በመላእክት ማመን ክፍል አስራ ሶስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
347 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት የስራ ድርሻቸው፡-
ረ/ በሰው ላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው፡-
6/ አላህ የሚወሳበት ስፍራ (መጃሊሱ-ዚክር) መገኘት፡-
መላእክት አላህን ሁሌም በመገዛትና እሱን በማውሳት፡ እንዲሁም እሱን በማወደስ ተግባር ላይ የተሰማሩ የመልካምነት አርአያ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው፡፡ ያ በመሆኑም፡ በዚህ ምድር ላይ ከሰዎች የሆኑ አማኝ የአላህ ባሪያዎች: አላህን በሚያወሱበት ስፍራ ላይ፣ ሃይማኖታዊ ዕውቀት በሚሰጥበት ስፍራ ላይ ይሰባሰባሉ፡ ይጠራራሉ፡፡ ቀጣዩ ሐዲሥ ሁኔታውን የበለጠ ይገልጸዋል፡-
حديث أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللهِ صلى الله عليه وسلم: إِنَّ للهِ مَلاَئِكَةً يَطُوفُونَ فِي الطُّرُقِ، يَلْتَمِسُونَ أَهْلَ الذِّكْرِ فَإِنْ وَجَدُوا قَوْمًا يَذْكُرُونَ اللهَ، تَنَادَوْا: هَلُمُّوا إِلَى حَاجَتِكُمْ قَالَ: فَيَحُفُّونَهُمْ بِأَجْنِحَتِهِمْ إِلَى السَّمَاءِ الدُّنْيَا قَالَ: فَيَسْأَلُهُمْ رَبُّهُمْ، وَهُوَ أَعْلَمُ مِنْهُمْ مَا يَقُولُ عِبَادِي قَالُوا: يَقُولُونَ، يُسَبِّحُونَكَ، وَيُكَبِّرُونَكَ، وَيَحْمَدُونَكَ، وَيُمَجِّدُونَكَ قَالَ: فَيَقُولُ هَلْ رَأَوْنِي قَالَ: فَيَقُولُونَ، لاَ وَاللهِ مَا رَأَوْكَ قَالَ: فَيَقُولُ وَكَيْفَ لَوْ رَأَوْنِي قَالَ: يَقُولُونَ، لَوْ رَأَوْكَ كَانُوا أَشَدَّ لَكَ عِبَادَةً، وَأَشَدَّ لَكَ تَمْجِيدًا، وَأَكْثَرَ لَكَ تَسْبِيحًا قَالَ: يَقُولُ فَمَا يَسْأَلُونِي قَالَ: يَسْئَلُونَكَ الْجَنَّةَ قَالَ: يَقُولُ وَهَلْ رَأَوْهَا قَالَ: يَقُولُونَ، لاَ وَاللهِ يَا رَبِّ مَا رَأَوْهَا قَالَ: يَقُولُ فَكَيْفَ لَوْ أَنَّهُمْ رَأَوْهَا قَالَ: يَقُولُونَ لَوْ أَنَّهُمْ رَأَوْهَا، كَانُوا أَشَدَّ عَلَيْهَا حِرْصًا، وَأَشَدَّ لَهَا طَلَبًا، وَأَعْظَمَ فِيهَا رَغْبَةً قَالَ: فَمِمَّ يَتَعَوَّذُونَ قَالَ: يَقُولُونَ مِنَ النَّارِ قَالَ: يَقُولُ وَهَلْ رَأَوْهَا قَالَ: يَقُولُونَ لاَ وَاللهِ مَا رَأَوْهَا قَالَ: يَقُولُ فَكَيْفَ لَوْ رَأَوْهَا قَالَ: يَقُولُونَ لَوْ رَأَوْهَا كَانُوا أَشَدَّ مِنْهَا فِرَارًا، وَأَشَدَّ لَهَا مَخَافَةً قَالَ: فَيَقُولُ فَأُشْهِدُكُمْ أَنِّي قَدْ غَفَرْتُ لَهُمْ قَالَ: يَقُولُ مَلَكٌ مِنَ الْمَلاَئِكَةِ: فِيهِمْ فُلاَنٌ، لَيْسَ مِنْهُمْ إِنَّمَا جَاءَ لِحَاجَةٍ قَالَ: هُمُ الْجُلَسَاءُ، لاَ يَشْقَى بِهِمْ جَلِيسُهُمْ. متفق عليه.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ በምድር ላይ የዚክር ሰዎችን (አላህን የሚያወሱትን) በመፈለግ የሚዟዟሩ መላእክት አሉት፡፡ እነዚህ መላእክት፡ አላህን የሚያወሱና የሚያወድሱ ህዝቦችን ካገኙ ‹‹ኑ ወደምትፈልጉት ነገር!›› በማለት እርስ በርስ ይጠራራሉ፡፡ ከዛም እነዚህን አላህን አውሺዎች በክንፎቻቸው በመክበብ ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ያካልላሉ፡፡ ከዛም ጌታቸው አላህ፡ ከነሱ በላይ በባሮቹ ጉዳይ ዐዋቂ ሆኖ ሳለ ‹‹ባሮቼ ምን እያሉ ነው?›› በማለት ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም ‹‹አንተን ከማይገባህ ባህሪ እያጠሩህ፣ ታላቅነትህን እየገለጹ፣ በጸጋዎችህ እያመሰገኑህ፣ በክብርህ እያላቁህ ነው›› በማለት ይመልሳሉ፡፡ አላህም ‹‹አይተውኛል እንዴ?›› ሲላቸው፡ ‹‹ወላሂ በፍጹም አላዩህም!›› ብለው ይመልሳሉ፡፡ አላህም ‹‹ሳያዩኝ እንዲህ ያከበሩኝ፡ ቢያዩኝ ኖሮስ?›› ሲላቸው፡ መላእክትም ‹‹ቢያዩህማ ኖሮ፡ ላንተ እጅግ የጠለቀ አምልኮ፣ እጅግ የላቀ ከበሬታ፣ እጅግ የበዛ ማጥራትን በፈጸሙ ነበር›› ይላሉ፡፡ አላህም ‹‹የሚጠይቁኝስ ምንን ነው?›› ሲላቸው፡ እነሱም ‹‹ጀነትን ይለምኑሀል›› ይላሉ፡፡ እሱም ‹‹አይተዋታልን?›› ሲላቸው፡ ‹‹ወላሂ በፍጹም አላዩዋትም!›› ይላሉ፡፡ አላህም ‹‹ቢያዩዋት ኖሮስ?›› ሲላቸው፡ መላእክትም ‹‹ቢያዩዋትማ ኖሮ፡ ለሷ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጉጉት፣ በጣም ከፍተኛ የሆነ ፍላጎትና ክጃሎት ይኖራቸው ነበር›› ይላሉ፡፡ ጌታችንም ‹‹ከምንድነው እንድጠብቃቸው የሚሹት?›› ሲላቸው፡ እነሱም ‹‹ከእሳት ነው!›› ይላሉ፡፡ ‹‹እሳትን አይተዋታል እንዴ!›› ሲላቸው ‹‹በፍጹም አላዩዋትም!›› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ‹‹ታዲያ ቢያዩዋት ኖሮስ?