በሃይማኖት ማስገደድ የለም!!

ሼር ያድርጉ
484 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

ዛሬ የምንመለከተው፡ ኢስላም፡- ሰዎች እስልምናን ካልተቀበሉ፡ ሸሀደተይንን (የአላህን አምላክነት እና የነቢዩ ሙሐመድን መልክተኝነት) ካልመሰከሩ ግደሏቸው ብሎ ያዛል የሚለውን ከንቱ የባዶ ሜዳ ጩኸት ነው፡፡

አምላካችን አላህ፡ ባሪያዎቹ ወደውና ፈልገው እንጂ፡ ጠልተውና ተገደው እንዲያመልኩት አይፈልግም፡፡ ለዚህም ትልቁ ማስረጃችን፡ በኢስላም ውስጥ እምነትም ሆነ ስራ አላህ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው መሟላት ከሚገባቸው ሶስት መስፈርት ውስጥ አንዱ ‹‹ኢኽላስ›› የሚባለው መኖሩ ነው፡፡
‹‹ኢኽላስ›› ማለት፡- የሚሰራን ማንኛውንም አይነት መልካም ስራ ለአላህ ብቻ ብሎ ማድረግ፡ ከምድራዊ ጥቅም ፍለጋና ከሰዎች እዩልኝ ስሙልኝ እራስን ማራቅና ማግለል ማለት ነው፡፡ አላህን ማምለክ የሚፈልግ ሰው፡ አምልኮቱም ፍሬያማ እንዲሆን በ‹‹ኢኽላስ›› ብቻ የሚተገብር መሆን አለበት፡፡ ታዲያ ሰዎች ተገደው፡ መሳሪያ ተደቅኖባቸው፡ ህይወታቸውን ለማትረፍ ብለው እንጂ ለአላህ ብለው ባይሰልሙና ባያምኑ ምኑ ጋር ነው ትርፋቸው? ማስገደዱስ ለምን? ለፍቶ መና ከመሆን ውጪ የሚያተርፉት ነገር የለምና!!፡፡
ኢስላም የሌላ እምነት ተከታዮችን ሃይማኖታቸውን ትተው ወደ ኢስላም እንዲመጡ ያስገድዳል የሚለው ተረት ተረት፡ ኢስላምን በጦር መሳሪያ ማሸነፍ ሲያቅታቸው፡ በሀሰት ወሬ ለማዳከም የሚደረግ የከንቱዎች መፍጨርጨር ነው፡፡ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው አይደል የሚባለው፡፡ እኛ:– በኢስላም አስተምህሮ ሰው እምነቱን ለቆ ወደ ኢስላም እንዲቀላቀል የምርጫ ጉዳይ እንጂ፡ ግዳጅ እንዳልተጣለበት ለማወቅ ከፈለግን ቀጣዩን ማስረጃዎች እንመልከታቸው፡-

1. በቀጥታ ቋንቋ፡-

አላህ በሃይማኖት ማስገድ እንደሌለ፡ ሰው የሚከተለውን እምነት ትቶ ወደ ኢስላም መምጣት ወይም በዛው ክህደቱ ላይ መዘውተር የግለሰቡ የምርጫ ጉዳይ እንደሆነ በማብራራት ይነግረናል፡-

” لَا إِكْرَاهَ فِي الدِّينِ قَدْ تَبَيَّنَ الرُّشْدُ مِنَ الْغَيِّ فَمَنْ يَكْفُرْ بِالطَّاغُوتِ وَيُؤْمِنْ بِاللَّهِ فَقَدِ اسْتَمْسَكَ بِالْعُرْوَةِ الْوُثْقَى لَا انْفِصَامَ لَهَا وَاللَّهُ سَمِيعٌ عَلِيمٌ ” سورة البقرة 256
“በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 256)፡፡

– ‹‹በሃይማኖት ማስገደድ የለም›› የሚለው፡- ሙስሊም ያልሆነ ሰው በጠቅላላ (ካፊሩ ኅብረተሰብ) ኢስላምን ኢንዲቀበል ማስገደድ አይቻልም ይለናል፡፡ ለምን? ብለን ጥያቄ ስናነሳ፡ መልሱም፡-

