በመላእክት ማመን ክፍል ሶስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
344 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
2/ የመላእክት ተፈጥሮአዊ ገጽታ፡-
በክፍል ሁለት ትምህርታችን ላይ ስለ መላእክት ‹ተፈጥሮአዊ ባሕሪ ጀምረን አራት ነገራትን ተመልክተን ነበር፡፡ እነሱም፡- ከብርሀን መፈጠራቸው፣ ክንፍ ያላቸው መሆናቸው፣ በሰው መመሰል እንደሚችሉና የሰማይ ነዋሪ መሆናቸውን፡፡ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ዛሬ ቀጣይ ክፍሉ ይቀርባል ኢንሻአላህ፡፡
ሠ/ ከሰው ቀዳሚ ፍጥረት ናቸው፡-
መላእክት የተፈጠሩት ከሰው በፊት ነው፡፡ ስለዚህ ከሰው አንጻር ጥንታዊና ቀዳሚ ናቸው ማለት ነው፡፡ ቀጣዩ አንቀጽ ይህንን ይገልጻል፡-
” وَإِذْ قَالَ رَبُّكَ لِلْمَلَائِكَةِ إِنِّي جَاعِلٌ فِي الْأَرْضِ خَلِيفَةً قَالُوا أَتَجْعَلُ فِيهَا مَنْ يُفْسِدُ فِيهَا وَيَسْفِكُ الدِّمَاءَ وَنَحْنُ نُسَبِّحُ بِحَمْدِكَ وَنُقَدِّسُ لَكَ قَالَ إِنِّي أَعْلَمُ مَا لَا تَعْلَمُونَ ” سورة البقرة 30
“(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤» ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ (እነርሱም) «እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» አሉ፡፡ (አላህ) «እኔ የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ» አላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡30)፡፡
ጌታ አላህ በዚህ አንቀጽ ስር ለመላእክት አንድ ነገር እየነገራቸው (እያሳወቃቸው) ነው፡፡ እሱም ሰው (አደም) የሚባለውን ፍጥረት በምድር ላይ እንደሚፈጥረውና ምትክም (አንዱ ሲሞት ሌላው የሚተካ) እንደሚያደርገው የሚያስረዳ ነው፡፡ አላህ ይህንን ለመላእክት መንገሩና ማሳወቁ፡ እነሱ በመፈጠር ቀዳሚ መሆናቸውን ያሳያል ማለት ነው፡፡
ረ/ እጅግ ግዙፍ ናቸው፡-
መላእክት ትልቀታቸው ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ሰው በሜትር የሚለኩ አናሳዎች አይደሉም፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ጉልበታቸውም ሰው ከሚገምተው በላይ ነው፡፡ ይህንን ከሚያመላክቱት መካከል፡-
1/ የሉጥ ህዝቦች ጥፋት፡- አላህ ሉጥ (ዐለይሂ-ሰላም) የነበረባትን መንደር አማኞቹን በማትረፍ ከሀዲዎቹን ያጠፋቸው በመላእክት በኩል ነው፡፡ መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ያችን መንደር ከነምድርዋና ነዋሪዎቿ በአንድ የክንፉ ጫፍ በማንሳት ወደ ሰማይ አደረሳቸው፡፡ በቅርቢቷ ሰማይ የሚገኙ መላእክት የውሻዎቹንና የዶሮዎቹን ጩኸት መስማት እስኪችሉ ድረስም አቀረበው፡፡ ከዛም ምድሪቷን ገለበጣትና ወደታች ለቀቃቸው፡፡ የአላህ ቃል ይህን ክስተት ጠቅለል ባለ መልኩ እንዲህ ይገልጸዋል፡-
