በመላእክት ማመን ክፍል አስራ ሁለት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
500 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት የስራ ድርሻቸው፡-
ረ/ በሰው ላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው፡-
5/ ምህረትን መለመን (ኢስቲግፋር)፡-
ጌታ አላህ መሀሪ አምላክ ነው፡፡ ለባሮቹ ከነፍሳቸውና ከወላጆቻቸው በላይ እጅግ አዛኝ ነው፡፡ በተውበት ወደሱ ለሚመለሱ ባሮቹ የእዝነት በሩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡ በከሀዲያን እና በአመጸኞችም ላይ ቅጣቱ እጅግ የበረታ ነው፡፡ ስለሆነም እሱ ማለት ምን አይነት አምላክ እንደሆነ እንዲህ በማለት ያስተዋውቃል፡-
” نَبِّئْ عِبَادِي أَنِّي أَنَا الْغَفُورُ الرَّحِيمُ * وَأَنَّ عَذَابِي هُوَ الْعَذَابُ الْأَلِيمُ ” سورة الحجر 50-49
“ባሮቼን እኔ መሓሪው አዛኙ እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡ ቅጣቴም እርሱ አሳማሚ ቅጣት መኾኑን (ንገራቸው)፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 15፡49-50)፡፡
አንድ የአላህ ባሪያ ለፈጸመው ጥፋት፡ ለሰራው ኃጢአት፡ ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ ወደ ጌታው በተጸጸተ ልብ ከተመለሰ አላህም ይምረዋል፡፡ ከአላህ እዝነትና ምህረት በፍጹም ተስፋ ሊቆርጥ አይገባውም፡-
” قُلْ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ أَسْرَفُوا عَلَى أَنْفُسِهِمْ لَا تَقْنَطُوا مِنْ رَحْمَةِ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ يَغْفِرُ الذُّنُوبَ جَمِيعًا إِنَّهُ هُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ ” سورة الزمر 53
“በላቸው፦ እናንተ በነፍሶቻችሁ ላይ ድንበር ያለፋችሁ ባሮቼ ሆይ! ከአላህ እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፤ አላህ ኃጢአቶችን በመላ ይምራልና። እነሆ እርሱ መሐሪው አዛኙ ነውና።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡53)፡፡
ቁም ነገሩ ጊዜው ሳያልፍብን የጌታችን ቀጠሮ (አጀል) ሳይመጣ፡ ወይም በቁጣው ሰበብ ቅጣቱ ሳያገኘን በፊት በፍጥነት በተውበት ወደሱ መመለስ ነው ያለብን፡-
” وَأَنِيبُوا إِلَى رَبِّكُمْ وَأَسْلِمُوا لَهُ مِنْ قَبْلِ أَنْ يَأْتِيَكُمُ الْعَذَابُ ثُمَّ لَا تُنْصَرُونَ ” سورة الزمر 54
“ቅጣቱም ወደ እናንተ ከመምጣቱና ከዚያም የማትረዱ ከመሆናችሁ በፊት፣ ወደ ጌታችሁ (በመጸጸት) ተመለሱ፤ ለርሱም ታዘዙ።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡54)፡፡
” إِنَّمَا التَّوْبَةُ عَلَى اللَّهِ لِلَّذِينَ يَعْمَلُونَ السُّوءَ بِجَهَالَةٍ ثُمَّ يَتُوبُونَ مِنْ قَرِيبٍ فَأُولَئِكَ يَتُوبُ اللَّهُ عَلَيْهِمْ وَكَانَ اللَّهُ عَلِيمًا حَكِيمًا * وَلَيْسَتِ التَّوْبَةُ لِلَّذِينَ يَعْمَلُونَ السَّيِّئَاتِ حَتَّى إِذَا حَضَرَ أَحَدَهُمُ الْمَوْتُ قَالَ إِنِّي تُبْتُ الْآنَ وَلَا الَّذِينَ يَمُوتُونَ وَهُمْ كُفَّارٌ أُولَئِكَ أَعْتَدْنَا لَهُمْ عَذَابًا أَلِيمًا ” سورة النساء 18-17
“ፀፀትን መቀበል በአላህ ላይ የሚገባው ለነዚያ ኀጢአትን በስሕተት ለሚሠሩና ከዚያም ከቅርብ ጊዜ ለሚጸጸቱት ብቻ ነው። እነዚያንም አላህ በነርሱ ላይ ጸጸትን ይቀበላል። አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው። ጸጸትንም መቀበል ለነዚያ ኃጢያቶችን ለሚሠሩ፣ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ እኔ አሁን ተጸጸትኩ ለሚልና ለነዚያም እነርሱ ከኃዲዎች ሆነው ለሚሞቱ አይደለችም። እነዚያ ለነሱ አሳማሚ ቅጣት አዘጋጅተናል።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡17-18)፡፡