– ‹‹ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ›› የሚለው ይሆናል፡፡ እውነት ከጸሀይ በላይ የበራና የደመቀ ነው፡፡ አላህ ነቢዩ ሙሐመድን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይ አድርጎ በመላክ፡ ቅዱስ ቁርኣንን ለሰዎች ሁሉ የህይወት መመሪያ ይሆን ዘንድ የመጨረሻ መለኮታዊ መጽሐፍ አድርጎ በማውረድ፡ እውነቱን ከሀሰት ለይቶ ገለጸው፡፡ ከዚህ በኋላ፡-

– ‹‹በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው›› በማለት፡- ፈቅዶና ፈልጎ በአላህ ብቸኛ አምላክነትና ተመላኪነት ያመነ፡ እንዲሁም በጣኦት (ከአላህ ውጭ የሚመለክ ማንኛውም አካል) አምልኮ የካደ ሰው፡ የዚህ ሰው ተስፋው፡-

– ‹‹ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ›› በማለት፡ ወደ ጀነት የሚያደርሰውን የህይወት ጎዳና (ኢስላም፣ ላኢላሀ ኢለሏህ) አስተማማኝ በሆነ መልኩ ያዘ ብሎ ይነግረናል፡፡ ከዛ ውጭ ለተረፈው ነገር ደግሞ፡-

– ‹‹አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው›› በማለት፡ የሰዎችን ንግግር ሰሚና አዳማጭ፡ የልባቸውንም ክፋትና ደግነት ዐዋቂ ጌታ እሱ ብቻ ስለሆነ፡ ተቆጣጣሪነቱ በኔ ይብቃ እያለ ነው ጌታችን፡፡

” وَقُلِ الْحَقُّ مِنْ رَبِّكُمْ فَمَنْ شَاءَ فَلْيُؤْمِنْ وَمَنْ شَاءَ فَلْيَكْفُرْ إِنَّا أَعْتَدْنَا لِلظَّالِمِينَ نَارًا أَحَاطَ بِهِمْ سُرَادِقُهَا وَإِنْ يَسْتَغِيثُوا يُغَاثُوا بِمَاءٍ كَالْمُهْلِ يَشْوِي الْوُجُوهَ بِئْسَ الشَّرَابُ وَسَاءَتْ مُرْتَفَقًا ” سورة الكهف 29
“እውነቱም፥ ከጌታችሁ ነው፤ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ፣ በላቸው፤ እኛ ለበደለኞች አጥርዋ በነሱ የከበበ የሆነችውን እሳት አዘጋጅተናል፤ (ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ፥ ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ፥ ይረዳሉ፤ መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቲም ምንኛ አስከፋች!” (ሱረቱል ከህፍ 29)፡፡

– ‹‹እውነቱም፥ ከጌታችሁ ነው በላቸው›› በዚህም አንቀጽ ላይ፡- የአማኞች ግዳጅ እውነቱ ያለው ከጌታ አላህ ዘንድ መሆኑን ማብራራትና መመስከር ብቻ እንደሆነ ይገልጽና፡ ከነሱ በኩል ደግሞ፡-

– ‹‹የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ፣›› በማለት፡ ከፈለጉ በዛው ክህደታቸው መዘውተር እንደሚችሉ፡ ያም ካልሆ ደግሞ የመጨረሻው ዓለም ጀነት ይሻለናል ካሉ ማመን እንደሚችሉ ገለጸላቸውና፡ ክህደቱን ለመረጡት ግን በመጨረሻው ዓለም፡-

– ‹‹እኛ ለበደለኞች አጥርዋ በነሱ የከበበ የሆነችውን እሳት አዘጋጅተናል›› በማለት፡ የሚጠብቃቸውን አስከፊ የጀሀነም ቅጣት ዘረዘር እንጂ፡ እስኪሰልሙ አስገድዷቸው፡ ወይንም ግደሏቸው አላለም፡፡