” فَلَمَّا جَاءَ أَمْرُنَا جَعَلْنَا عَالِيَهَا سَافِلَهَا وَأَمْطَرْنَا عَلَيْهَا حِجَارَةً مِنْ سِجِّيلٍ مَنْضُودٍ * مُسَوَّمَةً عِنْدَ رَبِّكَ وَمَا هِيَ مِنَ الظَّالِمِينَ بِبَعِيدٍ ” سورة هود 83-82
“ትእዛዛችንም በመጣ ጊዜ (ከተማይቱን) ላያዋን ከታችዋ አደረግን፤ (ገለበጥናት)፤ ተከታታይም የሆነ የሸክላ ድንጊያ በርሷ ላይ አዘነምን። ከጌታህ ዘንድ፣ ምልክት የተደረገባት ስትሆን (አዘነምናት) እርሷም ከበደለኞች ሩቅ አይደለችም።” (ሱረቱ ሁድ 11፡82-83)፡፡
2/ የሙሳ ህዝቦች አመጽ፡- ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ህዝቦቹ የተውራትን ህግ ለመቀበል አሻፈረኝ ባሉ ጊዜ፡ ጌታ አላህ መልአክን በመላክ፡ በዙሪያቸው የነበረውን ተራራ ነቅሎ ከበላያቸው እንደ-ዣንጥላ እንዲያደርገውና፡ ህጉን ከተቀበሉ ሊነሳላቸው ካልሆነም ላያቸው ላይ ሊወድቅባቸው እንደሆነ በመግለጽ አስፈራርቷቸዋል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَإِذْ نَتَقْنَا الْجَبَلَ فَوْقَهُمْ كَأَنَّهُ ظُلَّةٌ وَظَنُّوا أَنَّهُ وَاقِعٌ بِهِمْ خُذُوا مَا آتَيْنَاكُمْ بِقُوَّةٍ وَاذْكُرُوا مَا فِيهِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ ” سورة الأعراف 171
“የጡርን ተራራን ነቅለን ከበላያቸው እንደ ጥላ ኾኖ በአነሳነውና እርሱም በነርሱ ላይ ወዳቂ መኾኑን ባረጋገጡ ጊዜ (አስታውስ)፤ የሰጠናችሁን በብርታት ያዙ፤ ትጠነቀቁም ዘንድ በውስጡ ያለውን ተገንዘቡ (አልን)።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡171)፡፡
3/ የዐርሽ ተሸካሚዎች፡- ሰባት ሰማያት ከዚህ ስፋታቸውና ትልቀታቸው ጋር ‹‹ኩርሲይ›› ላይ ቢወረወሩ፡ ከኩርሲይ ትልቀት የተነሳ የሚኖራቸው ድርሻ፡ አንድ ጋሻ መሬት ላይ የተወረወረ ሰባት ሳንቲሞችን ያህል ነው፡፡ ሰባት ሰማያትን የሳንቲምን ያህል አሳንሶ የዋጠው ትልቁ ኩርሲይ ደግሞ ከዚህ ስፋቱ ጋር ‹‹ዐርሽ›› ላይ ቢወረወር፡ ከዐርሽ ትልቅነት አንጻር የሚኖረው ድርሻ፡ ሜዳ ላይ እንደተጣለ የእጅ ቀለበት ነው፡፡ (አስ-ሲልሲለቱ ሶሒሓህ 109)፡፡ ሸይኹል አልባኒይ (ረሒመሁላህ) ሶሒሕ ብለውታል፡፡
ታዲያ ‹ዐርሽ› ይህን ያህል ከሰማያትና ከኩርሲይ በላይ የሰፋና የተለቀ ፍጥረት ከሆነ፡ እሱን የሚሸከሙ መላእክትስ ምን ያህል ታላቅ ሊሆኑ ነው?
