በመላእክት ማመን ክፍል አንድ በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
494 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
1/ በመላእክት የማመን ደረጃው፡-
በመላእክት ማመን ከስድስቱ የእምነት ማእዘናት (አርካኑል ኢማን) ውስጥ አንድ ማእዘን ነው፡፡ የአንድ ሙስሊም እምነት በዚህ እስካላመነ ድረስ እምነቱ ሙሉ እና ቅቡል መሆን አይችልም፡፡
በመላእክት ማመን በገይብ (ከስሜት ህዋስ በራቀ ነገር) ማመን የሚባለው የእምነት ዘርፍ ውስጥ ይካተታል፡፡ በአይነ ስጋችን በዚህ ምድር ላይ በተፈጥሮአዊ ማንነታቸውና ቅርጻቸው ልናያቸው አንችልምና፡፡ ለነቢያት ግን ሊታዩ ይችላሉ፡፡
አላህ ይህንን አስመልክቶ በመላእክት ማመን እንደሚገባን በቃሉ በቁርኣን ላይ በሰፊው ነግሮናል፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በሐዲሣቸው ላይ አስተምረውናል፡፡ ከቁርኣን አንቀጾች ውስጥ ከፊሉ ይህንን ይመስላል፡-
” لَيْسَ الْبِرَّ أَنْ تُوَلُّوا وُجُوهَكُمْ قِبَلَ الْمَشْرِقِ وَالْمَغْرِبِ وَلَكِنَّ الْبِرَّ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَالْمَلَائِكَةِ وَالْكِتَابِ وَالنَّبِيِّينَ…” سورة البقرة 177
“መልካም ሥራ ፊቶቻችሁን ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም፡፡ ግን መልካም ሥራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነቢያትም፣ ያመነ ሰው ነው…” (ሱረቱል በቀራህ 2፡177)፡፡
” آمَنَ الرَّسُولُ بِمَا أُنْزِلَ إِلَيْهِ مِنْ رَبِّهِ وَالْمُؤْمِنُونَ كُلٌّ آمَنَ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِنْ رُسُلِهِ وَقَالُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا غُفْرَانَكَ رَبَّنَا وَإِلَيْكَ الْمَصِيرُ” سورة البقرة 285
“መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡:” (ሱረቱል በቀራህ 2፡285)፡፡
በነዚህ አንቀጾች መሰረት ‹‹በመላእክት›› ማመን ከእምነት ማእዘናት ውስጥ አንዱ መሆኑን ነው የምንረዳው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በመቆም በመላእክት መኖር አላምንም የሚል ወይንም እነሱን እንደ ጠላት የሚመለከት ሰው፡ እጣ ፈንታው ከእምነት አጥር የወጣ ከሀዲ (ካፊር) መሆን ብቻ ነው፡፡ አላህ በመላእክት የካዱትን ከሀዲያን (ካፊሩን/ኩፋር) ብሎ ሰይሟቸዋልና፡፡ ማስረጃውም ቀጥሎ ያለው የአላህ ቃል ነው፡-
” مَنْ كَانَ عَدُوًّا لِلَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَرُسُلِهِ وَجِبْرِيلَ وَمِيكَالَ فَإِنَّ اللَّهَ عَدُوٌّ لِلْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 98
“ለአላህና ለመላእክቱ ለመልክተኞቹም ለጂብሪልም ለሚካልም (ሚካኢል) ጠላት የኾነ ሰው አላህ ለ(እነዚህ) ከሓዲዎች ጠላት ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 98)፡፡
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ለመላእክቱ ጠላት የሆነ ሰው ከከሀዲዎች ጎራ መመደቡን መረዳት ይቻላል፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا آمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي نَزَّلَ عَلَى رَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي أَنْزَلَ مِنْ قَبْلُ وَمَنْ يَكْفُرْ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا بَعِيدًا ” سورة النساء 136
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ፣ እመኑ፤ በአላህና በመላክቱም፣ በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም፣ በመጨረሻውም ቀን የካደ ሰው፣ (ከሰውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 136)፡፡
በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሐዲሥ ላይም ይህንኑ እውነታ እናገኛለን፡፡ ዑመር ኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን፡- የአላህ መልክተኛ ዘንድ ተቀምጠው ሳለ፡ ከዚህ በፊት የማያውቁት አንድ ሰው ብቅ አለባቸው፡፡ ልብሱ እጅግ የነጻና ጸጉሩ የጠቆረ፡ የመንገደኝነት ምልክት የማይታይበት ሰው ነበር፡፡ ወደ አላህ መልክተኛ ዘንድ በመጠጋት ከፊታቸው ከተቀመጠ በኋላ ስለ ኢማን ምንነት ንገረኝ ብሎ ጠይቋቸዋል፡፡ እሳቸውም ኢማን ማለት ምን እንደሆነ ሲዘረዝሩለት ስድስቱን የእምነት ማእዘናት ጠቅሰዋል፡፡ ከነዛ ውስጥ አንዱ ‹‹በመላእክት ማመን›› የሚለው ነበር፡፤ (ሙስሊም የዘገበው)፡፡
በዚህም ሰበብ በመላእክት ማመን ከአንድ ሙስሊም የሚጠበቅ ዋና የእምነት ዘርፍ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው፡- በመላእክት ማመን ሲባል ምን ማለት ነው? የምናምነውስ እንዴት ነው? የሚለው ይሆናል፡፡
በተከታታይ ፕሮግራማችን እነዚህን ነጥቦች በአላህ ፈቃድ እንዳስሳቸዋለን ኢንሻአላህ፡፡