” قُلْ يَا أَيُّهَا الْكَافِرُونَ * لَا أَعْبُدُ مَا تَعْبُدُونَ * وَلَا أَنْتُمْ عَابِدُونَ مَا أَعْبُدُ * وَلَا أَنَا عَابِدٌ مَا عَبَدْتُمْ * وَلَا أَنْتُمْ عَابِدُونَ مَا أَعْبُدُ * لَكُمْ دِينُكُمْ وَلِيَ دِينِ ” سورة الكافرون 6-1
“በላቸው፦ እናንተ ከሐዲዎች ሆይ፣ ያንን የምትግገዙትን (ጣዖት አሁን) አልግገዛም። እናንተም አሁን የምግገዛውን (አምላክ አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም። እኔም ያንን የተገዛችሁትን (ወደፊት) ተገዢ አይደለሁም እናንተም እኔ የምግገዛውን (ወደፊት) ተገዢዎች አይደላችሁም። ለናንተ ሃይማኖታችሁ አላችሁ፤ ለኔም ሃይማኖቴ አለኝ።” (ሱረቱል ካፊሩን 1-6)፡፡

– ‹‹ያንን የምትግገዙትን አልግገዛም›› በዚህም አንቀጽ ላይ ለከሀዲያን በመላ፡ እነሱ የሚያመልኩትን የሀሰት አማልክት እኛ አሁንም ሆነ ወደፊት እንደማንገዛ፡ እንድንነግራቸው ጌታችን ያዘናል፡፡ እነሱም፡ በፈቃደኝነት እኛ የምንገዛውን እውነተኛ አምላክ አላህን ለመገዛት የማይፈልጉ መሆናቸውን (አላህ መልካም የሻለት ብቻ ሲቀር) ያስረዳንና መጨረሻም፡-

– ‹‹ለናንተ ሃይማኖታችሁ አላችሁ፤ ለኔም ሃይማኖቴ አለኝ በላቸው›› በማለት፡ እኛ የራሳችን የሆነ እውነተኛ ሃይማኖት (ኢስላም) አለን፡ እናንተ ደግሞ የራሳችሁ የሆነ የሀሰት ሃይማኖት (ከኢስላም ውጭ እውነት ስለሌለ) አላችሁ፡ ብለን መለያየታችንን እንድንነግራቸው እንጂ ወደኛ ሃይማኖት እንዲመጡ እንድናስገድዳቸው አላዘዘንም፡፡

2. በነቢዩ ተልእኮ፡-

ሌላው ኢስላም በሃይማኖት ማስገደድ አለመኖሩን ያወጀው፡ የነቢዩ ሙሐመድን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የተልእኮ ሚና በመግለጽ ነው፡፡ በብዙ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ላይ የሳቸውን ተልእኮ የመጨረሻ ግብ የሚገልጸው፡- ‹‹ባንተ ላይ ያለብህ መልእክቱን በተብራራ መልኩ ማድረስ ብቻ ነው›› እንዲሁም፡- ‹‹አንተ በነሱ ላይ አስገዳጅ አይደለህም፣ አልተሾምክምም›› በማለት ነው፡፡ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ኢስላም በሃይማኖት ያስገድዳል የሚባለው? እስኪ ቀጣዮቹን አንቀጾች እንመልከታቸው፡-

” فَإِنْ حَاجُّوكَ فَقُلْ أَسْلَمْتُ وَجْهِيَ لِلَّهِ وَمَنِ اتَّبَعَنِ وَقُلْ لِلَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ وَالْأُمِّيِّينَ أَأَسْلَمْتُمْ فَإِنْ أَسْلَمُوا فَقَدِ اهْتَدَوْا وَإِنْ تَوَلَّوْا فَإِنَّمَا عَلَيْكَ الْبَلَاغُ وَاللَّهُ بَصِيرٌ بِالْعِبَادِ ” سورة آل عمران 20
“ቢከራከሩህም :- ፊቴን ለአላህ ሰጠሁ፤ የተከተሉኝም ሰዎች (እንደዚሁ ለአላህ ሰጡ) በላቸዉ፤ ለእነዚያም መጽሐፍን ለተሰጡት ሰዎችና ለመሀይሞቹ፦ሰለችማሁን? በላቸዉ፤ ቢሰልሙም በእርገጥ ተመሩ እምቢ ቢሉም በአንተ ላይ ያለበህ ማድረስ ብቻ ነዉ:: አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው::” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 20)፡፡

