በመላእክት ማመን ክፍል አስራ አንድ በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
363 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት የስራ ድርሻቸው፡-
ረ/ በሰው ላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው፡-
4/ ሩሕን መውሰድ፡-
አላህ ሰውን በዚህ ምድር ላይ በመፍጠር፡ ህያው አድራጊ ጌታና አምላክ እንደሆነ ሁሉ፡ እንዲሁም የሚገድልና ህይወትን የሚወስድ እሱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ስልጣኑ ማንም አይጋራውም፡፡ በህይወትና በሞት ላይ ከሱ ውጪ ማንም ስልጣን የለውም፡፡ አላህ ህያው ያደረጋትን ነፍስ ለመግደል የሚችል፡ አላህ ሞት የወሰነባትን ነፍስ ህይወት መለገስ የሚችል አንድም ፍጡር የለም፡፡ ይኖራል ብሎ ማመን፡ በአላህ ጌትነት ላይ ማጋራት ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” إِنَّ اللَّهَ لَهُ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ يُحْيِي وَيُمِيتُ وَمَا لَكُمْ مِنْ دُونِ اللَّهِ مِنْ وَلِيٍّ وَلَا نَصِيرٍ ” سورة التوبة 116
“አላህ የሰማያትና የምድር ንግሥና የርሱ ብቻ ነው፤ ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፤ ለናንተም ከርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡116)፡፡
” كَيْفَ تَكْفُرُونَ بِاللَّهِ وَكُنْتُمْ أَمْوَاتًا فَأَحْيَاكُمْ ثُمَّ يُمِيتُكُمْ ثُمَّ يُحْيِيكُمْ ثُمَّ إِلَيْهِ تُرْجَعُونَ ” سورة البقرة 28
“ሙታን የነበራችሁ ስትኾኑ ሕያው ያደረጋችሁ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ሕያው የሚያደርጋችሁ ሲኾን ከዚያም ወደርሱ የምትመለሱ ስትኾኑ በአላህ እንዴት ትክዳለችሁ!” (ሱረቱል በቀራህ 2፡28)፡፡
” وَاللَّهُ خَلَقَكُمْ ثُمَّ يَتَوَفَّاكُمْ وَمِنْكُمْ مَنْ يُرَدُّ إِلَى أَرْذَلِ الْعُمُرِ لِكَيْ لَا يَعْلَمَ بَعْدَ عِلْمٍ شَيْئًا إِنَّ اللَّهَ عَلِيمٌ قَدِيرٌ” سورة النحل 70
“አላህም ፈጠራችሁ፤ ከዚያም ይገድላችኋል፤ ከናንተም ከዕውቀት በኋላ ምንንም ነገር እንዳያውቅ ወደ ወራዳ ዕድሜ የሚመለስ ሰው አልለ፤ አላህ ዐዋቂ ቻይ ነው።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡70)፡፡
በነዚህና መሰል አንቀጾች መሰረት፡ በህይወታችን ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው (በመፍጠርም ሆነ በመግደል) አላህ ብቻ ነው ብለን እናምናለን፡፡
ጌታ አላህ ይህንን ተግባር ደግሞ በሚፈልገው መልኩ ማከናወን ይችላል፡፡ ሲፈልግ በመለኮታዊ ቃሉ አማካኝነት ‹‹ሁን!›› በማለት ያደርጋል፡፡ ሲፈልግ መልአክን በመላክ የሚሻውን ይፈጽማል፡፡ ይህን ለምን እንዲህ አደረገ? የሚል ጠያቂ የለበትም (አል-አንቢያእ 21፡23)፡፡
ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ፡ የአላህ የበላይ ተቆጣጣሪነትና ዋና ፈጻሚነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡ ምድራዊ ቆይታችን ሲጠናቀቅና ሲያበቃ የሰዎችን ሩሕ ከአካላቸው በማውጣት እንዲወስድ ኃላፊነት የተጣለበት መልአክ አለ፡፡ ይህ መልአክ ‹‹መለኩል መውት›› (መልአከ ሞት) በሚል ስሙ ይታወቃል፡፡ ይህ መልአክ (የአላህ ሰላም በሱ ላይ ይሁን) የሚፈጽመው የጌታውን ትእዛዝ ነው፡፡ አላህ አድርግ ያለውን ነው የሚያደርገው፡፡ ከትእዛዙ ፍንክች አይልም፡፡ እኛም በዚህ ተግባሩ ልንወደው እንጂ ልንጠላው አይገባም፡፡ ከቤተሰብ ውስጥ አንዱን በመነጠል ሩሑን ይዞ ቢወጣ፡ አላህ ስላዘዘው እንጂ፡ እሱ በዛ ቤተሰብ ላይ ክፋትን አስቦ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለዚህ መልአክ የተሳሳተ አመለካካት ሊኖረን አይገባም፡፡ የሱን ስራ በተመለከተ ጌታ አላህ በቃሉ እንዲህ ይላል፡-
” وَقَالُوا أَإِذَا ضَلَلْنَا فِي الْأَرْضِ أَإِنَّا لَفِي خَلْقٍ جَدِيدٍ بَلْ هُمْ بِلِقَاءِ رَبِّهِمْ كَافِرُونَ * قُلْ يَتَوَفَّاكُمْ مَلَكُ الْمَوْتِ الَّذِي وُكِّلَ بِكُمْ ثُمَّ إِلَى رَبِّكُمْ تُرْجَعُونَ ” سورة السجدة 11-10
“በምድርም ውስጥ (በስብሰን) በጠፋን ጊዜ፣ እኛ በአዲስ መፈጠር ውስጥ እንኾናለን? አሉ በውነቱ ነርሱ በጌታቸው መገናኘት ከሐዲዎች ናቸው። ፦ በእናንተ የተወከለው #መልአከ_ሞት ይገድላችሗል፤ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ፣ በላቸው።” (ሱረቱ-ሰጅዳህ 32፡10-11)፡፡
በዚህ ሩሕን የመውሰድ ስራ ላይ መለኩል መውት (ዐለይሂ-ሰላም) ዋናው ተጠቃሽ ይሁን እንጂ፡ በሱ ስር ሆነው ይህንኑ ተግባር የሚያከናውኑ ሌሎች መልአኮችም አሉ፡፡ አላህም በቃሉ እንዲህ ይጠቅሳቸዋል፡-
” وَهُوَ الْقَاهِرُ فَوْقَ عِبَادِهِ وَيُرْسِلُ عَلَيْكُمْ حَفَظَةً حَتَّى إِذَا جَاءَ أَحَدَكُمُ الْمَوْتُ تَوَفَّتْهُ رُسُلُنَا وَهُمْ لَا يُفَرِّطُونَ ” سورة الأنعام 61
“እርሱም ከባሮቹ በላይ ሲኾን ሁሉን አሸነፊ ነው፡፡ በናንተም ላይ ጠባቂዎችን (መላእክት) ይልካል፡፡ አንዳችሁንም ሞት በመጣበት ጊዜ (የሞት) መልእክተኞቻችን እነርሱ (ትእዛዛትን) የማያጓድሉ ሲኾኑ ይገድሉታል፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡61)፡፡
” فَمَنْ أَظْلَمُ مِمَّنِ افْتَرَى عَلَى اللَّهِ كَذِبًا أَوْ كَذَّبَ بِآيَاتِهِ أُولَئِكَ يَنَالُهُمْ نَصِيبُهُمْ مِنَ الْكِتَابِ حَتَّى إِذَا جَاءَتْهُمْ رُسُلُنَا يَتَوَفَّوْنَهُمْ قَالُوا أَيْنَ مَا كُنْتُمْ تَدْعُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ قَالُوا ضَلُّوا عَنَّا وَشَهِدُوا عَلَى أَنْفُسِهِمْ أَنَّهُمْ كَانُوا كَافِرِينَ ” سورة الأعراف 37
