ችግሮቻችን

ሼር ያድርጉ
565 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

በኣላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን የመጨረሻ ነብይ ኾነው በተነሱት ሙሐመድ ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይኹን ብለን እንቀጥል፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ? ሰሞኑን ከኾነ ሰው ደጅ ተጣድኹና ከርሱና በዙሪያው ካሉ ኣንዳንድ ጋዶቹ ጋር ወግ ኣንስተን ስንጥል፣ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ግልሰቦች ሲነሱ የምሰማቸውን እጅግ ሚያስደነግጡም ሚያሳዝኑም ሐሳቦችን አገኘኹ፡፡ አገኘኹናም መሰል የሐሳብና ፍልስፍና መንሻፈፎች መንስዔያቸው ምን ሊኾን እንደሚችል ከግለሰቦቹ ማንነትና ከማውቀው እውነታ ጋር ለማጣጣም ሞከርኹ፡፡ እነሆ ዛሬ በነዚህ ጉዳዮች ከማለዳው ላወጋዎ በሎሚና ጤናኣዳም የተዋሐደውን ውኃዬን እየተጎነጨኹ ከመጽሐፍት ቤቴ ተጥጃለኹ፡፡ (ውኃውን እርሶም ይሞክሩት…)

[ ግለ- ሚዛን]

ሰዎች ስለ ኢስላም ያለን ምልከታ እጅጉን የተንሻፈፈ -ኮንኬቪቲ ወይም ኮንቬክሲቲ ያለው- በመኾኑ ከኢስላም ፊት ቆምን ሚታየን የተንጓለለና የጎበጠ ምስል ብቻ ከኾነ ሰንብቷል፡፡ ነገሮችን ምንመዝነው በኛው ባላዋቂው ኣእምሮችን በመኾኑ፣ መለኪያችን በምልዓት ከኛ ጋር ሚጣጠሙ ነገሮች መልካም ናቸው፤ የማይኋኋኑት ደግሞ ሆሳዕ ወይም ኋላ ቀር ናቸው፤ የሚል ግለ-ሚዛን ኾኗል፡፡ ከግለ-ሚዛን ተነስተን ኢስላማዊ አስተምህሮዎች ሃያ ኣንደኛውን ክፍለ ዘመን ማናገር ኣይችሉም! ምክንያቱም ሕግጋቱ ከሺኅ ዓመታት በፊት የተሰበኩ ናቸው፤ የዛሬ ኹነቶቻችን ደግሞ ፈጽሞ ከያኔው ይለያሉ፤ ኢስላም ዛሬ ላይ ከግል መረጃ በዘለለ መሰረታዊ ለኹነ ማሕበራዊ ቀውሶች መፍትሔ የለውም…ወዘተ የሚሉ ድፍረት የተሞላባቸው ንግግሮች ኾነዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በየመስጂዱ የሚሰጡትን ትምህርቶች፣ ኹጥባዎችንና የትምህርት ሥርዓቱን በግልብ ከመተቸት ወደ ኋላ ኣይሉም፡፡ ለነሱ የነሱን ፍልስፍና የማይጋራ ኹሉ በተሳሳተ መንገድ ላይ እየኳተነ ነው፡፡ ወዳጄ ይህ በሽታ እንደ ኮሌራ እየተሰራጨ እንደኾነ ይሰመርበት፤በተለይ ደግሞ ተምረናል በሚሉ ወጣቶች መካከል ሥርጭቱ እየተጋጋመ ነው፡፡ በየመገናኛው ይህንን እንጨት እንጨት የሚል ግርድፍ ፍልስፍናቸውንና ራዕያቸውን ያነሳሉ፤ከነሱ ዘንድ የተገኘ ቀድሞውኑ ለማበድ ዝግጅቱን የጨረሰ፣ ገና ቃላቸውን ሲሰሰማ ከእብደቱ ዓለም ይደባለቃል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከእነርሱ መካከል እንደ ኣንዱ ኾኖ እረሱም ቫይረሱን ማሰራጨት ይጀምራል፡፡

