በመላእክት ማመን ክፍል አስራ አምስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
351 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
6/ ኢብሊስ ‹ዲያብሎስ›፡-
እስካሁን ባሳለፍናቸው አስራ አራት ተከታታይ ክፍሎች ስለ መላእክት በአምስት ነጥቦች ዙሪያ መጠነኛ ግንዛቤን እንደጨበጥን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እነዚህም አምስት ነጥቦች፡-
ሀ/ በመላእክት ማመን በኢስላም ውስጥ ያለው ደረጃ ምን እንደሆነና፡ የስድስቱ አርካኑል ኢማን አንድ ማእዘን፡ በመላእክት ማመን እንደሆነ፡ በነሱ የማያምን ሰው ሙስሊም እንደማይሰኝ ሲሆን፡-
ለ/ የመላእክት ተፈጥሮአዊ ማንነትን በተመለከተ ዘጠኝ ነጥቦችን አንስተን እንደ አብነት ተመልክተናል፡፡
ሐ/ የመላእክት ስነምግባራቸውን በተመለከተ እንዲሁ ሶስት ምሣሌዎችን አንስተን ተመልክተናል፡፡
መ/ ስማቸውን በተመለከተ፡ ወደ አምስት የጋራ መጠሪያ ስሞችን አይተናል፡፤
ሠ/ የስራ ድርሻቸውን በተመለከተ ደግሞ፡ እስካሁን ድረስ ስንማር ነበር፡፡ አብዝሀኛውን ክፍል የያዘውም ይኸኛው ክፍል ነው፡፡ ለዛሬ አላህ ፈቃዱ ከሆነ የምንነጋገረው፡ ኢብሊስ ‹‹መልአክ›› ነበር ወይስ አልነበረም? የሚለውን ነጥብ ነው፡፡
1/ ለግንዛቤ ያህል፡- ኢብሊስ ማለት የጂንኖች ሁሉ አባት የሆነ፡ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን አደምና ሐዋእን (ዐለይሂማ-ሰላም) ከጀነት እንዲወጡ ሰበብ የሆነ፡ የሰው ልጆች ሁሉ ቀንደኛ ጠላት የሆነ ‹‹ጃን›› በሚባለው ስሙም የሚታወቅ ከሀዲ ፍጡር ነው፡፡
ኢብሊስ ከክህደቱ በፊት፡ ከመላእክት ጋር በመሆን አላህን የሚገዛ መልካም የአላህ ባሪያ ነበር እንጂ፡ በፍጥረታዊ ማንነቱ መልአክ አልነበረም! የሚለው የዑለማዎች አቋም ጠንካራና በማስረጃ የተደገፈ ነው፡፡ ጉዳዩ በዑለማዎች መካከል የሀሳብ ልዩነት (ኺላፍ) ቢንጸባረቅበትም፡ የሀሳብ ልዩነቱ ተጨማሪ ዕውቀት ከመሆን በዘለለ፡ በእምነት ጉዳይ ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ተቃራኒውን አቋም የያዘም አካል ተሳስቷል ከማለት ውጪ ሊወገዝ የሚችልበት መሰረታዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሆኖም ኢብሊስ ከመነሻውም መልአክ አልነበረም የሚለውን ረእይ በላጭ ሆኖ ስላገኘነው እሱን እናካፍላችሁ፡፡ እነዚህን ማስረጃዎች በመጠኑ እንመለከታቸዋለን፡-
ሀ/ ከእሳት የተፈጠረ መሆኑ፡-
ኢብሊስ የተፈጠረው ከእሳት ነበልባል ነው፡፡ መላእክት ደግሞ የተፈጠሩት ከኑር ‹ብርሀን› ነው፡፡ በዚህ ፍጥረታዊ ማንነቱ ከነሱ መለየቱ መልአክ ላለመሆኑ አንዱ ማስረጃችን ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” قَالَ مَا مَنَعَكَ أَلَّا تَسْجُدَ إِذْ أَمَرْتُكَ قَالَ أَنَا خَيْرٌ مِنْهُ خَلَقْتَنِي مِنْ نَارٍ وَخَلَقْتَهُ مِنْ طِينٍ ” سورة الأعراف 12
