በመላእክት ማመን ክፍል ሰባት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
350 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
5/ የመላእክት ግላዊ ስሞች እና የስራ ድርሻቸው፡-
ለ/ ጥሩንባ መንፋት፡-
ይህች ምድራዊ ዓለም ጊዜያዊና ጠፊ ነች፡፡ ስለሆነችም ነው አላህ ‹‹ዱንያ›› ብሎ የሰየማት፡፡ የቃሉ ትርጉም፡- ቅርቢቷ ማለት ነው፡፡ ‹‹ደና›› (ቀረበ) ከሚለው ግስ ነው የተራባችው፡፡ ለመጥፋት የቀረበች ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ምድራዊ ቆይታችን ዘላለማዊ ባለመሆኑ ከተወሰነ ቀይታ በኋላ እኛም በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይጠፋል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” كُلُّ مَنْ عَلَيْهَا فَانٍ * وَيَبْقَى وَجْهُ رَبِّكَ ذُو الْجَلَالِ وَالْإِكْرَامِ ” سورة الرحمن 27-26
“በርሷ (በምድር) ላይ ያለው ሁሉ ጠፊ ነው። የልቅናና የልግሥና ባለቤት የሆነው የጌታህ ፊትም ይቀራል። (አይጠፋም)።” (ሱረቱ-ራሕማን 55፡26-27)፡፡
” وَلَا تَدْعُ مَعَ اللَّهِ إِلَهًا آخَرَ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ كُلُّ شَيْءٍ هَالِكٌ إِلَّا وَجْهَهُ لَهُ الْحُكْمُ وَإِلَيْهِ تُرْجَعُونَ ” سورة القصص 88
“ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትግገዛ፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገሩ ሁሉ ከአላህ በቀር ጠፊ ነው፡፡ ፍርዱ የርሱ፤ ብቻ ነው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡88)፡፡
ይህች ዓለም ጠፊ መሆኗ የማይቀር መሆኑን ከተስማማን፡ ቀጣዩ ነጥብ እንዴት ነው የምትጠፋው? የሚለው ነው፡፡ ከአላህ ቃልና ከመልክተኛው ሐዲሥ በተገኘው መረጃ መሰረት በመጨረሻው ሰዓት ላይ አንድ መልአክ ከጌታው በታዘዘው መሰረት፡ አንዴ ጥሩንባውን ሲነፋው በሰማይም ሆነ በምድር ያለ ፍጥረት በጠቅላላ (አላህ የነጠለው ሲቀር) ይወድቃል ይሞታል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ዳግሞ በአላህ ትእዛዝ ሲነፋ ሙታን በጠቅላላ ከመቃብራቸው ይወጣሉ ይነሳሉ፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ያስተምራል፡-
” وَنُفِخَ فِي الصُّورِ فَصَعِقَ مَنْ فِي السَّمَاوَاتِ وَمَنْ فِي الْأَرْضِ إِلَّا مَنْ شَاءَ اللَّهُ ثُمَّ نُفِخَ فِيهِ أُخْرَى فَإِذَا هُمْ قِيَامٌ يَنْظُرُونَ ” سورة الزمر 68
“በቀንዱም ይነፍፋል፤ በሰማያት ውስጥ ያለው ፍጡርና በምድርም ውስጥ ያለው ፍጡር ሁሉ፣ አላህ የሻው ሲቀር በድንጋጤ ይሞታል፤ ከዚያም በርሱ ሌላ (መነፋት) ይነፋል፤ ወዲያውም እነርሱ (የሚሠራባቸውን) የሚጠባበቁ ሆነው ቋሚዎች ይሆናሉ።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡68)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሰረት በጥሩንባው (በቀንዱ) የሚነፋው ሁለት ጊዜ መሆኑን እንረዳለን፡፡ የመጀመሪያው ለሰዓቲቷ መቆም ፍጥረታት በሙሉ (አላህ የሻው ሲቀር) ማለቃቸውና መሞታቸው ሲሆን፡ ሁለተኛው ደግሞ ሙታን ነፍስ ዘርተው ዳግም መነሳታቸውና መቀስቀሳቸውን ለማብሰር ነው፡፡
በሐዲሥ ላይም እንደተረጋገጠው በጡሩንባው(በቀንዱ) የሚነፋው ሁለት ጊዜ ነው፡፡ በሁለቱ መነፋት መሀል ያለውን ክፍት ጊዜ ልኩ ምን ያህል እንደሆነ ከአላህ በስተቀር ማንም አያውቀውም፡፡ ሐዲሡ እንዲህ ይላል፡-
عن أبي هريرة رضي الله عنه قال : قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: ما بين النفختين أربعون . قال : أربعون يوما ؟ قال : أبيتُ ، قال : أربعون شهراً ؟ قال : أبيت ، قال : أربعون سنة ؟ قال : أبيت . قال : ثم يُنزل اللهُ من السماء ماء فينبتون كما ينبت البقل ليس من الإنسان شيء إلا يبلى إلا عظماً واحداً وهو عجْب الذنَب ومنه يركب الخلق يوم القيامة . رواه البخاري ( 4651 ) ومسلم ( 2955 ) .