– ‹‹ቢከራከሩህም:- ፊቴን ለአላህ ሰጠሁ፤ የተከተሉኝም ሰዎች (እንደዚሁ ለአላህ ሰጡ) በላቸዉ››፡- በማለት ከላይ በቁጥር 19 ላይ አላህ ዘንድ የተወደደ ሃይማኖት ኢስላም ብቻ መሆኑን ከገለጸ በኋላ፡ በሃይማኖት ጉዳይ ቢከራከሩህ፡ ያንተ ምላሽ፡- እኔና የተከተሉኝ ሰዎች ለአላህ እጅ ሰጥተናል (ታዘናል) ነው መሆን ያለበት አላቸው፡፡ ከዛም፡-

– ‹‹ለእነዚያም መጽሐፍን ለተሰጡት ሰዎችና ለመሀይሞቹ፦ሰለችማሁን? በላቸዉ›› በማለት፡ በወቅቱ የነበሩ ያልተማሩ ዐረብ ጣኦታውያንና የመጽሐፉን ሰዎች (አይሁድና ክርስቲያን) ሰልማችኋል ወይ? ለአላህ እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ናችሁ ወይ? ብለህ ጥርሪ አቅርብላቸው ብሎ አዘዛቸው፡፡ እነሱ ደግሞ፡-

– ‹‹ቢሰልሙም በእርገጥ ተመሩ እምቢ ቢሉም በአንተ ላይ ያለበህ ማድረስ ብቻ ነዉ›› በማለት፡ እሺ ብለው ኢስላምን ፈቅደውና ወደው ቢቀበሉ በእርግጥም ወደ እውነት ተመሩ፡ ካልፈቀዱና ካልፈለጉ ግን አንተ ግዳጅህ፡- መልእክቱን በተብራራ መልኩ ማድረስ እንጂ እነሱን እንዲሰልሙ ማስገደድ አይደለም ብሎ የሳቸውን ሚና ይገልጽና፡ ስለነሱ እንቢተኝነት ደግሞ፡-

– ‹‹አላህም ባሮቹን ተመልካች ነው›› በማለት፡ የባሮቹን ሁኔታ የሚቆጣጠረውና የሚመለከተው፡ የልባቸውን ሀሳብ የሚያውቀው እሱ ብቻ መሆኑን ይገልጻል፡፡

” قُلْ أَطِيعُوا اللَّهَ وَأَطِيعُوا الرَّسُولَ فَإِنْ تَوَلَّوْا فَإِنَّمَا عَلَيْهِ مَا حُمِّلَ وَعَلَيْكُمْ مَا حُمِّلْتُمْ وَإِنْ تُطِيعُوهُ تَهْتَدُوا وَمَا عَلَى الرَّسُولِ إِلَّا الْبَلَاغُ الْمُبِينُ ” سورة النور 54
“አላህን ተገዙ፤ መልክተኛውንም ታዘዙ፤ ብትሸሹም (አትጐዱትም)፤ በርሱ ላይ ያለበት የተገደደውን ማድረሰ ብቻ ነው፤ በናንተም ላይ ያለባችሁ፣ የተገደዳችሁት (መታዘዝ) ብቻ ነው፤ ብትታዘዙትም ትምመራላችሁ፤ በመልክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም፤ በላቸው” (ሱረቱ-ኑር 54)፡፡

– ‹‹አላህን ተገዙ፤ መልክተኛውንም ታዘዙ፤ ብትሸሹም (አትጐዱትም)›› በማለት፡ ለኛ የሚበጀን መንገድ፡- አላህን መገዛትና የላከውን መልክተኛ(ሙሐመድን) መታዘዝ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ከዚህ አምልኮና ታዛዥነት ብንሸሽ የምንጎዳው እራሳችንን እንጂ አላህንና መልክተኛውን እንዳልሆነ ያስረዳና፡ መልክተኛው እንደሆነ፡-