ደግሞም በተጨማሪ፡ ጌታችን አላህ ከራሳችን ኢስቲግፋር (ምህረት ጥየቃ) ሌላ፡ ለኛ አላህን ምህረት የሚለምኑልን መላእክትን መድቦልናል፡፡ አልሐምዱ ሊላሂ ረቢል-ዓለሚን፡-
” الَّذِينَ يَحْمِلُونَ الْعَرْشَ وَمَنْ حَوْلَهُ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ وَيُؤْمِنُونَ بِهِ وَيَسْتَغْفِرُونَ لِلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا وَسِعْتَ كُلَّ شَيْءٍ رَحْمَةً وَعِلْمًا فَاغْفِرْ لِلَّذِينَ تَابُوا وَاتَّبَعُوا سَبِيلَكَ وَقِهِمْ عَذَابَ الْجَحِيمِ ” سورة غافر 7
“እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት፣ እነዚያም በዙሪያው ያሉት፣ በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ፤በርሱም ያምናሉ፤ ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል፤ ስለዚህ ለነዚያ ለተጸጸቱት፣ መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው፣ እያሉ ለነዚያ ላመኑት ምሕረትን #ይለምናሉ።” (ሱረቱ ጋፊር/ሙእሚን 40፡7)፡፡
” تَكَادُ السَّمَاوَاتُ يَتَفَطَّرْنَ مِنْ فَوْقِهِنَّ وَالْمَلَائِكَةُ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ وَيَسْتَغْفِرُونَ لِمَنْ فِي الْأَرْضِ أَلَا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْغَفُورُ الرَّحِيمُ ” سورة الشورى 5
“(ከአላህ ፍራቻ) ሰማያት ከበላያቸው ሊቀደዱ ይቀርባሉ፤ መላእክትም ጌታቸውን እያመሰገኑ ያወድሳሉ፤ በምድርም ላለው ፍጡር ምሕረትን #ይለምናሉ፤ ንቁ አላህ እርሱ መሐሪው አዛኙ ነው።” (ሱረቱ-ሹራ 42፡5)፡፡
” هُوَ الَّذِي يُصَلِّي عَلَيْكُمْ وَمَلَائِكَتُهُ لِيُخْرِجَكُمْ مِنَ الظُّلُمَاتِ إِلَى النُّورِ وَكَانَ بِالْمُؤْمِنِينَ رَحِيمًا ” سورة الأحزاب 43
“እሱ ያ በናንተ ላይ እዝነትን የሚያወርድ ነው፤ መላእክቶችም ፥ (እንደዚሁ ምሕረትን #የሚለምኑላችሁ ናቸው) ፣ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያመጣችሁ ዘንድ (ያዝንላችኋል)፤ ለአማኞችም በጣም አዛኝ ነው።” (ሱረቱል አሕዛብ 33፡43)፡፡
وعن أبو أمامة الباهلي – رضي الله عنه – قال : «ذُكِرَ للنبيِّ -صلى الله عليه وسلم- رجلان : أحدهما عابد ، والآخر عالم ، فقال : فضلُ العَالِم على العَابِدِ كَفَضْلِي على أدْناكم ، ثم قال النبيُّ -صلى الله عليه وسلم- : إنَّ الله وملائِكَتَه وأهْلَ السَّمواتِ والأرضِ – حتى النَّملةَ في جُحْرِها ، والحيتان في البَحْرِ – لَيُصَلُّون على مُعَلِّم الناس الخيرَ» أخرجه الترمذي. وصلاة الملائكة دعاء واستتغفار. الترمذي 2685.
አቢ ኡማመተል-ባሂሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘንድ ሁለት ሰዎች ተወሱ፡፡ አንደኛው ዓቢድ (በአምልኮ ተግባር በጣብ ጎበዝ) ሌላኛው ደግሞ ዓሊም (የሃይማኖት ምሁር) ነበር፡፡ ከዛም መልክተኛው፡- ‹‹የሃይማኖት ምሁሩ በአቢዱ ላይ ያለው ብልጫ እኔ ከናንተ በሚያንሰው ላይ ያለኝ ብልጫ ያህል ነው፡፡›› ከዛም ቀጠሉና ‹‹አላህ፣ መላእክቱ፣ የሰማይና የምድር ነዋሪዎች፣ ጉንዳን እንኳ በጉድጓዷ፣ አሳዎችም በባህር ሆነው ሰዎችን መልካም ነገር ለሚያስተምር ዱዓ (ከአላህ ምህረትን) #ይለምናሉ›› አሉን” (ቲርሚዚይ 2685)፡፡
ይቀጥላል