ቁርኣን ስለ ቀደምት መጽሐፍት መበረዝ} {ክፍል ኣንድ}

ሼር ያድርጉ
551 Views

በኣላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን በተላኩ ነቢይ ሙሓመድ (ሠ) ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን እንቀጥላለን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ?! ሰሞኑን ትምህርት በመጀመሩ ምክንያት ከፌስ ቡክ ሰፈር ብዙም አልተጣድኹም ነበርና አውድማው እንዴት እንደዋለ እውቅና (መረጃ) የለኝም፡፡ ምን ጉዳይ ተነስቶ ምን እንደተጣለም እንደነ ኢስራኤል ዳንሳ “ሹክ” የሚል “ግልጠት” ስለሌለኝ የኾነውን መረዳት አልቻልኹም፡፡

ኣንድ ወዳጄ በውስጥ መስመር የኾኑ ድምጾችን እንድሰማ ጋብዘኝ፤ ከድምጹ እንደተረዳኹት “መምህሩ” ቁርኣን የነሱንና የኣይሁድ መጽሐፍት ስለ መበረዛቸው ምንም ሚያወራው ነገር እንደሌለ ግብታዊ ኾኖ ያወራል፡፡ በሌላ ድምጽ ደግሞ ራሱ ግለሰቡ ይኹን ወይም ሌላ ቁርኣን የክርስትያኑ መጽሐፍ እንደተጠበቀና እንዳልተበረዘ ያወራል… እናም ወዳጄ የዛሬ ወጋችን በዚህ ዙሪያ የሚደውር እንዲኾን መርጠናል፡፡

በመጀመሪያ ቁርኣን ሰለ መጽሐፍትና ጸሐፍት ዳራ ሲያወራ ስለ ኣይሑድ ወይም ክርስትያን መጽሐፍትና ጸሐፍት ብቻ እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡ ይህንን መንደርደሪያ ይዘን ቁርኣን ስለ ቀደምት መጽሐፍት ያተተውን በኣራት ከፍለን ማይት እንችላለን፡-

1ኛ) የኣይሁድና ክርስትያን መጽሐፍት በጥቅል መበረዛቸውን የሚያመላክቱ ጥቅሶች አሉ፡፡ብረዛው በምን መልኩ ስለመደረጉና የበረዛውም መጠን ምን ያህል እንደኾነ ግን አልተጠቀሰም፡፡

“(አይሁዶች) ከነሱ የኾኑ ጭፍሮች የአላህን ቃል የሚሰሙና ከዚያም ከተረዱት በኋላ እነርሱ እያወቁ‡ የሚለውጡት‡ ሲኾኑ ለናንተ ማመናቸውን ትከጅላላችሁን?” አልበቀራህ/75

“ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው ረገምናቸው፡፡ ልቦቻቸውንም ደረቆች አደረግን፡፡ ቃላትን ከቦታዎቻቸው ‡ይለውጣሉ‡፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተው፡፡ ከእነሱም ጥቂቶች ሲቀሩ ከነርሱ የኾነን ክዳት የምታውቅባቸው ከመኾን አትወገድም፡፡ ከእነርሱም ይቅርታ አድርግ እለፋቸውም፡፡ አላህ መልካም ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡” አልማኢዳህ/13

2ኛ) አይሁድ ባህታውያን ከእጃቸው ያለውን መጽሐፍ ኾን ብለው እንደሚሸሽጉና እውነታንም እንደሚደብቁ ሚተርኩ ጥቅሶች አሉ

“አላህ በሰው ላይ ምንም አላወረደም» ባሉም ጊዜ አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፡፡ (እንዲህ) በላቸው፡- «ያንን ብርሃንና ለሰዎች መሪ ኾኖ ሙሳ ያመጣውን መጽሐፍ ‡ክፍልፍሎች‡ የምታደርጉት ስትኾኑ ማን አወረደው? ‡(የወደዳችኋትን) ትገልጿታላችሁ ‡ብዙውንም ትደብቃላችሁ‡፡፡ እናንተም አባቶቻችሁም ያላወቃችሁትን ተስተማራችሁ፤» ኣንዓም/91

ኢማም ኢብኑ ሃዝም “አልፈስል ፊል ሚለል” (1/160 ) በሚል መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-

“ ኣንድ ሙስሊም ተውራትና ኢንጂል ተበርዘዋል ለማለት ምን ያሳፍረዋል ኣላህ በቃሉ በግልጽ እንዲህ እያለ “የአላህ መልክተኛ ሙሐመድ እነዚያም ከእርሱ ጋር ያሉት (ወዳጆቹ) በከሓዲዎቹ ላይ ብርቱዎች በመካከላቸው አዛኞች ናቸው፡፡ አጎንባሾች፣ ሰጋጆች ኾነው ታያቸዋለህ፡፡ ከአላህ ችሮታንና ውዴታን ይፈልጋሉ፡፡ ምልክታቸው ከስግደታቸው ፈለግ ስትኾን በፊቶቻቸው ላይ ናት፡፡ ይህ ‡በተውራት (የተነገረው)‡ ጠባያቸው ነው፡፡ ‡በኢንጂልም ውስጥ‡ ምሳሌያቸው ቀንዘሉን አንደአወጣ አዝመራና፣ (ቀንዘሉ) እንዳበረታው፣ እንደወፈረምና፣ ገበሬዎቹን የሚያስደንቅ ኾኖ በአገዳዎቹ ላይ ተስተካክሎ እንደ ቆመ (አዝመራ) ነው፡፡ (ያበረታቸውና ያበዛቸው) ከሓዲዎችን በእነርሱ ሊያስቆጭ ነው፡፡ አላህም እነዚያን ያመኑትንና ከእነርሱ በጎዎችን የሠሩትን ምሕረትንና ታላቅ ምንዳን ተስፋ አድርጎላቸዋል፡፡ “(አልፈትህ/29) ዛሬ ተውራትና ኢንጂል በሚባሉ መጽሐፍት ውስጥ ግን እነዚህ ነገሮች አልተገለጹም” በማለት የዛሬዎቹ መጽሐፎች ተውራትና ኢንጂል እንዳልኾኑ ይናገራል፡፡

3ኛ) መጽሐፎቹ በአጠቃላይ ከውጭ ጭማሪ እንደተደረገባቸው በግልጽ የሚያስረዱ ጥቅሶች አሉ፡፡

“ከእነሱም እርሱ ‡ከመጽሐፉ ያይደለ (ያልኾነ)‡ ሲኾን ከመጽሐፉ መኾኑን እንድታስቡ በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን የሚያጣምሙ ክፍሎች አሉ፡፡ እርሱ ከአላህ ዘንድ ያልኾነ ሲኾን «እርሱ ከአላህ ዘንድ ነውም» ይላሉ፡፡ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑም በአላህ ላይ ውሸትን ይናገራሉ፡፡ “ አልዒምራን/78

ቡኻሪ በዘገበው ሐዲስ̱ (2685) ላይ ኢብኑ ዓባስ (ረ) እንዲህ ይላል ፡-
“ የመጽሐፍት ሰዎች ኣላህ ያወረደውን እንደቀየሩ፤በእጆቻቸው መጽሐፍትን እንደለወጡና ጥቂት ዋጋ ይሸጡ ዘንድ ይህ ከኣላህ ነው እንዳሉ ቁርኣን ነግሯችኋል”

4ኛ) በመልክተኛው (ሠ) ዘመን ከቀደምት መጽሐፍት ብትክክል ከኣላህ የኾኑ ጥቂት አስተምህሮዎች እንደነበሩና እነዚያንም በመያዝ የመጽሃፍት ባልተቤቶች በሙሐመድ (ሠ) ያምኑ ዘንድ ቁርኣን ተናግሯል፡፡እነዚያ በመለክተኛው (ሠ) ዘመን የነበሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ግን ዛሬ ላይ የሉም፡፡
“እነርሱም ዘንድ ተውራት እያለች ‡በውስጧ የአላህ ፍርድ ያለባት ስትኾን‡ እንዴት ያስፈርዱሃል! ከዚያም ከዚህ በኋላ እንዴት ይሸሻሉ! እነዚያም በፍጹም ምእምናን አይደሉም፡፡ “ኣልማዒዳህ/43

“«እናንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ተውራትንና ኢንጂልን ‡ከጌታችሁም ወደ እናንተ የተወረደውን‡ እስከምታቆሙ (እስከምትሠሩባቸው) ድረስ በምንም ላይ አይደላችሁም» በላቸው፡፡ ከጌታህም ወደ አንተ የተወረደው ቁርኣን ከእነሱ ብዙዎቹን ትዕቢትንና ክህደትን በእርግጥ ይጨምርባቸዋል፡፡ በከሓዲያን ሕዝቦችም ላይ አትዘን፡፡ ” አልማዒዳህ/68

ወዳጄ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የመጽሐፉ ሰዎች በመጽሐፋቸውና በቁርኣንም እንዲፈርዱ መታዘዛቸውን ያስምሩበት፡፡ “ከጌታችሁ ወደ እናንተ የተወረደውን” የሚለው ሐረግ ቁርኣንን የሚያመላክት ነው፡፡ ተውራትና ኢንጅል በግዜው በውስጣቸው ባቀፉት እውነታ በተለይም ሙሐመድ (ሠ) የኣላህ መልክተኛ መኾናቸውን የሚያስረዱ ጥቅሶችን በመያዛቸው የመጽሐፍት ባለቤቶች እነዚያን ጥቅሶች በመጠቀም ቁርኣንን መዳኛቸው አድረገው እንዲቀበሉና በርሱም እንዲፈርዱ ያስቀደምናቸው ጥቅሶች በግልጽ ያሳስባሉ፡፡

———–ይቀጥላል———–