“(አላህ) ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? አለው፤ እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ፤ ከእሳት ፈጠርከኝ፤ እሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡12)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሰረት፡ ኢብሊስ ከእሳት እንደተፈጠረ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ አባቶቻችን ከዚህ በፊት ሲናገሩ አንድ የሰማሁት ነገር ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ይኖራል ብዬ ባልገምትም ላቅርበው፡- ጌታ አላህ ኢብሊስን፡ ለአደም ስገድ በተባለ ጊዜ ከመስገድ ያገደው ምን እንደሆነ ሲጠይቀው፡ ኢብሊስም ‹‹እኔ ከሱ እበልጣለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔን ከኑር ፈጠርከኝ እላለሁ ብሎ ተሳሳተና ከናር ‹እሳት› ፈጠርከኝ፡ እሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው›› ብሎ መለሰ፡፡ በዛውም ጌታ አላህ ‹‹በል ከናር አትውጣ ብሎ ከራሕመቱ አባረረው›› የሚል ነው፡፡
ይህ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢብሊስ ከእሳት መፈጠሩን ከራሱ ምስክርነት ብቻ ሳይሆን፡ ከጌታችንም ቃል ከነቢያችንም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሐዲሥ በግልጽ መረዳት እንችላለንና፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَخَلَقَ الْجَانَّ مِنْ مَارِجٍ مِنْ نَارٍ ” سورة الرحمن 15
“ጃንንም (የጂንኖች አባት) ከእሳት ከሆነ ነበልባል ፈጠርነው።” (ሱረቱ-ራሕማን 55፡15)፡፡
عَنْ عَائِشَةَ قَالَتْ قَالَ رَسُول اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- :« خُلِقَتِ الْمَلاَئِكَةُ مِنْ نُورٍ وَخُلِقَ الْجَانُّ مِنْ مَارِجٍ مِنْ نَارٍ وَخُلِقَ آدَمُ مِمَّا وُصِفَ لَكُمْ ». رَوَاهُ مُسْلِمٌ
የምእመናን እናት፡ እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንደነገረችን፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “መላእክት ከብርሀን ተፈጠሩ፡፡ ጃን (የጂንኖች አባት ኢብሊስ) ከእሳት ነበልባል ተፈጠረ፡፡ አደም ለናንተ (በቁርኣን) እንደተነገራችሁ (ከአፈር) ተፈጠረ” (ሙስሊም 2996)፡፡

ለ/ ጎሳው ከጂንኖች መሆኑ፡-
አምላካችን አላህ በቃሉ እንደነገረን፡ የኢብሊስ ጎሳ ከጂንኖች እንጂ ከመላእክት እንዳልሆነ ነው፡፡ ይህም እሱ መልአክ እንዳልነበር የሚያስረዳ ነው፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ كَانَ مِنَ الْجِنِّ…” سورة الكهف 50
“ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ (የሆነውን አስታውስ)። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፤ ከጋኔን (ጎሳ) ነበር…” (ሱረቱል ከህፍ 18፡50)፡፡

ሐ/ ዝርያዎች አሉት፡-