›› ሲላቸው፡ ‹‹ቢያዩዋት ኖሮማ፡ ከሷ እጅጉኑ የሸሹና የፈሩ ይሆኑ ነበር›› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ከዛም ጌታችን አላህ፡- ‹‹#እኔ_በርግጥም_ኃጢአታቸውን_እንደማርኳቸው_እናንተንም_ምስክር_አድርጌአለሁ›› ይላቸዋል፡፡ ከመላእክቶቹ መካከል አንድ መልአክም፡- ‹‹ከውስጣቸው እገሌ የሚባል ሰው አለ፡፡ ለጉዳዩ ብሎ እንጂ ለዚህ ዓላማ ያልመጣ›› ሲል፡ አላህም ‹‹እነዚህ አላህን ለማውሳትና ለመዘከር የተቀመጡ ናቸው፡፡ አብሯቸው የተቀመጠም እድለ-ቢስ አይሆንም!›› ይላል” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
በዚህ ታላቅ ሐዲሥ መሰረት፡ ጌታችንና አምላካችን አላህ በባሮቹ ጉዳይ ሁሉን ዐዋቂ ሆኖ ሳለ፡ መላእክትን ግን ስለ ባሮቹ ሁኔታ ይጠይቃቸዋል፡፡ ዓላማውም የሐዲሥ ሊቃውንት እንደገለጹት፡- መላእክትን በራሳቸው አንደበት ከአደም ልጆች ውስጥ በመልካም ስራ ላይ በመሳተፍ፡ ጌታቸውን አላህን በመዘከር፣ በማክበር፣ በማተለቅና ከማይገባው የጉድለት ባህሪ በማጥራት የሚዘክሩትና የሚያወድሱት መኖራቸውን ለማስመስከር ነው ወላሁ አዕለም፡፡
عَنْ أَبِى هُرَيْرَةَ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- « مَنْ نَفَّسَ عَنْ مُؤْمِنٍ كُرْبَةً مِنْ كُرَبِ الدُّنْيَا نَفَّسَ اللَّهُ عَنْهُ كُرْبَةً مِنْ كُرَبِ يَوْمِ الْقِيَامَةِ وَمَنْ يَسَّرَ عَلَى مُعْسِرٍ يَسَّرَ اللَّهُ عَلَيْهِ فِى الدُّنْيَا وَالآخِرَةِ وَمَنْ سَتَرَ مُسْلِمًا سَتَرَهُ اللَّهُ فِى الدُّنْيَا وَالآخِرَةِ وَاللَّهُ فِى عَوْنِ الْعَبْدِ مَا كَانَ الْعَبْدُ فِى عَوْنِ أَخِيهِ وَمَنْ سَلَكَ طَرِيقًا يَلْتَمِسُ فِيهِ عِلْمًا سَهَّلَ اللَّهُ لَهُ بِهِ طَرِيقًا إِلَى الْجَنَّةِ وَمَا اجْتَمَعَ قَوْمٌ فِى بَيْتٍ مِنْ بُيُوتِ اللَّهِ يَتْلُونَ كِتَابَ اللَّهِ وَيَتَدَارَسُونَهُ بَيْنَهُمْ إِلاَّ نَزَلَتْ عَلَيْهِمُ السَّكِينَةُ وَغَشِيَتْهُمُ الرَّحْمَةُ وَحَفَّتْهُمُ الْمَلاَئِكَةُ وَذَكَرَهُمُ اللَّهُ فِيمَنْ عِنْدَهُ وَمَنْ بَطَّأَ بِهِ عَمَلُهُ لَمْ يُسْرِعْ بِهِ نَسَبُهُ ». رواه مسلم
