በመላእክት ማመን ክፍል ሁለት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
464 Views

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
2/ የመላእክት ተፈጥሮአዊ ገጽታ፡-
በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ በጥቅሉ በመላእክት ማመን እንደሚገባን፡ በነሱ ማመንም ከእምነት ማእዘናት ውስጥ አንዱ መሆኑን እና ይህን እምነት አልቀበልም ብሎ የካደና ያስተባበለ ሰው ከኢስላም አጥር የወጣ ካፊር እንደሚሰኝ ተመልክተናል፡፡
በመጨረሻም በነሱ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነና ምን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በቀጣዩ ክፍል እናየዋለን ባልኩት መሰረት ቀጣዩን ክፍል ይዤ ቀርቤአለሁና ይከታተሉ፡-
ሀ/ ከኑር (ብርሀን) የተፈጠሩ ናቸው፡-
መላእክት የተፈጠሩት ከብርሀን ነው፡፡ እንደ ሰው ከአፈር ወይም እንደ ጂንኒ ከእሳት ነበልባል አይደለም የተሰሩት፡፡ ይህን በተመለከተ ቀጣዩ ሐዲሥ እንዲህ ይለናል፡-
عَنْ عَائِشَةَ قَالَتْ قَالَ رَسُول اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- :« خُلِقَتِ الْمَلاَئِكَةُ مِنْ نُورٍ وَخُلِقَ الْجَانُّ مِنْ مَارِجٍ مِنْ نَارٍ وَخُلِقَ آدَمُ مِمَّا وُصِفَ لَكُمْ ». رَوَاهُ مُسْلِمٌ
የምእመናን እናት፡ እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንደነገረችን፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “መላእክት ከብርሀን ተፈጠሩ፡፡ ጃን (የጂንኖች አባት ኢብሊስ) ከእሳት ነበልባል ተፈጠረ፡፡ አደም ለናንተ (በቁርኣን) እንደተነገራችሁ (ከአፈር) ተፈጠረ” (ሙስሊም 2996)፡፡
ለ/ ክንፍ አላቸው፡-
አላህ መላእክትን የክንፍ ባለቤት ያደረገ ነው፡፡ ባለ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት…ስድስት መቶ ድረስ በብዛቱ አንዱ ከሌላው የሚለያዩበት የሆነ ክንፍ አላቸው፡፡ ክንፍ ሲባል ግን በበራሪ አእዋፋት ላይ የምናየው ወይም በአንዳንድ እምነቶች ዘንድ በእጅ የተሰራውን ምስል ማለት አይደለም፡፡ መላእክትን በተፈጥሮአዊ ቅርጻቸው ካላየናቸው ስለ ክንፋቸውም ገለጻ መስጠት አንችልም፡፡ ምሣሌ መስጠትም አይሆንም፡፡ ክንፍ እንዳላቸው ግን በአላህ ቃልና በመልክተኛው ሐዲሥ እንዲህ ስለተነገረን እኛም ቃሉን አምነን እንናገራለን፡-
” الْحَمْدُ لِلَّهِ فَاطِرِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ جَاعِلِ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا أُولِي أَجْنِحَةٍ مَثْنَى وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ يَزِيدُ فِي الْخَلْقِ مَا يَشَاءُ إِنَّ اللَّهَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ ” فاطر 1
“ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሦስት ሦስትም፣ ባለ አራት አራትም፣ ክንፎች የሆኑ መልክተኞች አድራጊ፣ ለሆነው አላህ ይግባው፤ በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ቻይ ነውና።” (ሱረቱ ፋጢር 35፡1)፡፡
‹‹በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል›› የሚለው ኃይለ-ቃል አንደኛው ትርጉሙ፡ ይህንኑ የክንፍ መጠን ለሚሻው መልአክ ከአራትም በላይ ጨምሮ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ነው፡፡ ይበልጥ ደግሞ ቀጣዩ ሐዲሥ እውነታነቱን እንዲህ ያጎላዋል፡-
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ ابن مسعود رضي الله عنه قَالَ:- ” رَأَى رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ جِبْرِيلَ فِي صُورَتِهِ وَلَهُ سِتُّ مِائَةِ جَنَاحٍ كُلُّ جَنَاحٍ مِنْهَا قَدْ سَدَّ الْأُفُقَ…” رواه البخاري 4856 والترمذي 3237.
ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መልአኩ ጂብሪልን (ዐለይሂ-ሰላም) በተፈጥሮአዊ ማንነቱ ለርሱ ስድስት መቶ ክንፍ ያለው ሆኖ ተመልክተውታል፡፡ እያንዳንዱ ክንፍ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ያለውን በርግጥም ሸፍኖት ነበር” (ቡኻሪይ 4856፣ ቲርሚዚይ 3237)፡፡
ሐ/ በሰው መመሰል ይችላሉ፡-
ሌላው ተፈጥሮአዊ ችሎታቸው ነው፡፡ መላእክት በአላህ ፈቃድና በሱ ይሁንታ፡ ማንነታቸው ሳይቀየር በሰው ተመስለው መገኘት ይችላሉ፡፡ ያም አላህ ለሚፈልገው ዓላማና ጥበብ እንጂ ለሰርከስ ወይም ለሾው ተግባር አይደለም፡፡ ሰው ከተመሰሉባቸው አጋጣሚዎች መካከል፡-
1/ የኢብራሂም እንግዶች፡- ነቢዩላህ ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) በሐጀር (ዐለይሃ-ሰላም) በኩል ብቻ የመጀመሪያ ልጁን ኢስማዒልን (ዐለይሂ-ሰላም) ወልዶ ነበር፡፡ ኋላ ላይ አላህ በሚስቱ በሳረት (ዐለይሃ-ሰላም) በኩል ማኅፀኗን በመክፈት ተጨማሪ ልጅን (ኢስሐቅን) ሊሰጠው ሲፈልግ መላእክትን እግረ መንገድ አብሳሪ አድርጎ ልኮለታል፡፡
እነዚህ መላእክትም ዋና ተልኮአቸው የሉጥ ህዝቦችን በክህደታቸውና በአመጻቸው (የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መፈፀም) ምክንያት ከምድረ-ገጽ ማጥፋት ነበር፡፡ ወደ ኢብራሂምና ሉጥ (ዐለይሂማ-ሰላም) ሲመጡ ግን በሰው ተመስለው ነበር የመጡት፡፡ ስለሆነም ኢብራሂም ባያቸው ጊዜ ወዲያውኑ ወደቤት አስገብቶ የሚበላ ነገር አቀረበላቸው፡፡ መላእክቱ ግን ያቀረበውን ነገር ለመብላት እጃቸውን አልዘረጉም፡፡
” وَلَقَدْ جَاءَتْ رُسُلُنَا إِبْرَاهِيمَ بِالْبُشْرَى قَالُوا سَلَامًا قَالَ سَلَامٌ فَمَا لَبِثَ أَنْ جَاءَ بِعِجْلٍ حَنِيذٍ * فَلَمَّا رَأَى أَيْدِيَهُمْ لَا تَصِلُ إِلَيْهِ نَكِرَهُمْ وَأَوْجَسَ مِنْهُمْ خِيفَةً قَالُوا لَا تَخَفْ إِنَّا أُرْسِلْنَا إِلَى قَوْمِ لُوطٍ * وَامْرَأَتُهُ قَائِمَةٌ فَضَحِكَتْ فَبَشَّرْنَاهَا بِإِسْحَاقَ وَمِنْ وَرَاءِ إِسْحَاقَ يَعْقُوبَ ” سورة هود 71-69
“መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን በ(ልጅ) ብስራት በእርግጥ መጡት፤ ሰላም አሉት፤ ሰላም አላቸው፤ ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ፤ እጆቻቸውም ወደርሱ የማይደርሱ መሆናቸውን ባየ ጊዜ፣ ሸሻቸው፤ ከነሱም ፍርሃት ተሰማው፤፦ አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና አሉት። ሚስቱም የቆመች ስትሆን (አትፍራ አሉት) ሳቀችም፤ በኢስሐቅም አበሰርናት፤ ከኢስሐቅም በኋላ (በልጁ) በያዕቁብ (አበሰርናት)።” (ሱረቱ ሁድ 11፡69-71)፡፡
