በመላእክት ማመን ክፍል ዘጠኝ በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
507 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት የስራ ድርሻቸው፡-
ረ/ በሰው ላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው፡-
1/ ሩሕ መንፋት፡-
አካል በሕይወት መቆየት የሚያስችለው በውስጡ ሩሕ ‹መንፈስ› ሲኖር ነው፡፡ ያለ ሩሕ ህይወት የለም፡፡ አላህ የአካላችንም የሩሐችንም ፈጣሪና አምላክ ነው፡፡ ይህቺ ሩሕ መልክና ይዘቷ ምን እንደምትመስል ከፈጠራት አላህ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الرُّوحِ قُلِ الرُّوحُ مِنْ أَمْرِ رَبِّي وَمَا أُوتِيتُمْ مِنَ الْعِلْمِ إِلَّا قَلِيلًا ” سورة الإسراء 85
“ከሩሕም ይጠይቁሃል፤ ሩሕ ከጌታዬ ነገር ነው (እሱ በዕውቀቱ የተለየበት ነው) ከዕውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም፤ በላቸው።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡85)፡፡
ይህ ሩሕ በአካላችን ላይ የሚገባው ገና በእናታችን ማኅፀን ጽንስ እያለን ነው፡፡ ይህን ስራ በአላህ የበላይ ተቆጣጣሪነትና ፈጻሚነት እንዲያከናውን አንድ መልአክ ይላክና በማኅፀኑ ውስጥ በሚገኘው ጽንስ ላይ ይነፋዋል፡፡ ቀጣዩ ሐዲሥም ይህንን ያረጋግጣል፡-
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ ابن مسعود قَالَ حَدَّثَنَا رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- وَهُوَ الصَّادِقُ الْمَصْدُوقُ « إِنَّ أَحَدَكُمْ يُجْمَعُ خَلْقُهُ فِى بَطْنِ أُمِّهِ أَرْبَعِينَ يَوْمًا ثُمَّ يَكُونُ فِى ذَلِكَ عَلَقَةً مِثْلَ ذَلِكَ ثُمَّ يَكُونُ فِى ذَلِكَ مُضْغَةً مِثْلَ ذَلِكَ ثُمَّ يُرْسَلُ الْمَلَكُ فَيَنْفُخُ فِيهِ الرُّوحَ وَيُؤْمَرُ بِأَرْبَعِ كَلِمَاتٍ بِكَتْبِ رِزْقِهِ وَأَجَلِهِ وَعَمَلِهِ وَشَقِىٌّ أَوْ سَعِيدٌ…». أخرجه البخاري ومسلم.
ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- በንግግራቸውም ሆነ በተግባራቸው ፍጹም እውነተኛ፡ በሰዎችም ዘንድ ታማኝ የሆኑት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ ‹‹እያንዳንዳችሁ በናቱ ሆድ ውስጥ ለአርባ ቀናት ያክል የፍትወት ጠብታ ሆኖ ይቆያል፡፡ ከዛም በዚሁ አምሳያ የረጋ ደም ይሆናል፡፡ ከዛም በዚሁ አምሳያ የሚላመጥ የሆነ ቁራጭ ስጋ ይሆናል፡፡ ከዛም ወደዚህ ማኅጸን መልአክ ይላክና ሩሕ ይነፋበታል፡፡ አራት ነገራትንም እንዲጽፍ (እንዲወስን) ይታዘዛል፡፡ ሲሳዩን፣ ዕድሜውን፣ ስራውንና ዕድለኛ (የጀነት ሰው) ወይስ ዕድለ-ቢስ (የጀሀነም ሰው) መሆኑን..›› (ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት)፡፡
2/ ጠባቂያን፡-
መላእክትን ጨምሮ ፍጡራንን በአጠቃላይ በኃይሉና በጥበቡ የሚጠብቀው አላህ ብቻ ነው፡፡ ከአላህ ሌላ እውነተኛ ጠባቂ የለም፡፡ እርሱ ከጠባቂዎች ሁሉ መልካምና የተሻለ ጠባቂ ነው፡-
