ቁርኣናዊ ተግዳሮት – ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ

ሼር ያድርጉ
485 Views

{ከኢሊያሕ ማሕሙድ}

{…ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ}
በአላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በሆነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው መልእክተኛ (ሰ.ወ) ላይ ሰላምና እዝነት ይወርድ ዘንድ ለምነን እንቀጥላለን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ? ባባፈው ሳምንት ወንድም ኢጎ የቀደምት መጽኃፍት ዛሬም ድረስ ሳይበረዙ እንዳሉ ቁርኣን ይናገራ ወይ? ብሎ የመወያያ ተጠየቅ አንስቶ ነበር፡፡ ወደ ጉዳዩ ከመዝለቃችን በፊት ቀደም ካሉ የግሌ ጽሁፎች ውስጥ ይህችን ቁራጭ አንደመንደርደሪያ ያንብቧት፡፡
ኣላህ በቃሉ እንዲህ ይላል፡-

(በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ፡፡ እውነተኞችም እንደኾናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ፡፡) አልበቀራህ/22

ወዳጄ ይህ ጥቅስ መኪያ ከሚባሉ ከስደት በፊት ከተወረዱት ጥቅሶች መካከል ይመደባል፡፡ አላህ ተግዳሮቱን አስቀድሞም ከስደት በፊት (ቀብለል ሂጅራ) በነዚህ ጥቅሶች አስቀምጧል- ቀሰስ/49፣ኢስራእ/88፣ ሁድ/13፤ዩኑስ/37፡፡ በአልበቀራህ ያለውን ለየት የሚያደርገው አንዲትን ምዕራፍ እንዲያመጡ መገዳደሩና…ማምጣትም እንደማይችሉ ማወጁ ነው፡፡ በጃሂሊያ የነበሩ አንደበተ-ርቱዕ ገጣሚዎች በቋንቋው ድካ ከመድረሳቸው አኳያ በቁም በርካታ ስንኞችን ማንፎልፎል የሚችሉና በቋንቋ ችሎታቸውም ዘመን ተሻጋሪ መቼም የማይደረስበት የመጨረሻ ስልጣኔ ላይ የደረሱ ነበሩ፡፡ ግን ታዲያ የቁርኣን ብጤ አንድንም ምዕራፍ ማምጣት ለምን አልተቻላቸውም?

ምክንያት አንድ- የአላህ ባህሪ ስለሆነ

የጃሂሊያ ገጣሚዎች ምናልባት ስለ ሴት ተክለሰውነት፣ ስለሆነ ጦርነት፣ ስለጎሳቸው ታላቅነት፤ ስለራሳቸው የግጥም ክህሎት…ወዘተ የሚተርኩ እንጂ ልክ እንደቁርአን ስላለፉ ህዝቦች ታሪክ፣ ስለወደፊቱ ትንቢት፣ አምልኮአዊና አኗኗሪ ህግጋት፣ ሳይንሳዊ ጥቆማዎችን ያቀፉ አልነበሩም፡፡ ከዚያም ባሻገር ግጥሞቹ ለእርማትም ይቀርቡ የነበረበት ሁኔታ አለ፡፡ቁርአን ግን ከእርማትና ህየሳ የጠራ ነው፡፡

ወዳጄ በአልበቀራህ ያለውን “ከብጤው..” የሚለውን ቃል ልብ ብለው ሲያነቡ ቀድሞ ወደ ጭንቅላቶ የሚመጣው የቁርኣን ብጤ ወይም አምሳያ የሚል ትርጉም እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ቁርአን የአላህ ቃል ነው፤ ቃሉ ደግሞ ባህሪው ነው፤ ባህሪው ደግሞ ብጤ የለውም!!! {የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው}አሹራ/11

አላህ ለራሱ በሚያምርበት መልኩ እርሱ በሚያውቀም መልኩ ይናገራል፡፡ ንግግሩ በአጽናፈ አለም ውስጥ ያለውን ለማስተናበረ ከሆን -ከላም ተክውኒይ- ይባላል፡፡ ሸሪዓዊ ህግ ለማጽናት ወይም ለማስተላለፍ ሲሆን- ከላም ተሸሪዒይ- ይባላል፡፡ ሁለቱንም እንዴት እንደሚናገር አናውቅም-“ለምን?” ካሉ በቁርኣንም በሐዲስም ስላልተነገረን!!! ሁሉም ንግግሮቹ ግን ባህሪያቱ ናቸው፤ ሁሉም ባህሪያቱ ደግሞ አምሳያና ብጤ የላቸውም፡፡ ስለሆነም በዘመኑ የነበሩ የቋንቋ ልሂቃን ተግዳሮቱን መስበር አልቻሉም፡፡

