በመላእክት ማመን ክፍል አስራ ሰባት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
347 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
8/ በመላእክት የማመን ፍሬዎች፡-
በጌታችን አላህ ፈቃድ ለአስራ ስድስት ተከታታይ ክፍሎች “በመላእክት ማመን” በሚል ርእስ ስር፡ ስለ መላእክት ማንነት፣ ስሞቻቸው፣ ተፈጥሮአዊ ባሕሪይ፣ ስነ-ምግባር፣ የስራ ድርሻ፣ እና የመሳሰሉ ነጥቦችን ዳስሰናል አልሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡ የዛሬው የመጨረሻው ክፍላችን የሚሆነው፡- የአላህ ቃል የሆነው ቁርኣንና የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሐዲሥ ባስተማሩት መሰረት በመላእክት ማመናችን ምን ጥቅም ይሰጠናል? ፍሬዎቹስ ምንድናቸው? የሚለውን ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡

1/ እምነትን ማረጋገጥ፡-
አንዱና ዋነኛው ውጤት ነው!!፡፡ ከሃይማኖታችን ሶስቱ እርከኖች (ኢማን፣ ኢስላም፣ ኢሕሳን) ውስጥ፡ ኢማን ዋነኛውና ቀዳሚ ነጥብ ነው፡፡ ከእምነት ዘርፎች ውስጥ ደግሞ፡ ስድስቱ ማእዘናት (አርካኑል ኢማን) ተቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመላእክት ማመን፡ ከስድስቱ የእምነት ማእዘናት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በአምስቱ አምኖ በአንዱ የሚክድ ሰው ቢኖር፡ በስድስቱም የእምነት ዘርፎች የካደ ካፊር ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ እምነት አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሆነ ክፋይን አይቀበልምና፡፡ በመሆኑም በአላህ ቃልና በመልክተኛው ሐዲሥ ላይ በተቀመጠው መሰረት፡ በመላእክት ያመነ አንድ ሙስሊም ‹አማኝ› መሆኑን አረጋገጠ ማለት ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” آمَنَ الرَّسُولُ بِمَا أُنْزِلَ إِلَيْهِ مِنْ رَبِّهِ وَالْمُؤْمِنُونَ كُلٌّ آمَنَ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِنْ رُسُلِهِ وَقَالُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا غُفْرَانَكَ رَبَّنَا وَإِلَيْكَ الْمَصِيرُ” سورة البقرة 285
“መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡:” (ሱረቱል በቀራህ 2፡285)፡፡
ከዚህ እምነት ተቃራኒ በመቆም፡ በመላእክት የሚክድ ወይንም ለነሱ ጠላት የሆነ ሰው፡ አማኝ ሳይሆን ከሀዲ ‹ካፊር› ነው የሚባለው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” مَنْ كَانَ عَدُوًّا لِلَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَرُسُلِهِ وَجِبْرِيلَ وَمِيكَالَ فَإِنَّ اللَّهَ عَدُوٌّ لِلْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 98
“ለአላህና ለመላእክቱ ለመልክተኞቹም ለጂብሪልም ለሚካልም (ሚካኢል) ጠላት የኾነ ሰው አላህ ለ(እነዚህ) ከሓዲዎች ጠላት ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡98)፡፡
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ለመላእክቱ ጠላት የሆነ ሰው ከከሀዲዎች ጎራ መመደቡን መረዳት ይቻላል፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا آمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي نَزَّلَ عَلَى رَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي أَنْزَلَ مِنْ قَبْلُ وَمَنْ يَكْفُرْ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا بَعِيدًا ” سورة النساء 136
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ፣ እመኑ፤ በአላህና በመላክቱም፣ በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም፣ በመጨረሻውም ቀን የካደ ሰው፣ (ከሰውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡136)፡፡
ዛሬም በድጋሚ ላስታውስ የምፈልገው ነገር፡ በአብዝኃኞቻችን ዘንድ ስሙ ሲነሳ ጥሩ ያልሆነ ስሜት የሚፈጥርብን አንድ መልአክ አልለ፡፡ እሱም፡- መለኩል መውት ‹መልአከ ሞት› (ዐለይሂ-ሰላም) ነው፡፡ ይህ መልአክ የሚሰራው ጌታው ያዘዘውን ነው፡፡ ለአላህ ባሮች ምንም ጥላቻ የለውም፡፡ አላህ ምድራዊ ቆይታዋ እንዲያቆም የፈለጋትን ነፍስ፡ ይህን መልአክ በማዘዝ በስሩ ካሉት ሌሎች መልአኮች ጋር የሰውየው ሩሕ ከሰውነቱ እንዲወጣና እንዲሞት ይደረጋል፡፡ እኛ ግን ልክ እንደ ለሊት ሌባ በድንገት ቤታችን ዘው ብሎ የገባና አንዱን ሆን ብሎ በመግደል፡ የቤተሰቡን ደስታ ወደ ሀዘን የሚቀይር ይመስለናል፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት መስተካከል አለበት፡፡ መልአኩን ልንወደው እንጂ የጥላቻ ስሜት ሊሰማን አይገባም፡፡ ጌታው ያዘዘውን ሰራ እንጂ ምንም አላደረገም፡፡ ከሁሉም በላይ የፈጠረው አላህ ይውደደው፡፡