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከሙስሊም ወንድሙ ላይ፡ ከዱንያ ጭንቀቶች ውስጥ አንዱን ሰበብ በመሆን ያስወገደለት ሰው፡ አላህም ለዚህ ሰው ከቂያማ ቀን ጭንቀቶች አንዱን ጭንቀት ያስወግድለታል፡፡ ከሙስሊም ወንድሙ ላይ ችግርን ያቀለለ ሰው፡ አላህ በዱንያም በአኼራም ነገሮችን ያቀልለታል፡፡ የሙስሊም ወንድሙን ነውር የሸፈነ ሰው፡ አላህም በዱንና በአኼራ ነውሩን ይሸፍንለታል፡፡ አንድ የአላህ ባሪያ ሙስሊሙን በመርዳት ላይ እስካለ ድረስ፡ አላህም እሱን ይረዳዋል፡፡ ሃይማኖታዊ ዕውቀትን የሚፈልግ ሆኖ መንገድን የተጓዘ ሰው፡ አላህ በዚህ ሰበብ የጀነትን መንገድ ያገራለታል፡፡ ከአላህ ቤቶች ውስጥ በአንዱም ቢሆን ህዝቦች የአላህን መጽሐፍ የሚነቡ ሆነው፣ በመሀከላቸውም የሚጠናኑት ሆነው አይሰባሰቡም፡ በነሱ ላይ የቀልብ እርጋታ ቢወርድባቸው፣ የአላህ ራሕመት ቢሸፍናቸው፣ #መላእክት_ቢያካብቧቸው፣ አላህም እሱ ዘንድ ባሉት መላእክት ስማቸውን እያነሳ ቢያወድሳቸው እንጂ፡፡ (ከዚህ መልካም ተግባር) ስራው ወደኋላ ያስቀረው ሰው፡ ጎሳው (ምንም ቢሆን) ወደፊት አያደርገውም” (ሙስሊም)፡፡
7/ ከሰጋጆች ጋር አሚን የሚሉ፡-
عَنْ أَبِى هُرَيْرَةَ عَنِ النَّبِىِّ -صلى الله عليه وسلم- قَالَ :« إِذَا أَمَّنَ الْقَارِئُ فَأَمِّنُوا ، فَإِنَّ الْمَلاَئِكَةَ يُؤَمِّنُونَ ، فَمَنَ وَافَقَ تَأْمِينُهُ تَأْمِينَ الْمَلاَئِكَةِ غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ ». رَوَاهُ الْبُخَارِىُّ فِى الصَّحِيحِ
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ቃሪኡ (አሰጋጁ) አሚን ካለ፡ እናንተም ተከትላችሁ አሚን በሉ፡፡ (መላእክትም አሚን ይላሉና) አሚን ማለታችሁ ከነሱ አሚን ማለት ጋር ከተገጣጠመ (እኩል ከተገናኘ) ከዚህ በፊት የሰራችሁት (ትናንሽ) ኃጢአት በመላ (በአላህ ራሕመት) ይቅር ይባላል” (ቡኻሪይ)፡፡
በሐዲሡ መሰረት፡ ሶላቱል ጀመዓ በምንሰግድበት ወቅት፡ ድምጽ ከፍ ተደርጎ በሚቀራባቸው የሶላት ወቅቶች ላይ (መግሪብ፣ ዒሻእ፣ ፈጅር፣ ጁሙዓህ) ኢማሙ ፋቲሓን ጨርሶ አሚን ካለ፡ እኛም ከኋላው በመከተል አሚን ማለት ይገባናል፡፡ በዚህ ወቅት አሚን የሚሉ መላእክት አሉ፡፡ የኛ አሚን ማለት ከነሱ አሚን ማለት ጋር በእኩል ከተገጣጠመ፡ ከዚህ በፊት የተሰሩ ትናንሽ ጥፋቶች ሁሉ በአላህ ቸርነት ይቅር ይባላሉ፡፡ ከታላላቅ ኃጢአት ሁሌም ተውበት ማድረግ ግድ ነውና፡፡
ከሶላቱም ውጪ ቁርኣን የሚቀራ ሰው፡ ፋቲሓን ሲቀራ ብንሰማውና እንደጨረሰ አሚን ሲል አብረን አሚን ብንል፡ እዚሁ ሐዲሥ ውስጥ እንካተታለን የሚልም የዑለማዎች ረእይ አልለ፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡
ይህ እንግዲህ አላህ ለባሮቹ የከፈተው ኤግዚብሽን ነው፡፡ በጀመዓ ሶላቶች ላይ በመገኘት ኢማሙን ፋቲሓ ሲቀራ በማዳመጥ፡ እንደጨረሰም አሚን ሲል አብሮ ማለትና ከመላእክት አሚን ማለት ጋር እንዲገጥምልን በመከጀል ዱዓእ ማድረግ የኛ ድርሻ ነው፡፡ አላህ ይወፍቀን፡፡
ይቀጥላል