በመላእክት ማመን ክፍል አራት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
505 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
3/ የመላእክት ስነ-ምግባር፡-
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ስር ስለ መላእክት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ሊኖረን የሚገባውን እምነት በተመለከተ ዘጠኝ ምሣሌዎችን አንስተን ተነጋግረንበታል፡፡ ዛሬ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ስለ ስነ-ምግባራቸው ትምህርት ይሆነን ዘንድ የተወሰኑ ባህሪያቶቻቸውን አንስተን እንነጋገራለን፡፡ ኢንሻአላህ፡-
ሀ/ አምልኮ (ዒባዳህ)፡-
እጅግ በጣም ጎልተው ከሚታወቁበት ስነ-ምጋባራቸው አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አላህን ሁሌም መገዛት ለመላእክት እስትንፋሳቸው ነው፡፡ ከዒባዳህ ተዘናግተው አያውቁም፡፡ ሁሌም አላህን ያመልኩታል፡፡ ለሱም ያጎነብሳሉ ይሰግዳሉም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይነግረናል፡-
” وَمَا مِنَّا إِلَّا لَهُ مَقَامٌ مَعْلُومٌ * وَإِنَّا لَنَحْنُ الصَّافُّونَ * وَإِنَّا لَنَحْنُ الْمُسَبِّحُونَ ” سورة الصافات 166-164
“(ጂብሪል አለ) ከእኛም አንድም የለም፣ ለእርሱ የታወቀ ደረጃ ያለው ቢሆን እንጂ፡፡ እኛም (ጌታን ለመግገዛት) ተሰላፊዎቹ እኛ ነን፡፡ እኛም (አላህን) አጥሪዎቹ እኛ ነን” (ሱረቱ-ሷፍፋት 37፡164-166)፡፡
ከመልክተኛው ሐዲሥም እጅግ የሚገርም ነገር እንማራለን፡፡ ሐዲሡ እንዲህ ቀርቧል፡-
عَنْ جَابِرٍ ، قَالَ : قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : ” مَا فِي السَّمَاوَاتِ السَّبْعِ مَوْضِعُ قَدَمٍ وَلا شِبْرٍ وَلا كَفٍّ إِلا وَفِيهِ مَلَكٌ قَائِمٌ أَومَلَكٌ رَاكِعٌ أَومَلَكٌ سَاجِدٌ ، فَإِذَا كَانَ يَوْمَ الْقِيَامَةِ ، قَالُوا جَمِيعًا : سُبْحَانَكَ مَا عَبَدْنَاكَ حَقَّ عِبَادَتِكَ ، إِلا أَنَّا لَمْ نُشْرِكْ بِكَ شَيْئًا “رواه الطبراني في الأوسط.
ጃቢር ኢብኒ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በሰባቱ ሰማያት ውስጥ ለአላህ የቆመ፣ ወይንም ያጎነበሰ፣ ወይም ሱጁድ የወረደ መልአክ ቢኖር እንጂ፡ ለእግር ወይም ለስንዝር ወይንም ለመዳፍ ማሳረፊያ የሚሆን ክፍት ስፍራ የለም፡፡ የቂያም ቀንም (የትንሳኤ ቀን) ሁሉም መላእክት በአንድነት ጌታቸውን፡- ‹‹ከጉድለት ባህሪያት ሁሉ ጥራት ይገባህ!! እኛ ላንተ የሚገባህን አምልኮ ያህል አላመለክንህም›› ይሉታል” (ጦበራኒይ አል-ሙዕጀሙል አውሰጥ ሐዲሥ 3568)፡፡
ታዲያ መላእክት (ዐለይሂሙ-ሰላም) ከዚህ አስገራሚ ከሆነው የአምልኮ ስራቸው ጋር ከኛ ከአደም ልጆች የሚለያቸው ሶስት አይነት ሁኔታዎችም አሉ፡፡ እነሱም፡-
1- አይኮሩም፡- መላእክት አላህን ከመገዛት በፍጹም አይኮሩም አያስቡትምም፡፡ ለጌታቸው መተናነስ ፍጹማዊ ባህሪያቸው ነው፡፡ አላህም እንዲህ መስክሮላቸዋል፡-
” إِنَّ الَّذِينَ عِنْدَ رَبِّكَ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَيُسَبِّحُونَهُ وَلَهُ يَسْجُدُونَ ” سورة الأعراف 206
“እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት (መላእክት) እርሱን ከመገዛት #አይኮሩም፤ ያወድሱታልም፤ ለርሱም ብቻ ይሰግዳሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡206)፡፡
2- አያቋርጡም፡- የመላእክት አምልኮ እንደኛ ሰዎች በደቂቃዎችና በሰአታት የተገደበ አይደለም፡፡ ሁሌም ያለምንም ማቋረጥ አላህን እንደተገዙ ናቸው፡፡ ሰማይና ምድር በተፈጠሩበት ጊዜ ሱጁድ የወረደው በሱጁዱ ላይ እያለ፣ ያጎነበሰውም በዛው ሩኩዕ ላይ እያለ እራሳቸውን ቀና ሳያደርጉ ቂያማህ ይቆምባቸዋል፡፡ ሱብሓነከ ያ አላህ!!
