በመላእክት ማመን ክፍል አስር በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
333 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት የስራ ድርሻቸው፡-
ረ/ በሰው ላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው፡-
3/ መዝጋቢዎች፡-
ማንኛውም ከሰው የሚገኘውን፡ የነጻ ፈቃድ ውጤት የሆነውን ንግግርም ሆነ ተግባር፡ መልካምም ሆነ ክፉ የሚመዘግቡ መላእክት በእያንዳንዱ ሰው ላይ ተመድበዋል፡፡ እነዚህ መላእክት ክቡራን መላእክት ናቸው፡፡ ሰው ያልሰራውንና ያልተናገረውን በመጨመር፣ ወይንም የሰራውንና የተናገረውን በመቀነስ የሚያጎድሉ አይደሉም፡፡ እኛንም እነሱንም ተቆጣጣሪ የሆነውን አምላክ አላህን ይፈራሉና፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” كَلَّا بَلْ تُكَذِّبُونَ بِالدِّينِ * وَإِنَّ عَلَيْكُمْ لَحَافِظِينَ * كِرَامًا كَاتِبِينَ * يَعْلَمُونَ مَا تَفْعَلُونَ ” سورة الإنفطار 13-10
“ተከለከሉ፤ በውነቱ በፍርዱ ቀን ታስተባብላላችሁ። በናንተ ላይ ተጠባባቂዎች ያሉባችሁ፤ ስትሆኑ፤ የተከበሩ ጸሐፊዎች የሆኑ፤ (ተጠባባቂዎች)፤የምትሠሩትን ሁሉ የሚያውቁ” (ሱረቱል ኢንፊጣር 82፡10-13)፡፡
” وَلَقَدْ خَلَقْنَا الْإِنْسَانَ وَنَعْلَمُ مَا تُوَسْوِسُ بِهِ نَفْسُهُ وَنَحْنُ أَقْرَبُ إِلَيْهِ مِنْ حَبْلِ الْوَرِيدِ * إِذْ يَتَلَقَّى الْمُتَلَقِّيَانِ عَنِ الْيَمِينِ وَعَنِ الشِّمَالِ قَعِيدٌ * مَا يَلْفِظُ مِنْ قَوْلٍ إِلَّا لَدَيْهِ رَقِيبٌ عَتِيدٌ ” سورة ق 18-16
“የሰውን ልጅ የፈጠርነው እኛው ነን።ነፍሱ የምትጐተጉተውን (እንኳ ሳይቀር)ጠንቅቀን እናውቃለን።እኛ ለርሱ ከደም ጋን ጅማቱ ይበልጥ የቀረብን ነን፡፡ ሁለቱ ቃል ተቀባይ(መላእክት) በቀኙም በግራውም ተቀምጠው ቃሉን በሚቀበሉት ወቅት(የሚሆነውን አስታውስ)። ከቃል አንድንም አይናገርም ከርሱ ዘንድ(ቃሉን ለመመዝገብ)ዝግጁ የሆኑ መላእክት ያሉ ቢሆን እንጅ።” (ሱረቱ ቃፍ 50፡16-18)፡፡
ከዚያም የውሙል ቂያም (የትንሳኤው ዕለት) የስራ መዝገቡ ዝርዝር የተቀመጠበት መጽሐፍ ይሰጠውና፡ እንካ የስራህን ውጤት አንብብ! ዛሬ ተቆጣጣሪነት በራስህ ብቻ በቃ! ይባላል፡፡ (አላሁምመ የሚን ኪታበና ወየስሲር ሒሳበና)፡፡
” وَكُلَّ إِنْسَانٍ أَلْزَمْنَاهُ طَائِرَهُ فِي عُنُقِهِ وَنُخْرِجُ لَهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ كِتَابًا يَلْقَاهُ مَنْشُورًا * اقْرَأْ كِتَابَكَ كَفَى بِنَفْسِكَ الْيَوْمَ عَلَيْكَ حَسِيبًا ” سورة الإسراء 14-13
“ሰውንም ሁሉ በራሪውን (ሥራውን) በአንገቱ አስያዝነው፤ ለርሱም በትንሳኤ ቀን፣ የተዘረጋ ሆኖ የሚያገኘው የሆነን መጽሐፍ እናወጣለታለን። መጽሐፍህን አንብብ፤ ዛሬ ባንተ ላይ ተቆጣጣሪነት በነፍስህ በቃ (ይባላል)።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡13-14)፡፡
ሀ/ ስማቸው?
በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀውና እንደሚነገረው፡ እነዚህ ስራን መዝጋቢ የሆኑት ሁለት መላእክት ‹‹ዓቲድ›› እና ‹‹ረቂብ›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የነዚህ መላእክት ስም በቁርኣንም ሆነ በሐዲሥ አልመጣም አልተጠቀሰምም፡፡
በቁርኣኑ ላይ የተጠቀሰው ‹‹ረቂቡን ዓቲድ›› የሚለው የመላእክቱ ባሕሪ እንጂ የግል ስማቸው አይደለም፡፡ አንደኛው ‹ረቂብ› ሌላኛው ‹ዓቲድ› ይባላሉ ለማለት አይደለም፡፡ በዐረብኛው ቁርኣን ላይ ‹‹ረቂቡን ዓቲድ›› አለ እንጂ ‹‹ረቂቡን ወ ዓቲድ›› አለማለቱን በደንብ ያስተውሉ፡፡
‹ረቂብ› ማለት፡- ተቆጣጣሪና ነገሮችን የሚከታተል ማለት ሲሆን፡ ‹ዓቲድ› ማለት ደግሞ፡- ተመልካችና በስፍራው ተገኚ ማለት ነው፡፡ አዘለም አቀፈ ያው ተሸከመ ነው እንደሚባለው፡ ሁለቱም ቃላቶች መልእክታቸው፡- መላእክቱ ግለሰቡን የሚቆጣጠሩትና የሚከታተሉት፡ እንዲሁም ስራውን በአጠገቡ ሆነው የሚመለከቱ ማለት ነው ወላሁ አዕለም፡፡
በጉዳዩ ላይ ዋና ዋና (ሙዕተመድ) የሆኑ የተፍሲር ሊቃውንትን ሀሳብ ብትመለከቱ፡ ‹ረቂብ› እና ‹ዓቲድ› የሚለውን ለመላእክቱ መገለጫ ባሕሪ አድርገው እንጂ የግል መጠሪያ ስም አድርገው አላቀረቡትም (አልፈሰሩትም)፡፡ (ኢብኑ ጀሪር አጥ-ጠበሪይ፣ ኢማሙል በገዊይ፣ ኢማሙል ቁርጡቢይ፣ አል-ሓፊዝ ኢብኑ ከሢር፣ መሕሙድ ሹክሪ አሉሲይ (ሩሑል መዓኒይ)፣ አድዋኡል በያን (ሺንቂጢይ) እና ሌሎችም)፡፡
ለ/ አስፈላጊነቱ፡-
አላህ ሁሉን ነገር አስቀድሞ ከመከሰቱ በፊት በመለኮታዊ ዕውቀቱ ያውቀዋል፡፡ ማወቅም ብቻ አይደለም በለውሐል መሕፉዝ (በተጠበቀው ሰሌዳ) ላይ ተጽፎ እንዲቀመጥ ሰማይና ምድርን ከመፍጠሩ ከሀምሳ ሺህ ዓመት በፊት ቀድሞ ወስኖታል፡፡ ታዲያ መላእክት የኛን ስራ እንደ አዲስ መመዝገባቸውና መጻፋቸው ምን ጥበብ ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ምላሹም፡-
የአላህን ፍጹም ፍትሀዊነት በተግባር ለማሳየትና፡ ሰዎች ለጥፋታቸው ማመካኛ የሚሆን ምንም አይነት ሰበብ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ነው፡፡ በአንድ ነቢያዊ ሐዲሥ ላይ እንደተገለጸው፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “እንደ አላህ እሱ ዘንድ ምክንያት (ማስረጃ) የተወደደ ማንም የለም፡፡ ስለሆነም አላህ ነቢያትን በጀነት አብሳሪዎችና በጀሀነም አስጠንቃቂዎች አድርጎ ላከ፡፡ መለኮታዊ መጽሐፍትንም አወረደ” (ቡኻሪይ 7416፣ ሙስሊም 7170)፡፡
አላህ ከባሮቹ ተጨባጭ የሆነ ምክንያትን (ዑዝርን) ይወዳል፡፡ ስለሆነም በባሪያዎቹ ላይ ነቢያትና መልክተኞችን በመላክ፡ መለኮታዊ መጽሐፍቱን በማውረድ ማስረጃውን አቆመባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች ለሚሰሩት ጥፋት ነገ አላህ ዘንድ ላለመጠየቅ ምክንያት አይኖራቸውም ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ መላእክት ከኛ ጋር በመሆን የሰራነውን መዝግበው ነጌ ደግሞ የስራችንን ዋጋ ‹‹መጽሐፍህን አንብብ፤ ዛሬ ባንተ ላይ ተቆጣጣሪነት በነፍስህ በቃ›› ስንባል፡ የአላህ ፍጹም ፍትሐዊነት በተግባር ይገለጻል ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ፣ መላእክቱ፣ የሰውነት አካላቶቻችን ሁሉ በኛ ላይ ይመሰክራሉ ወይንም ይመሰክሩብናል፡፡ (ኪታብ፡- ሙዕተቀዱ ፊረቁል ሙስሊሚነ ወል-የሁደ ወን-ነሳራ፣ ወል-ፈላሲፈቱ ወል-ወሠኒዪን፣ ፊል-መላኢከቲል ሙቀረቢን፡ ዶክተር ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱል-ወሃብ አል-ዐቂል የመዲና ኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ መምህር ገጽ 167-168)፡፡
ከዚህ ውጪ የነቢያት ትምህርት ያልደረሰው ሰው ቀጥታ ለቅጣት እንደማይዳረግ አላህ በቃሉ እንዲህ ይነግረናል፡-
” مَنِ اهْتَدَى فَإِنَّمَا يَهْتَدِي لِنَفْسِهِ وَمَنْ ضَلَّ فَإِنَّمَا يَضِلُّ عَلَيْهَا وَلَا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَى وَمَا كُنَّا مُعَذِّبِينَ حَتَّى نَبْعَثَ رَسُولًا ” سورة الإسراء 15
“የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፤ የተሳሳተም ሰው፣ የሚሳሳተው (ጉዳቱ) በርሷ ላይ ነው፤ ተሸካሚም (ነፍስ፣) የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም፤ መልክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡15)፡፡
ይቀጥላል