በመላእክት ማመን ክፍል ስምንት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
350 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት ግላዊ ስሞች እና የስራ ድርሻቸው፡-
ሐ/ ዐርሽን መሸከም (ሐመለቱል ዐርሽ)፡-
ሰባት ሰማያት ከዚህ ስፋታቸውና ትልቀታቸው ጋር ‹‹ኩርሲይ›› ላይ ቢወረወሩ፡ ከኩርሲይ ትልቀት የተነሳ የሚኖራቸው ድርሻ፡ አንድ ጋሻ መሬት ላይ የተወረወረ ሰባት ሳንቲሞችን ያህል ነው፡፡ ሰባት ሰማያትን የሳንቲምን ያህል አሳንሶ የዋጠው ትልቁ ‹ኩርሲይ› ደግሞ ከዚህ ስፋቱና ትልቀቱ ጋር ‹‹ዐርሽ›› ላይ ቢወረወር፡ ከዐርሽ ትልቅነት አንጻር የሚኖረው ድርሻ፡ ሜዳ ላይ እንደተጣለ የእጅ ቀለበት ነው፡፡ (አስ-ሲልሲለቱ ሶሒሓህ 109)፡፡ ሸይኹል አልባኒይ (ረሒመሁላህ) ሶሒሕ ብለውታል፡፡
ታዲያ ‹ዐርሽ› ይህን ያህል ከሰማያትና ከኩርሲይ በላይ የሰፋና የተለቀ ፍጥረት ከመሆኑ ጋር የሚሸከሙት መላአክት ናቸው፡፡ እነዚህ መላእክቶች አላህ እንዳዘዛቸው ዐርሽን በመሸከም የጌታቸውን ትእዛዝ በመፈጸም አምልኮአቸውን ያከናውናሉ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ዐርሽን የሚሸከሙ መላእክት እንዳሉ በግልጽ እንዲህ ብሎ ይነግረናል፡-
” الَّذِينَ يَحْمِلُونَ الْعَرْشَ وَمَنْ حَوْلَهُ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ وَيُؤْمِنُونَ بِهِ وَيَسْتَغْفِرُونَ لِلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا وَسِعْتَ كُلَّ شَيْءٍ رَّحْمَةً وَعِلْمًا فَاغْفِرْ لِلَّذِينَ تَابُوا وَاتَّبَعُوا سَبِيلَكَ وَقِهِمْ عَذَابَ الْجَحِيمِ ” سورة غافر 7
“እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት፣ እነዚያም በዙሪያው ያሉት፣ በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ፤በርሱም ያምናሉ፤ ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል፤ ስለዚህ ለነዚያ ለተጸጸቱት፣ መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው፣ እያሉ ለነዚያ ላመኑት ምሕረትን ይለምናሉ።” (ሱረቱ ጋፊር (ሙእሚን) 40፡7)፡፡
ዛሬ በዱንያው ዓለም ዐርሽን የሚሸከሙት መላእክት ብዛታቸው ስንት ነው? በሚለው ላይ የኢስላም ሊቃውንት የተለያየ ሀሳብ አላቸው፡፡ የልዩነቱ መነሻም ከቁርኣንም ሆነ ከሶሒሕ ሐዲሥ በጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ መረጃ ባለመገኘቱ ነው፡፡ አብዝኃኛዎቹ አራት ናቸው የሚለውን ራእይ መርጠዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተነገሩ ሐዲሦችንም ለመረጃነት አቅርበዋል፡፡
ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ ትክክለኛ ቁጥራቸውን አላህ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እኛ ግልጽ ማስረጃ ስላልመጣልን ቁጥራቸውን ማወቅ አንችልም፡፡ አራት እንደሆኑ የሚናገሩ ማስረጃዎች ለማስረጃነት ብቁ ያልሆኑ ደካማ ሐዲሦች በመሆናቸው በነሱ መሰረት መናገር አንችልም ብለዋle፡፡ የተሻለውም ራእይ ወላሁ አዕለም ብሎ ማለፉ ነው፡፡
ነገ የውሙል ቂያም ደግሞ የሚሸከሙት ስምንት እንደሆኑ ቁርኣን እንዲህ ይናገራል፡-
” وَالْمَلَكُ عَلَى أَرْجَائِهَا وَيَحْمِلُ عَرْشَ رَبِّكَ فَوْقَهُمْ يَوْمَئِذٍ ثَمَانِيَةٌ ” سورة الحاقة 17