– ‹‹በርሱ ላይ ያለበት የተገደደውን ማድረሰ ብቻ ነው፤ በናንተም ላይ ያለባችሁ፣ የተገደዳችሁት (መታዘዝ) ብቻ ነው›› ብሎ የመልክተኛው ግዳጅ መልእክቱን ማድረስ እንደሆነና እሱም እንዳደረሰ ገልጾ፡፡ የናንተ ግዳጅ ደግሞ፡ መታዘዝ ነው በማለት እንዲታዘዙ ከነገራቸው በኋላ ውጤቱን ደግሞ፡-

– ‹‹ብትታዘዙትም ትምመራላችሁ፤ በመልክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም፤ በላቸው›› በማለት፡ መልክተኛውን የታዘዘ ሰው ቅኑን መንገድ እንደተመራ፡ እምቢ ላለ ሰው ደግሞ፡ የመልክተኛው ግዳጅ መልእክቱን ግልጽ በሆነ መልኩ ማድረስ እንጂ ማስገደድ እንዳልሆነ በመግለጽ ይቋጨዋል፡፡

” نَحْنُ أَعْلَمُ بِمَا يَقُولُونَ وَمَا أَنْتَ عَلَيْهِمْ بِجَبَّارٍ فَذَكِّرْ بِالْقُرْآنِ مَنْ يَخَافُ وَعِيدِ ” سورة ق 45
“እኛ የሚሉትን ሁሉ ዐዋቂ ነን፡፡ አንተም በእነርሱ ላይ አስገዳጅ አይደለህም፡፡ ስለዚህ ዛቻየን የሚፈራን ሰው በቁርኣን አስታውስ፡፡” (ሱረቱ ቃፍ 45)፡፡

– ‹‹እኛ የሚሉትን ሁሉ ዐዋቂ ነን›› በማለት፡ ከሀዲያን የነቢያችንን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ነቢይነት እንደሚስተባብሉና፡ እሱም ይህንን ሁኔታቸውን እንደሚያውቅ ከገለጸ በኋላ፡ ለሳቸው ደግሞ፡-

‹‹አንተም በእነርሱ ላይ አስገዳጅ አይደለህም›› በማለት፡ መልእክቱን በግልጽ ከማድረስ ውጪ ያንተን ነቢይነት እንዲመሰክሩ ማስገደድ አትችልም በማለት ይነግራቸዋል፡፡ ከዛ ይልቅ፡-

– ‹‹ስለዚህ ዛቻየን የሚፈራን ሰው በቁርኣን አስታውስ›› በማለት፡ የሳቸው ሚና የጌታውን የቂያም ቀን ዛቻን የሚፈራን ሰው በቁርኣን ማስታወስና መገሰጽ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በዚህ ዙሪያ የተነገሩ በጣም ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለናሙና ያህል ግን ሶስቱን እንደ ምሳሌ ካየናቸው፡ የተወሰኑትን ደግሞ በግል እንድትመለከቷቸው ምንጩን ልስጣችሁ፡-

(ሱረቱ-ኒሳእ 80፣ ሱረቱል ማኢዳህ 92.99፣ ሱረቱል አንዓም 104.107፣ ሱረቱ-ነሕል 82፣ ሱረቱል ዐንከቡት 18፣ ሱረቱ-ሹራ 48፣ ሱረቱ-ተጋቡን 12፣ ሱረቱል ጋሺየህ 22)፡፡