ምክንያት ሁለት- የሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አይነት

ወዳጄ ደግመው “ከብጤው” የሚለውን ቃል ሲመለከቱ ሙሐመድን ከሚመስል ሰው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ የሚል ትርጉም ይገለጽሎታል፡፡ እንደሚታወቀው ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ማንበብና መጻፍ የማይችሉ፤ ገጣሚ ያልነበሩና ከነብይነት በፊት ከገጣሚዎች ጋር ያልተቀማመጡ ናቸው፡፡ በዘመኑ የነበሩ የቁርኣን ብጤ እናመጣለን ሲሉ የነበሩ ገጣሚዎች የነበሩና ከሳቸው ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ያልበራቸው ነበሩ፡፡ ልክ እንደሳቸው ሁሉ ገና በልጅነቱ “ታማኝ” የሚል ቅጽል ስም የነበረው ከመካከላቸው አልነበረም፡፡ ከነሱ ውስጥ ጣኦትን ያላመለከ፤ በስተመጨረሻ የእውነት አምላክን ይፈልግ የነበረ -ማንበብና መጻፍ የማይችል- አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም ግለ-ታሪካቸው ከመልከተኛው ጋር የሚማሳል አልነበረም፡፡ ስለሆነም ከተመሳሳይ ሰው ምዕራፎችን ይዘው መምጣት አልቻሉም ፡፡
ምናልባት ወዳጄ “ዛሬ ላይስ ተግዳሮቱ ሊሰብር አይችልም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችሉ ይሆናል፡፡ “ልክ የሙሓመድ አይነት ታሪክ” አለኝ በሚል ማንበብና መጻፍ ከማይችሉ ገጠሬ ህዝቦች መካከል የሚነሳና የቁርአን አይነት አለኝ ብሎ ሚሞግት ብቅ ቢልስ? የሚል ጥያቄው ውል ሊልቦት ይችላል፡፡ ለወጉ ያህል የዚህ አይነት ሰው ከሆነ አካባቢ ተነሳ እንበል፡፡ መጀመሪያ የምንጠይቀው ተወረደልኝ የሚለው ቃል በአረብኛ መሆኑን ማስረገጥ ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ከሆነ ቁርአን በአረብኛ ነው የወረደውና ተወረደልኝ የሚለውን ለራስህ አንብበው እንለዋለን፡፡ ተወረደልኝ ያለው በአረብኛ ከሆነ ደግሞ የተወሰኑ ምሁራዊ ማብራሪያዎችን ልንሰጥ የግድ ይላል፡፡ እንደሚከተለው፡-
የአረብኛ ቋንቋ ልሂቃን ሰዋስዋዊ ህግጋትን ሲያረቁ ቁርኣንን፣ ሐዲስ̱ንና የአረቦችን ንግግር መሰረት አድረገው ነው፡፡ ቁርአንን መጠቀሙ ፈጽሞ አያጣላም፡፡ ለምን ሁሉም የአላህ ቃል ስለሆነ!!! ሐዲስ̱ ጋር ስንመጣ ግን ለዘጋቢዎቹ ለምሳሌ ለነቡኻሪ ሐዲሱ ሲደርሳቸው ቃል በቃል ነብዩ እነደተናገሩት ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባት አውሪዎቹ በራሳቸው ቃልና አባባል ሀሳቡን ሊያስተላልፉ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሐዲሶ̱ችን ለማስረጃነት ፈጽሞ አንቀበልም ያሉ ልሂቃን ሲኖሩ በተቀራኒው ሁሉንም ሐዲስ̱ ለማስረጃነት እንቀበላለን ያሉም አልተፉም-ለምሳሌ ኢብኑ ማሊክ፡፡
ይህ ጉዳይ እስከ ሃያኛው ክ.ዘ. ድረስ አጨቃጫቂ ሆኖ ቆየና ሼኽ ሙሓመድ አልኸዲር ሁሴን “አልቂያስ” በሚለው መጽሃፋቸው ውስጥ ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ እነዚህን ሐዲሶ̱ች ለማስረጃነት መጠቀም እንችላለን ብለው አሳማኝ መረጃ ካቀረቡ በኋላ ጭቅጭቁ ምዕራፉን ዘግቷል፡፡
1) ሐዲስ̱ ሙተዋቲር ፡- እነዚህ ሃዲሶች ስብስቦች ከስብስቦች (ጀመዓ ከጀመዓ) እያወሯቸው እኛ ድረስ የደረሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም በስብስቦቹ መካከል የቃላትና የአባባል ስምምነት ስላለ መሰል ሐዲሶችን ለመረጃነት መጠቀም እንችላለን፡፡ ይላሉ፡፡
2) የመልክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ደብዳቤዎች፡- እነዚህ ደብዳቤዎች መልክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ለተለያዩ ህዝቦች በተለያየ ግዜ የጻፏቸው ሲሆኑ እስከ አሁንም ድረስ በተለያዩ ድርሳናት ተጠብቀው የሚገኙ ናቸው፡፡ ደብዳቤዎቹ በይዘታቸው አጫጨር ከመሆናቸው አኳያ በቃል ለመያዝም የማይከብዱ ስለሆኑ በቃልም በድርሳናትም ስለተጠበቁ እነዚህን ለመረጃነት መጠቀም እንችላለን፡፡ይላሉ፡፡
3) ጀዋሚዐል ከሊም( ተቅላይ ቃላት)፡- እነዚህ ቃላት መልክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ከተሰጡት ተዓምራት ውስጥ ሚደበለቁ ናቸው፡፡ ቃላቱ እምቅ ሆነው ሰፊ መለእክትን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ ስለሆነም በሰሃባዎች (ረ.ዐ) አንደበት ሲደጋገሙና ሲተላለፉም የኖሩ ስለሆነ እንደ ማስረጃንት ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡ በማለት ያስረዳሉ፡፡
ወዳጄ ሼኹ ይህንን ከተናገሩ በኋላ በቋንቋ ልሂቃን መካከል የነበረው አለመግባባት እንደቀረ ልብ ይበሉ!!!