“መላእክትም በየጫፎችዋ ላይ ይሆናሉ የጌታህንም ዐርሽ በዚያ ቀን ስምንት መላእክት ከበላያቸው ይሸከማሉ።” (ሱረቱ አል-ሐቃህ 69፡17)፡፡
መ/ የጀነት ዘበኞች (ኸዘነቱል ጀንናህ)፡-
ጀነት ወደፊት የምትዘጋጅና የምትፈጠር የጸጋ ዓለም ሳትሆን፡ ቀድማ የተፈጠረች ለአማኞችም በየረመዷኑ በሮቿ እየተከፈቱ እሷን ለሚፈልጉ ሰዎች በእምነትና በመልካም ተግባር እንዲሽቀዳደሙ የምትጋብዝ ከአላህ ዘንድ ለመልካም ባሮቹ የተዘጋጀች የክብር ስጦታ ነች (አላህ በራሕመቱ ከነሱ ያድርገን)፡፡ ጀነት ቀድማ የተፈጠረች ለመሆኗ ቀጣዮች አንቀጾች ማስረጃ ናቸው፡-
” وَسَارِعُوا إِلَى مَغْفِرَةٍ مِنْ رَبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ ” سورة آل عمران 133
“ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ሆነች ገነት፥ አላህን ለሚፈሩ #የተዘጋጀች ስትሆን ተቻኮሉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡133)፡፡
” سَابِقُوا إِلَى مَغْفِرَةٍ مِنْ رَبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا كَعَرْضِ السَّمَاءِ وَالْأَرْضِ أُعِدَّتْ لِلَّذِينَ آمَنُوا بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ ذَلِكَ فَضْلُ اللَّهِ يُؤْتِيهِ مَنْ يَشَاءُ وَاللَّهُ ذُو الْفَضْلِ الْعَظِيمِ ” سورة الحديد 21
“ከጌታችሁ ወደ ሆነች ምሕረት ወርዷ እንደሰማይና ምድር ወርድ ወደ ሆነችም ገነት ተሽቀዳደሙ፤ ለነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ ላመኑት #ተዘጋጅታለች። ይህ የአላህ ችሮታ ነው፤ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፤ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው።” (ሱረቱል ሐዲድ 57፡21)፡፡
በነዚህ ሁለት አንቀጾች ውስጥ ‹‹ተዘጋጀች›› የሚለው ኃይለ-ቃል ጀነት ቀድማ መፈጠርዋን የሚያሳይ ነው፡፡ ወደፊት ትዘጋጃለች ሳይሆን ‹ተዘጋጀች› ተብሎ ተነግሮላታልና፡፡ እናም ይህች ጀነት ዘበኞች አሏት፡፡ ዘበኞቿ ስራቸው በውስጧ ለዘልዓለም የሚኖሩትን አማኝ የአላህ ባሪያዎች በእንኳን ደህና መጣችሁ መልካም አቀባበል መቀበል፣ የአላህ ሰላም በናንተ ላይ ይሁን በውስጧ ግቡና በጌታችሁ ጸጋ ተደሰቱ በማለት ማበሰር፣ ለጀነት እንግዶች አስፈላጊውን ነገር ማዘጋጀት ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይነበባል፡-
” وَسِيقَ الَّذِينَ اتَّقَوْا رَبَّهُمْ إِلَى الْجَنَّةِ زُمَرًا حَتَّى إِذَا جَاءُوهَا وَفُتِحَتْ أَبْوَابُهَا وَقَالَ لَهُمْ خَزَنَتُهَا سَلَامٌ عَلَيْكُمْ طِبْتُمْ فَادْخُلُوهَا خَالِدِينَ ” سورة الزمر73
“እነዚያ ጌታቸውን የፈሩት የተከፋፈሉ ጭፍሮችም ሆነው ወደ ገነት ይነዳሉ፤ በመጧትም ጊዜ፣ ደጃፎችዋ የተከፈቱ ሲሆኑ፣ ዘበኞችዋም ለነርሱ ሰላም በናንተ ላይ ይሁን፤ ተዋባችሁ፤ ዘውታሪዎች ሆናችሁ ግቧት፤ ባሏቸው ጊዜ (ይገቧታል)።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡73)፡፡