3. በአላህ ሁሉን ቻይነት፡-

ሌላው በሃይማኖት ማስገደድ እንደሌለ የሚያመላክተው ቅዱስ ቁርአናዊ ትምሕርት፡- የአላህን ያልተገደበ ፈቃድ በመግለጽ ነው፡፡ አላህ ሰዎች ሁሉ በአንድ ልብ በኃይልና በግዳጅ እንዲያምኑ ለማድረግ ቢፈልግ ኖሮ፡ በምድር ያሉ ነቢያትንና ተከታዮቻቸውን፡- አስገድዱ ከማለት ይልቅ እራሱ የሰዎችን ልብ በአንዴ መቀየር አይችልም ነበር? ይህንንስ ለማድረግ የሚያግደው ምን ኃይል ይኖራል? የአደም ልጆች ልብ በጠቅላላ ያለው በሱ መለኮታዊ እጅ ስር ነው፡፡ የፈለገውን እንደፈለገው ማድረግ ይችላል፡፡ ታዲያ ይህን ማድረግ እየቻለ ያላደረገው ግን፡ ሰዎች በምርጫቸው የፈለጉትን የእምነትን ጎዳና እንዲከተሉ እንጂ፡ እሱ ማድረግ አቅቶት፡ እኛ እንድናግዘውና ፈቃዱን እንድንፈጽምለት አይደለም፡፡ ለዚህ ሀሳብ ደጋፊ የሆኑ አንቀጾችን ደግሞ ቀጥለን እንመልከታቸው፡-

” وَإِنْ كَانَ كَبُرَ عَلَيْكَ إِعْرَاضُهُمْ فَإِنِ اسْتَطَعْتَ أَنْ تَبْتَغِيَ نَفَقًا فِي الْأَرْضِ أَوْ سُلَّمًا فِي السَّمَاءِ فَتَأْتِيَهُمْ بِآيَةٍ وَلَوْ شَاءَ اللَّهُ لَجَمَعَهُمْ عَلَى الْهُدَى فَلَا تَكُونَنَّ مِنَ الْجَاهِلِينَ ” سورة الأنعام 35
“(ኢስላምን) መተዋቸውም ባንተ ላይ ከባድ ቢኾንብህ በምድር ውስጥ ቀዳዳን ወይም በሰማይ ውስጥ መሰላልን ልትፈልግና በተአምር ልትመጣቸው ብትችል (አድርግ)፡፡ አላህም በሻ ኖሮ በቅኑ መንገድ ላይ በሰበሳባቸው ነበር፡፡ ከተሳሳቱትም ሰዎች በፍጹም አትኹን፡፡” (ሱረቱል አንዓም 35)

– ‹‹(ኢስላምን) መተዋቸውም ባንተ ላይ ከባድ ቢኾንብህ›› በማለት፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ለሰዎች ካላቸው እዝነትና ርኅራሄ የተነሳ የኢስላምን መልእክት ባለመቀበላቸው፡ ለጥፋት መዳረጋቸው እጅጉኑ ይጨንቃቸውና ያሳስባቸው እንደነበር ይገልጽና፡-

– ‹‹በምድር ውስጥ ቀዳዳን ወይም በሰማይ ውስጥ መሰላልን ልትፈልግና በተአምር ልትመጣቸው ብትችል (አድርግ)›› በማለት፡ እነዚህ ሰዎች ለእምነት የተዘጋጁ እንዳልሆኑ ገለጸላቸው፡፡ ከፈለግክም ደግሞ፡ ምድርን ሰርጉደህም ሆነ ወደ ሰማይ አርገህ እነሱን ሊያሳምናቸው የሚችል ተአምር አምጣና ሞክራቸው፡፡ እነሱ ግኑ አያምኑም ብሎ ነገራቸው፡፡ በግድ እንዲያምኑ ለማድረግ ቢሆንማ፡-

– ‹‹አላህም በሻ ኖሮ በቅኑ መንገድ ላይ በሰበሳባቸው ነበር›› በማለት፡ እኔ በፈቃዴ የሁሉንም ልብ በኃይል በመቀየር በቅኑ ጎዳና (በኢስላም) ላይ በሰበሰብኳቸው ነበር፡ ብሎ የሱን ሁሉን ቻይነት ያስረዳናል፡፡ ግን ያላደረገው፡ እምነት በፈቃደኝነት እንጂ በግዳጅ የሚፈጸም ነገር ባለመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም አንተ፡-

– ‹‹ከተሳሳቱትም ሰዎች በፍጹም አትኹን›› በማለት፡ አላህ በክህደታቸውና በአመጻቸው ምክንያት ሂዳያ ያልሻላቸውን ሰዎች፡ አንተ በመጨነቅ ሂዳያ እንዲያገኙ እያልክ ስህተት ውስጥ አትግባ አላቸው፡፡

