ቁርኣንን አንብቡ!

ሼር ያድርጉ
477 Views

በአቡ ሐይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1/ እንደሚታወቀው የረመዷን ወር ከተቀሩት 11 ወራቶች በተለየ መልኩ የቁርኣን ወር ነው፡፡ በዚህ ወር ከሚሰሩት የዒባዳህ (አምልኮ) ተግባራት ውስጥ ከጾሙ ቀጥሎ ቁርኣን መቅራት ከፍተኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በሐዲሥ እንደተነገረውም ከአላህ መጽሐፍ (ከቁርኣን) አንድን ፊደል የሚያነብ ሰው ከአስር እስከ ሰባት መቶ ከዛም በላይ አጅር (አምላካዊ ደሞዝን) እንደሚያገኝ ተገልጾአል፡፡ ከፊደል አልፎ ቃላትን፣ ከቃላት አልፎ አየትን (አንድን አንቀጽ)፣ ከአየት አልፎ ሱራን (አንድ ሙሉ ምእራፍ)፣ ከሱራ አልፎ ጁዝእን፣ ከጁዝእ አልፎ ሙሉ ቁርኣንን የቀራ ሰው፡ አላህ ከተቀበለው ምን ያህል ይሆን አጅሩ? አላህ ይወፍቀን፡፡

2/ አንዳንድ ሰዎች፡- እኔ ቁርኣን አላኸተምኩም (ሙሉ ሰላሳ ጁዝኡን አልቀራሁም)፡ የቀራሁት እስከ ሁለትና ሶስት ጁዝእ ድረስ ነው በማለት የቅሬታ ድምጽ ያሰማሉ፡፡ ሐቢቢ፡- በሐዲሡ ላይ እኮ ይህን ታላቅ አጅር ለማግኘት ቃል የተገባላቸው ‹‹ቁርኣንን ያኸተሙ›› ወይም ‹‹በቃል የሐፈዙ›› ሰዎችን አይደለም፡፡ ቃል የተገባው ከቁርኣኑ ውስጥ ከአንዲት ሐርፍ (ፊደል) ጀምሮ የቻሉትን ያክል ለመቅራት የወሰኑትን ነው፡፡ ታዲያ አንተና አንቺ ሁለት ወይም ሶስት ጁዝእ ከደረሳችሁ፡ ለምን እነዚህን በየቀኑ በመደጋገም አትቀሯቸውም? 30 ጁዝኡን የቀሩ ሰዎች ደጋግመው ሲያኸትሙ ካያችሁ፡ እናንተም 3ጁዝኡን ለምን ደጋግማችሁ አትቀሩም? አላህ ካደረሰን ደግሞ በቀጣዩ አመት ቁርኣንን ቀርተን እንደናንተው አኽትመን እንደርስባችኋለን የሚልን ተስፋ በልብ ሰንቃችሁ ማለት ነው፡፡

3/ አንዳንዶች ደግሞ፡- እኔ ምንም ቁርኣን አልቀራሁም በማለት ስሞታ ያቀርባሉ፡፡ አልገባችሁም እንጂ እናንተም የአቅማችሁን ቀርታችኋል!!፡፡ ምነው ሶላት ትሰግዱ የለም እንዴ? ብለን ብንጠይቃችሁ፡ እሱማ አዎ! የሚል መልስ ነው የምትሰጡን፡፡ ታዲያ ለሶላት ስትቆሙ ምንድነው የምትሉት? ብንላችሁስ፡ መልሳችሁ፡- ያው ፋቲሓና ቁል-ሁ ወይም ኢንና አዕጠይና የሚል ነው፡፡ እንግዲያውስ ሱረቱል ፋቲሓ፣ ኢኽላስ፣ ከውሠር የቁርኣን ክፍል አይደሉምን? እንዴታ! ናቸው እንጂ ብላችሁ ከተስማማችሁ፡ በሉ እናንተም እነዚህን የቁርኣን ክፍሎች ሶላት ላይ እንደምትቀሯቸው ሁሉ፡ ጊዜ ስጧቸውና ቁጭ ብላችሁ ደግሞ የቂርኣትን አጅር በመነየት በቃላችሁ ደጋግማችሁ ቅሯቸው፡፡ አላህ ዘንድ ተቀባይነትን ካገኘ ዋጋችሁ ታላቅ ይሆናልና፡፡

ምነው ዚክር የሚያበዙ ሰዎች አብዛኞቹ፡ የዚክሩን ምንጭ ከሐዲሥ የተማሩት መሰላችሁ እንዴ? ከመስጂድ በዓሊሞች፡ በዳዒዎች ሰበብ የሰሙት፣ ከመጽሐፍ ያነበቡት፣ በሲዲ ወይም በቴሌቪዥን ጣቢያ አማካኝነት በማዳመጥ የወረሱት እኮ ነው፡፡ እናንተም እነዚህን ቁርኣን በቃላችሁ ደጋግማችሁ ከመቅራት አትቦዝኑ እሺ? ለቀጣዩ ደግሞ ቁርኣንን ተምራችሁ፡ ሙስሐፉን (ዋናውን መጽሐፍ) በእጃችሁ ይዛችሁ በአላህ ፈቃድ ለመቅራት ከልባችሁ ወስኑ፡፡

አላህ ይርዳን፡፡
ወሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ

Shortlink http://q.gs/Ewioc