ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ለምን ከአራት በላይ ሚስቶችን አገቡ?

1,840 Views

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

ሙስሊም ያልሆኑ አካላት በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ይህ በርዕሱ ያስቀመጥነው ክፍል አብዝቶ የሚቀርብ ነው። “ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ለምን ብዙ ሚስት አገቡ?” የሚለው ጥያቄ ምናልባት ለአንዳንድ ሙስሊም ወገኖቻችንም በውስጣቸው የሚብላላ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችን አለፍ ሲልም እነዚህን ጋብቻዎች በመጥቀስ ሙስሊሞች ከተፈቀደላቸው የጋብቻ ኮታ (አራት ማግባት) በላይ እሳቸው ለምን አገቡ? ሲሉ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም አንዳንድ ኢስላምን የሚተቹ አካላት ደግሞ ብዙ የማግባት አላማ “ሴሰኝነት ነው” በሚል ድምዳሜ ረሱልን ”ﷺ” በሴሰኝነት ለመክሰስ ሲዳዳቸው ይስተዋላል (አላህ ይቅር ይበለን)

ይህንን አጀንዳ በሁለት መሠረታዊ ክፍሎች ገምደን ማብራራት እንችላለን። ጉዳዩን በተሟላ መልኩ ለመረዳት የሚከተሉትን ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች በተናጠል ለመመልከት እንሞክር፦

❐ ከጋብቻ ኮታ በላይ ማግባትን በተመለከተ

አላህ ﷻ በቁርአኑ እንደገለፀልን ለምዕመናን ከአንድ በላይ ማግባት ተፈቅዷል። ይህ ፍቃድ ግን ገደብም ጭምር አለው፤ ይኸውም የመጨረሻ ጣራው አራት ብቻ ነው (ከአንድ በላይ ማግባትን/Polygamy/ አስመልክቶ በአላህ ፍቃድ ሌላ ጊዜ ራሱን በቻለ ክፍል እመለስበታለሁ)።
ቁርአን እንዲህ ይላል፦

وَإِنْ خِفْتُمْ أَلَّا تُقْسِطُوا فِي الْيَتَامَىٰ فَانكِحُوا مَا طَابَ لَكُم مِّنَ النِّسَاءِ مَثْنَىٰ وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ ۖ فَإِنْ خِفْتُمْ أَلَّا تَعْدِلُوا فَوَاحِدَةً أَوْ مَا مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ ۚ ذَٰلِكَ أَدْنَىٰ أَلَّا تَعُولُوا

በየቲሞችም (ማግባት) አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ (ዝሙትንና ከተወሰነላችሁ በላይ ማግባትንም ፍሩ)፡፡ ከሴቶች ለእናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት ሦስት ሦስትም አራት አራትም አግቡ፡፡ አለማስተካከልንም ብትፈሩ አንዲትን ብቻ ወይም እጆቻችሁ ንብረት ያደረጉትን ያዙ፡፡ ይህ ወደ አለመበደል በጣም የቀረበ ነው፡፡ [ ሱረቱ አል-ኒሳእ – 3 ]

ታዲያ ጥያቄው የሚነሳው ከዚህ ነው። የተፈቀደው የጋብቻ ጣራ አራት ከሆነ ለምን እሳቸው ከዚያ በላይ አገቡ? የሚለው ነው። ይህ እንግዲህ ነብያትና ሌላው አማኝ በተወሰኑ ትዕዛዛት ዙሪያ ያላቸውን ልዩነትና አንድነት ካለመረዳት የመነጨ ጥያቄ ነው። ከዚህ በታች በመጠኑ ላብራራው፦

1- አንዳንድ ተግባራት ነብዩን ”ﷺ” ብቻ በተለየ የሚመለከቱ ትዕዛዛት ሲሆኑ መልእክቱም የሚመለከተውም እሳቸውን ብቻ ነው። ግልጽ ለማድረግ ያክል እሳቸው በነብይነታቸው ሳቢያ ከሌላው ሙስሊም የሚለዩ እንደመሆኑ መጠን ከጠቅላላ የኢስላም ህግጋት ውስጥ በተለየ መልኩ እሳቸውን የሚመለከቱ ፍቃድና ትእዛዛትም ነበሩ።