” وَلَوْ شَاءَ اللَّهُ مَا أَشْرَكُوا وَمَا جَعَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا وَمَا أَنْتَ عَلَيْهِمْ بِوَكِيلٍ ” سورة الأنعام 107
“አላህም በሻ ኖሮ ባላጋሩ ነበር፡፡ በእነሱም ላይ ጠባቂ አላደረግንህም፡፡ አንተም በእነሱ ላይ ኃላፊ አይደለህም፡፡” (ሱረቱል አንዓም 107)

– ‹‹አላህም በሻ ኖሮ ባላጋሩ ነበር›› በማለት፡ ከአላህ ውጪ ያለን አካል በማምለክ በአላህ ላይ ያጋሩ ሰዎች፡ አላህ ቢፈልግ ኖሮ በኃይል ማጋራታቸውን አስቁሞ ወደ እምነት መስመር መመለስ እንደሚችል ገለጸ፡፡ ነገር ግን ሰዎች በገዛ ምርጫቸው የፈለጉትን የእምነት መንገድ እንዲከተሉ ተዋቸው፡፡ ከዛም ለመልክተኛው፡-

– ‹‹በእነሱም ላይ ጠባቂ አላደረግንህም፡፡ አንተም በእነሱ ላይ ኃላፊ አይደለህም›› በማለት፡ እነሱን እንዲያምኑ በማድረግ ከኔ ቅጣት ልትጠብቃቸው አትችልም፡ ደግሞም ልትጠቅማቸውም አትችልም ብሎ ገለጸ፡፡

” وَلَوْ شَاءَ رَبُّكَ لَآمَنَ مَنْ فِي الْأَرْضِ كُلُّهُمْ جَمِيعًا أَفَأَنْتَ تُكْرِهُ النَّاسَ حَتَّى يَكُونُوا مُؤْمِنِينَ ” سورة يونس 99
“ጌታህም በሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሰዎች ሁሉም የተሰበሰቡ ሆነው ባመኑ ነበር፡፡ ታዲያ አንተ ሰዎችን አማኞች እንዲኾኑ ታስገድዳለህን?” (ሱረቱ ዩኑስ 99)፡፡

– ‹‹ጌታህም በሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሰዎች ሁሉም የተሰበሰቡ ሆነው ባመኑ ነበር›› በማለት፡ አሁንም ጌታ አላህ ቢፈልግ ኖሮ፡ በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ በመሰብሰብ እንዲያምኑ ማድረግ ይችል ነበር፡ ይህን ከማድረግ ሊከለክለው የሚችል ምንም ነገር የለም እያለ ነው፡፡ ያንን ከማድረግ የተወው ግን ሰዎች በምርጫቸው እንዲወስኑ ስለፈለገ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ቀጥሎም ለመልክተኛው፡-

– ‹‹ታዲያ አንተ ሰዎችን አማኞች እንዲኾኑ ታስገድዳለህን?›› በማለት፡ ያንተ ሚና መልእክቱን በተብራራ መልኩ ማድረስ እንጂ፡ መልእክትህን አምነው እንዲቀበሉ ማስገደድ አትችልም እያለ ነው፡፡

ስለዚህ በሃይማኖት ማስገደድ አለ የሚለው፡ የሀሰተኞች ከንቱ ልፈፋ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ጥቅሶችን ደግሞ በግል እንድትመለከቱት ላስቀምጥላችሁ፡-
(ሱረቱ ሁድ 118፣ ሱረቱ-ነሕል 9.93፣ ሱረቱ-ሰጅዳህ 13፣ ሱረቱ-ሹራ 8)፡፡

