በመላእክት ማመን ክፍል አምስት በአቡ ሀይደር

830 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
4/ የመላእክት ስሞች፡-
አምላካችን አላህ መላእክቱን በግል እና በጋራ መጠሪያ ስሞች ሰይሞአቸዋል፡፡ ለዛሬ የምንመለከተው መላእክት ከሚጠሩበት የጋራ (የወል) ስሞች ውስጥ የተወሰነውን በመጥቀስ ነው፡-
ሀ/ ሩሱል (መልክተኞች)፡- ጌታ አላህ በብዙ አንቀጾች ላይ መላእክትን ‹‹ሩሱል›› (መልክተኞች) ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ ለሚፈልገው ዓላማ ስለሚልካቸው ማለት ነው፡፡ ረሱል ማለት መልክተኛ ማለት ሲሆን፡ ሩሱል ደግሞ መልክተኞች ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-
” اللَّهُ يَصْطَفِي مِنَ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا وَمِنَ النَّاسِ إِنَّ اللَّهَ سَمِيعٌ بَصِيرٌ ” سورة الحج 75
“አላህ ከመላእክት ውስጥ #መልክተኞችን ይመርጣል፤ ከስዎችም፣ (እንደዚሁ) አላህ ስሚ ተመልካች ነው።” (ሱረቱል ሐጅ 22:75)፡፡
” الْحَمْدُ لِلَّهِ فَاطِرِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ جَاعِلِ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا أُولِي أَجْنِحَةٍ مَثْنَى وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ يَزِيدُ فِي الْخَلْقِ مَا يَشَاءُ إِنَّ اللَّهَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ ” سورة فاطر 1
“ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሦስት ሦስትም፣ ባለ አራት አራትም፣ ክንፎች የሆኑ #መልክተኞች አድራጊ፣ ለሆነው አላህ ይግባው፤ በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ቻይ ነውና።” (ሱረቱ ፋጢር 35፡1)፡፡
” قَالَ فَمَا خَطْبُكُمْ أَيُّهَا الْمُرْسَلُونَ * قَالُوا إِنَّا أُرْسِلْنَا إِلَى قَوْمٍ مُجْرِمِينَ * لِنُرْسِلَ عَلَيْهِمْ حِجَارَةً مِنْ طِينٍ ” سورة الذاريات 33-31
“እላንተ #መልክተኞች ሆይ ታዲያ ነገራችሁ ምንድነው? አላቸው። (እነርሱም)አሉ ፦ እኛ ወደ አመጠኞች ሕዝቦች ተልከናል። በነርሱ ላይ ከጭቃ የሆኑን ደንጊያዎች ልንለቅባቸው (ተላክን)።” (ሱረቱ-ዛሪያት 51፡31-33)፡፡
በነዚህ ሶስት የቁርኣን አንቀጾች መሰረት መላእክት ‹ሩሱል› (መልክተኞች) ተብለው ሊጠሩ እንደሚችሉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ለ/ ጁኑድ (ሰራዊት)፡-
ይህም መጠሪያ ስማቸው ነው፡፡ አላህ አማኞችን ለማጠናከርና ለማበርታት፡ ከሀዲዎችንም ለማዋረድ የመላእክት ሰራዊትን በከሀዲያን ላይ ይልክባቸዋል፡፡ እነሱም አማኞችን በማበረታታት ከሀዲያንን ያዋርዳሉ፡፡ በዚህም መሰረት ‹ጁኑድ› (ሰራዊት) ተብለው ይጠራሉ፡-
” ثُمَّ أَنْزَلَ اللَّهُ سَكِينَتَهُ عَلَى رَسُولِهِ وَعَلَى الْمُؤْمِنِينَ وَأَنْزَلَ جُنُودًا لَمْ تَرَوْهَا وَعَذَّبَ الَّذِينَ كَفَرُوا وَذَلِكَ جَزَاءُ الْكَافِرِينَ ” سورة التوبة 26
“ከዚያም አላህ እርጋታውን በመልክተኛውና በምእምናኖቹ ላይ አወረደ፤ ያላያችኋቸዉንም #ሰራዊት አወረደ፤ እነዚያን የካዱትንም በመግደልና በመማረክ አሰቃየ፤ ይህም የከሐዲያን ፍዳ ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡26)፡፡
” إِلَّا تَنْصُرُوهُ فَقَدْ نَصَرَهُ اللَّهُ إِذْ أَخْرَجَهُ الَّذِينَ كَفَرُوا ثَانِيَ اثْنَيْنِ إِذْ هُمَا فِي الْغَارِ إِذْ يَقُولُ لِصَاحِبِهِ لَا تَحْزَنْ إِنَّ اللَّهَ مَعَنَا فَأَنْزَلَ اللَّهُ سَكِينَتَهُ عَلَيْهِ وَأَيَّدَهُ بِجُنُودٍ لَمْ تَرَوْهَا وَجَعَلَ كَلِمَةَ الَّذِينَ كَفَرُوا السُّفْلَى وَكَلِمَةُ اللَّهِ هِيَ الْعُلْيَا وَاللَّهُ عَزِيزٌ حَكِيمٌ ” سورة التوبة 40