በአላህ ቃል ውስጥ እንደተነገረን ኢብሊስ ዝርያዎች አሉት፡፡ በዓለሙ ያሰማራቸው ጂንኒዎች (ሰይጣናት) የሱ ዝርያዎች ናቸው፡፡ እነሱንም ወዳጅና ረዳት አድርገን እንዳንከተል አላህ አስጠንቅቆናል፡፡ እንዲህ ይላል የአላህ ቃል፡-
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ كَانَ مِنَ الْجِنِّ فَفَسَقَ عَنْ أَمْرِ رَبِّهِ أَفَتَتَّخِذُونَهُ وَذُرِّيَّتَهُ أَوْلِيَاءَ مِنْ دُونِي وَهُمْ لَكُمْ عَدُوٌّ بِئْسَ لِلظَّالِمِينَ بَدَلًا ” سورة الكهف 50
“ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ (የሆነውን አስታውስ)። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፤ ከጋኔን (ጎሳ) ነበር፤ ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ፤ እርሱንና #ዘሮቹን እነሱ ለናንተ ጠላቶች ሲኾኑ፥ ከኔ ሌላ ረዳቶች አድርጋችሁ ትይዛላችሁን? ለበዳዮች ልዋጭነቱ ከፋ” (ሱረቱል ከህፍ 18፡50)፡፡
መላእክት ዝርያ የላቸውም፡፡ ጾታዊ መገለጫም (ወንድና ሴት) የላቸውም፡፡ ጂንኒዎች ዘንድ ግን ወንድ እና ሴት በመባል ሰው ዘንድ እንዳለው፡ እነሱም ዘንድ የጾታ ክፍፍል አልለ፡፡
” وَأَنَّهُ كَانَ رِجَالٌ مِنَ الْإِنْسِ يَعُوذُونَ بِرِجَالٍ مِنَ الْجِنِّ فَزَادُوهُمْ رَهَقًا ” سورة الجن 6
“እነሆም ከሰዎች የሆኑ #ወንዶች በጋኔን ወንዶች ይጠበቁ ነበሩ፤ ኩራትንም ጨመሩዋቸው።” (ሱረቱል ጂን 6)፡፡
ዐረብ ጣኦታውያን በወቅቱ ወደ አንድ ዋሻ ወይም ሸለቆ ሲደርሱ ፍርሀት ካደረባቸው ‹በዚህ ዋሻ ጌታ በሆነው እጠበቃለሁ› በማለት ጂንኒዎችን ከአላህ ሌላ ይማጸኑ እንደነበር ቅዱስ ቁርኣን ሲገልጽልን፡ እግረ መንገዱንም ‹በጋኔን ወንዶች› በማለት በወንድ ጾታ የሚታወቁ መኖራቸውንም አብሮ ነግሮናል፡፡ ወንድ መኖሩ ከተረጋጋጠ ደግሞ ሴት መኖሩ በራሱ አስረጂ ነው፡፡ ማንኛውም ነገር የሚታወቀው በተቃራኒው ነውና፡፡ በተጨማሪም የነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሐዲሥ ሁኔታውን በደንብ ይገልጸዋል፡-
عن أنس بن مالك رضي الله عنه أن النبي صلى الله عليه وسلم كان إذا دخل الخلاء قال : اللهم إني أعوذ بك من الخبث والخبائث . رواه مسلم.
አነስ ኢብኑ-ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ወደ መጸዳጃ ሲገቡ ‹‹አላህ ሆይ! እኔ #ከወንድና_ሴት ሰይጣናት በአንተ እጠበቃለሁ›› ይሉ ነበር፡፡ (ሙስሊም)፡፡

መ/ አመጸኛ መሆኑ፡-
መላእክት ዘንድ አመጽ አይታወቅም፡፡ እነሱ ከኃጢአት ርቀው በአምልኮ ተግባር ብቻ የተሰማሩ ፍጥረት ናቸው፡፡ እንኳን ጌታቸውን ሊያምጹ ይቅርና፡ በንግግር እንኳ አይቀድሙትም፡፡ እሱ ያላለውን አይሉም፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا قُوا أَنفُسَكُمْ وَأَهْلِيكُمْ نَارًا وَقُودُهَا النَّاسُ وَالْحِجَارَةُ عَلَيْهَا مَلائِكَةٌ غِلاظٌ شِدَادٌ لا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ ” سورة التحريم 6