ሶስተኛው ሰዋስዋዊ ህግ ለማርቀቅ ልሂቃን የተጠቀሙት መረጃ የአረቦች ንግግር ሲሆን ይኸውም 1ኛ) ቀይስ 2ኛ) በኑ ተሚም 3ኛ)ቁረይሽ 4ኛ) በኑ አሰድ 5ኛ) ከፊል በኑ ሁዘይር የሚባሉ ጎሳዎችን ዘይቤ ብቻ ነበር፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ጎሳዎች በርካታ የቋንቋ ልሂቃን የፈለቁባችውና ቁርአንም መልክተኛውም በነሱ ዘይቤ በመናገራቸው ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ልሂቃን የነዚህን ጎሳዎች ዘይቤ መረጃ አድርገው የተጠቀሙት በከተማ አካባቢ ከሚኖሩት እስከ ሁለተኛ ክ.ዘ.( ሂጅሪያ) ድረስ ሲሆን በገጠር አካባቢ ከሚኖሩ ደግሞ እስከ አራተኛ ክ.ዘ. (ሂጅሪያ) ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከሁለተኛ ክ.ዘ. በኋላ በከተማ የነበረው የሁሉም አረቦች ቋንቋ ስለተበረዘና በገጠረ የነበረው ደግሞ እስከ አራተኛ ክ.ዘ. ሳይበረዝ ስለቆየ መረጃዎቹን ከዚያ በፊት እነጂ በኋላ መውሰድ አንችልም የሚል የልሂቃን ታሪክን ያገናዘበ ስምምነት አለ፡፡
እና ወዳጄ ዛሬ አንድ አረብ ብድግ ብሎ የቁርኣን አይነት አመጣሁ፣ወረደልኝ ቢል- ዛሬ የአረብኛ ቋንቋ ተበርዟል፤ በተበረዘና በተሰባበረ አረብኛ ቁርአን ስላልወረደ ይዘህ የመጣኸው የቁርአን አምሳያ አይደለም…ብለን እንመልሰዋለን፡፡ ከዚህ አኳያ የቁርአን አይነት በመልክተኛው ዘመን መምጣት ካልቻለ ዛሬ ሊመጣ እንደማይችል እማይታበል ይሆናል፡፡ አላህም፡-
{ (ይህንን) ባትሠሩ ፈጽሞም አትሠሩትምና ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ድንጋዮች የኾነችውን እሳት ተጠበቁ፤ ለከሓዲዎች ተደግሳለች፡፡ }አልበቀራህ/23 – በማለት ተግዳሮቱ ዘላለማዊ እንደሆነ ይደመድማል፡፡ እኛም በዚሁ እንደምድም!!!

Shortlink http://q.gs/EyaDl