ወዳጄ ከላይ ያነሳነውን ሐሳብ የሚሞግቱ ወጣቶችን ቅደመ-ታሪክ ብንፈትሽ ብዝኋኑ እምብዛም ለኢስላማዊ አስተምህሮዎች ተጋላጭነት ያልነበረው፣የልጅነት ታሪኩ እንደነገሩ ያለፈ፣ ዛሬ ላይ ኢስላምን ለመማር ጊዜው አልፎብኛል፣ አልችልም፤ የሚል ስንፍና ውስጥ የወደቀና እጅጉንም ነፍሱን ብቻ ማዳመጥ የሚፈልግ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ገሚሱ ደግሞ በዙሪያው ባሉ አስተሳሰቦችና ባህሎች የተማረከና ለፍልስፍናዎቹ ለምለም መሬት በመኾኑ፣ ኹሉም አስተሳሰቦች በግርድፉ ልክ ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ መጥቷል፡፡ የጥሩ ተደራሲ ውጤት ኹሌም በድርሰቱ መቼት እጅግ መወሰድ፣መመሰጥና መንሰቅሰቅ ስለኾነ፣ ወጣቶቻችን የዚህ ሰለባ መኾናቸው ብዙም ላይደንቅ ይችላል፡፡

[መፍትሔው…]

ኣላህ ኣንድን ነብይ ከሌላው በኋላ ከሚያስነሳበት ኣራት ምክንያቶች ኣንዱ የቀድሞው ነብይ አስተምህሮ ከአኹኑ ዘመን ጋር መሄድ ሳይችል ሲቀርና አዳዲስ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ የሌለው እንደኾነ፣ አዲስ ነብይ በአዲስ አስተምሀሮ ይነሳል፡፡ ኣላህ መልክተኛውን ሙሐመድን (ሰ›ዐ›ወ) የመጨረሻ ነብይ አድርጎ ሲያስነሳ ከርሳቸው በኋላ ነብይ ኣይነሳም ብቻ ሳይኾን፣ ይዘውት የመጡት አስተምህሮም እስከ ትንሳዔ ዘመን ላሉ ኹሉም ዓይነት ችግሮች መፍትሔ ስላለው ነው፡፡ ኢስላም ይህን ዘመን ማናገር ኣይችልም ማለት በሌላ አባባል ሌላ ነብይ ከሌላ አስተምህሮ ጋር መነሳት አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግልጽ ክህደት ነው፡፡

ፍልስፍናዎች በኢስላም ቅኝት ከተቀኙ ቢያንስ ለራሳችን ፍሬኣማ ይኾናሉ፡፡ በኣላህ ፍቃድ ነገ ደግሞ ማሕበረሰቡን የሚጠቅሙም ይኾናሉ፡፡ ፍልስፍናዎቻችንን በኢስላም ለመቃኘት የመጨረሻው መፍትሄ ደግሞ ኢስላምን ለማወቅ መጣር፣ ኢስላምን መመዘኛ ለማድረግ መሞከርና ኢስላምን መኖር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የኣቦይ ገበርሐና ዓይነት በኹሉም አደባባይ ፈራጅ ልኹን፣ በኹሉም አውጫጭኝ ልጣድ የሚል ከንቱ የኣዋቂነት ዲስኩር፤ ይበልጡኑ ኣላዋቂነትንና “ንፍጥ ለቅላቂነትን” ያሳብቃል፡፡

[ተረቱ ይመስላቸዋልን?]

ሰውዬው የዶሮ ስጋ አማረውና ከዶሮ ገበያ ዶሮ ለመግዛት ወጣ ይባላል፡፡ ከዚያም ዶሮዋን ከቤቱ ጓሮ ሊያርዳት እየተሰናዳ እያለ ድንገት ከእጁ አፈትልካ አመለጠች፡፡ ዶሮዋን ለመያዝ አባራራት…አባረራት…የሰፍር ሕጻናትም አብረውት ረዥም መንገድ ዶሮዋን ለመያዝ ቢዳክሩም፣ ዶሮዋን ይበልጥኑ ፍጥነቷ እየጨመረች ከዓይናቸው ርቃ ሔደች፡፡ በስተመጨረሻም ሰውዬ ለልጆቹ “ ልጆች ተዋት ትሂድ አትድከሙ…ሥጋዋ እንደማይጣፍጥ መጀመሪያ ስገዛትም ታውቆኝ ነበር” አላቸው ይባል፡፡ ኢስላምን መመር የተሳናቸው ግን ለትችት ጉልበታቸው ኹሌም ብርቱ የኾኑ ወጣቶች የዚህ ሰውዬ ኣምሳያዎች ናቸው፡፡

الله الموفق

Shortlink http://q.gs/Eye2R