2/ የመርየም እንግዳ፡- የመላእክት አለቃ የሆነው መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ወደ መርየም ተልኮ የልጅ ብስራትን በድንግልናዋ እንደምታገኝ እንዲነግራት ከጌታው ታዟል፡፡ እሱም ትእዛዝን ተቀብሎ ወደሷ በመጣ ጊዜ በተፈጥሮአዊ ቅርጹ መልአክ ሆኖ ሳይሆን፡ በሰው ተመስሎ ነበር የመጣው፡-
” وَاذْكُرْ فِي الْكِتَابِ مَرْيَمَ إِذِ انْتَبَذَتْ مِنْ أَهْلِهَا مَكَانًا شَرْقِيًّا * فَاتَّخَذَتْ مِنْ دُونِهِمْ حِجَابًا فَأَرْسَلْنَا إِلَيْهَا رُوحَنَا فَتَمَثَّلَ لَهَا بَشَرًا سَوِيًّا * قَالَتْ إِنِّي أَعُوذُ بِالرَّحْمَن

ِ مِنْكَ إِنْ كُنْتَ تَقِيًّا * قَالَ إِنَّمَا أَنَا رَسُولُ رَبِّكِ لِأَهَبَ لَكِ غُلَامًا زَكِيًّا ” سورة مريم 19-16
“በመጽሐፉ ዉስጥ መርየምንም ከቤተ ሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለየች ጊዜ (የኾነዉን ታሪኳን) አዉሳ። ከነሱም መጋረጃን አደረገች፣ መንፈሳችንንም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን፤ ለርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት። ፦ እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ፤ ጌታህን ፈሪ እንደ ኾንክ፣ (አትቅረበኝ) አለች። ፦ እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ፣ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት።” (ሱረቱ መርየም 19፡16-19)፡፡
3/ የወዳጅ ዚያራ፡- ለአላህ ብሎ የወደደውን አንድ ሙስሊም ወንድሙን ለመዘየር (ለመጎብኘት) የሄደው ወጣት ዘንድ የተከሰተ ክስተት ነው፡-
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ، عَنْ رَسُولِ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : ” أَنَّ رَجُلا زَارَ أَخًا لَهُ فِي قَرْيَةٍ ، فَأَرْصَدَ اللَّهُ عَلَى مَدْرَجَتِهِ مَلَكًا ، فَقَالَ : أَيْنَ تُرِيدُ ؟ فَقَالَ : أُرِيدُ أَخًا لِي فِي هَذِهِ الْقَرْيَةِ . فَقَالَ : هَلْ لَهُ عَلَيْكَ مِنْ نِعْمَةٍ تَرُبُّهَا ؟ قَالَ : لا ، إِلا أَنِّي أُحِبُّهُ فِي اللَّهِ . قَالَ : إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكَ بِأَنَّ اللَّهَ تَبَارَكَ وَتَعَالَى أَحَبَّكَ كَمَا أَحْبَبْتَهُ ” رَوَاهُ مُسْلِمٌ
አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ አሉ፡- “አንድ ሰው በአንድ መንደር የሚኖር ሙስሊም ወንድሙን ለመጎብኘት ሄደ፡፡ አላህም በዚህ ሰው ጉዞ ላይ በመንገዱ የሚጠብቀው መልአክን ላከበት፡፡ ከዛም መልአኩ፡- ‹‹የት ትሄዳለህ?›› አለው፡፡ ሰውየውም፡- ‹‹በዚህ መንደር ውስጥ አንድ ወንድም አለኝ!›› በማለት መለሰለት፡፡ መልአኩም፡- ‹‹ከሱ የምታገኘው ጥቅም አለህን?›› ሲለው፡ እሱም፡- ‹‹የለኝም! ብቻ እኔ ለአላህ ብዬ ስለወደድኩት ነው የምጎበኘው›› አለው፡፡መልአኩም፡- ‹‹እኔ ከአላህ ዘንድ ወደ አንተ የተላክሁ መልክተኛው ነኝ፡፡ ሰውየውንም ለአላህ ብለህ እንደወደድከው አላህም አንተን እንደወደደህ ልነግርህ (ተልኬ) ነው›› አለው” (ሙስሊም 2567)፡፡
መ/ የሰማይ ነዋሪ ናቸው፡-
የመላእክት የመኖሪያና የመገኛ ቀበሌ ሰማይ ነው፡፡ ሰማይ በመላእክት አምልኮ የተጨናነቀች ውድ ስፍራ ናት፡፡ ወደዚህ ምድር አላህ ለሚፈልገው ዓላማ ተልከው ከሆነ እንጂ በፍጹም አይወርዱም፡፡ በጥቅሉ ‹የሰማይ ነዋሪ› በመባል ይታወቃሉ፡-
” وَكَم مِّن مَّلَكٍ فِي السَّمَاوَاتِ لا تُغْنِي شَفَاعَتُهُمْ شَيْئًا إِلاَّ مِن بَعْدِ أَن يَأْذَنَ اللَّهُ لِمَن يَشَاء وَيَرْضَى ” سورة النجم 26
“በሰማያት ውስጥ ካለ መልአክም ብዙዎች (ሊማለዱለት) ለሚሻውና ለሚወደው ሰው ከፈቀደ በኋላ ቢሆን እንጅ ምልጃቸው ምንም አትጠቅምም።” (ሱረቱ-ነጅም 53፡26)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹‹በሰማያት ውስጥ ካለ መልአክም›› የሚለው፡ የመላእክት ኑሮ በሰማይ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡
” أَفَغَيْرَ دِينِ اللَّهِ يَبْغُونَ وَلَهُ أَسْلَمَ مَنْ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ طَوْعًا وَكَرْهًا وَإِلَيْهِ يُرْجَعُونَ ” سورة آل عمران 83
“በሰማያትና በምድር ያሉ ሁሉ፤ በዉድም በግድም ለርሱ የታዘዙ ወደርሱም የሚመለሱ ሲኾኑ (ከሐዲዎች) ከአላህ ሃይማኖት ሌላን ይፈልጋሉን?” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡83)፡፡
” وَمَا نَتَنَزَّلُ إِلَّا بِأَمْرِ رَبِّكَ لَهُ مَا بَيْنَ أَيْدِينَا وَمَا خَلْفَنَا وَمَا بَيْنَ ذَلِكَ وَمَا كَانَ رَبُّكَ نَسِيًّا ” سورة مريم 64
“(ጂብሪል፤ አለ) በጌታህም ትእዛዝ እንጂ አንወርድም፤ በፊታችን ያለው በኋላችንም ያለዉ፣ በዚህም መካከል ያለዉ ሁሉ የርሱ ነው፤ ጌታህም ረሺ አይደለም።” (ሱረቱ መርየም 19፡64)፡፡
” يُنَزِّلُ الْمَلَائِكَةَ بِالرُّوحِ مِنْ أَمْرِهِ عَلَى مَنْ يَشَاءُ مِنْ عِبَادِهِ أَنْ أَنْذِرُوا أَنَّهُ لَا إِلَهَ إِلَّا أَنَا فَاتَّقُونِ ” سورة النحل 2
“ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ መላእክትን ከራእይ ጋር በፈቃዱ ያወርዳል፤ (ከሐዲዎችን በቅጣት) አስጠንቅቁ፤ እነሆ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም ፍሩኝም ማለትን (አስታውቁ በማለት ያወርዳል)።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡2)፡፡
ይቀጥላል!!