2/ የአላህን ታላቅነት፡-
ይህም ታላቅ የሆነ ጥቅም ነው፡፡ በሰፈራችን ያለ ባለ ሰባትና ስምንት ፎቅ ህንጻ መመልከታችን፡ ለመሀንዲሱ፣ ለአርክቴክቸሩና ለግንበኞቹ ያለን አክብሮት ይጨምራል፡፡ ለካ አእምሮ ይህንንም መስራት ይችላል! ያስብላል፡፡ ከሀገር ወጣ ስንል ደግሞ ባለ ሰባና ሰማንያ ፎቅ ህንጻዎችን በአንድ መንደር እንደ ሰልፈኛ ተደርድረው ስንመለከት፡ አግራሞታችን የበለጠ እየጨመር፡ ባለሙያዎቹንም እጅግ እየተደመምንባቸው የነሱን ጥበበኝነትና ታላቅነት እንመሰክራለን፡፡
እንግዲያውስ በአንድ ሜትር እና በሁለት ሜትር መሀል የሚመላለስ ቁመት ያለው ‹ሰው› የተባለው ፍጥረት፡ አሰራሩና አፈጣጠሩ ሲደንቀን፡ ‹ሱብሐነከ ያረብ!› ጌታችን አላህ ሆይ! ከጉድለት ባሕሪያት ሁሉ ጥራት የተገባህ ነህ! እንዳልነው ሁላ፡ በዛው መልክም፡ በአይነ ስጋችን ያላየናቸው ግን በአይነ ልቦናችን አምነን በመቀበል መኖራቸውን ያጸደቅነው መላእክት፡ አፈጣጠራቸው ከሰው አንጻር እጅግ በጣም ታላቅ መሆኑ፡ ለጌታችን ያለን ከበሬታ ይጨምራል፡፡ የሱንም ታላቅነት ይበልጡኑ እንገነዘባለን ማለት ነው፡፡
በክፍል ሶስት ላይ በተወሰነ መልኩ የመላእክትን ግዙፍነት አይተናል፡፡ በሉጥ ዘመን አላህ አመጸኛ ህዝቦችን ማጥፋት ሲፈልግ፡ መልአኩ ጂብሪልን (ዐለይሂ-ሰላም) በማዘዝ በአንድ የክንፉ ጫፍ ምድሪቷን ከነ-ነዋሪዎች በማንሳት ወደ ሰማይ ጫፍ እንዳደረሳቸውና ከዛም ወደታች እንደገለበጣቸው፣ የሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ህዝቦች የተውራትን ህግ ለመቀበል ባመጹ ጊዜ፡ መልአኩ በዙሪያቸው የነበረውን ተራራ ነቅሎ በማንሳት ላያቸው ላይ እንደ ጥላ እንዳደረገባቸውና፡ ህጉን ካልተቀበሉ ሊወድቅባቸው እንደሆነ በመግለጽ ማስፈራራቱን፣ ከፍጥረታት ሁሉ እጅግ የገዘፈ የሆነውና ሰማያትን እንደ ዱንኳን የሚሸፍን የሆነው ዐርሽን የሚሸከሙ መላእክት መኖራቸው፣ ከዐርሽ ተሸካሚ መላእክቶችም ስለ አንዱ በሐዲሥ እንደተነገረው፡ ከጆሮው እስከ ትከሻው ሰባት መቶ አመት ሊያስኬድ የሚችል ርቀት ያለው ግዙፍ መልአክ መሆኑን አውስተን ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ለኛ የሚስተላልፈው መልእክት፡- እነዚህን ታላላቅ መላእክት መፍጠር የቻለ አላህ፡ እሱ ምን ያህል ታላቅ የሆነ አምላክ መሆኑን ነው!! ‹‹አላሁ አክበር!!››፡፡