” الَّذِينَ يَحْمِلُونَ الْعَرْشَ وَمَنْ حَوْلَهُ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ وَيُؤْمِنُونَ بِهِ وَيَسْتَغْفِرُونَ لِلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا وَسِعْتَ كُلَّ شَيْءٍ رَّحْمَةً وَعِلْمًا فَاغْفِرْ لِلَّذِينَ تَابُوا وَاتَّبَعُوا سَبِيلَكَ وَقِهِمْ عَذَابَ الْجَحِيمِ ” سورة غافر 7
“እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት፣ እነዚያም በዙሪያው ያሉት፣ በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ፤በርሱም ያምናሉ፤ ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል፤ ስለዚህ ለነዚያ ለተጸጸቱት፣ መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው፣ እያሉ ለነዚያ ላመኑት ምሕረትን ይለምናሉ።” (ሱረቱ ጋፊር (ሙእሚን) 40፡7)፡፡
عَنْ جابر بن عبد الله رضي الله عنهما – :أنَّ النبيَّ -صلى الله عليه وسلم- قال : «أذِنَ لى أنْ أُحَدِّثَ عن مَلَكٍ من ملائكَةِ اللَّهِ من حَمَلَةِ العرْشِ : أنَّ مَا بينَ شَحْمَةِ أُذُنِهِ إلى عَاتِقِهِ : مَسِيرةُ سَبْعِمَائةِ عَامٍ».أخرجه أبو داود 4727. مشكاة المصابيح 5661.
ጃቢር ኢብኒ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የዐርሽ ተሸካሚ ከሆኑ የአላህ መላእክቶች ውስጥ ስለ አንዱ መልአክ እንድናገር ተፈቀደልኝ፡፡ (ይህ መልአክ) ከጆሮው አንስቶ እስከ ትከሻው ያለው ሰባት መቶ አመት ያስኬዳል” (አቡ ዳዉድ 4727፣ ሚሽካቱል-መሷቢሕ 5661)፡፡
ሱብሐነላህ!! አላህ ፍጡራን እሱን ከሚመጥኑትና ከሚገምቱት ነገር ጥራት ይገባው!! ይህ ፍጥረት የሆነው መልአክ ከጆሮው እስከ ትከሻው ሰባት መቶ

አመት ያህል ዘመን የሚፈጅ ጉዞ ካስኬደ፡ ሙሉ ማንነቱስ ምን ሊሆን ነው?
ሰ/ ፆታዊ መገለጫ የላቸውም፡-
ሌላው መላእክት ከተቀረው የአላህ ፍጥረታት የሚለዩበት አንዱ የፆታ ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ዘንድ ወንድና ሴት የሚባል ክፍፍል የለም፡፡ በዘር የሚባዙ አይደሉምና፡፡ መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) መጣ፣ ሄደ፣ ተናገረ የምንለው የቋንቋ ህግ ስለሆነ እንጂ የፆታ ጉዳይ ሆኖብን አይደለም፡፡ ስለዚህ መላእክትን በፆታ መግለጽ አይቻልም፡፡ በተለይ እነሱን በሴት ፆታ የሚገልጻቸው (ሴት ናቸው የሚል) ከኢስላም የወጣ ካፊር ይባላል፡፡ ይህ ተግባር የጣኦታዊያንና በመጨረሻው ዓለም የማያምኑ ሰዎች ስራ በመሆኑ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” وَجَعَلُوا الْمَلَائِكَةَ الَّذِينَ هُمْ عِبَادُ الرَّحْمَنِ إِنَاثًا أَشَهِدُوا خَلْقَهُمْ سَتُكْتَبُ شَهَادَتُهُمْ وَيُسْأَلُونَ ” سورة الزخرف 19
“መላክትን እነሱ የአልረሕማን ባሮች የሆኑትን ሴቶች አደረጉ፤ ሲፈጠሩ ነበሩን? መመስከራቸው በርግጥ ትጻፋለች፤ ይጠየቃሉም።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡19)፡፡