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በሁለቱ መነፋት መሀከል ያለው ጊዜ አርባ ነው፡፡ ሰዎችም (አቡ ሁረይራን) አርባ ቀን ነውን? ሲሉት፡ ከመናገር እምቢ አልኩኝ! አርባ ወር ነውን? ሲሉት፡ ከመናገር እምቢ አልኩኝ! አርባ ዓመት ነውን? ሲሉት፡ ከመናገር እምቢ አልኩኝ! በማለት መለሰላቸው፡፡ ከዛም (ከዐርባው በኋላ) ከሰማይ (ከዳመና) ውሀን ወደ ምድር ያወርዳል፡፡ ሙታንም ቡቃያ እንደሚበቅለው የበሰበሰው አካላቸው ዳግም መብቀል ይጀምራል፡፡ ከሰው ሰውነት ውስጥ ‹ዐጅቡ-ዘነብ› ከተሰኘው አጥንት በስተቀር ያልበሰበሰ ምንም የለም፡፡ ከሱ ነው ሰው የቂያም ቀን ወደ ሰውነቱ ተመልሶ እንዲመጣ የሚቀናጀው፡፡” (ቡኻሪይ 4651፣ ሙስሊም 2955)፡፡
ከዚህ ሐዲሥ የምንወስዳቸው ብዙ ቁም-ነገራት አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
1/ በጥሩንባው (በቀንዱ) የሚነፋው ሁለት ጊዜ መሆኑን፡፡
2/ በሁለቱ መነፋቶች መሐከል ያለው ክፍተት አርባ መሆኑን፡፡ ነገር ግን ይህ አርባ የተባለው፡ ለቀን ይሁን ለወር ወይም ለዓመት በግልጽ የተነገረ ነገር ባለመሆኑና፡ አቡ ሁረይራም (ረዲየላሁ ዐንሁ) ሲጠየቅ ቀን ነው፣ ወር ነው፣ ዓመት ነው ብሎ በአንዳቸው ላይ ላለመናገር እምቢታን ማሳየቱ ጉዳዩን ከአላህ በስተቀር የሚያውቀው የለም ወደሚለው ድምዳሜ ይመራናል፡፡
3/ በሁለተኛው መነፋት ሰዓት፡ ሙታን ከመቃብራቸው ዳግም እንደሚነሱና፡ አነሳሳቸውም ልክ ቡቃያ እንደሚበቅለው፡ እነሱም የበሰበሰውና አፈር የሆነው ገላቸው ወደቦታው ተመልሶ እንደሚበቅል ነው ማለት ነው፡፡
4/ ሰው ሁሉ ከሞተ በኋላ ወደ አፈር እንደሚመለስና፡ አፈር እንደሚበላው ከሐዲሡ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን በሌሎች ሐዲሦች እንደተረጋገጠው ምድር የነሱን ገላ ከመብላት እርም የተደረገባት ክቡራን የአላህ ፍጥረቶች አሉ፡፡ እነዚህም ነቢያት ናቸው፡፡
عَنْ أَوْسِ بْنِ أَوْسٍ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- « إِنَّ مِنْ أَفْضَلِ أَيَّامِكُمْ يَوْمَ الْجُمُعَةِ فِيهِ خُلِقَ آدَمُ وَفِيهِ قُبِضَ وَفِيهِ النَّفْخَةُ وَفِيهِ الصَّعْقَةُ فَأَكْثِرُوا عَلَىَّ مِنَ الصَّلاَةِ فِيهِ فَإِنَّ صَلاَتَكُمْ مَعْرُوضَةٌ عَلَىَّ ». قَالَ قَالُوا يَا رَسُولَ اللَّهِ وَكَيْفَ تُعْرَضُ صَلاَتُنَا عَلَيْكَ وَقَدْ أَرِمْتَ يَقُولُونَ بَلِيتَ. فَقَالَ « إِنَّ اللَّهَ عَزَّ وَجَلَّ حَرَّمَ عَلَى الأَرْضِ أَجْسَادَ الأَنْبِيَاءِ ». رواه أبو داود (1047) وصححه الألباني في صحيح أبي داود .
