ቀብሩን ቆፋሪ ትውልድ

ሼር ያድርጉ
481 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

አዲስ ትውልድ ኹሌም የተፈጠረበት ዘመን ያስረከበውን ተቀብሎ ሚያሻሽለውን አሻሽበሎ ቢያንስ እሱ ከተፈጠረበት ዘመን የተሻለ ዘመንን ለሚቀጥለው ትውል ለማውረስ ይተጋል፡፡ ያ ሲኾን ትውልድ ከትውልድ የተሻለ አየር መተንፈስ ይችላል፡፡ አናጻሪዊ ነጻነትና ብልጽግና እየተጎናጸፈ ይዘልቃል፡፡ ከነጻነት ኹሉ ትልቁ ነጻነት፤ከስልጣኔም ኹሉ ትልቁ ስልጣኔ ደግሞ የኣስተሳሰብ ነጻነትና ስልጣኔ ነው፡፡ የኣስተሳሰብ ልቀት ከሌለ፤ቁሳዊው ስልጣኔ ብቻውን መልካም ስብዕናን አይፈጥርም፡፡ ለዚህ ማሳያችን ደቡብ አፍሪቃ ናት፡፡ ኹሉም ዓይነት ቁሳዊ ስልጣኔ ቢኖራትም ከግብረገባዊው ስልጣኔ ግን ክፉኛ የተራቆተች ናት፡፡ ስለኾነም ሰዎች ለነፍሳቸው እንኳ እየሰጉ ሚኖሩባት ምድር ኾናለች፡፡ኢስላማዊው ስልጣኔ ፈጥሮት የነበረው ምድራዊ ክስተት የሰብዕናም የቁስም ስልጣኔ ነበር፡፡ ሰዎች በሰውነታቸው ብቻ የሚከበሩበት፤የሃሳብ የበላይነት ብቻ የሚያሸንፍበት፤አውሮጳውያኑን እንኳ ሳይቀር ያማለለ የስልጣኔ ጣራ ነበር፡፡ በጊዜው ሳይንስን መማር የፈለጉ አውሮጳውያን ሙስሊሙ ዓለም ዘንድ ኼደው ሳይንሱንም የሙስሊሙን ድንቅ ስብዕናም ጭምር ተምረው ይመለሱ ነበር፡፡ ከኢንዶኔዥያ እስከ ሞሮኮ ድረስ የተዘረጋው ድንቅ የኢስላም ኸሊፋዊ ግዛት ዓለምን ኹሉ ያማለለ በሰው ልጅ ታሪክ ግዙፉ የስልጣኔ ዘመን ነበር፡፡ ታዲያ ያ ታላቅ ግዛት በነማን ፈረሰ ከተባለ፤ የመጀመሪያዎቹ አፍራሾች ሙስሊሞች ራሳችን ነን፡፡ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ከሌሎች የሚሰጡንን ገጸ-ባህሪያት በመላበስ ከጸረ-ኢስላም አካላት ጋር በማበር ኺላፋው ከውስጥ እንዲናድ ምክንያት ኾንን፡፡ በስተመጨረሻም ኺላፋው ወደቀ፤ ፍልስጤም በነእንግሊዝ እጅ ወደቀች፤ለኢስራኤልም ተላልፋ ተሰጠች፡፡የቅርቡ የነኢራቅና ሶሪያ ታሪክም ከዚህ የዘለለ አይደለም፡፡ ከውስጥ የኾኑ የሰይጣን አጋሮች ስለ መብት ሰበኩን፤ እውነት መስሎን “መብት… መብት” በሚል መፈክር ተንጋግተን ከአደባባይ ወጣን፤ከዚያም እንደማይሳካልን እያወቁ በመሳሪያ መታገል ይሻላችኋል አሉን፤ በመሳሪያ ትግል ጀመረን…በስተመጨረሻ ራሳቸው ጦር ይዘው ገብተው አጠፉን፡፡ ዛሬ ላይ በሙስሊሙ ሐገር ህልማቸው የነበረውን ቤተ-እምነታቸውን ያለቁጥር ገደብ እየገነቡ ሙስሊሙን ለማጥመቅ ጠብ እርግፍ እያሉ ነው፡፡ ኢራቅ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ ራሱ ጆርጅ ቡሽ ለህዝቡ ሲናገር “ በዓረቡ ምድር የሰራነውን በቅጡ ተረድታችኹት በነበር፤ ልክ እንደ ማሾ ላይ ሰቅላችኹ በጉጉትና ስስት ትመለከቱን ነበር” ነው ያለው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በሰባዎቹ ሳዳም ሑሴንን የስልጣን ማማ ላይ ሰቀሉት፤ ሰቀሉትናም በዘጠናዎቹ ኩዌትን ውረር አሉት፡፡ ወረረ፡፡ ከዚያም ክተት አውጀው ሰላሳ ሀገራት ኢራቅን ደበደቡ፡፡ ሚሊዮን ሕጻናት በርሃብ ብቻ አለቁ፡፡ በትሪሊየን የሚቆጠር ዶላር ከኢራቅ ባንክ በነአሜሪካ ተዘረፈ፡፡ ነዳጅ ከወንዝ እንደሚቀዳ ውኃ ያለምንም ርህራሄ ተጭኖ ወደነ አሜሪካ ተላከ፡፡ በስተመጨረሻም ሳዳም ከፍልስፍናቸው አፈነገጥኹ ሲል ከተቀረቀረበት ጉድጓድ አውጥተው የሙስሊሙን ስነ-ልቦና ለመጉዳት ኾን ብለው በዒድ አልኣድሃ ምድር ሰቀሉት፡፡ የሊቢያው ጋዳፊም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ታሪክ አለው፡፡ሙስሊሙን ለማጥቃት በሙስሊሙ መካከልም የአቋምና ተቋም ልዩነት በመፍጠር ማፈራረስም ያውቁበታል፡፡ አቋሞቹን ሲፈጥሩ በሙስሊም ስም ገብተው ከቁርኣንና ሐዲስ̱ እየጠቀሱ ነው፡፡ ከዚያም ከነሱ አመለካከት ውጭ ስትኾን የኾነ ስም ይሰጡኻል፤ ወይም ገና ሲያደራጁህ የኾነ መለያ ይፈጥሩልኻል፡፡ በዚህ መልኩ ከዚህም ከዚያም ኣንጃዎችን በመፍጠር ሙስሊሙን ለማናከስ አስፈላጊውን ግብኣት ኹሉ ያቀርባሉ፡፡ኢኢስላማዊ አምልኮ የሚፈጽምባቸው የፈራረሱ ቀብሮች ዳግም እንዲታደሱ ዳጎስ ያለ በጀት ይመድባሉ፡፡ ከዚያም እንደ አስፈላጊነቱ እነዚህን ሰዎች የሚመክር ሳይኾን፤ በዘገደው ከኢስላም የሚያስወጣ ሌላ አንጃ ደግሞ ያቋቁማሉ፡፡ ኹለቱ “እሳት” ና “ጭድ” ኣንጃዎች የራሳቸው ጠላቶች በፈጠሩላቸው መድረክ ላይ ቄብ ብለው በአርበኝነት መንፈስ ይተውናሉ፤ ጠላቶቻቸው ደግሞ ተውኔቱን በነጻ ይታደማሉ፡፡ወዳጄ ዛሬ ላይ ኹላችንም ጥሩ ተደራሲ ኾነን የተለያዩ ጸረ-ኢስላም ገጸ-ባህሪያትን እየተወን እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡ ገሚሱ እኔ እንዲህ ነኝ በሚል ከርሱ ውጪ ያለውን ከኢስላም እንደ ወጣ ኹሉ በዱምዱሙ ሲወቅጥ፤ ተወቃጬም በራሱ ሜዳ ሌላኛውን እንደ ድኩላ ሲያሳድ መመልከት የለት ለት ኹነት ኾኗል፡፡ ኹሉም ሌላኛውን ፈጽሞ ጥላቻ በተመላበት መልኩ ሲያወግዝ “ለኣላህ ብዬ ነው” በሚል ስሜት ሲኾን ማየት ደግሞ፤ ምነኛ ህዝቤ ከእውቀት ማዕድ እንደተራበ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ መቼም አምስት ሳንቲም የጠፋበት መቶ ብሮችን ከፍሎ ሳንቲሙን እንደማያስፈልግ ኹለችንንም ያስማማል፡፡ ጠፋ ላልነው ኢስላማዊ አካሄድ መነጋገር ካለብን ሌላ የባሰ ጥፋት በማይፈጥር መልክና ቁመና እንጂ፤በቡሃ (ራስ በራ) ላይ ቆሮቆሮ መፍጠር፤ ለሰደድ እሳት ጭድ ማቀበል ዓይነት አካሄድ፤ ከእብደት በላይ ገላጭ ቃል ቢኖር እንኳ በቂ አይኾንም፡፡ ኣላህ ሙስሊም ብሎ የጠራውን ኣካል የኛን “መዝሙር”ስላልዘመረ ብቻ “የነንትናን ስርዓት (ሚንሃጅ) ናፋቂ” በሚል የወል መጠሪያ መጎንተል፤ ሃቅን መናገር ተደርጎ የታሰበበት ዘመን ላይ የበላይነትን መናፈቅ፤ እንደ ሙሳ (ዐ) በትር ከድንጋይ ውስጥ ኮለል ያለ ውኃ ለማፍለቅ የመሞከር ያህል ነው፡፡ እንደማይሳካ እየታወቀ የሚደረግ ሙከራ ደግሞ በትክክል ምን መሰራት እንዳለበት ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ የሰሞንኛው የርስ በርስ ጦር ሰበቃ ፌስ ቡክ ራሱ እንዲያስጠላ ምክንያት ሳይኾን የቀረ አይመስለኝም፡፡ስለዚህም ወጣቶች ሆይ እስኪ መጀመሪያ ወደ እቀውቀት ማዕድ እንቅረብ፤እውቀት ለበሽታ ኹሉ መድኃኒት ነው፡፡ በእውቀት የታነጸ መንፈስ መፍትሄ አቅራቢ እንጂ እሳት ለኳሽ አይኾንም፡፡ ከባድ ዝናብ መጥቷል ሲባል ካሸንዳው ተጠለል ሳይኾን፤ ከዋሻው ተሸሸግ የሚል ይኾናል፡፡ ችግሮች በሙስሊም ዘንድ እያንዣበቡ ካለ፤ለችግሩ መሻገሪያ ድልድይ ይኾናል፡፡ በፌስ ቡክና ኢንተርኔት ላይ ብቻ የተመሰረተ እውቀት መሳይ እውቀት ያልኾነው ነገር ደግሞ ለዚህ ብቁ አያደርግም፡፡መፍትሄው ከመሻይኽ ዘንድ መጣድ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ያለው ማጠናከሪያ እንጂ መሰረታዊ ሊኾን አይችልም፡፡ “አንብብ” ብሎ የጀመረው መለኮታዊ ራዕይ ኣማኞቹን ከእውቀት ጋር ለማጣመር ምን ያህል ኃያል ምክር እንደኾነ የዘነጋ ትውልድ አርነት ሊወጣ አይቻለውም፡፡ቸር እንሰንብት

 

Shortlink http://q.gs/Eye4N