” قَالَ هَلْ آمَنُكُمْ عَلَيْهِ إِلَّا كَمَا أَمِنْتُكُمْ عَلَى أَخِيهِ مِنْ قَبْلُ فَاللَّهُ خَيْرٌ حَافِظًا وَهُوَ أَرْحَمُ الرَّاحِمِينَ ” سورة يوسف 64
“ከአሁን በፊት በወንድሙ ላይ እንዳመንኳችሁ እንጅ በርሱ ላይ አምናችኋለሁን? አላህም #በጠባቂነት (ከሁሉ) የበለጠ ነው፤ እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው፤ አላቸው።” (ሱረቱ ዩሱፍ 12፡64)፡፡
እሱ ጌታችን አላህ እኛን በቅጣት ከፈለግን፡ ከቅጣቱ ሊያተርፈን የሚችል ሌላ ጠባቂ የለንም፡፡
” قُلْ مَنْ يَكْلَؤُكُمْ بِاللَّيْلِ وَالنَّهَارِ مِنَ الرَّحْمَنِ بَلْ هُمْ عَنْ ذِكْرِ رَبِّهِمْ مُعْرِضُونَ ” سورة الأنبياء 42
“ከአልረሕማን (ቅጣት) በሌሊትና በቀን #የሚጠብቃችሁ ማነው? በላቸው፤ በውነቱ እነሱ ከጌታቸው ግሣጼ (ከቁርአን) ዘንጊዎች ናቸው።” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡42)፡፡
እውነታው ይህ ከሆነ: መላእክት ‹ጠባቂ› ሆነው ተመድበዋል ስንል፡ አላህ ባዘዛቸው መሰረት ሰበብ በመሆን ሰውን በንቃተ-ህሊናውም ሆነ በመኝታው፣ በመኖሪያ ሰፈሩም ሆነ በጉዞ ወቅት፣ በሰላሙም ጊዜ ሆነ በጦርነት ጊዜ እንዲጠብቁት የተመደቡ አልሉ ማለታችን ነው፡፡ እነሱ ይጠብቁናል ብለን ግን መመካታችንና ተስፋችን ከአላህ ወደነሱ ለአፍታ እንኳ ዞር ሊል አይገባውም፡፡ ይህ በአላህ ማጋራት ‹ሺርክ› ነውና፡፡ ወይንም እነሱን እንዲጠብቁን አንማጸናቸውም፡፡ አላህ እኛን ጉዳት እንዲነካን ፈቃዱ ከሆነ እነሱ ዘወር ከማለት ውጪ ምንም ሊያደርጉ አይችሉምና፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” لَهُ مُعَقِّبَاتٌ مِنْ بَيْنِ يَدَيْهِ وَمِنْ خَلْفِهِ يَحْفَظُونَهُ مِنْ أَمْرِ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ لَا يُغَيِّرُ مَا بِقَوْمٍ حَتَّى يُغَيِّرُوا مَا بِأَنْفُسِهِمْ وَإِذَا أَرَادَ اللَّهُ بِقَوْمٍ سُوءًا فَلَا مَرَدَّ لَهُ وَمَا لَهُمْ مِنْ دُونِهِ مِنْ وَالٍ ” سورة الرعد 11
“ለርሱ (ለሰው)፥ ከስተፊቱም ከኋላውም፥ በአላህ ትእዛዝ (ከክፉ) የሚጠብቁት ተተካኪዎች (መላእክት) አልሉት፤ አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ፥ በነፍሶቻቸው ያለውን (ሁኔታ) እስከሚልውጡ ድረስ አይለውጥም፤ አላህምበሰዎች ላይ ክፉን በሻ ጊዜ ለርሱ መመለስ የለውም፤ ለነርሱም ከርሱ ሌላ : ምንም #ተከላካይ የላቸውም።” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡11)፡፡
” وَهُوَ الْقَاهِرُ فَوْقَ عِبَادِهِ وَيُرْسِلُ عَلَيْكُمْ حَفَظَةً حَتَّى إِذَا جَاءَ أَحَدَكُمُ الْمَوْتُ تَوَفَّتْهُ رُسُلُنَا وَهُمْ لَا يُفَرِّطُونَ ” سورة الأنعام 61
“እርሱም ከባሮቹ በላይ ሲኾን ሁሉን አሸነፊ ነው፡፡ በናንተም ላይ ጠባቂዎችን (መላእክት) ይልካል፡፡ አንዳችሁንም ሞት በመጣበት ጊዜ (የሞት) መልእክተኞቻችን እነርሱ (ትእዛዛትን) የማያጓድሉ ሲኾኑ ይገድሉታል፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡61)፡፡
” إِنْ كُلُّ نَفْسٍ لَمَّا عَلَيْهَا حَافِظٌ ” سورة الطارق 4
“ነፍስ ሁሉ በርሷ ላይ ጠባቂ ያለባት እንጅ ሌላ አይደለችም።” (ሱረቱ-ጣሪቅ 86፡4)፡፡
እነዚህ ጠባቂ መላእክት ‹‹አል-ሙተዐቂቡን›› (ተተካኪዎች) በመባልም ይታወቃሉ ወላሁ አዕለም፡፡ በቀኑና በለሊቱ ክፍል ስለሚቀያየሩ፡፡ ቀጣዩ ሐዲሥ ይህን ያብራራል፡-
عَنْ أَبِى هُرَيْرَةَ أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- قَالَ « يَتَعَاقَبُونَ فِيكُمْ مَلاَئِكَةٌ بِاللَّيْلِ وَمَلاَئِكَةٌ بِالنَّهَارِ وَيَجْتَمِعُونَ فِى صَلاَةِ الْفَجْرِ وَصَلاَةِ الْعَصْرِ ثُمَّ يَعْرُجُ الَّذِينَ بَاتُوا فِيكُمْ فَيَسْأَلُهُمْ رَبُّهُمْ وَهُوَ أَعْلَمُ بِهِمْ كَيْفَ تَرَكْتُمْ عِبَادِى فَيَقُولُونَ تَرَكْنَاهُمْ وَهُمْ يُصَلُّونَ وَأَتَيْنَاهُمْ وَهُمْ يُصَلُّونَ ». رواه البخاري ومسلم.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በለሊትና በቀን መላእክት በናንተ ላይ ይተካካሉ፡፡ በሶላተል ፈጅር እና ሶላቱል ዐስር ላይም ይገናኛሉ፡፡ ከናንተው ጋር ያደሩትም መላእክት ወደ ሰማይ ይወጣሉ፡፡ አላህም በባሮቹ ሁኔታ ከነሱ በላይ ዐዋቂ ሆኖ ሳለ፡- ‹‹ባሮቼን በምን ሁኔታ ላይ ትታችኋቸው መጣችሁ?›› በማለት ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም፡- መጀመሪያም ስንመጣ ሶላት ላይ (ዐሱር እየሰገዱ) አገኘናቸው፡፡ ትተናቸው ስንወጣም (ፈጅር) እየሰገዱ ነበር በማለት ይመልሳሉ” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ከዚህ ታላቅ ሐዲሥ የምንማረው ቁም ነገር፡-
ሀ/ ጠባቂ መላእክት በሰው ላይ መመደባቸውን፡፡
ለ/ እነዚህም መላእክት ለሁለት ተከፍለው በፈረቃ የሚሰሩ መሆኑን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ከፈጅር እስከ ዐሱር ሲሆን፡ ሁለተኞቹ ደግሞ ከዐሱር እስከ ፈጅር ለሊቱን ሙሉ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሐ/ እነዚህ መላእክት ወደ ሰማይ በሚወጡበት ጊዜ፡ አላህ ስለ ባሮቹ ጉዳይ ይጠይቃቸዋል፡፡ ጉዳዩን ከነሱ በላይ እያወቀው ማለት ነው፡፡ ዓላማውም ኢብኑ ሐጀር (ረሒመሁላህ) ፈትሑል-ባሪ ላይ እንደገለጹት፡- ሰውን ለመፍጠር የፈለገበትን ሚስጥር አሁን በተግባር እነሱን በማስመስከር ሊያሳያቸው ፈልጎ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አደምና ዝርያዎቹን እንደሚፈጥር ባሳወቃቸው ጊዜ፡- ‹‹ደምን የሚያፈስና ኃጢአትን በመስራት ምድርን የሚያበላሽ ታደርጋለህን?›› ብለው ሳለ፡ ጌታችን ደግሞ ‹‹እናንተ የማታውቁትን አውቃለሁ›› ብሎ ነግሯቸው ነበር (አል-በቀራህ 2፡30)፡፡ አሁን በተግባር እንዲህ አይነት መልካም ባሮች እንዳሉትና እነሱ እንዳሰቡት ደም አፍሳሽና በኃጢአት ላይ ብቻ ተመላላሽ እንዳልሆኑ በማሳየትና በማስመስከር ጥበቡን ገለጠላቸው ማለት ነው ወላሁ አዕለም፡፡ (ፈትሑል-ባሪ 2/36)፡፡
ይቀጥላል