” وَلَهُ مَنْ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَنْ عِنْدَهُ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَلَا يَسْتَحْسِرُونَ * يُسَبِّحُونَ اللَّيْلَ وَالنَّهَارَ لَا يَفْتُرُونَ ” سورة الأنبياء 20-19
“በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉም የርሱ ነው፤ እርሱ ዘንድ ያሉትም (መላእክት) እርሱን ከመገዛት አይኮሩም፤ አይሰላቹምም። በሌሊትና በቀንም ያጠሩታል፤ #አያርፉም።” (ሱረቱል አንቢያእ 21:19-20)፡፡
3- አይሰላቹም፡- አላህን ሁሌም እየተገዙት ለአፍታ ያህል እንኳ ከዒባዳ ተግባራቸው ሳያቋርጡ፡ ግን የመሰላቸትና የመሳነፍ ስሜት ፈጽሞ አይታይባቸውም፡፡ አላህ ስንት አይነት ባሪያዎች አሉት!!
” فَإِنِ اسْتَكْبَرُوا فَالَّذِينَ عِنْدَ رَبِّكَ يُسَبِّحُونَ لَهُ بِاللَّيْلِ وَالنَّهَارِ وَهُمْ لَا يَسْأَمُونَ ” سورة فصلت 38
“(አጋሪዎቹ) ቢኮሩም፣ እነዚያ በጌታህ ዘንድ ያሉት (መላእክት) በቀንም በሌሊትም ለርሱ ያወድሳሉ፤ እነርሱም #አይሰላቹም።” (ሱረቱ ፉሲለት 41፡38)፡፡
ለ/ ኸውፉሏህ ‹አላህን መፍራት›፡-
ይህም ሌላኛው ስነ-ምግባራቸው ነው፡፡ መላእክት አላህን እጅግ በጣም ፈሪዎች ነው፡፡ ከኃያልነቱ የተነሳ እጅግ በጣም ተጨናቂዎች ናቸው፡፡ ምንም አመጽ ላይ ባይወድቁም ቅጣቱን ግን በጣም ይፈራሉ፡፡ አላህ ሊወደድ ብቻ ሳይሆን ሊፈራም የሚገባው ጌታ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉና፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
” وَيُسَبِّحُ الرَّعْدُ بِحَمْدِهِ وَالْمَلَائِكَةُ مِنْ خِيفَتِهِ…” سورة الرعد13
“ነጐድጓድም አላህን በማመስገን ያጠራል፣ መላእክትም እርሱን ለመፍራት (ያጠሩታል)…” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡13)፡፡
” وَلِلَّهِ يَسْجُدُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ مِنْ دَابَّةٍ وَالْمَلَائِكَةُ وَهُمْ لَا يَسْتَكْبِرُونَ * يَخَافُونَ رَبَّهُمْ مِنْ فَوْقِهِمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ ” سورة النحل 50-49
“ለአላህም በሰማያት ያለው ከተንቀሳቃሻም በምድር ያለው ሁሉ መላክትም ይሰግዳሉ፤ እነርሱም አይኮሩም። ጌታቸውን ከበላያቸው ሲሆን ይፈሩታል፤ የታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡49-50)፡፡
” يَعْلَمُ مَا بَيْنَ أَيْدِيهِمْ وَمَا خَلْفَهُمْ وَلَا يَشْفَعُونَ إِلَّا لِمَنِ ارْتَضَى وَهُمْ مِنْ خَشْيَتِهِ مُشْفِقُونَ ” سورة الأنبياء 28
“በፊታቸው ያለውንና በኋላቸው ያለውንም ሁሉ ያውቃል፤ ለወደደውም ሰው እንጅ ለሌላው አያማልዱም፤ እነሱም እርሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተጨናቂዎች ናቸው።” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡28)፡፡
ሐ/ ጻድቅነት፡-
መላእክት እንደ ሰው በኃጢአት ባህር የተዘፈቁ አይደሉም፡፡ ሁሌም የአምላካቸውን ትእዛዝ በመጠበቅ እሱን ብቻ በማምለክ በንጽህና የሚኖሩ ፍጥረታት ናቸው፡፡ እንኳን ኃጢአት ላይ ሊወድቁ ይቅርና ጌታቸውንም እንኳ ብንግግር አይቀድሙትም፡፡ እጅግ አደበኞች ናቸው፡፡ ኃጢአት የማያውቃቸው ንፁህ ፍጥረታት ናቸው፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا قُوا أَنفُسَكُمْ وَأَهْلِيكُمْ نَارًا وَقُودُهَا النَّاسُ وَالْحِجَارَةُ عَلَيْهَا مَلائِكَةٌ غِلاظٌ شِدَادٌ لا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ ” سورة التحريم 6
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና በተሰቦቻችሁን መቀጣጠያዋ ሰዎችን ደንጊያዎች ከሆነች እሳት ጠብቁ፤ በርሷላይ ጨካኞች፣ ኀይለኞች የሆኑ መላእክት አሉ፤ አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጡም፤ የሚታዘዙትን ሁኡ ይሠራሉ።” (ሱረቱ-ተሕሪም 66፡6)፡፡
” وَقَالُوا اتَّخَذَ الرَّحْمَنُ وَلَدًا سُبْحَانَهُ بَلْ عِبَادٌ مُكْرَمُونَ * لَا يَسْبِقُونَهُ بِالْقَوْلِ وَهُمْ بِأَمْرِهِ يَعْمَلُونَ ” سورة الأنبياء 27-26
“አልረሕማንም (ከመላእክት) ልጅን ያዘ አሉ፤ ጥራት ተገባው፤ አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናችው፤ በንግግር አይቀድሙትም፤ (ያላለውን አይሉም)፤ እነሱም በትእዛዙ ይሠራሉ።” (ሱረቱል አንቢያእ 26-27)፡፡
ይቀጥላል