” إِنَّ الَّذِينَ لَا يُؤْمِنُونَ بِالْآخِرَةِ لَيُسَمُّونَ الْمَلَائِكَةَ تَسْمِيَةَ الْأُنْثَى* وَمَا لَهُمْ بِهِ مِنْ عِلْمٍ إِنْ يَتَّبِعُونَ إِلا الظَّنَّ وَإِنَّ الظَّنَّ لا يُغْنِي مِنَ الْحَقِّ شَيْئًا ” سورة النجم 27-28
“እነዚያ በመጨረሻይቱ ዓለም የማያምኑት፣ መላእክትን በሴት አጠራር ይጠራሉ። ለነሱም በርሱ ምንም ዕውቀት የላቸውም፤ ጥርጣሬን እንጅ ሌላን አይከተሉም፤ ጥርጣሬም ከእውነት ምንም አያብቃቃም” (ሱረቱ-ነጅም 53፡27-28)፡፡
ሸ/ ብዛታቸውን ማንም አያውቀውም፡-
የመላእክት ብዛትን ከፈጠራቸው አላህ በስተቀር ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ እጅግ ቡዙ ስለሆኑ በቢሊየንና በኳትሪሊየን ሊገለጹ አይችሉም፡፡
“… وَمَا يَعْلَمُ جُنُودَ رَبِّكَ إِلَّا هُوَ وَمَا هِيَ إِلَّا ذِكْرَى لِلْبَشَرِ” سورة المدثر 31
“…የጌታህንም ሰራዊት (ልክ) ከርሱ በቀር ማንም አያውቅም፤ እርሷም (የሰቀር እሳት) ለሠዎች መገሠጫ እንጂ ሌላ አይደለችም።” (ሱረቱል ሙደሢር 74፡31)፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከበይቲል መቅዲስ ወደ ሰማይ በወጡበት (ባረጉበት) ጊዜ፡ በሰባተኛው ሰማይ ላይ በይቱል-መዕሙር (በዒባዳ የተገነባው ቤት) ታያቸው፡፡ ከዛም ስለ ሁኔታው ጂብሪልን (ዐለይሂ-ሰላም) ጠየቁት፡፡ እሱም፡- ‹‹ይህ በይተል መዕሙር ይባላል፡፡ በየቀኑ ሰባ ሺህ መላእክቶች ለአምልኮ ተግባር ይጎበኙታል፡፤ አንዴ ጨርሰው ከወጡ (ከመላእክቶቹ ብዛት የተነሳ) ለሁለተኛ ጊዜ አይመለሱም አላቸው›› (ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት)፡፡
በይቱል መዕሙር በምድራዊው ከዕባህ አቅጣጫ የሚገኝ የሰማይ ቤት ነው፡፡ ይህ የአምልኮ ስፍራ ከተገነባበት ጊዜ አንስቶ እስከ ቂያማ ቀን ድረስ በየቀኑ ሰባ ሺህ መላእክት ለአምልኮት የሚጎበኙት ከሆነ አጠቃላይ ቁጥራቸው ስንት ሊሆን ነው እንግዲያውስ?
ቀ/ የአላህ ባሮች ናቸው፡-
ሌላው የመላእክት ተፈጥሮአዊ ማንነት ባሮች መሆናቸው ነው፡፡ መላእክትም እንደተቀረው የአላህ ፍጥረት እነሱም የአላህ ባሪያና ፍጥረት እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ልጅ የለውምና ልጁ አይደሉም፡፡ ሁሉን ቻይ ነውና ጓደኛው ወይም የስራ አጋሩ አይደሉም፡፡ እነሱ የአላህ ባሮች ናቸው፡-
” إِنْ كُلُّ مَنْ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ إِلَّا آتِي الرَّحْمَنِ عَبْدًا ” سورة مريم 93
“በሰማያትና በምድር ያለዉ ሁሉ (በትንሣኤ ቀን)፣ ለአልረሕማን ባሪያ ኾነዉ የሚመጡ እንጂ ሌላ አይደሉም።” (ሱረቱ መርየም 19፡93)፡፡
” وَقَالُوا اتَّخَذَ الرَّحْمَنُ وَلَدًا سُبْحَانَهُ بَلْ عِبَادٌ مُكْرَمُونَ ” سورة الأنبياء 26
“አልረሕማንም (ከመላእክት) ልጅን ያዘ አሉ፤ ጥራት ተገባው፤ አይደለም (መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናችው፤” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡26)፡፡
ይቀጥላል