“(ነቢዩን) ባትረዱት እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ሆኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ አላህ በእርግጥ ረድቶታል ሁለቱም በዋሻዉ ሳሉ ለጓደኛዉ ነዉና ባለ ጊዜ አላህ እርካታዉን በርሱ ላይ አወረደ፤ ባላያችኋቸዉም #ሰራዊት አበረታው፤ የነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ፤ የአላህም ቃል እርሷ ከፍተኛ ናት፤ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡40)፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اذْكُرُوا نِعْمَةَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ جَاءَتْكُمْ جُنُودٌ فَأَرْسَلْنَا عَلَيْهِمْ رِيحًا وَجُنُودًا لَمْ تَرَوْهَا وَكَانَ اللَّهُ بِمَا تَعْمَلُونَ بَصِيرًا ” سورة الأحزاب 9
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ብዙ ሰራዊት በመጣችባችሁና በነሱ ላይ ነፍስንና ያላያችኋትን #ሰራዊት በላክን ጊዜ፣ በናንተ ላይ (ያደረገላችሁን) የአላህ ጸጋ አስታውሱ፤ አላህም የምሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው።” (ሱረቱል አሕዛብ 33፡9)፡፡
ሐ/ አል-አሽሀድ (ምስክሮች)፡-
በትንሳኤው ዓለም (የውሙል ቂያም) አላህ መላእክትን በባሪያዎቹ ላይ በምድራዊ ህይወታቸው ለሰሩት ጥፋት ምክንያት እንዳይኖራቸው መስካሪ አድርጎ ያቀርባቸዋል፡፡ መላእክትም ባዩትና በሰሙት ነገር በፍትህ ይመሰክራሉ፡፡ በዚህም ሰበብ ‹‹አል-አሽሀድ›› (ምስክሮች) ተብለው ይጠራሉ፡-
” مَنْ أَظْلَمُ مِمَّنِ افْتَرَى عَلَى اللَّهِ كَذِبًا أُولَئِكَ يُعْرَضُونَ عَلَى رَبِّهِمْ وَيَقُولُ الْأَشْهَادُ هَؤُلَاءِ الَّذِينَ كَذَبُوا عَلَى رَبِّهِمْ أَلَا لَعْنَةُ اللَّهِ عَلَى الظَّالِمِينَ ” سورة هود 18
“በአላህ ላይ እብለትን ከሚቀጣጥፍም ይበልጥ በዳይ ማነው? እነዚያ በጌታቸው ላይ ይቀረባሉ፤ #መስካሪዎቹም፦ እነዚህ በጌታቸው ላይ የዋሹ ናቸው ይላሉ፤ ንቁ የአላህ ርግማን በበዳዮች ላይ ይኹን።” (ሱረቱ ሁድ 11፡18)፡፡
” وَنُفِخَ فِي الصُّورِ ذَلِكَ يَوْمُ الْوَعِيدِ * وَجَاءَتْ كُلُّ نَفْسٍ مَعَهَا سَائِقٌ وَشَهِيدٌ ” سورة ق 21-20
“በቀንዱም ውስጥ ይነፋል።ያ (ቀን) የዛቻው(መፈፀሚያ) ቀን ይሆናል። ነፍስም ሁሉ ከእርሷ ጋር ነጂና #መስካሪ ያለባት ኾና ትመጣለች፡፡” (ሱረቱ ቃፍ 50፡20-21)፡፡
መ/ መለኡል አዕላ (የላይኛው አድማስ ነዋሪ)፡-
መላእክት የላይኛው ዓለም የሰማይ ነዋሪዎች በመሆናቸው ‹አል-መለኡል አዕላ› (የላይኛው አድማስ ነዋሪዎች) በመባል ይታወቃሉ፡-
” إِنَّا زَيَّنَّا السَّمَاءَ الدُّنْيَا بِزِينَةٍ الْكَوَاكِبِ * وَحِفْظًا مِنْ كُلِّ شَيْطَانٍ مَارِدٍ * لَا يَسَّمَّعُونَ إِلَى الْمَلَإِ الْأَعْلَى وَيُقْذَفُونَ مِنْ كُلِّ جَانِبٍ ” سورة الصافات 8
“እኛ ቅርቢቱንሰማይ በከዋክብት ጌጥ አጌጥናት። አመጸኛም ከሆነ ሰይጣን ሁሉ መጠበቅን ጠበቅናት። #ወደላይኛዉ ሰራዊት አያዳምጡም። ከየወገኑም ሁሉ ችቦ ይጣልባቸዋል።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 37፡6-8)፡፡
” قُلْ هُوَ نَبَأٌ عَظِيمٌ * أَنْتُمْ عَنْهُ مُعْرِضُونَ * مَا كَانَ لِيَ مِنْ عِلْمٍ بِالْمَلَإِ الْأَعْلَى إِذْ يَخْتَصِمُونَ * إِنْ يُوحَى إِلَيَّ إِلَّا أَنَّمَا أَنَا نَذِيرٌ مُبِينٌ ” سورة ص 70-67
“በላቸው «እርሱ (ቁርኣን) ታላቅ ዜና ነው፡፡ «እናንተ ከእርሱ ዘንጊዎች ናችሁ፡፡ (በአደም ነገር) «በሚከራከሩ ጊዜ #በላይኛው ሰራዊት ለእኔ ምንም ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ «ወደእኔም አስፈራሪ ገላጭ መኾኔ እንጂ ሌላ አይወረድልኝም» (በል)፡፡” (ሱረቱ ሷድ 38፡67-70)፡፡
ይቀጥላል