እንደ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ ለመጥቀስ ያክል የሌሊት ስግደት (ተሀጁድ) ለሌላው ሙስሊም ማህበረሰብ ቢያደርገው የሚወደድና መልካም ትሩፋትም የሚያገኝበት ነው፤ ነገር ግን የግዴታ ትእዛዝ አይደለም። በተቃራኒው ነብዩን ”ﷺ” በተመለከተ ግን ግዴታና እንዲያደርጉት በተለየ መልኩ ለሳቸው የቀረበ ትእዛዝ ነበር። ካለምንም አሳማኝ ምክንያትም እንዲያልፋቸው አይጠበቅም ነበር። አላህ ﷻ ይህንን በማስመልከት እንዲህ ይላቸዋል፦

وَمِنَ اللَّيْلِ فَتَهَجَّدْ بِهِ نَافِلَةً لَّكَ عَسَىٰ أَن يَبْعَثَكَ رَبُّكَ مَقَامًا مَّحْمُودًا
ከሌሊትም ላንተ ተጨማሪ የኾነችን ሶላት በእርሱ (በቁርኣን) ስገድ፡፡ ጌታህ ምስጉን በኾነ ስፍራ በእርግጥ ያቆምሃል፡፡ (ሱረቱ አል-ኢስራእ – 79)

በተጨማሪም

“ሌሊቱን ሁሉ ጥቂት ሲቀር ቁም፤ (ስገደ)፡፡
ግማሹን (ቁም)፤ ወይም ከርሱ ጥቂትን ቀንስ፡፡ (ቁርአን 73፥2-3)

ሌላው ሙስሊም የግዴታ ሰላቶችን ሰግዶ ማረፍ የሚችል ሲሆን እሳቸው ግን ሌሊቱን በመስገድ እንዲያሳልፉ ታዘዋል። ይህ በተለየ መልኩ ለሳቸው የቀረበ ትእዛዝ ሲሆን በሀዲስ እንደተገለፀልን እሳቸውም ትእዛዙን እግራቸው እስኪያብጥ ድረስ በመስገድ ይጠብቁ ነበር (ሰለዋቱ ረቢ ወሰላሙሁ አለይሂ)

ከዚህም በተጨማሪ በሀዲስ እንደተቀመጠው ነብዩ ሙሐመድ ”ﷺ” ፆምን አከታትለው ይፆሙ ነበር። ይህም ማለት የዛሬ ፆማቸውን ሳይፈቱ ነገም በዛው የረሀብ ሆዳቸው ሌላ ፆምን ይቀጥሉ ነበር ማለት ነው። መሠል ተግባራት የሚመለከቱት በተለየ መልኩ እሳቸውን እንጅ መላውን አማኝም አልነበረም። ጋብቻን አንስቶ “ለራሳቸው እንዲመቻቸው” ነው ብሎ የሚተች ግለሰብ ይህንንስ ምን ይለው ይሆን? የተለየ ተግባራትን ለሳቸው የሚመርጡ ቢሆን ኖሮ የሚመቻቸውን ብቻ በመለየት ለራሳቸው ይሸልሙ ነበርንጅ ራሳቸው ላይ ችግር የሚፈጥሩ ጫናዎችን በማምጣት ህይወታቸውን ባላስጨነቁ ነበር። ነገር ግን የትእዛዙ መሠረት እሳቸው አይደሉምና የሚመጡ ተግባራት ተችዎች እንደሚሉት “የሚመቿቸው” ብቻ አልነበሩም።