” أَفَمَنْ يَعْلَمُ أَنَّمَا أُنْزِلَ إِلَيْكَ مِنْ رَبِّكَ الْحَقُّ كَمَنْ هُوَ أَعْمَى إِنَّمَا يَتَذَكَّرُ أُولُو الْأَلْبَابِ * الَّذِينَ يُوفُونَ بِعَهْدِ اللَّهِ وَلَا يَنْقُضُونَ الْمِيثَاقَ * وَالَّذِينَ يَصِلُونَ مَا أَمَرَ اللَّهُ بِهِ أَنْ يُوصَلَ وَيَخْشَوْنَ رَبَّهُمْ وَيَخَافُونَ سُوءَ الْحِسَابِ * وَالَّذِينَ صَبَرُوا ابْتِغَاءَ وَجْهِ رَبِّهِمْ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَأَنْفَقُوا مِمَّا رَزَقْنَاهُمْ سِرًّا وَعَلَانِيَةً وَيَدْرَءُونَ بِالْحَسَنَةِ السَّيِّئَةَ أُولَئِكَ لَهُمْ عُقْبَى الدَّارِ * جَنَّاتُ عَدْنٍ يَدْخُلُونَهَا وَمَنْ صَلَحَ مِنْ آبَائِهِمْ وَأَزْوَاجِهِمْ وَذُرِّيَّاتِهِمْ وَالْمَلَائِكَةُ يَدْخُلُونَ عَلَيْهِمْ مِنْ كُلِّ بَابٍ * سَلَامٌ عَلَيْكُمْ بِمَا صَبَرْتُمْ فَنِعْمَ عُقْبَى الدَّارِ ” سورة الرعد 24-19
“ከጌታህ ወዳንተ የተወረደው እውነት መሆኑን የሚያውቅ ሰው፥ እንደዚያ እርሱ ዕውር እንደ ሆነው ሰው ነውን? የሚገሠጹት የአእምሮ ባለ ቤቶች ብቻ ናቸው። እነዚያ በአላህ ቃል ኪዳን የሚሞሉ፥ የጠበቀውንም ኪዳን የማያፈርሱ ናቸው። እነዚያም አላህ እንዲቀጠል በርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቀጥሉ፥ ጌታቸውንም የሚያከብሩ፥ መጥፎንም ቁጥጥር የሚፈሩ ናቸው። እነዚያም የጌታቸውን ውዴታ ለመፈለግ የታገሡ፥ ሶላትንም አዘውትረው የሰገዱ እኛ ከሰጠናቸው ሲሳይም በምስጢርም ሆነ በግልጽ የመጸወቱ፥ ክፉውንም ነገር በበጎ የሚገፈትሩ ናቸው፤ እነዚያ ለነሱ መጨረሻይቱ ምስጉን አገር አለቻቸው። (እርሷም) የመኖሪያ ገነቶች ናት፤ ይገቡባታል፤ ከአባቶቻቸውም ከሚስቶቻቸውም ከዝርያቸውም መልካም የሠራ ሰው (ይገባታል)፤ መላእክትም በነሱ ላይ ከየደጃፉ ሁሉ ይገባሉ። ሰላም ለናንተ ይሁን (ይህ ምንዳ) በመታገሣችሁ ነው የመጨረሻይቱም አገር ምን ታምር (ይሏቸዋል)።” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡19-24)፡፡
ሠ/ የጀሀነም ዘበኞች (ኸዘነቱ-ናር)፡-
ጀሀነም ወደፊት የምትዘጋጅና የምትፈጠር የቅጣት ዓለም ሳትሆን፡ ቀድማ የተፈጠረች ለአማኞችም በየረመዷኑ በሮቿ እየተከረቸሙ ከሷ መራቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ከክህደትና ኃጢአት ተግባር እራሳቸውን እንዲያርቁ የምታስታውስ፣ ለከሀዲያንና ለበዳዮች ደግሞ ተገቢ የሆነውን የስራቸውን ዋጋ በቅጣት ለማቅመስ ከአላህ ዘንድ ለሰይጣንና ተከታዮቹ የተዘጋጀች የቅጣት ስፍራ ነች (አላህ በራሕመቱ ከሷ ነጃ ይበለን)፡፡ ጀሀነምም እንደ ጀነት ቀድማ የተፈጠረች ለመሆኗ ቀጣዮች አንቀጾች ማስረጃ ናቸው፡-
” وَإِنْ كُنْتُمْ فِي رَيْبٍ مِمَّا نَزَّلْنَا عَلَى عَبْدِنَا فَأْتُوا بِسُورَةٍ مِنْ مِثْلِهِ وَادْعُوا شُهَدَاءَكُمْ مِنْ دُونِ اللَّهِ إِنْ كُنْتُمْ صَادِقِينَ * فَإِنْ لَمْ تَفْعَلُوا وَلَنْ تَفْعَلُوا فَاتَّقُوا النَّارَ الَّتِي وَقُودُهَا النَّاسُ وَالْحِجَارَةُ أُعِدَّتْ لِلْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 24-23
“በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ፡፡ እውነተኞችም እንደኾናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ፡፡ (ይህንን) ባትሠሩ ፈጽሞም አትሠሩትምና ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ድንጋዮች የኾነችውን እሳት ተጠበቁ፤ ለከሓዲዎች #ተደግሳለች፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡23-24)፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَأْكُلُوا الرِّبَا أَضْعَافًا مُضَاعَفَةً وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ * وَاتَّقُوا النَّارَ الَّتِي أُعِدَّتْ لِلْكَافِرِينَ ” سورة آل عمران 131-130
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ አራጣን የተነባበሩ እጥፎች ሲሆኑ፥ አትበሉ፤ ትድኑም ዘንድ አላህን ፍሩ። ያችንም ለከሐዲዎች #የተደገሰችዉን እሳት ተጠንቀቁ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 130-131)፡፡
በነዚህ ሁለት አንቀጾች ውስጥ ‹‹ተደገሰች›› የሚለው ኃይለ-ቃል ጀሀነም ቀድማ መፈጠርዋን የሚያሳይ ነው፡፡ ወደፊት ትዘጋጃለች ሳይሆን ‹ተደገሰች› ተብሎ ተነግሮላታልና፡፡ እናም ይህች ጀሀነም ዘበኞች አሏት፡፡ ዘበኞቿ ስራቸው በውስጧ ለዘልዓለም የሚኖሩትን ከሀዲያንና አመጸኛ የአላህ ባሪያዎችን በወቀሳና በትችት መጎንተልና መቅጣት፣ በውስጧ ግቡና የጌታችሁን ቅጣት ቅመሱ በማለት ማስቆጨት፣ መልክተኞች ተልኮላችሁ፡ መጽሐፍት ወርዶላችሁ ምን ከሀዲ አደረጋችሁ? በማለት መውቀስ ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይነበባል፡-
” وَسِيقَ الَّذِينَ كَفَرُوا إِلَى جَهَنَّمَ زُمَرًا حَتَّى إِذَا جَاءُوهَا فُتِحَتْ أَبْوَابُهَا وَقَالَ لَهُمْ خَزَنَتُهَا أَلَمْ يَأْتِكُمْ رُسُلٌ مِنْكُمْ يَتْلُونَ عَلَيْكُمْ آيَاتِ رَبِّكُمْ وَيُنْذِرُونَكُمْ لِقَاءَ يَوْمِكُمْ هَذَا قَالُوا بَلَى وَلَكِنْ حَقَّتْ كَلِمَةُ الْعَذَابِ عَلَى الْكَافِرِينَ * قِيلَ ادْخُلُوا أَبْوَابَ جَهَنَّمَ خَالِدِينَ فِيهَا فَبِئْسَ مَثْوَى الْمُتَكَبِّرِينَ ” سورة الزمر72-71
“እነዚያ የካዱትም፣ የተከፋፈሉ ጭፍሮች ሆነው ወደ ገሀነም ይነዳሉ፤ በመጧትም ጊዜ ደጃፎችዋ ይከፈታሉ፤ ዘበኞችዋም ከናንተ የሆኑ መልክተኞች የጌታችሁን አንቀጾች በናንተ ላይ የሚያነቡላችሁ የዚህንም ቀን መገናኘት የሚያስጠነቅቋችሁ አልመጡዋችሁምን? ይሏቸዋል፤ የለም መጥተውናል፤ግን የቅጣቲቱ ቃል በከሐዲዎች ላይ ተረጋገጠች ይላሉ። የገሀነም ደጃፎች በውስጧ ዘውታሪዎች ስትሆኑ ግቡ፤ የትዕቢተኞችም መኖሪያ ምን ትከፋ! ይባላሉ።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡71-72)፡፡
የጀሀነም ዘበኞች አለቃ ‹ማሊክ› (ዐለይሂ-ሰላም) በመባል ይታወቃል፡-
” وَنَادَوْا يَا مَالِكُ لِيَقْضِ عَلَيْنَا رَبُّكَ قَالَ إِنَّكُمْ مَاكِثُونَ ” سورة الزخرف 77
“ማሊክ ሆይ! ጌታህ በኛ ላይ (በሞት) ይፍረድ እያሉ ይጣራሉም፤ እናንተ (በቅጣቱ ውስጥ) ዘላለም ኗሪዎች ናችሁ ይላቸዋል።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡77)፡፡
ይቀጥላል