4. ከስራ ተቀባይነት አንጻር፡-

ሌላው በኢስላም በሃይማኖት ማስገደድ የለም የምንልበት ምክንያት ደግሞ ይህ ነው፡፡ አንድ ሰው ስራው አላህ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ማመኑ ግድ ነው፡፡ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያላመነ ሆኖ መልካም ስራን ቢሰራ፡ በኢስላም ስራው ከንቱ ነው ይባላል፡፡ መናፍቃን (ሙናፊቆች) በምላሳቸው አምነናል እያሉ፡ በሰውነታቸውም የሙስሊሞችን የአምልኮ ተግባር (ሶላት፣ ሐጅ..) እየፈጸሙ፡ ግን በመጨረሻው ቀን ከከሳሪዎች የሚሆኑት ለምንድነው? ልባቸው አምኖ ስላልተቀበለው አይደል? ታዲያ ዛሬ አንድ ሙስሊም ያልሆነን ግለሰብ በመሳሪያና በኃይል በማስገደድ ውስጡ ያላመነበትን ኢስላምን በምላሱ እንዲመሰክር ብናደርገው፡ ለሱ ምን ይጠቅመዋል? እኛስ ምን ትርፍ እናገኛለን?

አላህ መናፍቃንን በምላሳቸው በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል እያሉ፡ የነቢዩ ሙሐመድን መልክተኝነት እንመሰክራለን እያሉ፡ ጌታችን ግን አላመኑም ውሸተኞች ናቸው፡ በመጨረሻው ዓለምም አሳማሚ ቅጣት አላቸው ይለናል፡፡ ቀጥሎ የሚቀርቡትን ጥቅሶች እንመልከታቸው፡-

” وَمِنَ النَّاسِ مَنْ يَقُولُ آمَنَّا بِاللَّهِ وَبِالْيَوْمِ الْآخِرِ وَمَا هُمْ بِمُؤْمِنِينَ * يُخَادِعُونَ اللَّهَ وَالَّذِينَ آمَنُوا وَمَا يَخْدَعُونَ إِلَّا أَنْفُسَهُمْ وَمَا يَشْعُرُونَ * فِي قُلُوبِهِمْ مَرَضٌ فَزَادَهُمُ اللَّهُ مَرَضًا وَلَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ بِمَا كَانُوا يَكْذِبُونَ ” سورة البقرة 10-8
“ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡ አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡ በልቦቻቸው ውስጥ (የንፍቅና) በሽታ አለባቸው፡፡ አላህም በሽታን ጨመረባቸው፡፡ ለነርሱም ይዋሹ በነበሩት ምክንያት አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 8-10)፡፡

” إِذَا جَاءَكَ الْمُنَافِقُونَ قَالُوا نَشْهَدُ إِنَّكَ لَرَسُولُ اللَّهِ وَاللَّهُ يَعْلَمُ إِنَّكَ لَرَسُولُهُ وَاللَّهُ يَشْهَدُ إِنَّ الْمُنَافِقِينَ لَكَاذِبُونَ ” سورة المنافقون 1
“መናፍቃን በመጡህ ጊዜ አንተ የአላህ መልክተኛው መሆንህን በእርግጥ (ምለን) እንመሰክራለን ይላሉ፤ አላህም አንተ በ እርግጥ መል ዕክተኛ መሆንህን ያውቃል፤ አላህም መናፍቃን (ከልብ እንመሰክራለን በማለታቸው) ውሸታሞች መኾናቸውን ይመሰክራል።” (ሱረቱል ሙናፊቁን 1)፡፡

እንግዲያውስ ጉዳዩ እንደዛ ከሆነ፡ ሳይወዱ በግዳቸው ኢስላምን እንዲቀበሉ የሚደረጉ ሰዎች ካሉ፡ ምን ሊጠቅማቸው ይችላል? በመሆኑም ኢስላም በሃይማኖት ማስገደድን አያምንም፡፡

አምላካችን አላህ ሆይ! ከሞት በፊት ትክክለኛ ተውበትን፣ በሞት ጊዜ ሸሀዳን፣ በቀብር ውስጥ ጽናትን፣ በአኼራ ደግሞ ጀነትን በራሕመትህ ወፍቀን፡፡ ከገርገራ ጭንቀት፣ ከቀብር ፈተና እና ከጀሀነም እሳትም ቅጣት አርቀን፡፡

የአላህ ሰላምና መልካም ውዳሴ በነቢያችንና በቤተሰቦቻቸው፡ ፈለጋቸውንም በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን፡፡

Shortlink http://q.gs/ExaSp