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና በተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችን ደንጊያዎች ከሆነች እሳት ጠብቁ፤ በርሷላይ ጨካኞች፣ ኀይለኞች የሆኑ መላእክት አሉ፤ አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጡም፤ የሚታዘዙትን ሁኡ ይሠራሉ።” (ሱረቱ-ተሕሪም 66፡6)፡፡
” وَقَالُوا اتَّخَذَ الرَّحْمَنُ وَلَدًا سُبْحَانَهُ بَلْ عِبَادٌ مُكْرَمُونَ * لَا يَسْبِقُونَهُ بِالْقَوْلِ وَهُمْ بِأَمْرِهِ يَعْمَلُونَ ” سورة الأنبياء 27-26
“አልረሕማንም (ከመላእክት) ልጅን ያዘ አሉ፤ ጥራት ተገባው፤ አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናችው፤ በንግግር አይቀድሙትም፤ (ያላለውን አይሉም)፤ እነሱም በትእዛዙ ይሠራሉ።” (ሱረቱል አንቢያእ 26-27)፡፡
ኢብሊስ ግን ከዚህ በተቃራኒ የቆመ አመጸኛና ከሀዲ ነበር፡፡ ይህም መልአክ እንዳልነበር ጠቋሚ ነው፡-
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ كَانَ مِنَ الْجِنِّ فَفَسَقَ عَنْ أَمْرِ رَبِّهِ…” سورة الكهف 50
“ለመላእክትም ለአደም ስገዱ፥ ባልናቸው ጊዜ (የሆነውን አስታውስ)። ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፤ ከጋኔን (ጎሳ) ነበር፤ ከጌታውም #ትእዛዝ ወጣ…..” (ሱረቱል ከህፍ 18፡50)፡፡

ሠ/ ሐሰኑል-በስሪይ (ረሒመሁላህ)፡-
ሐሰኑል በስሪይ ከ21-110 ሒጅሪ. የነበሩ ታላቅ ታቢዒይ ናቸው፡፡ እኚህ የኢስላም ሊቅ፡- ኢብሊስ ለአይን ቅጽበት ያህል ጊዜ እንኳ መልአክ ሆኖ አያውቅም፡፡ እሱ:- አደም የሰዎች ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነው፡ የጂኖች ሁሉ መጀመሪያቸው ነበር ይላሉ፡፡ ይኸው ቃላቸው፡-
قال الحسن البصري: ما كان إبليس من الملائكة طرفة عين قَط، وإنه لأصل الجن ، كما أن آدم أصل البشر. رواه ابن جرير بإسناد صحيح عنه . اهـ (تفسير الطبري : سورة البقرة 34: رقم 696).
ረ/ ፈታዋ-ለጅነህ፡-
በስዑድ ዐረቢያ የሚገኘው የዑለማዎች ፈትዋ ቋሚ ኮሚቴ በጥያቄ ቁጥር 7815፣ ጥራዝ ሶስት፣ ገጽ 509 ላይ፡- ኢብሊስ ከጂንኒዎች እንጂ ከመልአኮች አልነበረም የሚለውን ረእይ በመምረጥ፡ በሱረቱል ከህፍ ቁ 50 ያለውን እንደማስረጃ ይጠቀማሉ፡፡ እንዲሁም የሐሰኑል በስሪይን ንግግር ያቀርባሉ፡፡
ሰ/ ሸይኽ ፈውዛን (ሐፊዘሁላህ)፡-
ዱክቱር ሷሊሕ ቢን ፈውዛን ቢን ዐብዱላህ አል-ፈውዛን (ሐፊዘሁላህ) በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው የሰጡት መልስ፡- ይህ በዑለማዎች መሀል የሀሳብ ልዩነት ያለበት ነው፡፡ ሆኖም ትክክለኛው አካሄድ ‹ኢብሊስ ከመልአኮች አልነበረም› የሚለው ነው በማለት፡ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ (አል-ሙንተቃ ሚን ፈታዋ አል-ፈውዛን ጁዝእ 33 ገጽ 7፣ ጥያቄ ቁ 14)፡፡
ይቀጥላል