዎ! የነብዩ ዓላማ ተሳካ፡፡ አቡሱፍያን ሙሐመድ የልጄ ባል ሊሆን አይችልም ብሎ ሳይደነፋ መልካም ፈቃዱን ገለፀ፡፡ የኋላ ኋላም ኢስላምን ለመቀበል በቃ፡፡እነሆ ነብዩ የባለስልጣኑን የአቡ ስፋያን ልጅ ከስደት አገር አስጠርተው ማግባታቸው ለተራ ወሲባዊ ጥማት አለመሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡ ለስሜትነ ፍላጎትን ለማርካትቢሆን ኖሮ ደጋግመን እንደጠቀስነው ልጃገረዶችን በአይነት መቀያየር የሚያዳግታቸው አልነበረም፡፡ ታዲያ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ወደ ሀበሻ ባሏ የሞተባትን ጤና የለሽሴት ፍለጋ መልእክት መላካቸው ለወሲብ ነው ብንል የውሸት ውሸት አይሆንብንም? በእርግጥ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) አቡ ሱፍያንን ልጅ ያገቡት ከላይ እንደጠቀስነው አቡሱፍያን በነብዩ እና በሙስሊሞች ላይ ግፍ መከራና ስደት ከሚያቀነባብሩት ሰዎች አንዱ በመሆኑ የበኒ ኡመያ ነገድ መሪዎች በኢስላም ላይ ያላቸውን መጥፎ አመለካከትና ጥቃት እንዲቀንሱና ልባቸውም ወደ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) መለስ እንዲል ነበር፡፡ እንዲሁም ረምላ(ረ.ዐ) ለአላህና ለመልክተኛው(ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ)) ስትልየተሰቃየች ባሏን ያጣች የዓረብያ በረሃ ተራራ ሸለቆና ባህር ሳይበግራት ሀበሻ ድረስ የተሰደደች ሴት መሆናንዋ ለዚህ ከፍተኛ አስተዋፅኦዋ ክብርና ለርሷም ደህንነት ሲሉ አግብተዋታል፡፡

لَّا يَحِلُّ لَكَ النِّسَاءُ مِن بَعْدُ وَلَا أَن تَبَدَّلَ بِهِنَّ مِنْ أَزْوَاجٍوَلَوْ أَعْجَبَكَ حُسْنُهُنَّ إِلَّا مَا مَلَكَتْ يَمِينُكَ ۗ وَكَانَ اللَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ رَّقِيبًا [٣٣:٥٢]

‹‹ከዚህ በኋላ….ሴቶች ላንተ አይፈቀዱልህም ከሚስቶችም መልካቸው ቢደንቅህም እንኳ በነርሱ ልታላውጥ (አይፈቀዱልህም) አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡›› (ሱረቱ አል-አህዛብ 33፡52)

Shortlink http://q.gs/F4a5c