በርግጥም ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ነብይ እንደመሆናቸው መጠን ከተራው አማኝ የተለየ ትዕዛዛትን ይቀበሉ ነበር። ነብይ የሆነ ሰው ከአምላክ የተመረጠ ከመሆኑ ጀምሮ ከተራው ማህበረሰብ የሚለዩት መጠነኛ ህግጋቶች ይኖራሉ። የነዚህ ጋብቻዎችን ጥበብ ለተመለከተም ሰው አላህ ﷻ ለምን በተለየ መልኩ ለሳቸው ፍቃድ እንደሰጠ እንረዳለን (የጋብቻዎቻቸውን ጥበብ ስንዘረዝር በሰፊው እንመለከተዋለን)

2- በሁለተኛ ደረጃ የሚቀርበው ጥያቄ “በርግጥ ጋብቻቸውስ ስጋዊ ፍላጎት የታለመበት ነበር?” የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ ተገቢው መልስ “በፍፁም” የሚል ነው። ከዚህ በታች በመጠኑ ምክንያቶችን ለማስቀመጥ ልሞክር፦

❐ የመጀመሪያው ነጥብ ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ከአንድ በላይ ሚስቶችን ያገቡት በወጣትነታቸው ሳይሆን እድሚያቸው ከ50 ዓመት ካለፈ በኋላ ነበር። እስከዛው ድረስ የነበረቻቸው ብቸኛ ሚስት ኸዲጃ (ረ.ዐ) ብቻ ነበረች። የሚደንቀው ደግሞ ኸዲጃን ሲያገቡ ከሳቸው በእድሜ 15 አመት ያህል ትበልጣቸው ነበር። ከዚያም በተጨማሪ እሷ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ያገባች ሴት ነበረች..! እሷ ከሞተች በኃላ እንኳን ትዳር ሲመሰርቱ ለቀጣይ አራት አመታት ብቸኛ ሚስታቸው ሁና የዘለቀችው ሰውዳዕ (ረ.ዐ) ነበረች። በነዚህ የወጣትነታቸው ጊዜያት ሁሉ የነበራቸው አንድና አንድ ሚስት ብቻ ነበር። አስቡት የጋብቻዎቻቸው መንስኤ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ሴሰኝነትና ተያያዥ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ተገቢው ጊዜ ወጣትነታቸው ይሆን ነበር። ክስተቱ ግን ከዚህ የተለየ ነበር።

❐ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ሁሉም የነብዩ ”ﷺ” ሚስቶች ከአኢሻ በስተቀር ባሎቻቸው የሞቱባቸው ወይንም የተፈቱ ነበሩ፡፡ አሁንም በተመሳሳይ የምንጠይቀው ጥያቄ እንደተባለው እውን ነብዩ ”ﷺ” ፍላጎታቸው ሴሰኝነት ቢሆን ኖሮ ያገባሉ ተብሎ የሚታሰበው የተመረጡ ደናግላንና ቆነጃጅት ሴቶችን ነው ወይንስ ባሎቻቸው የሞቱባቸውና አጋዥ አልባ ሚስኪኖችን? የሚለው ነው።
ይህ ከጤነኛ አእምሮ የሚፈልቅ አመክንዬ ሊሆን አይችልም። “ሴሰኛ” ተብሎ የሚወቀስ ሰው መገለጫዎቹ በርግጥም ይታወቃሉ። ሴሰኛ ሰው ከመነሻው ወደ ትዳር የመምጣት እድሉ ጠባብ ነው። ቢመጣም ለስሜቱ ቅርብ የሆኑ ምርጫዎች ይታወቃሉ። ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ከነዛ ባህርያት ሁሉ ፈጽሞ የራቁ ነበሩ። ይህንን አስመልክቶ ሊኖር የሚችለው ቀጣይ ጥያቄ “ታዲያ ለምን አገቡ?” የሚለው ነው። ይህንንና ከጋብቻዎቻቸው ጀርባ ያሉ ጥበቦችን አላህ ﷻ ፍቃዱ ከሆነ በሌላ ጹሁፋችን የምንዳስሰሳቸው ይሆናል።