“በአላህ ላይ ውሸትን ከቀጠፈ ወይም በአንቀጾቹ ከአስዋሸ ሰው ይበልጥ በዳይ ማን ነው? እነዚያ (ከተጻፈላቸው) ከመጽሐፉ ውስጥ ሲኾን ዕድላቸው ያገኛቸዋል፤ (የሞት) መልክተኞቻችንም የሚገድሏቸው ሆነው በመጡባቸው ጊዜ፣ ከአላህ ሌላ ትግገዟቸው የነበራችሁት የት አሉ? ይሏቸዋል፤ ከኛ ተሰወሩን ይላሉ፤ እነርሱም ከሃዲያን እንደነበሩ በነፍሶቻቸው ላይ ይመሰክራሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡37)፡፡
እነዚህ መልአኮች በጥቅሉ ለሁለት ይከፈላሉ፡፡ ‹‹አን-ናዚዓት›› እና ‹‹አን-ናሺጣት›› በመባል፡፡
‹‹አን-ናዚዓት›› በመባል የሚታወቁት መላእክት፡- የከሀዲያንን ሩሕ በኃልና በማስጨነቅ እንዲሁም በቅጣት መንጭቀው የሚያወጡት ሲሆኑ፡
‹‹አን-ናሺጣት›› በመባል የሚታወቁት መላእክት ደግሞ፡- የሙእሚኖችን ሩሕ በርህራሄና በስሱ የሚያወጡት ናቸው፡፡ (አላሁመ ሀውዊን ዐለይና ሰከራተል መውት)፡፡ የአላህ ቃል ስለነዚህ ሁለት ክፍሎች እንዲህ ይናገራል፡-
” وَالنَّازِعَاتِ غَرْقًا * وَالنَّاشِطَاتِ نَشْطًا ” سورة النازعات 2-1
“በኃይል አውጪዎች በሆኑት፤ በቀስታ መምዘዝንም መዛዦች በሆኑት፤ መላእክት እምላለሁ” (ሱረቱ-ናዚዓት 79፡1-2)፡፡
” الَّذِينَ تَتَوَفَّاهُمُ الْمَلَائِكَةُ طَيِّبِينَ يَقُولُونَ سَلَامٌ عَلَيْكُمُ ادْخُلُوا الْجَنَّةَ بِمَا كُنْتُمْ تَعْمَلُونَ ” سورة النحل 32
“እነዚያ በመልካም ሁኔታ ላይ ሆነው መላእክት ሰላም በናንተ ላይ እያሉ፣ የሚገድሏቸው ናቸው፤ ትሠሩት በነበራችሁት ሥራ ገነትን ግቡ፣ (ይባላሉ)።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡32)፡፡
” وَلَوْ تَرَى إِذْ يَتَوَفَّى الَّذِينَ كَفَرُوا الْمَلَائِكَةُ يَضْرِبُونَ وُجُوهَهُمْ وَأَدْبَارَهُمْ وَذُوقُوا عَذَابَ الْحَرِيقِ ” سورة الأنفال 50
“እነዚያንም የካዱትን መላእክት ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን እየመቱ የቃጠሎንም ስቃይ ቅመሱ (እያሉ) በሚገድሏቸው ጊዜ ብታይ ኖሮ ( አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር)።” (ሱረቱል አንፋል 8፡50)፡፡
ሌላው በተጨማሪ ማወቅ ያለብን ነገር፡ መለኩል መውት (ዐለይሂ-ሰላም) ‹‹ዐዝራኢል›› ተብሎ የሚጠራበት ስሙ ከቁርኣንም ሆነ ከሐዲሥ መረጃ እንደሌለው ነው፡፡ በመሆኑም ዐዝራኢል የሱ ስም ነው ወይም አይደለም ብለን ውሳኔ መስጠት አንችልም ማለት ነው፡፡ በቁርኣን ላይ በተጠቀሰው ስሙ ‹‹መለኩል መውት›› ብለን እንጠራዋለን ወላሁ አዕለም (አል-ቢዳየቱ ወን-ኒሃየህ 1/49፣ ፈይዱል ቀዲር 3/32፣ ፈታዋ ኢብኑ ዑሠይሚን 3/161)፡፡
ይቀጥላል