አውስ እብኑ አውስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከሳምንቱ ቀናቶቻችሁ ሁሉ በላጩ የጁሙዓ ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን (አባታችን) አደም ተፈጠረ፣ በዚሁ ቀን ሞተ፣ በዚሁ ቀን በቀንዱ (በጡሩንባው) በመነፋት ፍጥረት በጠቅላላ (አላህ የሻው ሲቀር) ይጠፋል፣ በዚሁ ቀን ቂያማህ ይቆማል፡፡ ስለዚህም በዚህ ቀን በኔ ላይ ሶላዋትን አብዙ፡፡ የናንተ ሶላዋት እኔ ዘንድ ትቀርብልኛለችና፡፡ (ሶሓቦቹም ‹ረዲየላሁ ዐንሁም›)፡- አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የኛ ሶላዋት በርሶ ላይ አፈር ከሆኑ በኋላ እንዴት ነው የሚደርሶት? በማለት ጠየቁ፡፡ እሳቸውም፡-‹‹አላህ የነቢያትን አካል በምድር ላይ (እንዳትበላ) እርም አድርጎባታል›› በማለት መለሱ” (አቡ ዳዉድ 1047)፡፡
የማሊኪይ መዝሀብ ተከታይ የሆኑት ኢብኑ ዐብዲል-በር (ረሒመሁላህ) በተጨማሪ የሹሀዳእ (የሰማእታትን) አካል ምድር እንደማትበላው መረጃ አልለ በማለት ይጠቁማሉ፡፡ ወላሁ አዕለም (አት-ተምሂድ 18/173)፡፡
5/ አፈር ከምትበላቸው የሰውነት ክፍል ውስጥ አንድ ልትበላው የማትችለው ክፍል አልለ፡፡ እሱም ‹ዐጅቡ-ዘነብ› ይባላል፡፡ በእንግሊዝኛው (Tail bone) ይመስለኛል ወላሁ አዕለም፡፡ ከጀርባ አጥንታችን መጨረሻ ላይ ያለው ትንሹ ክፍል ማለት ነው፡፡
ታዲያ ይህንን ኃላፊነት በመውሰድ እንዲነፋ በታዘዘ ሰዓት በጡሩንባው የሚነፋው መልአክ ኢስራፊል (ዐለይሂ-ሰላም) በመባል ይጠራል፡፡ ስለዚህ መልአክ የአላህ መልክተኛ እንዲህ ይነግሩናል፡-
عن أبي هريرة رضي الله عنه قال : قال رسول الله صلى الله عليه و سلم : إن طرف صاحب الصور مذ وكل به مستعد ينظر نحو العرش مخافة أن يؤمر قبل أن يرتد إليه طرفه كأن عينيه كوكبان دريان هذا حديث صحيح الإسناد و لم يخرجاه. رواه الحاكم في المستدرك.

ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የቀንዱ (የጥሩንባው) ባለቤት አይኑን ዝቅ አድርጎ ድንገት በዛው ሰዓት ብታዘዝስ በሚል ፍራቻ ኃላፊነት ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ እይታውን ወደ ዐርሽ በማድረግ፡ ከአሁን አሁን ታዘዝኩ ብሎ ከመጠባበቅ ለአፍታ እንኳ አልተወገደም…” (ሓኪም አል-ሙስተድረክ 8676)፡፡
ሱብሐነላህ! ጌታውን አላህን እንዴት እንደሚፈራው፡፡ ያ ረብ አንተን መፍራትን በግልጽም በስውርም ወፍቀን፡፡