3/ የቀልብ መረጋጋትን፡-
ፍጹም እውነተኛ ጠባቂ አላህ ብቻ ነው (ዩሱፍ 12፡64)፡፡ በአላህ የበላይ ተቆጣጣሪነት እኛን ሰበብ ሆነው የሚጠብቁን መላእክቶች በኛ ላይ መመደባቸው ደስታችን ነው፡፡ መረጋጋትን እናገኛለን፡፡ ልብቻን ግን ወደ አላህ እንጂ ወደነሱ በፍጹም አይዞርም!!፡፡ ምክንያቱም አላህ እኛን ጉዳት እንዲያገኘን ፈቃዱ የሆነ ጊዜ እነዚህ መላእክት ምንም ሊያደርጉልን አይችሉምና (አል-አንቢያእ 21፡42)፡፡ ጋርድ ‹ጠባቂ› ተደርገው መመደባቸው ግን ለኛ ሃሴትና መረጋጋት ነው!! ብቻውን በምሽት የሚሄድ እግረኛ፡ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከሚሄደው ቀን ጋር እኩል የሆነ ነጻነት እንደማይሰማው ውስጡ ይነግረዋል፡፡

4/ ለመልካም ስራ ጉጉት፡-
በክፍል አራት ላይ ‹‹የመላእክት ስነ-ምግባር›› በሚለው ርእስ ስር፡ መላእክት ከሚለዩበት አንዱ ባሕሪያቸው ‹አምልኮ› መሆኑን አይተናል፡፡ እነዚህ መላእክት ሁሌም ጌታቸውን አላህን ያመልኩታል፡፡ ከአምልኮ ፈጽሞ አያቋርጡም፡፡ በአላህ አምልኮ ላይ ምንም ኩራት ሳይኖርባቸው፣ ሳይሰላቹና ሳያቋርጡ ነው የሚኖሩት፡፡ ይህን የተረዳ ሙስሊም ደግሞ፡ እሱም አቅሙ በፈቀደው መጠን፡ በዒባዳህ ላይ ይተጋል ማለት ነው፡፡

5/ አላህን ፈሪነት፡-
ከላይ እንዳየነው፡ መላእክት ከዚህ ግዝፈታቸው ጋር ለአላህ ተናናሾች ናቸው፡፡ አላህን በእጅጉ ይፈሩታል፡፡ ለቃሉ ይንቀጠቀጣሉ፡ ሱጁድም ይወርዳሉ፡፡ ታዲያ እኛ ደካማዎቹ የአላህ ባሪያዎች ከዚህ የምንማረው ነገር የለምን? እኛም አላህን በእጅጉ እንድንፈራ የልብ ተነሳሽነት እንዲኖረን ይጋብዘናል፡፡
የአንድን ነገር ታላቅነት በተረዳን ቁጥር፡ ለዛ ነገር የሚኖረን ፍርሀት አብሮ ይጨምራል፡፡ አይጥ ሲያይ የሚፈራው ልባችን አንበሳ በምናይበት ጊዜ እንዳለው አይደለም፡፡ ባለ አራት ጎማ የሆነው የቤት መኪና በአጠገባችን ሲያልፍ እንዳይጎዳን ከምንጠነቀቀው በበለጠ መልኩ፡ ባለ 22 ጎማ ተሳቢ መኪና ቢመጣ ደግሞ የበለጠ ሽሽታችን ይጨምራል፡፡ የፍጡራን ሁሉ አስገኚና ፈጣሪ የሆነውን አላህን መላእክት በእጅጉ መፍራታቸው፡ እኛም አላህን ምን ያህል መፍራት እንዳለብን የሚያስተምር ነው፡፡

6/ ለመጨረሻው ዓለም መልካም ዝግጅትን፡-
የጀነት ዘበኛ የሆኑ መላእክት፡ በውስጧ ሁልጊዜ ዘውታሪ የሆኑ አማኝ ባሮች በትንሳኤው ዓለም ወደሷ ሲመጡ፡ እንኳን ደህና መጣችሁ! በማለት በመልካም አቀባበል ሲቀበሏቸው፡ በጥሩ መስተንግዶ ሲያስተናግዷቸው፡ እኔም ከነሱ ልሁን! በማለት የማይመኝ ሙስሊም የለም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ የመልካም ስራና የተስተካከለ እምነት ውጤት እንጂ፡ የምኞት ብቻ ባለመሆኑ፡ ነገም እኛ ከጀነት እንግዶች ለመሆን እና ይህን የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተጠቃሚ ለመሆን፡ ከዛሬ ጀምሮ በትክክለኛ እምነትና በመልካም ስራ ላይ መበርታት እንዳለብን እንማራለን ማለት ነው፡፡ አላህ ይወፍቀን፡፡
ተፈፀመ!!